Print this page
Saturday, 15 August 2020 14:39

በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ወንድ ተዋንያን ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ፎርብስ መጽሄት የ2020 የፈረንጆች አመት የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ወይም ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ወንድ የፊልም ተዋንያንን ዝርዝር ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገ ሲሆን ባለፈው አመት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው ዋይኔ ጆንሰን ዘንድሮም በ87.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡
የቀድሞው የሪስሊንግ ተጫዋችና ሬድ ኖቲስ በሚለው ፊልም የሚታወቀው ተዋናዩ በኔትፍሊክስ ድረገጽ ከሚታዩት ፊልሞቹና ፕሮጀክት ሮክ ከተሰኘው የአካል ብቃትና የአልባሳት ኩባንያው ያገኘውን ገቢ ጨምሮ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 87.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ፎርብስ አስታውቋል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙት ቀዳሚዎቹ 10 የፊልም ተዋንያን በድምሩ 545.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የጠቆመው ፎርበስ፣ ሩብ ያህሉን ገቢ ያገኙትም ኔትፍሊክስ ከሚባለውና ፊልሞችን በአንተርኔት አማካይነት በስፋት ከሚያሳየው ኩባንያ መሆኑን ገልጧል:: በአመቱ ሁለተኛውን ከፍተኛ ገቢ ያገኘው የአለማችን ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ሬድ ኖቲስና ሲክስ አንደርግራውንድ በተባሉት ፊልሞች ላይ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሪያን ሬኖልድስ መሆኑን የጠቆመው መጽሄቱ፣ ተዋናዩ በአመቱ 71.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
ታዋቂው የፊልም ተዋናይና ፕሮዲዩሰር ማርክ ዋልበርግ በ58 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ቤን አፍሊክ በ55 ሚሊዮን ዶላር አራተኛ፣ ቪን ዲዝል በ54 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ በያዙት ባለ ከፍተኛ ገቢ የአለማችን ተዋንያን መካከል የተካተተው ብቸኛው የቦሊውድ ተዋናይ ህንዳዊው አክሻይ ኩማር ሲሆን በ48.5 ሚሊዮን ዶላር የስድስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ሊል ማኑኤል ሚሪንዳ እና ዊል ስሚዝ (በተመሳሳይ 45.5 ሚ. ዶላር)፣ አዳም ሳንድለር (41 ሚ. ዶላር) እና ጃኪ ቻን (40 ሚ. ዶላር) እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሰባተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአመቱ የአለማችን ባለ ከፍተኛ ገቢ ወንድ የፊልም ተዋንያን መሆናቸውንም ፎርብስ መጽሄት ያወጣው ዝርዝር ያሳያል፡፡

Read 1557 times
Administrator

Latest from Administrator