Saturday, 21 July 2012 09:55

የመንግስት መሪ ሲታመም ምን ያህል ያሳስባል?

Written by  አለሙ ከድር
Rate this item
(1 Vote)

ብዙ አሰብኩ፤ ከራሴ  ጋር ተከራከርኩ

1.እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት አሳሳቢነቱ ይብሳል

2.አይ፤ የመንግስት መሪ ሲታመም የትም አገር  አሳሳቢ ነው

1.ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለአገራችን እንግዳ ነገር ነው

2.አይዞህ፤ ኢትዮጵያ የምትተዳደረው በህገመንግስት ነው

1.በስከነ ንቃት ፋንታ  ድንዛዜና መደናበር የበዛበት ባህል ያሰጋል

2.ተረጋጋ፤ የኢትዮጵያ ህልውናኮ በ”ኪነጥበቡ” ለዘመናት ዘልቋል

1.የመንግስት መሪ  መታመም ለወር ያህል ምስጢር ሆኗል

2.ምስጢራዊነት’ኮ  የድርጅትን ጥንካሬ የሚያስመሰክር ነው

ጉዳችንንኮ አየነው። እስቲ አስቡት። ስለ አገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር የጤና ሁኔታ፤ ከወሬ ወሬ ያለፈ የተጨበጠ መረጃ ሳናገኝ ሳምንታት መቆጠር ነበረባቸው? ሌላው አለም “ስልጡን የመረጃ ዘመን” ላይ ነው፤ እኛ ግን ገና “ኋላቀር የወሬ ዘመን” ላይ ነን። በዚህ አባባል የማይስማሙ ሰዎች፤ “በኢንተርኔት እንጠቀማለን” የሚል መከራከሪያ ሊያመጡ ይችላሉ። በፌስቡክ ቅብብሎሽ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ሁኔታ ብዙ ነገር እንዳነበቡና እንደሰሙ መጥቀሳቸውም አይቀርም። ምን ዋጋ አለው? ቴክኖሎጂውማ ያለ ጥርጥር ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነው። ግን፤ የተጨበጠ መረጃ ለማሰራጨትና ለመቀበል ችለንበታል? ወይስ የወሬ ወሬ ነው?

“ከወሬ ባህል” ያልወጣ አገር

የወሬ ወሬማ ጥንትም ነበር። ድግስ ላይ የአዝማሪ አሽሙር፣ በዋርካ ጥላ ስር የ”አዋቂ” ንግርት፣ መንገድ ላይ የእረኛ ግጥም፣ እልፍኝ ውስጥ የታላላቆቹ (የቤተመንግስት ባለሟሎችና የተቀናቃኝ ተስፈኞች) ሹክሹክታ፣ በየጎጆው የእሳት ዳር ጭምጭምታ ድሮ በሽ በሽ ነበር... የወሬ እጥረት አጋጥሞ አያውቅም። ዛሬም እንደጥንቱ፤ ወሬ በሽበሽ ነው። የመረጃ ሳይሆን የወሬ ባህል፤ እንደጥንቱ ዛሬም ከኛው ጋር ነው። የተቀየረ ነገር ቢኖር፤ የምንኖርበት አለም ከድሮው የተለየ መሆኑ ነው። ድሮ ኢንተርኔት አልነበረም፤ ዛሬ ኢንተርኔት አለ። ፌስቡክ አለ። የወሬ ባህላችንን የምንተውንበት መድረክ ነው የተቀየረው - የዋርካ ጥላ ስርና ከእረኛ ግጥም ወደ ኢንተርኔትና ወደ ፌስቡክ ተዛውረናል። ግን እንደ ድሮው ወሬ እናገኛለን እንጂ የተጨበጠ መረጃ ግን የለም።

እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታመሙ አራት ሳምንት አልፏቸዋል ተብሎ የለ? የወሬ ወሬና ጭምጭታ ሰምተን ዝም ልንል አንችልም። የተጨበጠ መረጃ ለማግኘት ጉዳዩን በቀጥታ ወደሚመለከታቸው አካላት አዙረን ጠበቅን። የመንግስት ሬድዮና ቲቪ ከፍተን ተከታተልን። ግን ምንም መረጃ የለም። በማግስቱም እንዲሁ።

ከሳምንት በኋላስ? አየን ሰማን፤ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ሁኔታ ምንም መረጃ የለም። ቢሆንም ግን፤ የዜና ሰአት በደረሰ ቁጥር፤ አይናችንን ቲቪው ላይ መትከላችን፤ ጆሯችንን ወደ ሬድዮው አቅጣጫ መቀሰራችን አልተቋረጠም። ገና ዜና አንባቢው ብቅ ሲል ወይም ድምፁ ሲሰማ፤ አንዳች የተጨበጠ መረጃ ለማግኘት እንጠብቃለን። “ትልቁና ዋናው ዜና” ተብሎ በቀዳሚነት የምትሰሙት ዜና ግን ኩም የሚያደርግ ነው። የቴፒ የእርሻ ማእከል፤ በቅመማ ቅመሞች ላይ የሚያካሂደው ጥናትና ምርምር መጠናከር እንዳለበት ተገለፀ የሚል ቀዳሚ ዜና ስትሰሙ አስቡት። ሃሙስ እለት በሰባት ሰአት በቲቪ የተላለፈው ቀዳሚ ዜና ይሄው ነበር።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ሁኔታ ዙሪያ፤ በፌስቡክ፤ በስራ ቦታና በመጠጥ ቤት  የጎዳናና የጓዳ ወሬ ሞልቷል። የተጨበጠ መረጃ ነው ያጣነው። በ21ኛው ክፍለዘመን ላይ ሆነን፤ ከ19ኛው ክፍለዘመን ጋር የሚመሳሰል “የወሬ ባህል” ውስጥ የምንኖር መሆናችን በጣም አሳሳቢ ነው።

 

በስልጣን ሽግግር የምትሳቀቅ አገር

የጠ/ሚ መለስ የጤና ሁኔታና አንደምታዎቹ አሳሳቢ መሆናቸውን አልዘነጋሁትም። በየትኛውም አገር፤ የመንግስት መሪ ሲታመም አሳሳቢ መሆኑ አያከራክርም። በተለይ እንደኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ደግሞ እግጅ ያሳስባል። የቅርብ ጊዜ የአገሪቱን ጉዞ ስንቃኝ፤ አፅናኝ ታሪክ አናገኝም። በሁለት መቶ አመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፤ አንዴም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አልተካሄደም።

መሪ የጠፋበት “ዘመነ መሳፍንትን” ጨምሮ፤ የአፄ ቴዎድሮስ እና የአፄ ዮሃንስን ዘመን ተመልከቱ - አነሳስና አወዳደቃቸው በቀውስ ወይም በጦርነት የታጀበ ነው። በአፄ ምኒልክ ዘመንም እንዲሁ፤ ያለቀውስ የስልጣን ሽግግር አልተከናወነም - በድብቅ ለአመታት የተካሄደው ውስብስብ የቤተመንግስት ሽኩቻ ንግስት ጣይቱን ለእስር ከመዳረጉም ባሻገር፤ ጦርነትንም አስከትሏል። የንግስት ዘውዲቱ ከሌሎቹ ይለያል፤ ከመነሻውም እንደሌሎቹ ነገስታት ሙሉ ስልጣን አልያዙም። ታሪካቸውም በአብዛኛው ተቀብሮ እንዲቀር ተደርጓል።

የአፄ ሃይለስላሴ ዘመን ማብቂያ ደግሞ የባሰ ነው፤ ከአፄው ስንብት ጋር አገሪቱን ያተራመሰ የእስር እና የግድያ ቀውስ ነግሷል። የደርግ ወይም የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም መጨረሻም እንዲሁ፤ በጦርነት የተከበበ እንደነበር ይታወቃል - ብዙዎች ያለቁበት ጦርነት። እነዚህን የአገራችን ታሪኮች ስንመለከት ስጋት ካላደረብን የ”ስጋት” ትርጉም ተቀይሯል ማለት ነው።

በስልጣኔ ደህና እንደተራመዱት እንደ አሜሪካና እንደ እንግሊዝ አይነት ታሪክ የለንም። ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለአገራችን እንግዳ ነው። ታዲያ የመንግስት መሪ ሲታመም፤ እጅግ አሳሳቢ ቢሆንብንና ብንሰጋ ምኑ ይገርማል? ደጋፊም ይሁን ተቃዋሚ ለውጥ የለውም። ኮ/ል መንግስቱ ከስልጣን የወረዱ ጊዜ፤ ስጋት ያላደረበትና የአገሪቱ ሁኔታ ያላሳሰበው ሰው ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ያኔ የደርግ ደጋፊዎች ስጋት ነበረባቸው። ተራው ዜጋ ሰግቷል። ኢህአዴጎችም በተለይ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ “በደርግ ውድቀት ማግስት ምን ይፈጠር ይሆን?” በሚል እጅግ ስጋት አድሮባቸው እንደነበር መግለፃቸው ይታወሳል።

“ቢያሳስበንና ብንሰጋስ የት እንደርሳለን?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ፤ ምላሽ ለመስጠት ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ፤ ዞሮ ዞሮ የስልጣን ሽግግር መካሄዱኮ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ስላሰጋን ወይም ስላሳሰበን፤ የስልጣን ሽግግሩ ላልተወሰነ ጊዜ አይራዘምልንም፤ ወይም በአንዳች ተአምር የስልጣን ሽግግሩ ሰላማዊና ቅፅበታዊ አይሆንልንም። አገሪቱ ውስጥ በሰፈነው የፖለቲካ ስርአትና ባህል መሰረት የስልጣን ሽግግር መከናወኑ ላይቀር ነገር፤ ሲያሰጋን ውሎ ሲያሳስበን ቢያድር ምን ጥቅም አለው? የፖለቲካ ስርአትና ባህል እንደሆነ፤ በአንድ እለት ወይም በአንድ አመት የሚለወጥ ነገር አይደለም።

እንዲያም ሆኖ፤ መስጋትና ማሰብ ያስፈልጋል። አንደኛ፤ ለጊዜውም ቢሆን፤ ከክፉ አማራጮች ለመጠንቀቅና ለመራቅ፤ ሻል ያሉ አማራጮችንም ለማወቅና ለመምረጥ ይጠቅማል። ሁለተኛ፤ በረዥም ጊዜ እይታም፤ የሚያስተማምን ስልጡን ስርአትና ባህል ለመገንባት አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

ለነገሩ የዚህን ያህል አከራካሪ መሆን አልነበረበትም። በቃ፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ታሪክ የሌላት አገር ውስጥ ነው የምንኖረው። እናም፤ በህፃንነት ወይም በአላዋቂነት ምክንያት ካልሆነ በቀር፤ ቢያንስ ቢያንስ የስልጣን ሽግግር ላይ ትርምስ እንዳይፈጠርና ጥፋት እንዳይደርስ፤ ማንም ጤናማ ሰው የአገሪቱ ሁኔታ ሊያሳስበው ይገባል። የመንግስት መሪ ሲታመምም አሳሳቢነቱን መካድ ሞኝነት ይሆናል። እንደ አውሮፓና እንደ አሜሪካ አይነት ታሪክ የለንማ። የአገራችን የስልጣን ሽግግር ታሪክ፤ የሚወደድና የሚያስቀና አይደለማ።

 

ማረጋጊያና መተማመኛ

ጠ/ሚ መለስ እንደታመሙ ከመንግስት በኩል በይፋ ሳይነገረን ቢቆይም፤ አሁን ከህመማቸው እያገገሙና እየተሻላቸው መሆኑን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሰምተናል። ስጋታችንን ሊቀንስልን የሚችል ዜና ነው። ከዚህም በተጨማሪ፤ ከኢህአዴግ መሪዎች የሚሰነዘርልን ማረጋጊያና ማፅናኛ እንደሚኖር አያጠራጥርም።

ኢህአዴግ በከፍተኛ ችግሮች የተጋፈጠና ብዙ ፈተናዎችን ያለፈ ጠንካራ ድርጅት መሆኑን መሪዎቹ ሲናገሩ፤ የአመራር መተካካት በጭራሽ አሳሳቢ ሊሆን አይችልም ይላሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ አገሪቱ የምትተዳደረው በአንድ ሰው ሳይሆን በህገመንግስት ነው የሚሉት የኢህአዴግ መሪዎች፤ መቼም ቢሆን የስልጣን ሽግግር የሚከናወነው በህገመንግስቱ መሰረት ስለሆነ ሰላማዊ እንደሚሆን አያጠራጥርም ይላሉ።

ከኢህአዴግ መሪዎች የምንሰማቸውን ማረጋጊያና ማፅናኛ ሃሳቦችን አምነን እንቀበል? “እንደ አፋቸው ያድርግልን” ብንልስ? በእርግጥ በህገመንግስቱ መሰረት የተካሄደው የ97ቱ ምርጫ ሰላማዊ አልነበረም። እንዲያውም በኢህአዴግ ዘመን እጅግ አሳሳቢ ተብለው ከተጠቀሱት ሶስት ክስተቶች መካከል፤ የ97ቱ የምርጫ ቀውስ አንዱ እንደሆነ ጠ/ሚ መለስ በአንድ ወቅት ተናግረዋል። ምርጫ ማለት በቀጥታ ከስልጣን ሽግግር ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑን አስተውሉ። እናስ፤ አሳሳቢው ቀውስ የተፈጠረው በ”ህገመንግስት” እጦት ሳቢያ ነው? አሁን ያለው ህገመንግስት፤ በ97ም ነበር። ታዲያ፤ “አገሪቱ የምትተዳደረው በህገመንግስት ስለሆነ አትስጉ” የሚል ማረጋጊያ የተሟላ እፎይታ ሊሰጠን ይችላል?

ይህም ብቻ አይደለም። ጠ/ሚ መለስ ከ97ቱ የምርጫ ቀውስ በላይ እጅግ አሳሳቢ የነበሩ ሁለት ነገሮችን ጠቅሰዋል። አንደኛው፤ በደርግ ውድቀት ማግስት የነበሩ ወራት በጣም አሳሳቢ ጊዜያት እንደነበሩ ገልፀዋል - ጠ/ሚ መለስ። የስልጣን ሽግግር ጉዳይ ነው። በጠ/ሚ መለስ የተጠቀሰው ሌላው እጅግ አሳሳቢ ክስተት፤ የኢህአዴግ አመራር ውስጥ በ1993 ዓ.ም. የተከሰተው ክፍፍል ነው። ይሄኛውም የስልጣን ጥያቄ ነው - የስልጣን ሽግግር ጉዳይ።

ይታያችሁ። በኢህአዴግ ዘመን ከሁሉም በላይ እጅግ አሳሳቢና አስጊ ናቸው ተብለው የተገለፁት ሶስቱ ክስተቶች፤ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከስልጣን ሽግግር ጋር የተያያዙ ናቸው። የስልጣን ሽግግር እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት አሳሳቢ ሳይሆን ቀርቶ እንደማያውቅ ከዚህ መረዳት ይቻላል። እንግዲህ በ93ቱ የኢህአዴግ ክፍፍል እና በ97ቱ ምርጫ ላይ፤ ከስልጣን ሽግግር ጋር በተያያዘ እጅግ አሳሳቢ ቀውሶች የተፈጠሩት፤ ህገመንግስት ሳይኖር ቀርቶ አይደለም። ወደፊትስ በስልጣን ሽግግር ጉዳይ ላይ፤ ህገመንግስቱ እንዴት ሙሉ ለሙሉ ማስተማመኛ ሊሆን ይችላል? ለጊዜው ገና እዚያ ደረጃ ላይ አልደረስንም እላለሁ። ምናልባት፤ ህገመንግስቱ ትንሽም ይሁን ትልቅ የተወሰነ ያህል ፋይዳ ይኖረዋል ብንል ያስማማን ይሆን? በዚያ ላይ፤ ሌሎች ማረጋጊያና ማፅናኛ ምክንያቶች ሲጨመሩበት፤ የተሻለ ውጤት ሊኖረው ይችላል።

ሌላ አይነት ማፅናኛና መተማመኛ አይታያችሁም? አልፎ አልፎ ሳትሰሙት የቀራችሁ አይመስለኝም። መቼም በግልፅ አናውቀው ይሆናል እንጂ፤ ይህች አገር ለምዕተ አመታት በህልውና የቀጠለችው ያለ ምክንያት ሊሆን አይችልም። አንዳች ምክንያት የሚኖረው አይመስላችሁም?

 

“ተአምረኛ” አገር

በአገሪቱ ላይ የደረሱ ፈተናዎችና ጥፋቶችኮ ለቁጥር ያስቸግራሉ። ግን ለሺህ አመታት ህልውናዋን ሳታጣ ዘልቃለች። አንዳች ነገር፤ አንዳች ሃይል ቢኖራት ነው። በእርግጥ፤ “ያ ነገር፤ ያ ሃይል ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ አሳማኝ መልስ ሲቀርብ አላየሁም። ታዲያ፤ “ኢትዮጵያ አንዳች ሃይል ሳይኖራት አይቀርም” የሚለው መላምት ብቻውን የት ያደርሰናል? ስጋታችንን ሊቀንስልን ይችላል? “እንረጋጋ፤ የአገሪቱ ሁኔታ ብዙም ሊያሳስበን አይገባም” ብለን መተማመን እንችላለን? ያን ያህልም አስተማማኝ መፅናኛ ሆኖ ባይታያችሁ አልተሳሳታችሁም። ከመላምት ተሻግረን፤ አገሪቱ አንዳች ሃይል እንደያዘች እርግጠኛ ብንሆን እንኳ፤ ብዙ አያስኬደንም።  ምንነቱ በግልፅ ባልታወቀ አንዳች ሃይል ላይ እምነት መጣልና መፅናናት ቂልነት ይሆናል።

ቢሆንም ግን፤ ነገሩን አቃልሎ ማየትና ወደ ጎን መተውም ከቂልነት አይተናነስም። የአገሪቱ ህልውና ምዕተ አመታትን ማስቆጠሩ አይካድም። የሺህ ዘመናት የአገር ህልውናን ማናናቅ ከባድ አላዋቂነት ነው። በቃ፤ ይህች አገር ብዙ ነገር አልፋለች። ብዙ መንግስታትና መሪዎች ተፈራርቀውባታል። ግን ይሄው አለች። ብዙ ግጭቶችንና ጦርነቶችን አስተናግዳለች - የውጭ ወረራዎች፤ የእርስ በርስ ግጭቶች፤ ሃይማኖታዊ ጦርነቶች እየተከታተሉና እየተደራረቡ ከታች እስከ ላይ፤ ከግራ እስከ ቀኝ በእሳት ተለብልባለች። ግን ይሄው አሁንም አለች።

ዘመነ መሳፍንት በሚባለው ወቅት፤ በዘርና በቋንቋ፤ በጎጥና በወንዝ ተከፋፍለው በሚናቆሩ የጦር አበጋዞች ተዳክማ ያለ መንግስት መሪ ብትጎሳቆልም፤ ህልውናዋ ጨርሶ አልጠፋም። አንዳንዴም ተቀልዶባታል። አፄ ሚኒልክ በእርጅና ዘመናቸው በህመም ተሸንፈው ህይወታቸው ካለፈ በኋላ፤ ለ7 አመታት ሌላ መሪ በይፋ ሳይተካ “በአፄ ምኒልክ ዙፋን” ስር የቆየች አገር ነች። በብልህ መሪዎች ዘመን ብቻ ሳይሆን ብልህነት በጠፋበት ዘመንም ያልጠፋች አገር ነች። ሌላው ይቅርና፤ ጭካኔንና ጥይትን ዋነኛ መለያዎቹ ባደረው የደርግ እና የኮ/ል መንግስቱ አስተዳደር ስርም አልፋለች። ታዲያ ይህች አገር፤ አንዳች ሃይል ባይኖራት ይህን ሁሉ ማለፍ ትችል ነበር? ይህን ማስተባበል ቀላል አይደለም።

ነገር ግን ከላይ እንደገለፅኩት፤ በእርግጠኛነት “የአገሪቱን ህልውና ለዘመናት ጠብቆ ያኖረ አንዳች ሃይል አለ” ብንል እንኳ፤ መተማመኛ ሊሆነን አይችልም። እሺ... ያ የማናውቀው አንዳች ሃይል፤ “ድሮ ድሮ ህያው ሃይል ነበር” እንበል። ግን፤ በዘመናት ብዛት አርጅቶና ተዳክሞ፤ ተሸርሽሮና ተሟጥጦ፤ ተንጠፍጥፎ ካለቀለትኮ፤ ትዝታው ብቻ ነው የሚቀረው። ምንነቱን ካላወቅነው፤ ልናድሰውና ልናጠናክረው አንችልም። ስረመሰረቱን ካላወቅነው፤ ልንጠግነውና ልንገነባው አንችልም። እስካሁን የአገሪቱን ህልውና ሲጠብቅ የነበረው “አንዳች ሃይል”፤ ዛሬም ድረስ ህያው መሆኑን እስካላወቅን ድረስ፤ መተማመኛ ሊሆነን አይችልም።

እኔን እንደሚመስለኝማ፤ የኢትዮጵያን ህልውና ሲጠብቅ የኖረው አንዳች ሃይል፤ ጨርሶ የማይታወቅ አንዳች ሚስጥር አይደለም። ያ “ጥንታዊው ስልጣኔ” ነው፤ የኢትዮጵያ “አንዳች ሃይል”። ጥንታዊው ስልጣኔ ደግሞ ድሮ ተዳፍኖ ጠፍቷል። አንዳንድ የፅሁፍና የሃውልት ቅርሶች ብቻ ናቸው ዛሬ ድረስ የዘለቁት። ቅርሶች ግን፤ የስልጣኔ ውጤትና መታሰቢያ፤ የስልጣኔ ውጫዊ ገፅታና ማስታወሻ እንጂ፤ ህያው ስልጣኔን አይወክሉም። የአገር ህልውናም ተመሳሳይ ነው። በአንዳች ስልጣኔ ወይም ሃይል መነሻነት የተመሰረተው አገር፤ እንደ ቅርስ ለብዙ ዘመናት ሊቀጥል ይችላል - “አንዳች ሃይል” ብለን የምንጠራው ጥንታዊ ስልጣኔ ድሮ ጥንት የሞተ ቢሆንም።

 

 

Read 2875 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 10:02