Thursday, 20 August 2020 10:38

በሻሸመኔ በጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ቦምብ በወረወረ የኦነግ ሸኔ አባል ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(17 votes)

 

በሻሸመኔ ከተማ የውስጥ ለውስጥ የጸጥታ ስራን በማከወን ላይ በነበሩ ጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ቦምብ በወረወረ የኦነግ ሸኔ አባል ላይ እርምጃ መወሰዱን ፖሊስ ገለፀ። ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ተኩል አካባቢ በሻሸመኔ ከተማ 01 ወይም አዋሾ ቀበሌ አካባቢ የጸጥታ ሀይሎች አካባቢያዊ  ቅኝት ሲያደርጉ ነው ከድር ቱሌ የተባለ ግለሰብ የእጅ ቦምብ ወርውሮ ሊያመልጥ ሲል እርምጃ የተወሰደበት።

በዚህም የተጠርጣሪው ህይወት ሲያልፍ ቦምብ ከተወረወረባቸው የጸጥታ ሀይሎች መካከል በአንዱ ላይ ጉዳት ደርሶ ፣በመልክ ኦዳ ሆስፒታል ክትትል እየተደረገለት መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል፡፡  የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ፥ ከተጠርጣሪው እጅ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ መገኘቱን አስታውቋል።

ከድር ቱሌ የተባለው ይህ ተጠርጣሪ መታወቂያው የአርሲ ዞን ሸርካ ወረዳ ነዋሪ እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን፥ ሁለት ሞባይል፣ ገንዘብና ትጥቅ መያዣ ቀበቶ ይዞ ነበር ተብሏል። የከተማው ፖሊስ መምሪያ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሀይል እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል፤ እንደ ፋና ዘገባ፡፡ የሻሸመኔ ከተማ አሁን ላይ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ለወደሙና ጉዳት ለደረሰባቸው ድጋፍ የማድረጉ ተግባርም ተጠናክሮ ቀጥሏል ተብሏል፡፡

የከተማዋ ነዋሪ ከጸጥታ አካሉ ጋር ተናቦ እየሰራ ባለው ስራ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ያለው ፖሊስ፤ የተዘረፉ ንብረቶችም እየተመለሱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Read 8299 times