Print this page
Thursday, 20 August 2020 00:00

“መነሻችን መደመር፤ መጨረሻችን ብልፅግና ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ብልፅግና አማራ ክልል ላይ ነፍስ እየዘራ ነው
 
            - የአቶ ሽመልስ ንግግር በአማራ ብልጽግና ተገምግሟል
            - ስለ “ኮንፉዩዚንግ”ና ኮንቪንሲንግ” ምን አሉ?

       ከመምህርነት እስከ የአዴፓ ጽ/ቤት ም/ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ወራትን አስቆጥረዋል - አቶ ግዛቸው ሙሉነህ። ከትናንት በስቲያ ለሥራ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በወቅቱ የሀገሪቱ ፖለቲካ በክልሉ እንቅስቃሴ፣ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሰሞኑ አነጋጋሪ ንግግርና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ሰፋ ያለ ቆይታ ከአቶ ግዛቸው ሙሉነህ ጋር አድርጋለች እነሆ፡-


            ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የክልሉን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በመገደላቸው በክልሉ ላይ የስነ ልቦና ስብራትን ጨምሮ በርካታ ጫናዎች ደርሰው ነበር ያ ጊዜ እንዴታ ታለፈ?
እውነት ነው ያን ጊዜ የፓርቲ ፅ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ም/ኃላፊ ነበርኩ፡፡ እንግዲህ በለውጥ ሂደቱ ውስጥ ሁሉም እንደሚያስታውሰው ከሁለት ዓመት በፊት አጠቃላይ የነበረው ሥርዓት ችግር ገጥሞት ህዝቡና መሪው ድርጅት ውስጥ የለውጥ ሃይሎች ባደረጉት እንቅስቃሴ ወደ ለውጠ ተገብቷል፡፡ ለውጡም ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ ለውጡ ሲደረግ በአንድ በኩል ለውጥ የሚፈልገው ሃይል አለ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡ ጥቅሜን ያሳጣኛል የሚል ቡድንም አለ፡፡ ለለውጥ ሲባል ደግሞ በጣም በርካታ ሰው በነፃነት እንዲቀላቀል ነው የተደረገው፡፡ ለውጡ ሲመጣ ሪፎርም እንጂ አብዮት አይደም የተደረገው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ባህርዳር ብቅ ብለው ነበር:: ምክንያታቸው የዘንድሮውን የ5ቢ.አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ ማጠናቀቂያ ለማከናወን ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከችግኝ ተከላው ማጠናቀቂያ ባሻገር ለሌላ ፖለቲካዊ ዓላማ መምጣታቸውም ይነገራል?
ጥሩ! እንግዲህ የሰሞኑን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ ብልጽግና ፓርቲ እንደ ፓርቲ በየክልሉ ኮንፍረንስ እያካሄደ ያለበት ወቅት ነው፡፡ ኦሮሚያ ላይም ደቡብም በየራሳቸው እያካሄዱ ነው ያሉት፡፡ አማራም እንደ ብልጽግና ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ጉባኤውን እያደረገ ነበር:: የሁለት ቀን ኮንፍረንስ ነበረን፡፡ ያነሳሽውን ጥያቄ በቀጥታ ለመመለስ ዶ/ር ዐቢይ ሰሞኑን ወደ ባህርዳር መጥተዋል፡፡ የመጡት ግን በድንገት አይደለም፡፡ የመጡበት ዋና አላማ ቀደም ሲል የአረንጓዴ አሻራ በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር 5 ቢ. ችግኝ ለመትከል እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አማራ ክልል በዚህ መርሃ ግብር 190 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ቀን ተክለናል፡፡ መክፈቻውን ዶ/ር ዐቢይ ሃዋሳ አድርገውታል፡፡ መዝጊያው ደግሞ ባህርዳር ነበር የሚሆነው፡፡ በአጋጣሚ ይሄ የመዝጊያ መርሃ ግብር እኛ ከምናደርገው የብልፅግና ኮንፍረንስ ጋር ተገጣጠመ፡፡ ለእኛ ጥሩ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጠቅመንባቸዋል:: እንደ አማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩን መዝጊያ አድርገዋል፡፡ በብልጽግና ጉባኤም ላይ ለህዝቡ መልዕክት አስተላልፈዋል:: የብልጽግና ፕሬዚዳንት እንደመሆናቸው የጉባኤው ማጠቃለያ ላይ መጥተው መልዕክት እንዲያስተላልፉ ተጋብዘው ነበር፤ መጥተው ያንን አድርገዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር አለ፣ በማህበራዊ ሚዲያ የአማራ ብልጽግና አመራር ተከፋፍሏል፤ ሚስተር እከሌ “ይህንን አንስቷል፤ ሚስተር እከሌ ይህንን ሃሳብ አልተቀበለም” የሚል ነገር ተናፍሷል:: የተከፋፈለ አመራር የለም፡፡ የሚከፋፈልም የለም፤ በብልጽግና፡፡ ሃሳባችንና አጀንዳችን አንድ ነው፡፡ ዋነኛው አጀንዳችን ብልጽግና ነው አለቀ፡፡ መነሻችን መደመር፤ መጨረሻችን ብልጽግና ነው፡፡ ይሄው ነው፡፡ ሌላው አሉባልታ ነው፡፡
የሁለቱ ቀን ኮንፍረንስ ትኩረት ምን ምን ነበር?
ይሄ መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ በዋናነት በስብሰባው ላይ አጠቃላይ ለውጡን እንዴት እየተመራ ነው፡፡ ባለፉት አመታት በተለይም በዚህ ዓመት ለውጡን እንዴት መራነው? የህዝቡን ጥያቄ ወይስ የሚመልስ፣ ለህዝቡ ወገንተኝነት ያለው አመራር በክልሉ እውን አድርገናል ወይስ? አላደረግንም? ብልጽግና ፓርቲ እግር ተክሎ ለህዝብ ሰርቷል አልሰራም? በለውጥ ሂደት ውስጥ ውስጥ ከገጠመን ችግር እንዴት ነበር የወጣነው? ከልማት አኳያ ያረጋገጥነው ጥያቄ ምንድን ነው? አሁንስ በመሰረታዊነት የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? የሚሉት ተፈትሸዋል፤ ተገምግምዋል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ መድረክ ተገምግመው የተቀመጠው ድምዳሜ፤ ከለውጡ አኳያ በርካታ አወንታዊ እርምጃዎች ሄደናል። ለውጥ እየተመዘገበ ነው፤ በተለይም በዚህ ዓመት ከሰኔ 15ቱ ጥቃት በኋላ ከነበረብን አንጐቨር፤ ከነበረብን ወደ አዘቅት የሚያወርድ የስነልቦና ስብራት ወጥተን ህይወት ያለው አመራር ሰጪነት ለመፍጠር ጥረት አድርገናል። በተለይ በክልሉ ውስጥ የነበረውን የሰላም እጦት ወደ ትክክለኛ መስመር አምጥተነዋል። ይሄ በለውጥ አመራር ሰጪነት የመጣ ነው። በአማራ ብልፅግናና ከፌደራልም ካለን ግንኙነት ጋር ተያይዞ የፈጠርነው እውነታ ስለሆነ በቀላሉ የምናየው አይደለም። በተለይ ከአማራ ክልል አኳያ በጣም አንገብጋቢ ጥያቄ የነበረው የሰላም እጦት ነበር። እዛም እዚህም ግጭት ይነሳል፤ ሰው ይሞታል ይፈናቀላል። በሌላ አካባቢ የሚኖረው አማራ ሁሉ ጥቃት ይደርስበት ነበር። ይሄንን ሁሉ እንዴት ነበር የመራነው? ብለን ስንገመግም ከነበረበት የተሻሻለና ከፍተኛ እመርታ ያመጣንበት ነው። ምንም እንኳን የቀሩ ነገሮች ቢኖሩም፤ ከልማት አኳያም በርካታ ስራ ተሰርቷል። በተለይ በግብርናው መስክ፣ በመሰረተ ልማት፣ በማህበራዊ መስክ የተሰሩ በርካታ መልካም ስራዎች አሉ። እነዚህን አስመርቀናል። ውሃ፣ መንገድና በርካታ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል። የአማራ ህዝብ ያነሳቸውና በጥያቄነት ያቀረባቸው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ አንዱና ዋነኛው ነበር። ከዚህ አንፃር በተለይ በመሰረተ ልማት ብዙ ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው፡፡ በእቅድ የተያዙም አሉ። የተጀመሩም አሉ። ይሄ በኮንፍረንሱ በአዎንታዊ መልክ ነው የተገመገመው።
ሌላው የታሪክ ትርክት ነው። ከታራክ ትርክት አኳያ በአብዛኛው የአማራን ህዝብ ጠላት የሚያደርግና የተዛባ ትርክት ነው በአብዛኛው የሚታየው። ነገር ግን አሁን በብልፅግና ውስጥ ለውጥ ሲመጣ፣ ይሄ የታሪክ ትርክት መቀየር አለበት ብለን ቢያንስ አጀንዳ አድርገነው ይሄ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ የሚባለው ነገር ቢያንስ በሰነድ ደረጃ አይታተምም፡፡ ይህ እንግዲህ በአማራ ህዝብ ላይ የሚነገረውን የተዛባ ነገር ለማስተካከል የሚደረግ እንቀስቃሴ ነው። ቢያንስ ሌሎች ህዝቦች የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የቤኒሻንጉልና የሌሎችም ክልል ህዝቦች ይህንን አጀንዳ ማዳመጥ ጀምረዋል። የታሪክ ትርክቱ ስህተት እንዳለበትና መስተካከል እንደሚገባው ማመን ጀምረዋል። ለረጅም ጊዜ ሲዘራ የነበረ ዘር በመሆኑ በአንዴ ባይጠፋም አጀንዳ መሆኑም ትልቅ ነገር ነው። ሌላው የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ናቸው፡፡
የእነ ራያና ወልቃይትን ጉዳይ ማለትዎ ነው?    
እውነት ነው የነራያና ወልቃይት ጉዳይ ማለት ነው። ይሄ እስካሁን ያልተመለሰ ነገር ግን መመለስ እንዳለበት ፓርቲው አቋም ወስዷል። ሌላው ያልተፈታው የአማራ ህዝብ ጉዳይ የበጀትና የሀብት ምደባ ነው፤ ገና አልተቋጨም፡፡ በ1999 ዓ.ም የተደረገው የቤትና ህዝብ ቆጠራ ራሱን የቻለ ችግር ጥሎ አልፏል። እንደሚታወሰው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአማራ ህዝብ ተቀንሶ ነው የተቆጠረው፡፡ ከተቆጠረም በኋላ ዳታው በግባቡ ያልሰፈረበት በመሆኑ ይህንን የአማራ ህዝብ አጥብቆ እንደሚታገለውና ጥያቄው መመለስ እንዳለበት አቋም ተይዟል። ቀጣዩ የቤትና ህዝብ ቆጠራ እስኪደረግ ድረስ ይህን ታሳቢ ያደረገ ልዩ ሲስተም ተዘርግቶ፣ ክልሉ ሊደገፍ ይገባለ የሚል ውሳኔም ተላልፏል። ሌላው የጉባኤው አጀንዳ፣ የህገ መንግሥት ማሻሻል ጥያቄ ነበር። ህገ-መንግስቱ ሲረቀቅ የአማራ ህዝብ ውክልና አልነበረም፤ አልተሳተፉምም፤ ተገቢ ውክልና ያላገኘ ህገ-መንግስት በመሆኑ ከትርክቱ ጀምሮ አማራን ጨቋኝ የሚያደርግና በሌሎች ወንድም ህዝቦች እንደ ጠላት የሚያስቆጥር፣ የጨቋኝ ተጨቋኝ መጥፎ ሀሳብ የያዘ ነው። ስለሆነም ሙሉ በሙሉ ህገ-መንግስቱ ሙልጭ ብሎ ይውደቅ የሚል ሀሳብ የአማራ ህዝብ ባይኖረውም፣ ህገ-መንግስቱ ውስጥ መስተካከል ያለባቸው ጥያቄዎች አሉ። እነዚህም ተለይተው ተገምግመዋል። የዶ/ር ዐቢይ በጉባኤው ላይ መገኘትም ይህንን ማዕከል አድርጐ ማጠቃለያ ለመስጠት እንጂ ሌላ ተልእኮ የለውም።
የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ባደረገው ስብሰባ ብዙዎች ተገምግመዋል፡፡ አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች ከፓርቲው ውክልናና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ታግደዋል። በእናንተ በኩል በአመራሩ ላይ የተወሰደ እርምጃ አለ?
በዚህ ኮንፍረንስ ተሳታፊውም አመራር ነው:: በነገራችን ላይ ተጋባዥ እንግዶች ይኖራሉ። የወጣት አመራሮችም ተሳትፈውበታል። እስከዞን ድረስ ተሳታፊ ሆነዋል። ቅድም ያነሳሁልሽ የግምገማ ይዘቶች ናቸው ያሉት። እኛ አመራሩን ስንገመግመው፤ አሁን ላይ የብልፅግና አመራር ክልል ላይ ነፍስ እየዘራ ነው። ክልሉን ከነበረበት አዘቅት መንጥቆ እያወጣ ነው። ቀደም ሲል ሰው ዋስትና አጥቶ መንግሥት አለ የለም የሚል ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ፣ በኢመደበኛ አደረጃጀት ወደመመካት የደረሰበት ጊዜ ነበር። አመራሩ ከዚያ ሁሉ ነገር ህዝቡን አውጥቶ፣ ክልሉን አሁን ላለበት ደረጃ ያደረሰ በመሆኑ፣ በጣም ሰፊ ለውጥ በማምጣቱ በአዎንታዊ ሁኔታ ነው አመራሩ የገመገመው። ስለዚህ በዚህ ደረጃ እርምጀ የሚያስወስድ ግምገማ አልገመነምንም። ነገር ግን አመራሩ አሁንም ራሱን መፈተሽና የበለጠ መጠንከር አለበት። ምከንያቱም ምንም እንከን የለውም፤ ሙሉ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ጐጠኝነት አለ የለም የሚል አከራካሪ ሁኔታ ነበር፡፡ የት ጋ ነው ያለው? የሚል፡፡ ግን በግልፅ የሚታይ ጐጠኝነት የለም። የሚታዩ ችግሮችን በደረስንበት ጊዜ እናርማለን ሌሎች ቀጣይ መድረኮችም ይኖራሉ:: ይሄ ብቻ አይደለም ብለን ተስማምተናል፡፡ አመራሩ መስመር ካለፈ ለምሳሌ ሌብነት ካለ አንደራደርም፡፡ በአንድነት ጉዳይም እንደዙሁ በዴሞክራሲና በመደመር ጉዳይ ላይ ለድርድር አንቀመጥም፡፡ እነዚህን ዋና ዋና ፒላሮች አልፎ በተገኘ አመራር ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን።
ወደ ሰሞኑ አነጋጋሪ ጉዳይ እንምጣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከ7ወር በፊት አድርገውታል፡፡ የተባለ ንግግር ወጥቷል፡፡ ፓርቲያችሁ ንግግሩን አጀንዳ አድርጐ አልተነጋገረበትም?
የሽመልስ አብዲሳን ንግግር በማህበራዊ ሚዲያ እንደ ማንኛውም ሰው እኔም አይቼዋለሁ፤ አድምጨዋለሁ። እንዳልሽው ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ናቸው። ምን አይነት ሰው እንደሆኑ እናውቃቸዋለን። በብልፅግናም ውስጥ አብረን ነን። ቀጥታ ላነሳሽው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ጉዳዩን አይተነዋል። ነገር ግን ይሄ በጉባኤው ላይ ዋነኛ አጀንዳችን አልነበረም። ዋና ዋና አጀንዳዎቻችን ቀደም ሲል የዘረዘርኩልሽ ጉዳዮች ናቸው። ነገር ግን የሽመልስን ንግግር በተመለከተ ሰውየው እንዴት እንዲህ አይነት ንግግር ተናገሩ የሚል ጥያቄ ሰው ያነሳል። እኛም ዘንድ በእግረ መንገድ ተነስቷል። የሆነ ሆኖ ጉዳዩን በጣም አግዝፈንም በጣም አንኳሰንም አላየነውም። ነገር ግን እዚ ላይ የተገለፁት ንግግሮች ልክ አይደሉም።
ንግግሩን የአቶ ሽመልስ የግል ንግግር ነው ብላችሁ ነው የወሰዳችሁት ወይስ?
ላነሳልሽ ነው። ንግግሮቹ ትክክል አይደሉም:: የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የብልፅግና ፓርቲ አቋም ነው ብለንም አልወሰድንም። እንዲህ አይነት አቋምም ሊይዝ አይችልም። ምክንያቱም እንደ ብልፅግና ለውጥ እንዴት መጣ፣ የአማራ ህዝብ ምንድን ነው? ቋንቋው የት ላይ ነው ያለው የሚለው በግልፅ ስለሚታወቅ ማለቴ ነው። የአማራ ህዝብ ደግሞ የሞተበት ለውጥ ነው። ስለዚህ ንግግሩ ልክ እንዳልሆነ ገምግመናል:: የግለሰብም ቢሆን ቅድም እንዳልኩሽ፤ አቶ ሽመልስን በተግባር እናውቃቸዋለን።  ብዙ እየሰሩ ያሉ መሪ ናቸው። አሁን በቅርቡ እንኳን የሀጫሉን ሞት ተከትሎ እየደረሰ ያለውን ጥፋት፣ ህዝቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞትና መፈናቀል እንዴት አድርገው መልክ ለማስያዝና ህግ ለማስከበር እየሰሩ ያሉት ሥራ ለዚህ ማሳያ ነው። ከዚህ አኳያ ንግግራቸው ልክ አለመሆኑን ገምግመን፣ በራሳችን መድረክ ራሱ ብልፅግና ጉዳዩን ወስዶ እንዲገመግምና፣ እንዲያርም ግን አቅጣጫ ተቀምጧል።
ሰሞኑን የአማራ ብልፅግና አመራሮች ተከፋፈሉ የተባሉት በዚሁ በአቶ ሽመልስ ንግግር ጉዳይ ነበር? እናንተ ግን ምንም ክፍፍል እንደሌለ አስተባብላችኋል፡፡ ከእርሶ ልስማው ብዬ እንጂ…
በሽመልስ ንግግር ተከፋፈሉ የሚለው የማህበራዊ ሚዲያ አሉባልታ ነው። አሉባልታው አገር ለማተራመስ ተቀናጅቶ ነው ማህበራዊ ሚዲያው የሚሰራው። እኛ እንዲህ አይነቱን የመረጃ ምንጭም አናደርገውም። እንደነገርኩሽ ነገሩን አግዝፈንም አቅልለንም አላየነውም። ማንነታችንን እናውቃለን። በዚህ ለውጥ መምጣት ውስጥ ለውጡን እንደፈለጉ አድርገው እንደሰሩት የተናገሩበት ነው አንዱ ትክክል ያልሆነው ንግግር። በለውጡ ደግሞ የአማራ ህዝብና ፓርቲ ምን ያህል መከራውን እንደበላና ምን ያህል የህይወት መስዋዕትነትን እንደከፈለ ዓለምም አገርም የሚያቀው ነው:: ከዚህ አንፃር ንግግሩ ትክክል አይደለም፡፡ የፓርቲ አቋም ይሆናል ብለንም አናምናም። ይህንን በተመለተ ብልፅግና ፓርቲ ወስዶ እንዲገመግመውና እርምት እንዲደረግበት ተነጋግረንበታል። ንግግሩ ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለቤንሻንጉልም ለአፋሩም ለደቡቡም ትክክል አይሆንም ምክንያቱም ሌሎችም ለለውጡ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።
ሌላው በንግግሩ ውስጥ ያለውና ትክክል ያልሆነው “አሳምነንም አደናግረንም” የሚለው ነው። ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ እኛን “ኮንቪንስ” የሚያደርገን (የሚያሳምነን) የአማራ ህዝብ ጥያቄ ነው። ብልፅግና ላይ ያለን የአማራ አመራሮች ኮንቪንስ የሚያደርገን የህዝቡ የልማት ጥያቄ መመለስና እድገት ብቻ ነው። ወደ ለውጡ ስንገባም ህዝቡ ጥያቄው አልተመለሰም፤ የመልካም አስተዳደር ችግሩ አልተቀረፈም፡፡ ፖለቲካዊ ጥያቄው አልተመለሰም በሚል እንጂ ኮንቪንስ ያደረገን ሽመልስ ሊሆን አይችልም። ኮንፊውዝድ የሚሆንም የለም። በነገራችን ላይ እንደውም ሽመልስ እንደ ግለሰብ ራሱን ቢያይ ኮንፊዩዝድ የሚሆነው እሱ ይመስለኛል። ሽመልስ ስራው ጥሩ ነው እንደብልፅግናም የሚሰራው ጥሩ ነገር አለ ነገር ግን ንግግሩ ትክክል አይደለም። በእርግጠኝነት የምነግርሽ ግን የአማራን ህዝብ ጥቅምና ክብር በሚነካ በማንኛውም ነገር እንደማንደራደር አስምረን ነው የተወያየነው።
“አማርኛ ቋንቋ ወርዷል” ሲሉ የተናገሩትስ?
ለዚህ ነው ይታረም ያልነው። ዝርዝር ሁኔታው ውስጥ ላለመግባት ነውኮ ነገሩን በጠቅላላው የነገርኩሽ፡፡ በነገራችን ላይ “አማርኛ ወርዷል” ተብሎ በግምት የሚነገር ቋንቋ አይደለም። እንዴት ወረደ፣ በምን ምክንያት ወረደ የሚለው ጥናትና ትንታኔ ያስፈልገዋል። አማርኛ ሊወርድም አይችልም፤ በምንም አይነት ሊወርድ አይችልም። አማርኛ ብዙ ተናጋሪ እንዳለው እናውቃለን። ቋንቋ ሞተ የሚባለው ተናጋሪ ሲያጣ ነው፤ ሲተረጐም እኮ አማራ ጠፋ እንደማለት ነው። አሁን ላይ አማርኛ የሚናገር ጠፍቷል ወይ፤ የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛ አይደለም ወይ? ስለዚህ ነው ልክ አይደለም፤ መታረም አለበት የምንለው።
እንደው ይሄ ንግግር ከየት ሾልኮ የወጣ ይመስልዎታል?
ይሄ ጥናት ይጠይቃል። አንዱ ልብ መባል ያለበት፤ እንደውም ንግግሩ ከ7 እና 8 ወር በፊት የተደረገ እንደሆነ ነው የተገለፀው። አሁን በዚህ ሰዓት ለምን ወጣ? የሚለው ራሱን የቻለ አከራካሪ ጥያቄ ነው። ሌላ ግጭት መቀስቀሻ ነው። በደንብ መታወቅ ያለበት፤ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች እሳትና ጭድ እንደሆኑ ለዘመናት ሲሰበክ ነበር። የእነዚህ ህዝቦች አንድ መሆን የሚያስቀናው ቡድን አለ። የነዚህ ህዝቦች አንድ መሆን አገርን አንድ አድርጐ ለመምራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ምክንያቱም ብዙ የህዝብ ቁጥር አላቸው። አንድ ሲሆኑ አገርን አንድ ማድረግ ይቻላል። ሁለቱ አንድ እንዳይሆኑ ነው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ሲሰራ የነበረው። ሁለቱ እንዲጋጩ የሚሰራው ቡድን ደግሞ ለውጡን የማይልገው ቡድን ነው።
ይሄ ቡድን ማን ነው?
በአንድ በኩል ኦነግ ሸኔ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ የህወሃት ቡድን አለ። እነዚህ ሁለት ቡድኖች እጃቸው ሊኖር እንደሚችል መገመት ተገቢ ነው። ከዚህ ውጪ ሊሆን  እንደማይችል መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከትግራይ ክልል የልዩ ሀይል አባላት ከድተው ወደ አማራ ክልል እንደገቡ ይነገራል፡፡ እውነት ነው? እውነት ከሆነ ምን ያህል ናቸው?
ወደ 30 የሚሆኑ ሃይሎች ከትግራይ ወሰን አካባቢ እየሾለኩ መጥተዋል። ከነዚህ ውስጥ 20ዎቹ የታጠቁ ናቸው። እውነት ነው እነዚህን ሰዎች ተቀብለናል፡፡ እዚያው አካባቢ ብዙ ሳይርቁ ትጥቃቸውን አስፈትትን ሰዎቹን ተቀበለናል፡፡ ዜጐች ናቸውና።

Read 2450 times
Administrator

Latest from Administrator