Sunday, 23 August 2020 00:00

የፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞች የሸገር ፕሮጀክቶችን አደነቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  የአዲስ አበባን ገጽታ ይለውጣል የተባለው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት በሀገሪቱ ለሚከናወኑ ቀጣይ ልማቶች አነቃቂ መሆናቸውን ፖለቲከኞች  ገለፁ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነትና ልዩ ክትትል እየተከናወኑ በሚገኙ የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡት ፖለቲከኞቹ፤  ለአዲስ አበባ አዲስና የተዋበ ገጽታ የሚያላብሱ በመሆናቸው ሊደገፉ የሚገባቸው ናቸው ብለዋል፡፡
“አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ የፀዳችና ማራኪ መሆን አለባት የሚለው እሣቤ በሁላችንም ውስጥ አለ” የሚሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ፤ የተከናወኑት ስራዎችም በማይደበቅ ሁኔታ የሚያስመሰግኑ ናቸው ብለዋል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ረገድ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም የከተማዋን ጥንታዊ ቅርሶች በማይጐዳ መልኩ መከናወን እንዳለባቸው ግን አልሸሸጉም አቶ አዳነ፡፡
የከተማዋን ነባር ታሪክ የሚያሳዩ ቅርሶች እንዳይነሱና እንዳይበላሹ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ያሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፤ የሚሠሩት ፕሮጀክቶች የገንዘብ ምንጭም በግልጽ መታወቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
መሠረተ ልማቱን መስራትና ከተማዋን ማስዋቡ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበትን ያህል በሀገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እነዚህን ፕሮጀክቶች መልሶ እንዳያወድም አስተማማኝ የማድረግ ተግባርም ትኩረት እንዲሰጠው አቶ አዳነ ጠቁመዋል:: “በሀገሪቱ አውዳሚ እየሆኑ የመጡት የፀጥታ መደፍረሶች አስተማማኝ በሆነ መልኩ እልባት ማግኘት እስካልቻሉ ድረስ ፕሮጀክቶቹ አደጋ ላይ ናቸው” ሲሉ ያስጠነቀቁት ፕሬዚዳንቱ፤ መንግስት ከፕሮጀክቶቹ ጐን ለጐን የሀገሪቱን ፀጥታ አስተማማኝ በማድረጉ ረገድ መበርታት አለበት ብለዋል፡፡
የኢህአፓ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ተሰማ በበኩላቸው፤ የልማት ፕሮጀክቶቹ በአጠቃላይ በጐና መልካም መሆናቸውን ጠቁመው፤ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ግን እንዳሉ ይገልፃሉ፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ሀገራዊ አንድነትና ስሜት በመፍጠር ረገድ የጐላ ድርሻቸው እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፤ ቀደም ብለው ቢጀመሩ ኖሮ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከሩ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክቱ ነበር ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ሲተገበሩ ከቀዬአቸው እንዲነሱ የሚገደዱ ዜጐች ጉዳይም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ፡፡
ለተፈናቃዮቹ ተመጣጣኝ ካሣ ከመክፈል ጐን ለጐን፣ በዘላቂነት የተስተካከለ የህይወት ጐዳና ውስጥ መግባታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚሉት የኢህአፓ ሊቀመንበር፤ ፕሮጀክቶች ሲከናወኑ ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
የህብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው፤ የተሠራው ስራ ድንቅ መሆኑን ገልፀው፤  የዚህ ፕሮጀክት ሃሳብ ከየት እንደመነጨ እውቅና መስጠት ግን ይገባል ይላሉ፡፡
በተለይ የእንጦጦ ፕሮጀክት በ1988 ዓ.ም አሁን በተሠራበት መንገድ እንዲሠራ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ኮሚቴ አቅዶ እንደነበር ያወሱት አቶ ግርማ፤ ለሃሳቡ ባለቤት እውቅና መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
“ያም ሆኖ ፕሮጀክቱ አሁን የተሠራበት ጥራትና ፍጥነት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፤ ለዚህም ጠ/ሚኒስትሩ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ” ሲሉ ለዶ/ር ዐቢይ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል አሁን ሀገሪቱ ከምትገኝበት የማህበራዊና ፖለቲካዊ ውጥንቅ አንፃር 5 ቢሊዮን ብር መድቦ ይህን ፕሮጀክት ለማከናወን ቅድሚያ የመስጠቱ ጉዳይ ጥያቄ እንሚያጭርባቸው አቶ ግርማ ተናግረዋል፡፡
በፕሮጀክቱ በእጅጉ ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁት፤ አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር አለማየሁ አረዳ ፤ሀገሪቱ ብዙ ችግር እያለባት ለምን ይሄ ቀደመ በሚለው ሃሳብ እንደማይስማሙ ይገልፃሉ፡፡ “ባለችን ጊዜ ሁሉ ጥቅም የሚሰጥ ስራ ብንሰራ፣ ምን ልንፈጥር እንደምንችል ያሳየኝ ፕሮጀክት ነው” በማለት፡፡
“አዲስ አበባ እውነትም እንደ ስሟ እንደምትሆን ያመለከተኝ ፕሮጀክት ነው” ያሉት ዶ/ር አለማየሁ፤ በዚህ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግራ አጋቢ ሁኔታ ውስጥ ለመንፈስ ምግብ የሚሆን ነገር ተሠርቶ ሲታይ በጣም የሚያስደስት ነው ብለዋል፡፡
“አዲስ አበባ እንደዚህ ተውባ በማየቴ ደስተኛ ነኝ፤ መንፈሳችንንም የሚያጐለብትና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ሥራ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል - አንጋፋው ፖለቲከኛ፡፡
የሸገር ፕሮጀክት ሃሳብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚተገበር ያስታወቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በጐንደር ጐርጐራ፣ በኦሮሚያ ወንጪና በደቡብ ፕሮጀክቶቹ  እንደሚጀመሩ ይፋ አድርገዋል፡፡
እነዚህን ፕሮጀክት ለማከናወን 6 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉን “ገበታ ለሀገር” በሚል የራት መርሃ ግብር ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡    

Read 7902 times