Print this page
Monday, 24 August 2020 17:55

“ረሃብ ትችላለህን” ቢሉት፤ “ኧረ ጥጋብም እችላለሁ” አለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከለታት አንድ ቀን በትልቅነታቸው የተከበሩ፣ በየጊዜው በሚካሄዱ ጦርነቶች ድል በማድረጋቸው የተፈሩ፣ አንድ የድሮ ጊዜ ንጉሥ ነበሩ፡፡
ንግሥቲቱም እንደዚሁ፤ ንጉሡን በምክርም በማገዝ፤ በዘመቻ ጊዜ ስንቅ በማዘጋጀትም የመኳንንቱንና የመሳፍንቱን ሚስቶች አስተባብሮ በመምራትም በዙፋኑ ዙሪያ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡
ንጉሡና ንግስቲቱም በመዝናኛ በጨዋታ ጊዜያቸው፣ ወግ እየጠረቀ የግጥም ቃል እያዋጣ፣ ፈገግ ፈገግ የሚያሰኙ ቀልዶች አሰማምሮ በማቅረብ የሚታወቅ የንጉሥ አጫዋች ነበር፡፡ ንጉሡ ይጭኑት አጋሠስ፣ ይለጉሙት ፈረስ፣ ያጋጤቡት ወርቅ፣ ያስጥሉት ጠጅ፣ ያስጠምቁት ጠላ፣ የተትረፈረፋቸው ቢሆንም መንፈሳዊ ሃሴትን ይጉናፀፉ ዘንድ፣ ያ የንጉሥ አጫዋች ከምንም የሚበልጥባቸው ነውና እንደ አይናቸው ብሌን ይንከባከቡት ነበር፡፡ አንድ ቀን እንደተለመደው ግብር ገብቶ፣ ሰው ሁሉ በልቶ ጠጥቶ ከተሸኘ በኋላ፣ ልዩ አስተያየት የሚደረግላቸው የተባሉ የቅርብ የቅርብ ሰዎች ማለትም መኳንንቱና መሳፍንቱ እንዲሁም ባለሥልጣናቱ ልዩ መስተንግዶ ተደርጐላቸው በሉ ጠጡ፤ ተዝናኑ፤ ወደየማደሪያቸውም ተሸኙ፡፡
እነሆ የንጉሡና የንግሥቲቱ ማረፊያ ሰዓት ተቃረበ፡፡ በዚህ ሰዓት ግን በመካከል መላአከ ሞት በድንገት ተከስቶ በድግሱ አጠገብ ሲያልፍ፣ የንጉሡን አጫዋች ትኩር ብሎ አይቶት ይሄዳል፡፡
 ያ የንጉሥ አጫዋች ክፉኛ ልቡ ደነገጠ፡፡ ንጉሡና ንግሥቲቱ ወደ መኝታ ቤታቸው ይገባሉ፡፡ ድንክዬው የንጉሡ አጫዋችም ወደ መኝታው ይሄዳል፡፡ ሆኖም እንቅልፍ አልወሰደውም፡፡ ያስጨነቀው ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ወደ ንጉሡ መኝታ ቤት ሄዶ በሩን አንኳኳ፡፡
“ማነህ” አሉ፤ ንጉሡ
“እኔ ነኝ አጫዋችዎ”
ተነስተው አገኙት፡፡
“ምነው ምን ሆነሃል? አሉት”
“ዛሬ እያጫወትኮት ሳለ መላዕከ ሞት መጥቶ ትክ ብሎ አይቶኝ ሄደ፡፡ የምደበቅበት ቦታ ካላገኘሁኝ ይዞኝ ሊሄድ ነው የመጣው፡፡ ልቤ ክፉኛ ፈርቷል፡፡ ንጉሥ ሆይ፤ ያሽሹኝ እባክዎ!”
ንጉሡም ጥቂት አሰብ አድርገው፤ “ግዴለም በአሁን ጊዜ ሩቅ አገር ህንድ ነው፤ ነገ ጠዋት ወደዚያ ትሄድና ጥቂት ቀን ቆይተህ ትመለሳለህ፡፡ እኔም በፀሎቴ አምላኬን እማፀንልሃለሁ፡፡ በል አሁን ተረጋግተህ ተኛ፡፡” ብለው ወደ መኝታቸው ገቡ፡፡
ጠዋት የንጉሡ አጫዋች ተሰነዳድቶ ሲጨርስ መርከቡ መጥቶለት ወደ ህንድ አገር ተጓዘ፡፡
መድረሱን አረጋገጠ፡፡
ከዚያን ቀን ጀምሮ ነጋ ጠባ ያጫዋቻቸውን ነገር ለማወቅ ሌት ተቀን ፀሎት ማድረሳቸውን ተያያዙት፡፡
ከአንድ ሳምንት ምህላ በኋላ መላዕከ ሞት ተገለጠላቸው፡፡
“ንጉሥ ሆይ፤ ምን እርዳታ አስፈለግዎት?” ሲልም ጠየቃቸው፡፡
“ምነው? አጫዋቼን፣ መንፈስ መሰብሰቢያዬን፣ የቤተ መንግሥት መዝናኛ ፈጣሪዬን፣ የጭንቅ ጊዜ አንደበቴን ልትወስደው አሰብክ? አላሳዝንህምን?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
መላዕከ ሞትም “ንጉሥ ሆይ፤ እርግጥ ነው መጥቼ አይቼዋለሁ፤ ትኩር ብዬም አስተውዬዋለሁ”
“ታዲያ ስለምን ይዘኸው ልትሄድ አሰብክ?”
“እኔ ትኩር ብዬ ያስተዋልኩትኮ በአንድ ምክንያት ብቻ ነው፡፡”
“መላዕክ ሆይ፤ ያ ምክንያትህ ምን ይሆን?”
 “ንጉሥ ሆይ ትኩር ብዬ ያየሁት፣ እኔ ከአምላክ የታዘዝኩት ከህንድ አገር አምጣው ተብዬ ነው፤ እዚህ እየሩሳሌም ውስጥ ምን ያደርጋል ብዬ ነው!” አለ፡፡
እንግዲህ የንጉሥ አጫዋች ወደማይቀርለት ቦታ፣ ወደተፃፈለት ሥፍራ ሄዷለ ማለት ነው፡፡
*   *   *
ጐበዝ፤ “የተፃፈ ነገር ከመፈፀም አይቀርም” የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አለመዘንጋት ነው፡፡
እንቁ የልጅነት የሥነ ጽሑፍ አባታችን ደራሲ ከበደ ሚካኤል፤
“እንዲሁም በዓለም ላይ፣
አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ
ከመሆን የማይቀር!”
ሲሉ ጠቅለል አድርገው ገልፀውልናል፡፡ ምንም እንኳ ሰዋዊ በሆነው ተጨባጭ አለም የህይወት ነብር - ወገ ቢር ህሊናዊው (Subjective) እንዲሁም ነባራዊው (Objective) ብለን በመክፈል የሁለቱን ውህደት እንደ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተያያዥ መስተጋብር፣ ትርጉም ሰጥተን ለህልውናችን ፍቺ ለማድረግ በመሞከር የእጣ ፈንታን ፍፃሜ - ነገር ለማመላከት የሰው ልጅ ዓለም ከተፈጠረ፣ ታሪክ ከተጀመረ፣ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ እንደ ጣረ፣ እንደተፍጨረጨረ አለ፣ በመንፈስም በሥጋም ጽድቅና ኩነኔን፤ ክፉና በጐን “በተቃራኒዎች አንድነትና ትግል” መንዝሮ በተለያየ መንገድ ለማጤን ሲሞክር መኖሩ ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡
ከሰፊው ሁለንተናዊ ዓለም ወደ ጠባቡ ዓለም መምጣት አይቀሬ ነው፡፡ ዛሬ ከዓለም በታሪክ ታይቶና ሆኖ በማያውቅ መልኩ (unprecedented) የተከሰተ፣ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ፣ ጠቢባንን ሁሉ የተፈታተነ፣ ቀሳፊ በሽታ (ኮሮና) ሰለባ ከመሆኗ በመነሳት እንደ የኃይማኖቱ ፈርጅ በፀሎትና በምህላ እልባቱን መማፀን ከቤተሰብ ወደ ህብረተሰብ፣ ከሀገር ወደ ዓለም በሰፋ መልኩ ምኞትና ተስፋውን የሙጥኝ ማለቱን ሌት ተቀን ተያይዞታል፡፡ ይህም ግዴታ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ያም ሆኖ በሳይንሳዊ አመክኖዮአዊና ሥነ አዕምሮአዊ መንገድ የህክምና ቴክኖሎጂን እጅህ ከምን እና የየአቅምን ጥንቃቄና የችግር ማቃለያን መንገዶች ሁሉ መሻቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ጥናቱን ይስጠን!
አገራችንም በሽታው መግባቱ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ የተያዙ፣ ተገልለው ማቆያ ገብተው ተገቢው ክትትል የሚደረግላቸው፣ ያገገሙና ህይወታቸው ምን ደረጃ እንደደረሰ ያለፈውንና የአሁኑን ስታትስቲካዊ ቀመር ለማስቀመጥና የአቅምን ያህል እለታዊ ጊዜያዊ ዘገባ ማቅረቡ ፍፁም ባይባልም፣ እየተሻሻለና እድገቱ ለውጥ እያሳየ መምጣቱን፣ ቁጥሩ ግን እየበዛ መቀጠሉን የማሳወቅና መረጃ የመስጠት ተግባሩ የሚበረታታ ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆኖ የህዝባችን የአንድ ሰሞን ብቻ ስነስርዓት አክባሪነትና መመሪያ ተቀባይነት የጉዳዩን አሳሳቢነት በአስከፊ መልኩ እንድንታዘብ ያደረገ ሲሆን፤ አሌ የማንለው የችግር አሻራውን ተራራ አከል ደረጃ እየደረሰ መሆኑን ማጤን ተገደናል:: የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ውትወታዊ ማስጠንቀቂያውንና ትምህርታዊ ምክሩ ቢያታክትም፣ ዛሬም መደገሙ ተገቢ ነው እንላለን፡፡
በየቦታው የሚፈነዳው ግጭትና ሁከት፣ ነውጥና የመሣሪያ ዝውውር (የዕጽም ጭምር) ጐርፍ፣  በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡ “የምበላው ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ” እንደሚባለው ነው፡፡ ዛሬ ትምህርት በተቋረጠበት፣ ሥራ አገም ጠገም በሆነበት፤ ከኮሮና ውጭ ያሉ የሌሎች የበሽታ ሁኔታ አስጊ በሆነበት ሥራ አጥነትና መፍትሔው መላው በጠፋበት ሁሉንም ለማቃለል መሞከሩ ቢበረታታም፤ ችግራችን ዛሬም ጭንቅላት የሚያሲዝ ነው፡፡
“ግመሎቹ ይሄዳሉ ውሾቹ ይጮሃሉ” የሚለው የሚታይ ቢሆንም፤ ግመሎቹም አልቆሙም ውሾቹም ላንቃቸው አልተዘጋም፡፡ በየትኛውም መስክ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችም የመደራደሪያ ጠረጴዛ ከነመኖሩም አለ ብለው ማሰቡን ያጡት ይመስላሉ፡፡
ድርድርን የበላው ጅብ አልጮህ ማለቱ እርግጥ ነው፡፡ በአንፃሩ በሌላው ወገን ጭራሽ ዘራፌዋውም እንደቀጠለ ነው፡፡ ጐረቤት አገሮች በአባይ ግድብ አይናቸው እንደቀላ መሆኑ፤ አሳሳቢነቱን ጋብ አላደረገውም፡፡ በአንጻሩ ችግኝ መትከሉና ወቅቱን መሻማቱ ብልህነት ነው፡፡ በዚህ መሃል ስርዓተ አልበኝነትን በቅጡ መዋጋት ተገቢ ነው:: “ወንጀሎች ሌብነቶች፣ የችሎት ግቢ መጣበቦች ጥሩ ምልኪ መስለው አይታዩንም፤ ዲሞክራሲው ዛሬም ውጥር ግትር ነው፡፡ የእኩልነት የወንድማማችነት የመብትና ነፃነት ሁኔታ የልባችን ሞልቷል ማለት ገና አያስደፍርም፤ ሥር ነቀልና ጥብቅ ሂደትን ይጠይቃል፡፡ የግድቡ ሙሌት የአንድነት መንፈስ መፍጠሩን ማድነቅ ተገቢ ሆኖ፣ አሁንም ጥንቃቄንና በዓይነ ቁራኛ ማየትን ይሻል፡፡ የላዕላይ - መዋቅሩ የሥልጣን ሽግሽግ ከ1966ቱ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” የሚል መፈክሩ ወጥቶ እውነተኛ የለውጥ መንፈስ ማንገቡን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የዜሮ ድምር ጨዋታ እንዳልሆነ ያየነውን ያህል፣ የፓርኮች፣ የቅርስ ቦታዎችና ልዩ ልዩ የቱሪስት መስህቦች ህልውና ላይ ትኩረት መስጠቱ ይበል ማሰኘቱን በአጠቃላይ አዎንታዊ ጉዳዮች አንፃር አጥጋቢ መሆኑን ስናይ፤ “ረሀብ ትችላለህን?” ቢሉት” ኧረ ጥጋብም እችላለሁ አለ” የተባለውን ተረት ሳንዘነጋ፤ መሬት በረገጠ መልኩ መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡


Read 10376 times
Administrator

Latest from Administrator