Sunday, 23 August 2020 00:00

"የዝሆን አይነ ምድር ኮሮናን ያድናል" በሚል በውድ እየተሸጠ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት በተዳረጉባት ናሚቢያ፣ ከሰሞኑ የዝሆን አይነ ምድር ለኮሮና ቫይረስ ፍቱን መድሃኒት ነው የሚል ያልተጨበጠ መረጃ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ፣ ነገርዬው በውድ ዋጋ በመሸጥ ላይ እንደሚገኝና በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መሻማት መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡
የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ወር ብቻ በእጥፍ በጨመረባትና ስጋት ባየለባት በናሚቢያ የሚገኙ የባህላዊ ህክምና ባለሙያዎች የዝሆንን አይነ ምድር መታጠንና ማሽተት ለጉንፋን፣ ለነስር፣ ለራስ ምታትና ለሌሎችም የጤና እክሎች ፍቱን መድሀኒት እንደሆነ ሲናገሩ መቆየታቸውን የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፤ ከሰሞኑ ደግሞ በማህበራዊ ድረገጾች ነገርዬው ከኮሮና ያድናል የሚል መረጃ መሰራጨቱንና ብዙዎች መሻማት መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡
ከ4 ሺህ 464 በላይ ሰዎች በኮሮና የተጠቁባት ናሚቢያ የጤና ሚኒስትር ካሉምቢ ሻንጉላ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ ዜጎች ባልተረጋገጠ መረጃ ተገፋፍተው ከኮሮና ቫይረስ ለመዳን ሲሉ ላልተገባ ወጪ በመዳረግ የዝሆን አይነ ምድር መጠቀማቸውን እንዲያቆሙ ማሳሰባቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ለሌላ የጤና እክል እንዳይጋለጡ ያላቸውን ስጋት መግለጻቸውንም አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሮሚዮ ሙዩንዳ በበኩላቸው፤ የዝሆን አይነ ምድር ፍለጋ የአገሪቱን ብሔራዊ ፓርኮች ጥሰው በመግባት ላይ የሚገኙ ዜጎች፣ ከዚህ ድርጊታቸው ካልታቀቡ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቃቸው ተነግሯል፡፡


Read 1128 times