Monday, 24 August 2020 00:00

የልዕልናና የትሕትና ተምሳሌት ወርኀ ነሐሴ

Written by  በአዲሱ ዘገየ
Rate this item
(0 votes)

"--ነሐሴ በአብዛኛው የሀገሬው ማኅበረሰብ ዘንድ የዐረም ሥራ ይሰራባታል፡፡ የነሐሴ ግብር ዐረምንና የተማሩትን ማረም ይሆናል፡፡ ዐረምን መንቀል ወይም ማስወገድ ማለት ደግሞ፣ ክፉ/እኩይ አሉታዊ ባህርይን ነቅሎ ማስወገድ ማለት ነው፡፡ ዐረመ፤ ኮተኮተ፣ ነቀለ፤ ግድፈትን መላ፤ ትርፍን አስገለለ የሚል ፍቺ አለው፡፡ ዐረም ሁለት የሙያ መስኮችን ያስታውሳል፤ የተማረን ያልተማረን፣ የሚጽፍና የማይጽፍን፣ የቃልና የጽሑፍ ሰው መሆንን ወዘተ፡፡"
             

            “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር” የሚል አባባል አለ፡፡ እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት፤ የጌታ ኢየሱስ እናት ማርያም ዕለተ ረፍት ጥር 21 ቀን ሲከበር በዓለ ክብሯ አስተርእዮ ይሰኛል፤ ይኸውም ረፍቷ የታየበትና የተገለጠበትን ሁኔታ ይገልጻል፡፡ “እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ፣ ገብስ የሚደርሰው ለፍልሰታ” ሲባል ፍልሰታ ማለት ባንድ ወገን መፍለስ፣ መነቀል፣ መውጣት፣ መሰደድ ማለትን ያሳያል (ከምድራዊ ዓለም ወደ ሰማያዊ፣ ከሥጋዊ ወደ መንፈሳዊ)፡፡
ፍልሰታ ከነሐሴ 1-16 ቀናት ያሉትን ወርኀ ጾም የምትወክል ስያሜ ናት፡፡ በዚህችም ባንድ ወገን የገብስ አዝመራ መድረሱን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ያዘረዘረውን የገብስ እሸት ከመመገብ በፊት በጾሙ ጊዜያት ከምግብ መከልከል ያለ መሆኑ ይታይባታል:: የማርያም ሥርዓተ ቀብር በነሐሴ 16 ቀን እንደሚከበር ሰነዶች ያወሳሉ፡፡ ቀብር ሲባልም ነሐሴ 16 የሚከበርላት ምክንያት እመቤታችን ከመቃብር ተነስታ ወደ ሰማይ የመውጣቷንና የማረጓን ክስተት ለመዘከር ነው፡፡ በዚህቺ ምርጥ፣ ልዩ፣ ቅዱስ የበዓል ክብር ላይ የሀገሬው አርሶ አደር እጁን ከዕርፍ ይለያል፤ በዚህችውም ዕርፍ መጣያ ቀን አድርጎ ያከብራታል ማለት ነው፡፡ ፍልሰታ፣ ዕርፍ ከእርሻ ተለይቶ የሚቀመጥባት ቀን ናትና፡፡
ከላይ በምሳሌያዊ ንግግሩ የተወሱ ሁለቱ ወራት ማለትም ጥር እና ነሐሴ እትማማች ናቸው፡፡ እትማማች ያደረጋቸው ደግሞ ዕለተ መባቻቸው በተመሳሳይ ቀን መከበሩ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ተመጋጋቢ፣ ተሟሟይና ተቀራራቢ ዓመታዊና ወራዊ ክብረ በዓላት በጋራ መዘከራቸው ነው:: ከእነዚህ አንዱ ከላይ የቀረበው የሞትና የቀብር ኩነት አንድነታቸውን ያሳያል፡፡ በዚህ ፍቺ ቀብር ጉድጓድ መውረድ ሳይሆን ወደ ሰማይ መውጣትን ወይም ዕርገትን/ልዕልናን፣ ሉዓላዊ ማዕረግን ያመለክታል፡፡
ሁለቱን ወራት ለማነጻጸር ያህል ጉልህ ያንድነት መልኮችን ብቻ ማውሳት በቂ ነው:: ስለዚህ በወርኀ ጥር ከሚከበሩ በዓላት መካከል ጥር 6 ቀን ግዝረተ-ኢየሱስና የኤልያስ ዕለተ ዕርገት ሲከበርባት፣ በነሐሴ 16 ቀን ከሚከበረው የማርያም ዕርገት ጋር ይናበባል፡፡ ጥር 7 ቀን ደግሞ ሦስቱ ሥላሴ የባቢሎን ግንብ/ሠገነት፣ ፎቅ ያፈረሱበት በዓል ስትወክል፣ በአንጻሩ ነሐሴ የሚለው ቃል ፍቺ ፎቅ በፎቅ ላይ መገንባትን፣ ወደ ሰማይ መውጣትን ታሳያለች፡፡ ከዚህ ባሻገር በነሐሴ ወደ ሰማይ ያረገችው ማርያም የተጸነሰችበት ዕለት ናት፡፡
ጥር 10 ቀን ውሃን በማቋቻ፣ የመገደብ፣ የመከተር ሥራ የተሰራባት ሲሆን፣ በቀጣዩ ጥር 11 ደግሞ የኢየሱስ ጥምቀት፣ ጥር 12 ኢየሱስ በሠርግ ቤት ተገኝቶ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ የለወጠባቸው ዕለታት ይከበራሉ፡፡ በአንጻሩ ወርኀ ነሐሴ የውሃ ወር ናት፡፡ በከፊል የወሯ መጋቢ ስንቡላ ኮከብ ስትሰኝ፣ ሰንቢል የመጠጥ እሸት ማለት ናት፤ ይህቺ የመጠጥ ዓይነት በጅምር በመብሰል ደረጃ ያለች ግን ያልተጣራች ጉሽ ማለት ናት:: ከዚህ በተጨማሪ ስንቡላ ጋሬዳ ማኅበራዊ ድግስ ማለት ስትሆን (የሠርግ ቤት ድግስ መሳይ) ግን መናኛ፣ ቀጭን የመጠጥ ዓይነት ታሳያለች፡፡
ከተራ የሚለው ቃል የውሃ ማቆር ሂደትን የሚገልጽ እንደ መሆኑ ሁሉ፣ ወርኀ ነሐሴ ግድብና ፎቅ መገንባትንና ውሃን ለመገደብ ትመረጣለች፡፡ ጥምቀት የሕዳሴ፣ የለውጥ፣ የትምርት ተምሳሌት እንደ ሆነች ሁሉ፣ በነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው የደብረ ታቦር ተራራ ከፍ ከፍ ማለትን፣ መክነፍን፣ ማረግን፣ ትምርትን፣ ብርሃንን ወዘተ ይወክላል፡፡
ጥር 18 ቀን ሰበር/ዝርወተ-አፅሙ ለጊዮርጊስ ይከበራል፤ በነሐሴ 16 ቀን ደግሞ በተመሳሳይ የማርያም ዕርገትና ፍልሰተ-ዓፅሙ ለጊዮርጊስ ይከብርበታል፡፡ ጥር 21 ቀን አስተርእዮ ማርያም የማርያምን ዕለተ ረፍት ስትወክል፣ በአንጻሩ ነሐሴ 7 በጽንሰቷ፣ ነሐሴ 15 በረፍቷ ምክንያት የሐዋርያትን ስብሰባ፣ ነሐሴ 16 ቀን ዕርገቷ፣ ነሐሴ 21 ቀን የንግሥት-ኢሌኒና ንግሥተ-ሣባ ልደት ይከበሩባቸዋል፡፡ ጥር 22 ቀን መልአኩ ኡራኤል የተሾመባትን በዓለ ንግሥ ስትይዝ፣ ኡራኤል የጥበብና የዕውቀት ጽዋዕ ያጠጣልና፣ ከነሐሴ 13 አቻው የደብረታቦር በዓል፣ የማርያም ዕርገት፣ የነሐሴ ሠገነት፣ የአንስት ነገሥታት በተለይም ጥበብን ፍለጋ ንጉሥ ሰሎሞን ዘንድ የተጓዘችው ንግሥት ሣባ፣ የጥበብ ኀሠሣ አጀማመር ወይም ልክፍት ጋር ማቆራኘት ይቻላል፡፡ በተቃራኒ መልኩ ወርኀ ሐምሌ ላይ (ሐምሌ 5) ቀን ሥርዓተ-ሲመታቸው የተከበረላቸው አቡነ ጳውሎስ ነሐሴ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕለተ ረፍታቸው ሲነገር፣ ከጥር 29 ቀኑ የአቡነ ታዴዎስ ረፍት ጋር ማነጻጸር፤ ዕለተ ልደቱ ወረፍቱ አወዛጋቢ የነበረው የቀድሞው ጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ዕለተ ረፍቱ በመገናኛ ብዙኀን የታወጀው ነሐሴ 15 ቀን በማርያም ረፍት ምክንያት ሐዋርያት ከተሰባሰቡበት በዓል ጋር ባንድነት ተከብሯል፡፡
ወርኀ ነሐሴ ያዘለችው ትርጉም አንድም፣ ናሴ በሚል ስያሜዋ መጨረሻ፣ መደምደሚያ፣ መካተቻ፣ ማብቂያ አጋጣሚንና ክስተትን ትወክላለች፡፡ አንድም፣ ናሕስ፤ ናስ ግንብ መደብ፡፡ ደርብ፣ ሰገነት፣ ተሥላስ፣ መረባ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ…ወዘተ ቁመት በማሳከል ቤትና ፎቅን መገንባትን፣ መደረብን፣ ላይ በላይ መካብን፣ መደርደርን ታሳያለች፡፡ በሌላ የቃሉ ፍቺ ደግሞ የግንብ ጣራ፣ ባጥ፣ ጠፈር፣ መዋቅር፣ ቅስት፣ ዕቅድ በስተላይ ያለው (ከአፈር፣ ከመሬት፣ ከኖራ፣ ከሣር፣ ከገል፣ ከቆርቆሮ ከሸራ፣ ከላስቲክ፣ ከድንኳን ወዘተ) መከደንን ጉልላትነትን፣ ቁንጮነትን አመልካች ትርጉም ይዛለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የልብስ ዘርፍ ጫፍ፣ ክፈፍ ናሴ ትሰኛለች፡፡ ወርኀ ናሴ የመስከረም 12ኛ ተራን፣ መደምደሚያ ላይ መገኘትን፣ ፍጻሜን ታወሳለች፡፡
በአበገደ የፊደል ተራ መሠረት አስራ ሁለተኛዋ ፊደል ላሜድ ትሰኛለች፡፡ ላሜድ ስመ ፊደል ናት፡፡ ትርጓሜዋም የአሌፍ 12ኛ ፊደል ማለት ናት፡፡ ፍችዋም ተማሪነት ወይም ምሁርነት ባንድ ወገን፣ ጀማሪ ተማሪና ምሁር በሌላ ወገን ማለት ናት፡፡ ላሜድ የሚለው ፊደል ወደ ልምድ ወይም ተልሚድ ይወስዳል፡፡ የተልሚድ ፍችም ተማሪ ደቀመዝሙር ማለት ነው፡፡ የተማረና የተመራመረ እንደማለት፡፡ 12 ማለት 12 ናት፤ ሁለቱ የአኃዝ ወኪሎች እርስ በርስ ሲደመሩ ማለትም 1 + 2 = 3 ይሰጣሉ፡፡ የአስራ ሁለት ቁጥር ተምሳሌታዊ ፋይዳ ያንድን የጊዜ መጠን ፈረቃ ማብቃት፣ መቆረጥ፣ መፈጸም፣ መደምደም እንዲሁም የአዲስ ሕይወት ጅማሮ ዋዜማን ታመላክታለች፡፡
ነሐሴን በመጋቢ ኮኮቦቿ በመመራት ስትፈከር የሚከተሉትን ያንድነት መልኮች ከእህቷ ጥር ትዋሳለች፡፡ ነሐሴን ወይም ናሴን በከፊል የአሰድ እሳት ባህርይ፣ በከፊል ደግሞ የስንቡላ መሬት ባህርይ እየተፈራረቁ ይገዟታል፡፡ ወቅቱ ደግሞ የውሃ ባህርይ የነገሠበት ነው፡፡ ውሃ ከእሳት ጋር በጽሩይነት ወይም በብርሃናማ መልክ፣ ከመሬት ጋር ደግሞ በቀዝቃዛነት ትዛመዳለች፡፡ ወርኀ ጥር በሐጋይ/በጋ ወቅት የሚታወቅ ባህርይን ትይዛለች፡፡ ይኸውም የጸሐይን መግረር፣ መጠንከር፣ ማንጸባረቅ የምትገልጽ ወር ስትሆን፣ የወሯ መጋቢ ኮከብ ደግሞ ውሃ ቀጂ፣ ከታሪ፣ አቋች አካልን ታሳያለች:: ይህቺው በአንጻሯ ወደ ነሐሴ/ክረምት ወራት ወርዳ ወቅቱን በውሃ ግዛት፣ ወሩን በከፊል በእሳት፣ በከፊል በመሬት የከዋክብት ምግብና ትገዛለች፡፡ ይህም የወራቱን የዝምድና መልክ ማመላከቻ አብነት ነው፡፡
ነሐሴ በገዥ ኮከቦቿ እሳትና መሬትነት እሳቱ የተስፋ፣ የዕውቀት፣ የብርሃንና የምሥራች ዋዜማና ተምሳሌት ያደርጋታል:: ነሐሴ በከፊል እሸት አዝላ፣ አበባ ታቅፋ፣ ስትታይ ዐተር አብቦባት፣ ገብስ ዘርዝሮባት ትታያለች፡፡ ይህቺ ወርም ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት በየፊናቸው ደመናውን፣ ጉሙን፣ ጭጋጉን፣ ጭፍናውን እየሾለኩ አልፎ አልፎ ምድርን ሲያበሩ፣ ሲያሞቁና ሲያረጉ ታሳያለች፡፡ እንዲሁም መሬታዊው ኮከቧ በሐምሌ ስትዋልል አልረጋ ብላ የቆየች መሬት መርጋት፣ መምጠጥ፣ መድረቅ ወዘተ አኳኋኖችን ማስተናገዷ የተፈጥሮ ሐቅ ነው (በተለይ በእኛ አካባቢ)፡፡ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት፣ እንዲሁም አሰልቺው የክረምት ዝናብ ከቡሄ በኋላ አይኖሩም ተብሎ በሀገሬው ዘንድ ይታመናል፡፡ ስንበል ከሰብለ ይወጣል፤ ፍችውም ሰብል መሆን መዘርዘር፣ መውለድ መጨርቋት፣ መሸት፣ ማፍራት፣ ፍሬ መያዝ፣ መሸከም ነው፡፡ የእሸት ፍሬ፣ ዛላ፣ እልፍ ዝሪት፣ አዝመራ፡፡ ሰንበል፤ እሸት፣ የእሸት፣ ዛላ፣ ነዶ፣ ጥይት:: ሰንቢል የመጠጥ እሸት፤ ዝርዝር መጠጥ፤ ጉሽ፡፡ ጋሬዳ ማኅበራዊ ድግስ፡፡ ስንቡል ሰንበልት፤ ጥሩ ሽቶ ናርዶሳዊ ከዕጣን አንዱ ወይም ዛጎል የባህር ሽቱ፡፡ ስንቡላ ለ12 የኮከብ መናዝል አንዱ፤ ሽቱ የሽቱ ዛላ፣ ሽቷም ማለት ነው፡፡ የሽቱ ቡቃያ፣ ቅጠል፤ የባሕር ዛጎል፣ ባሕረ ወጥ ሽቱ ማለት ነው፡፡
ከላይ የቀረበው ፍቺ የውሃማነት፣ የነፋሳማነት፣ የመሬታማነትና የእሳታማነት ባህርያትን ባንድነት ማስተናገድ ይዟል፡፡ ወርኀ ነሐሴ በተማረው ወይም ባልተማረው የሀገሬው ዜጋ ግብር/ተግባር አንጻር ትገለጻለች፡፡ በዚህም የሚማረውን ባርባ ቀናት ለማስተማር፣ የማይማረውን ደግሞ ባርባ ዓመቱ እንዳይማር ትወስናለች:: የደብረ ታቦርን ክስተት ብናስብ እንኳ የሚገባቸው፣ የማይገባቸው፣ የሚባንኑ፣ የማይባንኑ፣ ማገዶ ፈጂ፣ ማገዶ ቆጣቢ ወዘተ ተማሪዎች መኖራቸውን ያረጋግጣል፡፡ በዚህ የተነሳ በመባነንና ባለመባነን የሚመረጡና የማይመረጡ እንዳሉ ማመላከቻ ናት፡፡
ነሐሴ በአብዛኛው የሀገሬው ማኅበረሰብ ዘንድ የዐረም ሥራ ይሰራባታል፡፡ የነሐሴ ግብር ዐረምንና የተማሩትን ማረም ይሆናል:: ዐረምን መንቀል ወይም ማስወገድ ማለት ደግሞ፣ ክፉ/እኩይ አሉታዊ ባህርይን ነቅሎ ማስወገድ ማለት ነው፡፡ ዐረመ፤ ኮተኮተ፣ ነቀለ፤ ግድፈትን መላ፤ ትርፍን አስገለለ የሚል ፍቺ አለው፡፡ ዐረም ሁለት የሙያ መስኮችን ያስታውሳል፤ የተማረን ያልተማረን፣ የሚጽፍና የማይጽፍን፣ የቃልና የጽሑፍ ሰው መሆንን ወዘተ፡፡ ዐራሚ፤ የሚያርም፣ ያረመ እህልን መጻፍን ማለት ነው፡፡ ዐረም ከቡቃያ ውስጥ የሚነቀል በያይነቱ ቅጠልና ሳር ማለት ነው፤ ወደ ልዕልና ለመውጣት የሚያሳንሱ ባህርያትን ማስወገድ ማረም ይሰኛል፡፡ አልያ ዐረም ተጫነበት ያስብላል፡፡ ዐረም ሲጫን ደግሞ መደበቅ፣ ኅቡዕ መሆን፣ መሠወር ያስከትላል፤ በተለይም ነውርና ገመናን:: ማረም ፋይዳው መንቀል ማስገለል፣ ማስተካከል ማጽዳት ነው፡፡ ማረሚያ፤ ያረም መንቀያ ዶማ መኮትኮቻ፤ የጽፈት ማስተካከያ ቀለም ብርዕ፣ እርሳስ ይወክላል:: ማሳ፣ ደብተር፣ ሥራ፣ ይታረማሉ፡፡
ወርኀ ነሐሴ ከጾመ ፍልሰታ ጋር እኒህ ተግባራት ቢሳኩ ወሯን ምርጥ ያደርጋታል:: አንደኛው የደብረታቦር ተማሪዎች እንደሚያደርጉት የገበሬን ማሳ ማረም:: ሁለተኛ የተማሪው ትምርት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ መገምገም ናቸው:: አሳረመ፤ ዐረምን አስነቀለ፣ አስኮተኮተ፤ የመጻፍን የደብዳቤን ቃል ጉድለት አስመላ:: ታረመ፤ ተተወ፣ ተከለከለ፣ ተለየ፣ ተቀደሰ፡፡ ተነቀለ፣ ተኮተኮተ፣ ተወገደ፣ ጸያፉ፣ ስተቱ፣ ግድፈቱ፡፡
በመጨረሻም፣ ወርኀ ጥር ወነሐሴ መማሪያ፣ ርኩስ-ከቅዱስ መለያ፣ የልዕልና-ወትሕትና ማዕረግ ማሳያ፣ የመምህርና ደቀመዝሙር መተካከያ መውጫና መውረጃ መሰላል ናት፡፡ ብንኖር የሁለቱን ወራት ዓለማቀፋዊ ዋጋ እናያለን፡፡

Read 1194 times