Friday, 28 August 2020 00:00

የአቬሴና የልደት ቀን - የኮሮና ወረርሽኝን ለሚፋለሙ የህክምና ባለሙያዎች ዝክር መዋል ያለበት ቀን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በአሁኑ ወቅት የጤና ባለሙያ ሠራተኞቻችን በመላው ከተማችን፣ አገራችንና ህዝባችን ውስጥ በፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) በሽታ ፊት ለፊት በግንባር ላይ እየተፋለሙት በመላው ዓለም በዚህ ታይቶ በማይታወቅ ቀውስ ራሳቸውን ለዚህ ቫይረስ አጋልጠው ይገኛሉ፡፡
ሀኪሞቻችን፣ ነርሶቻችን፣ የላብራቶሪ ቴክኒሻኖቻችን፣ የአምቡላንስ ሹፌሮች እና የመጀመሪያ መልስ ሰጪዎች ፣ የፋርሚሲ ባለሙያዎቻችንና እያንዳንዱ ለበሽተኞች እንክብካቤ ድጋፍ የሚያደርጉ ሁሉ በዚህ ክፉ ቀን ለችግሩ ምላሽ እየሰጡና በእጅጉ ተጋላጭ ለሆነው የህብረተሰባችን ክፍል እንክብካቤም በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በየዕለቱና በተለይም በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ለምትከፍሉት መስዋዕትነት ከሁሉም ወገን ምስጋና ይድረሳችሁ! ለታታሪነታችሁ ለቁርጠኝነታችሁ፣ ለፅናታችሁና ለጀግንነታችሁ የእኛ ጥልቅ ምስጋናና አድናቆት ሊቸራችሁ ይገባል:: ለበሽተኞች የምትሰጡት አገልግሎት የአያሌዎችን ነፍስ እየታደገና ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣ ነው፡፡
በዚህ ዓመት በተለይም ውድ ወገኖቻችንን ሲንከባከቡና ሲደግፉ እንዲሁም አገራችንን በማራመድ ተግባር ላይ ተሰማርተው ሳለ፣ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን የተነጠቁ የግንባር ሠራተኞቻችንን እንዘክራለን - እናስታውሳለን፡፡
በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ህይወታቸውን የተነጠቁ ሠራተኞችን (ነርሶቻችን፣ ሃኪሞቻችን፣ የእንክብካቤ ባለሙያዎቻችንና ሌሎች ቁልፍ ሠራተኞቻችንን) ውለታ መቼም ቢሆን አንዘነጋውም - ሁሌም ባለ ዕዳ ነን!

አቡ አሊ ሲና (አቬሴና) ማነው?
አቡ አሊ ሲና በስፋት የሚታወቀው አቬሴና በተባለው የላቲን ስሙ ሲሆን የፐርሺያ ሃኪምና ፈላስፋ ነበር፡፡ በቡኻራ በ980 የተወለደው አቬሴና፤ በ1037 በኢራን ሃማዳን ውስጥ ነው ያረፈው፡፡ በዘመኑ እጅግ ታዋቂና ስመ-ጥር ሃኪም፣ ፈላስፋ፣ የኢንሳይክሎፒዲያ ቀማሪ፣ የሂሳብ ሊቅና የህዋ ተመራማሪም ነበር፡፡
ወደርየለሽ የማስታወስ ችሎታ የተቸረው ህፃኑ አቬሴና፤በ10 ዓመቱ በቁራንና በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች ጥናት በእጅጉ የተካነ ነበር፡፡ ፍልስፍና ማጥናት የጀመረው የተለያዩ የግሪክ፣ ሙስሊምና ሌሎች ፅሁፎችን በማንበብ ነው፡፡ ሎጂክና ሜታፊዚክስ ከስራቸው ቁጭ ብሎ ያስተማሩትን መምህራን፣ በዕውቀት ለመላቅም ፋታ አልወሰደበትም፡፡
ከዚያ በኋላ፤ 18 ዓመት እስኪሞላው ድረስ ራስን በማስተማር ሥራ ላይ ተጠምዶ ቆየ፡፡ ከፍተኛ የንባብ ፍቅርና ጉጉትም ነበረው፡፡ በዚህም በእስልምና ህግና በህክምና ሙያ፤ በመጨረሻም፣ በሜታፊዚክስ የተካነ ለመሆን በቅቷል፡፡  ወጣቱ ሃኪም በ17 ዓመቱም የቡኻራ ንጉስ የነበረውን ኑህ ኢብን ማንሱር፤ በወቅቱ አሉ በተባሉት ሃኪሞች  እንደማይድን ይቆጠር ከነበረ በሽታ በማከም ፈውሶታል፡፡
ንጉሱ ከበሽታው ማገገሙን ተከትሎ፣ ወጣቱን ሃኪም ሊሸልመው ፈልጐ ነበር፤ ነገር ግን አቡ አሊ ሲና የንጉሱን በመፃሕፍት የታጨቀ ቤተ መፃሕፍት ለመጠቀም እንዲፈቅድለት ብቻ ነበር የሻተው፡፡ ለዚህ የበለፀገ የሳማኒድስ (ከአረብ ወረራ በኋላ በኢራን የተነሳ የመጀመሪያው ታላቅ አገር በቀል ሥርወ መንግስት) የንጉሳዊ ቤተመፃሕፍት ተደራሽ መሆኑ - በተለይም ለምሁራዊ ሰብዕናው መበልፀግ አጋዥ ነበር:: 21 ዓመት ሲሞላው ሁሉንም የመደበኛ ትምህርት ዘርፎች በስኬት ያጠናቀቀ ሲሆን በላቀ የህክምና ባለሙያነቱም ሰፊ ተቀባይነትና ዝናን ለመቀዳጀት በቅቷል፡፡  
በአስተዳደርነትም ጭምር ያገለገለው አቡ አሊ ሲና፤ ለጥቂት ጊዜ ያህል በፀሐፊነት ለመንግስትም አገልግሏል፡፡ አቬሴና በተለያዩ የኢራን ገዢዎች ቤተ መንግስቶች ውስጥ በህክምና ባለሙያነትና በፖለቲካ አስተዳዳሪነት መስራቱን ቀጠለ - የአባሲድ ሥልጣን በተፈረካከሰ ጊዜ ብቅ ባሉ አያሌ ወራሽ የኢራን መንግስታት ወቅት፡፡ በኋላ ላይም ወደ ሬይ፣ ቀጥሎም ወደ ሃማዳን ተጉዟል፡፡ “Al – qanun fi al - tibb” የተሰኘውን ዝነኛ መጽሐፉን የፃፈውም በሃማዳን ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የሃማዳን ንጉስ የነበሩትን ሻምስ አል ዳውላህ ተጠናውቷቸው ከነበረ ከፍተኛ የቁርጠት በሽታም ፈውሷቸዋል፡፡ ከሃማዳን በቀጥታ ያመራው ወደ ኢስፋሃን ሲሆን አያሌ እንደ ቅርስ የሚቆጠሩለትን የጽሑፍ ሥራዎቹን ያጠናቀቀው እዚህ ነበር፡፡
አቪሴና ከ500 በላይ መፃሕፍትና መጣጥፎችን ጽፏል፡፡ ሁለቱ ሥራዎቹ - “Daneshnameh e-Alai” (የፍልስፍና ሳይንስ ኢንሳይክሎፒዲያ) እና በ pulse ላይ  የምታነጣጥር አነስተኛ የጥናት ጽሑፉ ግን በአፍ መፍቻ ቋንቋው በፋርሲ ነበር የተፃፉት::
ከዚህ በተጨማሪም፤ ስለ ተፈጥሮ ፍልስፍና፣ ስለ አስትሮኖሚ፣ ስለ ሥነ- መለኮትና ሜታፊዚክስ እንዲሁም ስለ ህክምና፣ ስለ ሥነልቦና፣ ስለ ሙዚቃ፣ ስለ ሂሳብና ፊዚካል ሳይንሶችም ጽፏል፡፡ የፐርሺያ ባለ አራት ስንኞች ግጥም (ሩባያት) እና የአጫጭር ግጥሞች ደራሲ እንደሆነም ይነገራል፡፡
አቬሴና ከዚያ በኋላ በተለያዩ የ ኾራሳን ከተሞች ሲዘዋወር የቆየ ሲሆን በኋላም ማዕከላዊ ኢራንን ይገዛ ወደ ነበረው የቡዪድ ልኡላን ቤተ መንግስት አምርቷል፤ መጀመሪያ ወደ ሬይ (ከዘመናዊ ቴህራን አቅራቢያ)፣ ከዚያም ወደ ቃዝቪን  የተጓዘው አቬሴና፤ እንደተለመደው በህክምና ባለሙያነት ነበር የሚተዳደረው፡፡ በሰሜናዊ ፐርሺያ የበለፀገች ከተማ የነበረችው የሬይ ንጉስን ከሜላኮሊያ በማከም ከበሽታው የፈወሰ ሲሆን እኒህን ምልከታዎቹን በኋላ ላይ “State of the Human Soul” በተሰኘ ጽሑፉ ገልፆታል:: በእነኚህ ከተሞች በቂ የማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ማግኘት ያልቻለ ሲሆን ሥራውን ለመቀጠል ወሳኝ የሆነውን ሰላምና መረጋጋትም ተነፍጐ  ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ በምዕራብ - ማዕከላዊ ኢራን ወደ ሃማዳን ተጓዘ - ሌላው የቡዪድ ልኡል (ሻምስአድ - ዳውላህ) ገዢ ወደነበረበት ሥፍራ ማለት ነው፡፡
ጉዞው በአቬሴና ህይወት ውስጥ የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮን አብስሮለታል፡፡ የቤተ መንግስት ሃኪም ሆኖ ከማገልገሉም በላይ በገዢው ዘንድ በነበረው ተወዳጅነትም ሁለት ጊዜ የከፍተኛ ባለሥልጣንነት ሹመት እስከማግኘት ደርሷል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰውም፤ የሃማዳንን ንጉስ ከከፋ የሆድ ቁርጠት ህመም አክሞ ማዳንም ችሏል፡፡
ከሃማዳን ወደ ኢስፈሃን በመጓዝም፣ በፊዚክስና ሜታፊዚክስ ላይ የሰራቸውን እንደ ቅርስ የሚቆጠሩ አያሌ ጽሑፎች አጠናቅቋል፡፡ በመጨረሻም ወደ ሃማዳን ተመልሶ በ1037 በሃይለኛ የሆድ ቁርጠት ህመም ህይወቱ አልፏል፡፡
የህክምና ሳይንስ መርህ ተደርጐ የሚቆጠረው አቬሴና፤ በህክምናና በአርስቶቴሊያን ፍልስፍና ዘርፎች ባበረከተው አስተዋጽኦው ይበልጥ ይታወቃል፡፡ ሁለቱ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ሥራዎቹ - “The Book of Healing” እና በምዕራቡ ዓለም የህክምና መርህ በሚል የሚታወቀው “Al Qanun” የተሰኙት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሳይንሳዊ ኢንሳይክሎፒዲያ ሲሆን ሎጂክ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሥነልቦና፣ ጂኦሜትሪ፣ አስትሮኖሚ፣ አሪትሜቲክና ሙዚቃን ያካትታል፡፡ ሁለተኛው (Circa 1030 A.D) በህክምና ሳይንስ ታሪክ እጅግ ዝነኛ ከሆኑት መፃሕፍት አንዱ ተደርጐ የሚቆጠር ነው፡፡
“The canon” የህክምና ሳይንስ መርህ ወይም ሚዛን ለመሆን የበቃ ሥራው ሲሆን በአውሮፓ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ከሂፖክራተስ (460-377B.C) እና ጋሌን (129-199A.D) ሥራዎች ጋር በእኩል ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነበር፡፡ “The Canon of Medicine” አምስት መፃሕፍትን የያዘ ነው፡፡ እነዚህ መጽሐፍት በአናቶሚ፣ ፊዚዮሎጂና ፌርማኮሎጂ (መጽሐፍ 1 እና 2) ያለውን ዕውቀት በስልትና በተጠና መንገድ ይመድባሉ፡፡ ሌላው የበሽታ ጥናት ዘርፍ፤ የውስጣዊ አካላትን በሽታዎችና ዓይነተኛ የበሽታ ምልክቶች በጋሌን የአመዳደብ ሥርዓት መሰረት ይገልፃል (መፅሐፍ 3)፤ ትኩሳት (መፅሐፍ 4) እና ማቴሪያል ሜዲካል (መፅሐፍ 5) ናቸው፡፡
አቬሴና በዚህ የመጨረሻ መጽሐፉ፤ 760 መድሃኒቶችን ከአዘገጃጀት መመሪያዎች ጋር የሚገልጽ ሲሆን፤  በአጠቃላይ “The Canon of Medicine” በ1ሺ ገፆች ተቀንብቦ፣ በግምት አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ቃላትን የያዘ ሲሆን፤ በስልታዊ መንገድ የተፃፈ ነው፡፡
“Canon” መጠነ - ሰፊ ታዋቂነትን የተቀዳጀው በ15ኛውና 16ኛው ክ/ዘመን ቲፖግራፊ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ነው፤ ነገር ግን እስከ 18ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ድረስ ተፅእኖው በመላው አውሮፓ ፀንቶ ቆይቷል፡፡

አቬሴና ለዘመናችን ያስፈልገን ይሆን?
ፈር ቀዳጅ የሆነ ሥራው - “Al-Qanun” ከህክምና ጽሑፍና አካዳሚያዊ መርሀ ግብሮች ዕድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ሲሆን በመድሃኒቶች ታሪካዊ ትውስታ ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ ነበር:: በታሪክ ሊቁ ጃማል ሙሳቪ መሰረት፤ በሙስሊሙ ዓለምና በአውሮፓ ህይወቱ ካለፈ በኋላ ባሉት 600 ዓመታትም የአቬሲና ሥራዎች በመድሃኒቶች ዕድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ቀጥሎ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት የአቬሴና ሌጋሲ የፀረ - ወረርሽኙን ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያገዘ እንደሆነ የህክምና አዋቂዎች ለዓለም በኩራት እያስታወሱ ነው፡፡  
ለመጀመሪያ ጊዜ.  እ.ኤ.አ በ1025 የተጠቀሰውና #የመድሀኒቶች መርህ (The Canon of Drugs); በሚለው 5ኛ ቅፅ የህክምና ኢንሳይክሎፒዲያው  አቪሴና፤ በሳይንሳዊ ስራው የኳራንቲን ወይም የለይቶ ማቆያ ትክክለኛ ፅንሰ-ሃሳብን  በሽታ እንዳይሰራጭ፣ ለመቆጣጠር  እንዴት እንዳስቀመጠው ሳይጨምሩ፤ ሳይቀንሱ አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ በአብዛኛው በምክንያታዊነት  ሊወደስ በሚገባው ትውስታ ውስጥ፣ የተዘነጋው ወሳኙ እውነታ፣ አቪሴና የህክምና ሳይንቲስት ብቻ ሳይሆን፣ በተጨማሪም ታላቅ የፍልስፍና አዋቂ መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ.፣ ቀደም ባለው ታሪካዊ የመድሀኒት ሳይንስ ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበረው አቪሴና፣ በተጨማሪም ወጤታማ ፈላስፋም ነበር፡፡


Read 3235 times