Tuesday, 25 August 2020 05:53

ባልንጀሮቹ

Written by  ሌሊሣ ግር
Rate this item
(5 votes)

…ጊዜያዊ እንጂ ለዘላቂነት ደስታ የማይሰጥ፤ ለአጭር ጊዜ እንጂ በቆይታ ህይወትን የሚጐዳ ነገር ሁሉ “ሱስ” ተብሎ ሊጠቃለል ይችላል፡፡ ፍርሀት፣ ጥርጣሬና አምባገነንነትም ከዚሁ ተክለ ቁመና ግራና ቀኝ ኪስ ቢፈተሹ ተደብቀው ይገኛሉ፡፡
         
            መርዶቂዮስ ስድስተኛውን ሲጋራውን እየለኮሰ እንደለመደው እለታዊ ማማረሩን ጀመረ፡፡ ማማረሩ ራሱ የሱሱ አንድ አካል ሆኗል፡፡ እድሜው በሰላሳዎቹ አጋማሽ ገደማ እንደሆነ ይገመታል፡፡ አብረውት ያሉት ሁለቱ ጓደኞቹ ግን እውነተኛ እድሜው ከሚገመተው በላይ እንደሆነ ያውቃሉ:: “ጋቢናሽ ቻይ ስለሆነና በዘርሽ ቶሎ የማትሸብቺ አይነት ስለሆንሽ እንጂ” እያሉ በጓደኛቸው ላይ መጠነኛ አመጽ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ፊሊፕስ የመሆኑ ሚስጥር አይገባቸውም፡፡
“መርዶቂዮስ እኮ ፊቱ ያልተበላሸው ብዙ ውሃ ስለሚጠጣ ነው” ብለው አንድ ሰሞን ከመኝታ ሲነሱና ወደ መኝታ ሲሄዱ፤ ሁለት ሁለት ሊትር ውሃ በእጃቸው አፍንጫቸውን ጥርቅም አድርገው ይጋቱ ነበረ፡፡ ብሩኬ ከሁሉም በዕድሜ ያንሳል፡፡ ሱስ በጀመረ ስድስተኛ አመቱ ፀጉሩ ሸበተ፡፡ አሸባበቱ ደግሞ ላሽ የበላው ሰው መልሶ ፀጉር ሲያበቅል አናቱ ዥንጉርጉር እንደሚሆነው ነው፡፡ ጥቁሩን ከነጩ ለማመሳሰል በተለያየ ፀጉር ቆራጭ አማካሪነት ጥሯል፡፡ በጥረቱ እንዲያውም ጭንቅላቱ የዳማ መጫወቻ ሰሌዳ መሰለ፡፡ ባርኔጣ መድፋት የጀመረው ያኔ ነው፡፡ አንድ ለውጥ በሰውነቱ ላይ ሲከሰት ጠፋ ብሎ ይመለሳል፡፡ ባርኔጣ ማድረግ ጀምሮ ትንሽ ሳይቆይ፣ ፀጉሩ ከመሃል አናቱ ጀምሮ በሁሉም አቅጣጫ መሸሽ ጀመረ፡፡
መርዶቂዮስ ግን ከውስጥ ነው ብልሽቱ እንጂ ከፊት ለፊት ብዙም የሚታይ ለውጥ አልነበረም፡፡ የውስጥ ብልሽቱ መገለጫ ምሬቱ ነው፡፡ ስድስተኛ ሲጋራው ላይ ይጀምራል፡፡ ምሬቱ የተለያየ አይነት መግቢያ አለው፡፡ አንዳንዴ ከአስተዳደጉ ይነሳል:: ሌላ ጊዜ አይቀርልኝም ብሎ ከሚፈራው አጨራረሱ፡፡ ዛሬ ምሬቱን የጀመረው ከአባቱ ነው፡፡
“አባቴ ገና ጡት ጠብቼ ከእናቴ እቅፍ ከመውረዴ ሲጋራ እንድገዛ ሱቅ ላከኝ፤ ቤት ውስጥም ያጨስብኝ ነበር፡፡ እናም በአባቴ ምክንያት ነው የሲጋራ ሱሰኛ የሆንኩት:: ምንም ማድረግ የማይቻል እጣ ፈንታ ነው--” ብሎ ሲጋራውን እንደ ደመኛ ጥሎ ረገጠው፡፡
ቱርካና የወሬ ጥራት ደረጃ መዳቢ ሚኒስቴር ነው፡፡ ሁለቱን ጓደኞቹን ሲመክር ለሰማው ምኑም ነገር ውስጥ የሌለበት ይመስላል፡፡ ሱሱን በፀጋ መቀበሉ ሱስ የሌለበት ያስመስለዋል፡፡
“እህትህና እናትህ እንዴት በአባትህ ሲጋራ ሳይለከፉ ቀሩ ታዲያ…ወይንስ እነሱ የሱስ ክፍል በተፈጥሮ የላቸውም?”
“እኔን’ጃ ሴቶች እኮ ፍላጐታቸውን መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ ልክ ወሲብ ላይ እነሱ እየተቸገሩልህ አንተ ግን እያስቸገርካቸው እንደሚያስመስሉት፡፡ በዛ ላይ ጀምረውም በቀላሉ መተው ይችላሉ፡፡ ያቺ አንድ ሰሞን ይዘሃት የምትመጣዋ የዩኒቨርስቲ ተማሪዋ እንኳን ስራ ስትይዝ ቀጥ አደረገችው አይደል! ሲጋራዋንና አንተን አንድ ላይ አራግፋ አይደለም የጠፋችው!”…
ቱርካና በሃይል እግሩን አንስቶ በመሳቅ ከየትም አቅጣጫ የተሰነዘረበትን ፍላፃ መመከት ይችላል፡፡ አንድ ሰሞን ይዟት የሚመጣት ሴት ድንገት ያኔ ብቻ ትዝ እንዳለችው አይነት ቀለል አድርጐ ስቆ ያልፈዋል፡፡
ስለ ራሱ የሚሰጠው መረጃ ጥቂት በመሆኑ ስሜቱ ምን እንደሆነ አይታወቅም:: ሱሱንም ሲጠቀም ፀዳ ብሎ ነው፡፡ ራሱን ጥሎ ለተመልካች ትኩረት እድል አይሰጥም:: እንቅልፉን አብዝቶም ይሁን አሳንሶ ተኝቶ አይመጣም፡፡ በሃይል የነቃም ሆነ የደነዘዘ አይመስልም፡፡ ወደ አፉ የሚያስገባው ጫት ራሱ ሲቀምስና ሲጐርሰው አይታይም:: ከት ብሎ ሲስቅ ቅጠል ተለድፎ የሳቁን መልዕክት ወደ ሱሰኝነቱ እንዲሸጋገር ክፍተት አይሰጥም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ “እኔ የጫት ትርጉሙ ራሱ እኮ አይገባኝም፤ አይሞቀኝም አይበርደኝም፡፡ ልመርቅን ብዬ ስበላ ብውል መንጋጋዬን እንጂ ሌላ ቦታ ያዝ አያደርገኝም” ይላል፡፡
ጉራ እንደሆነ ሁለቱ ጓደኞቹ ቢያውቁም ማረጋገጫ ስለሌላቸው ምንም ሊሉት አልቻሉም፡፡ አልፎ አልፎ ትንሽ ስንጥቅ ሲያገኙ እሱ ላይ ተረባርበው ደጋግመው  ለመቀጥቀጥ ይጥራሉ፡፡ እግሩን አንስቶ ስቆ የመጡበት አቅጣጫ እንዲጠፋቸው ያደርጋል፡፡
የሦስቱ ጓደኝነት መሰረቱ ሱስ ነው:: አስር ሰዓት ለጫት አንድ ጓሮ ተሰልፈው ይገኛሉ:: ከዛ ጓሮ ወጥተው ወደሚቀጥለው ጓሮ እልፍ ሲሉ ደግሞ ጨብሲው አለ:: ሶስቱም በልባቸው ግን ሱሱ ለዘላቂነት መድረስ ከሚፈልጉበት እንደሚያግዳቸው ያውቁታል፡፡ ስለ ሱሳቸው ሳይሆን በዙሪያው ስላለው ነገር ያወራሉ፡፡ ስለ ፖለቲካው፣ ስለ ተባለው አዳዲስ ቀልድ፣ ስለ ሀሜቱ ስለ ነቆራው… ሲጋራውና ጫቱ በደንብ ይጨባበጣሉ፡፡ መርዶቂዮስ ማማረር ይጀምራል፡፡
“እኛ የምናውቃቸው ሰዎች ሁሉ ወይ ጴንጤ ሆነዋል፣ ወይ አሜሪካ ገብተዋል፣ ወይ አግብተው ወልደዋል ወይ ሞተዋል:: እኛ ብቻ እዚህ ቤት ተተክለን ቀርተናል፡፡ የሆነ ገድግድማ ሳያስደርጉብን አልቀረም:: አንዳንዴ እንደው የጦር ጀት አብራሪ ብሆን ብዬ እመኛለሁ፡፡ ይኼንን ቤትና ይሄንን ሰፈር ለመደብደብ፡፡ እኔ ራሴም እንደ ካሚካዚ ጀቱን እዚሁ ጥዬው ከእነ ሱሴ ቢያከትምልኝ ጥሩ ነበር…”
ከሆነ ደረጃ በኋላ ሁለቱ አይሰሙትም:: ብሩኬ ከኪሱ መስታወቱን አውጥቶ መልኩን ማጥናት ይጀምራል፡፡ ለዚሁ ሰዓት የሚያስቀምጣት ቶሎ ቶሎ የምታድግ ፂም አለችው፡፡ በከንፈሩ ዙሪያና በጉንጮቹ ላይ ያደገች፡፡ ቀስ እያለ መከርከም ይጀምራል፡፡ ይኼም የሱሱ አካል ይሁን ወይንም ራሱን የቻለ ሱስ ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡ ከብሩኬ ጭምር፡፡ ምክንያቱም ሁሌ ሲቅም ፀጉር አስተካካይ ይሆናል፡፡ ሳይቅም የቀረበት ቀን ስለሌለ ሲቅም የሚያደርገው ነገር ሁሌ የሚያደርገው ነገር ነው፡፡
መቃሚያ ቤቱ ውስጥ የሚላላከውን ልጅ “መፍዙዝ” ነው የሚሉት፡፡ መጀመሪያ ይጣላ ነበር፡፡ በኋላ አቅም ሲያንስው ስሙን ለመቀበል ተገደደ፡፡ የሆነ ነገር መናገር ጀምሮ ይጠፋዋል፡፡ “ከ” ያለበት ቃል ተደጋግሞ ከተጠራ “ኮካ” ከፍቶ መጥቶ “ስታዙ ሰምቻለሁ” እያለ ክርክር ውስጥ ይገባል፡፡ የሴትየዋ ዘመድ ነው፡፡ ሴትየዋ የቤቱ ባለቤት ናት፡፡ የንግድ ፈቃድ ያለው ፎቶዋ በግሮሰሪው ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል:: የተለየ እንግዳ ካልሆነ ሦስቱ ጓደኛሞች የሚቅሙበት ጓሮ ማንም አይመጣም:: እነሱ ይዘው የሚመጡት ሰው ከአንድ አይበልጥም፡፡ ምክንያቱም ከሦስት ሰው በላይ የሚያስተናግድ ቦታ የለም፡፡ አንድ የጓሮዋ አባል በጓደኞቹ ላይ የስነልቦና ጫና ማሳደር ሲፈልግ ሴት ይዞ ይመጣል፡፡ ሴቶቹ ሴት መሆናቸው ብቻ ግማሽ ነጥብ ያሰጣል:: ሙሉ ነጥብ የሚያገኝ ጫና ፈጣሪ፤ ቆንጆ ሴት ይዞ መምጣት የቻለ ነው፡፡ ቆንጆ ወይንም ወጣት መሆኗ ራሱ የቁንጅናን ትርጉም ያስረሳቸዋል፡፡
ባለፈው ቱርካና በላይ በላዩ የምታጨስ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ይዞ መጥቶ ነበር፡፡ እንዴት እንዳገኛት አልነገራቸውም፡፡ ታክሲ ኮንትራት አንዳንድ ጊዜ እየተቀበለ ይሰራል:: መቼ እንደሚሰራና መቼ እንደሚያቆም አይነግራቸውም፡፡ ለመረጃ ክፍት አይደለም::
የሚመጡት ተጋባዥ እንግዶች ወንድም ሆኑ ሴት ሱስ ሊኖርባቸው የግድ ይላል፡፡ ሱስ ከሌለባቸው እንኳን መመሳሰል ስላለባቸው የግድ በዛኑ ቀን ይጀምራሉ፡፡ ልምድ ያለውና የሌለው መሆኑን በአጫጫስ፣ በአወራሩና በአቃቃሙ ያውቃሉ፡፡ ብዙ ጫት በሰባት ኮካ ቅሞ የታመመውና ወላጆቹ በመኪና ተጠርተው የወሰዱትን ልጅ ማን እንዳመጣው አያስታውሱም፡፡ ወደ ጓሮ መፍዙዝ አዝኖለት አስገብቶት ሊሆን ይችላል፡፡… ሰው ይመጣል ይሄዳል፤ እነሱ ግን ቋሚ ናቸው፡፡
መርዶቂዮስ አማርሮ ሲጨርስ የሆነ ጽሑፍ ነገር ማገላበጥ አለበት፡፡ ጋዜጣ ገዝቶ ይመጣል፡፡ የሚነበብ ነገር ባይኖረውም፣ እሱ ግን የሰዓቱን ፍላጐት መሙላት ስላለበት ያነበዋል፡፡ ቱርካናና ብሩክ ስለለመዱት ብዙም ትኩረት አይሰጡትም:: አንዳንድ ጊዜ፣ በስንት የጨረቃ ኡደት አንዴ፣ አንድ ወረቀትን ብዙ ቦታ አጥፎ ለመፃፍ ይሞክራል፡፡ በጭንቅላቱ ያሰበው ነገር ግን በእስክሪብቶ አድርጐ ከወረቀቱ ጋር ሲነካው፣ እስክሪብቶው ወደ ኤሌክትሪክ እሳት መለኪያ ቴስተርነት ይለወጣል፡፡ እሳት ወይንም መብራት ግን በእስክሪብቶው ላይ በርቶ አይታይም፡፡ ፊደሎቹ አይኖሩም:: አጥፎ ያዘጋጀውን መልሶ ወደ ኪሱ ይከታል፡፡ በዚህ ሙከራው ላይ ማንም እንዲቀልድበት አይፈልግም፡፡ እነሱም ገፍተው አይመጡበትም፡፡ እሱ በሌለበት “ሎሬት ዛሬ አልመጣም” ይባባላሉ፡፡ ቀድሞም ሆነ ዘግይቶ ሳይመጣ የሚቀር ግን ከመሃከላቸው የለም፡፡ ያ ሰባት ኮኮ ጠጥቶ የታመመው ልጅ ራሱ ብዙ አስራ ሶስት ወር ፀጋዎች ካለፉ በኋላ ተመልሶ መጣ፡፡ ስለ ሱስ ጥናት ያካሄደው በራሱ ህይወት ላይ ይመስል ህይወቱን ዘክዝኮ ነገራቸው፡፡ መጀመሪያ ቀን በጆሮአቸው ብቻ ሳይሆን በአፋቸውም ወሬው እንዲገባ ገርበብ አድርገው ተመስጠዋል፡፡ በኋላ እየደጋገመ ተመሳሳይ ነገር እንደሚያወራና ሲያወራ ደግሞ የሚያደምጠው ሰው የግድ ማግኘት እንዳለበት ሲያውቅ፣ እየተጠቃቀሱ የወሬውን ባለቤት እንደ ኳስ መቀባበል ጀመሩ፡፡ አንዱ ሲሰማው ሌላው እንዲያርፍ ወይንም እያወራ ሳለ የሚሰማው ሰው ተነስቶ “መጣሁ” ብሎ ሲሄድ፣ አየር ላይ በወሬ ጀርባው ደርቆ እንዲቀር አደረጉ፡፡ ልጁ ሰው ቢኖርም ባይኖርም እንደሚያወራ አስመስከረ:: ፒቲሽን ፈርመው መፍዙዝ እንዲያግደው አደረጉ፡፡ ነገር ግን የሚያወራቸው ነገሮች በእርግጥም አስደናቂ ነበሩ፡፡
መርዶቂዮስ እስክሪብቶው ወረቀቱን ሲነካ እሳት እየጠፋበት ባያስቸግረው፣ ቢጽፋቸው ውብ ድርሰት የሚወጣቸው የህይወት ተሞክሮ ታሪክ ነበሩ፡፡ እውነትም ይሁኑ ውሸት መሳጭ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሰው ናቸውና ሰለቹ፡፡ መጀመሪያ ቀን በተመስጦ ጀምረው፣ እንባ ባቆረዘዘ መነካት የቀፀሉት ተረክ ሦስተኛ ጊዜ ሲደገምላቸው፣ ልጁን መሃል አስገብተው፣ በኩርኩም ለመዝገን ሁሉ ዳዳቸው፡፡
አዲስ ሰው ከሚመጣ እነሱው በለመዱት ወሬ ታጅበው ተናቁረውና ተግባብተው የሚለያዩት ይሻላቸዋል፡፡ ቢያንስ ራሳቸውን ሲያዳምጡ አይረባበሹም፡፡ በጥሞና ሁሉም የራሱ አለም ውስጥ በሚገባበት የምርቃናው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ዝምታ በመሃላቸው ይነግሳል፡፡
ብሩኬ ፀጉሩ ረግፎ ካለቀ በኋላ ሌላ በሽታ ወጣበት፡፡ የውፍረት በሽታ፡፡ በፀጉሩ ምክንያት ያየውን መከራ፣ በውፍረቱም ላይ መፍትሔ ለማግኘት የተሰጠውን ምክር ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጣረ፡፡ ሩጫ ለመሮጥ ሞክሮ እንደማይሆን አወቀ፡፡ ፈረንጅ መሆን ያስፈልጋል፡፡ አበሻ መሃል እየሮጡ ውፍረት ለመቀነስ ሰው ሲያሽሟጥጥ ምንም ጉዳይ ላለመስጠት ፈረንጅ መሆን ያስፈልጋል፡፡ እሱ ደግሞ ፈረንጅ አይደለም፡፡ ጂም ገባ፡፡ ምግብ ቀነሰ፡፡ ካርቦን የሚባል ምግብ ቀነስኩ አለ፡፡ የሚሞክረው ብዙ፤ የሚያገኘው ውጤት ግን ምንም ሲሆንበት ለፈጣሪ ሰጥቶት ቁጭ አለ፡፡ ቁጭ ያለው “ወይ አንተ አትተወው፤ ወይ እሱ አይተውህ” የተባለበት ሱስ ላይ ነው፡፡ በጣም ወፍራም ሰው ሲጋራ ሲያጤስ እንደሚያስቅ ቱርካና የተገለፀለት ቀን እያየው ሲስቅ ዋለ፡፡ ዝም የሚባባሉበት ቅጽበት እስኪደርስ በቀልድና በለበጣ ይወጋጋሉ፡፡ ይሄም የሱስ አንዱ አካል ነውና፡፡ ብሩኬ ለእንግዳ የሚለቀቀውን አንድ ሪዘርቭ ወንበር ከራሱ የቀድሞ መቀመጫ ወንበር ጋር አንድ ላይ ገጥሞ መቀመጥ ጀመረ፡፡ መፍዙዝ በድርጊቱ አልተስማማም፡፡ ሰው እስኪመጣ ብትፈቅድለት ምናለ ብለው ጓደኞቹ ቢያግዙለትም አልሰማቸውም፡፡ የሁለት ወንበር የመቀመጫ ክፍያ እየከፈለ እንዲሄድ አደረገው፡፡
መፍዙዝ ችግር ያለበት ሰው አይወድም:: የሚያማርር፣ ዝም ብሎ የሚለፈልፍ፣ ብር ሳይኖረው የሚመጣ፣ ብዙ የሚያወራ፣ የሚጨነቅ ሰው አይወድም፡፡ በንግድ ስራው ላይ የተላከበት ሰይጣን ነው የሚመስለው፡፡ እሱ የሚወደው የተሟላ ሰው ነው፡፡ ወይንም የተሟላለት የሚመስል ሰው፡፡ በራሱ ውስጥ ያለውን ጭቅጭቅ የሚያባብስበት ሳይሆን የሚያረጋጋው ሰው፡፡ ጫት ረብሰኝ የሚለውንም እናቱን ከሰደበበት እኩል ነው የሚቆጥረው፡፡ መፍዙዝ ሌላው ነገር ላይ ቢፈዝም፣ ለጥል የሚያነሳሳውን ነገር ከምንም ውስጥ መፍጠርን በተመለከተ ግን ንቁ ነው፡፡
መፍዙዝ የሚወደው ቱርካናን ነው:: ይወደው ነበር እስኪጠላው ድረስ:: መጥላቱን ከማወቁ በፊት ግን ለምን እንደጠላው ለማረጋገጥ አንድ ቀን ሽንቱን ሲሸና ተከትሎ አድብቶ አየው፡፡ ሽንቱን ሲሸና ሁሌ ለምን ሰው እንደማያስከትል በተደጋጋሚ አይቶ ነው የተከተለው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይዞ የሚወጣቸውን ሴቶች ምንም እንደማይነካቸው፣ አንድ ዲሲ ሰፈር አልጋ ቤት የሚያከራይ ዘመዱ፣ ቱርካና ወደ ጫት ጓሮው ሲገባ አይቶ አጫወተው፡፡
“ሴቶቹን ይዞ ይመጣል ግን ልብሱን ሳያወልቅ ነው አቅፎ የሚያድረው፡፡ የሆነ ችግር አለበት” አለው፡፡ መፍዙዝ ለነገር ሲሆን ነቃ፡፡ እንደ ዲቴክቲቭ ሆነ:: የዲቴክቲቭ ቀልቡ ወደ ሽንት መሽኛው መራው፡፡ ተከተለው፡፡ ቱርካና ወደ ኋላ እየተገላመጠ ሲሸና በሌላ ቀዳዳ አይጥ አክሎ ራሱን አሳንሶ ተሸሽጐ አየው፡፡ ምንም ችግር የለበትም፤ ከቀለም በስተቀር:: ሽንት መሽኛው እንደ ዝሆን ጥርስ ነጭ ናት:: የፈረንጅ አይነት ቅላት ሳይሆን የበሽታ ይመስላል፡፡  
“ምንድን ነው ይኼ ነጭ የሚያደርግ በሽታ… ቁስል የለውም ቆዳ ግን ቀይ ያደርጋል?” ብሎ ሁለቱ ጓደኞቹ ብቻ ባሉበት ቱርካና ሳይመጣ ጠየቀ፡፡ ከጠየቀ በኋላ ስለ ለምጽ ለማስረዳት ሲጥሩ “ታዲያ ፊት ላይ ነው እንጂ እንትን ላይ ይወጣል እንዴ?” ብሎ ወደ ዋናው ነገር መጣ፡፡
ቱርካና ገና ተመልሶ የሶስቱን ፊት ሲያይ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መልኩ ላይ የነበረው መረጋጋት ጠፋ፡፡ ጫቱ ራሱ በከንፈሩ ዳር ተጠራቅሞ ታየ፡፡ ከዛ ቀን በኋላ እዛ ቤት አልተመለሰም፡፡ ወሬው ግን እሱ ርቆ ወዳለበት ሰፈር ድረስ ተጉዞ መጣ፡፡ ከብዙ አስራ ሶስት ፀሐዮች በኋላ አንድ ቀን የራሱን ታሪክ ደጋግሞ የሚያወራው ልጅ አገኘው:: ሲያገኘው ብዙ ሱሶች ጨምሯል፡፡ በአረቄ ተነስቶ ነው በአረቄ የሚተኛው፡፡
መሳቅ አቁሟል፡፡ በታች የጀመረው ለምጽ በግራ እጁ በኩል ብቅ ማለቱን ማንም እንዳያይበት የግራ እጁን ከጃኬቱ ኪስ አያወጣም፡፡ ግራ እጁን ሁሌ በኪሱ ከማድረጉ የተነሳ በግራ በኩል ከትከሻው ጀምሮ ስላለ ቀኙ ደግሞ ደነደነ፡፡ የመጠጥ መለኪያ ከማንሳት ውጭ በዛ እጁም የሚሰራው ስራ አልነበረም፡፡ መሀል ላይ ትንሽ ይቅማል፡፡ በእጁ ሲወጣ መውጫ ያጣው ነጩ ቀለም፣ በከንፈሩ ላይ መታየት ጀመረ፡፡ ፊቱ ላይ ከመድረሱ በፊት ለመሞት የቆረጠ ይመስል አጠጣጡን የእልህ አደረገው፡፡ ሴቶች ባሉበት አካባቢ ቆሞ መሳደብ ይወዳል፡፡
እነ ብሩክ ሱስ ያመጣባቸውን መከራ ከኋላ ጀምረው ሲዘክሩ፣ ቱርካናን ረስተውት አያውቁም፡፡ መፍዙዝ ተንኮል ባሰበ ቁጥር ንቁ እንደሚሆን ያውቅ ይመስል ሁሌ ግጭት እንደፈለገ ነው፡፡
“ሁለታችሁም ውጡልኝ” ብሎ ኮሌታቸውን ይዞ ያስወጣቸው ቀን፣ ምላሻቸው መለማመጥ መሆኑን ሲያይ ለአይኑ አስጠሉት፡፡ አሁን የሱሰኛ በሱሰኛ ላይ ባርነት እየተለማመደባቸው ይገኛል፡፡ የፈለገውን እንዲያደርጉ ሲያዝ ይተባበራሉ:: የብሩክን ወንበር ወስዶበታል:: ቡሩኬ ውፍረቱ ከአንጀት መርዘም ምክንያት ይሆናል ተብሎ የአንጀቱን ርዝመት ለማሳጠር ገንዘብ የሚያገኝበትን አማራጭ እየፈለገ እንደሆነ ለመርዶቂዮስ ይነግረዋል:: መርዶቂዮስ ጠቅላላ ምኞቱ ራሱን መግደል እንደሆነ ሲቅም ይናገራል:: ሲጠጣ ብሩክንና መፍዙዝን ከመግደል እንደማይመለስ ይዝታል፡፡ ጠዋት ዛቻውንም ምኞቱንም ይረሳቸዋል፡፡ እንደተለመደው እለቱ ይቀጥላል፡፡ እለት በእለት ላይ፣ አመት በአመት ላይ ፀጋው የተገፈፈ ፀሐይ በህይወት ሱሰኞች ላይ እየወጣና እየጠለቀ፣ የምንዱባንን እድሜ እየጨረሰ፣ የራሱን እድሜ ያረዝማል፡፡       

Read 1909 times