Saturday, 29 August 2020 10:20

የአሜሪካው ኩባንያ ከኢትዮጵያ ሸሪኮች ጋር የገባውን ውል ሰረዘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  ግዙፉ የአሜሪካ የህፃናት ልብስ አከፋፋይ ኩባንያ ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ ያዘዘውን በሚሊዮን ዶላር የሚገመት ዋጋ ያለውን የአልባሳት ትዕዛዝ በመሠረዙ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ልብስ አምራች ኩባንያዎች ለከፍተኛ ኪሣራ መዳረጋቸው ተገለፀ፡፡
ዘ ቺልድረን ፓላስ (ቲሲፒ) የተሰኘው ግዙፉ የአሜሪካ የህፃናት ልብስ አከፋፋይ ኩባንያ፣ በመጋቢት ወር ከተለያዩ በኢትዮጵያ የሚገኙ የልብስ ኦምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች ጋር የህፃናት ልብስ እንዲያቀርቡለት ስምምነት መፈፀሙን የጋርዲያን ዘገባ ያመለክታል፡፡
ይሁን እንጂ ኩባንያው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ምክንያት በማድረግ ውል ማቋረጡን እንደገለፀላቸው ዘ ጋርዲያን ያነጋገራቸው አምራቾች አስረድተዋል፡፡ ኩባንያው ከአንድ የልብስ አምራች ብቻ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የግዥ ውል ተፈራርሞ እንደነበር ያወሳው ዘገባው፤ ኩባንያው በኮቪድ-19 ሰበብ ውል በማቋረጡ ምርቶች ለብልሽት፣ ኩባንያዎችም ለከፍተኛ ኪሣራ ተዳርገዋል  ብሏል፡፡
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙና ከአሜሪካው ኩባንያ ጋር ውል የፈፀሙ ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው በአግባቡ ደሞዝ ለመክፈል መቸገራቸውንም ዘገባው አትቷል:: የህፃናት ልብስ አከፋፋይ ኩባንያው ዋነኛ የንግድ ሸሪኮቹን በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርከ የሚገኙትን ፒቪ ኤች፣ ጄሲፔኒ እንዲሁም ኤች ኤንድ ኤም አድርጐ ለአመታት ከእነሱ ልብስ እየሸመተ መቆየቱም ተመልክቷል፡፡
ከኩባንያዎቹ ጋር በመጋቢት 2012 የገባውን ውል መተግበር ያልቻለው በኮሮና ምክንያት የአለም እንቅስቃሴ በመገታቱ መሆኑን የኩባንያው ሥራ አስፈፃሚ አስታውቀዋል፡፡
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርከ ከሚሠሩ ሠራተኞች 95 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንና ወርሃዊ ደሞዛቸውም 26 ዶላር (850 ብር) መሆኑን የጠቆመው ዘ ጋርዲያን፤ ይህም በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ ከተሠማሩትና በወር 95 ዶላር ከሚከፈላቸው የባንግላዲሽ ሠራተኞች እንዲሁም በወር 326 ዶላር ከሚከፈላቸው ቻይናውያን ሠራተኞች ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው ብሏል፡፡  


Read 13598 times