Saturday, 29 August 2020 10:20

የተሳሳቱ ርዕዮተ አለማዊ ትርክቶች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለጥቃት አጋልጠዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 5ቢ.ብር የሚገመት የምዕመን ንብረት ወድሟል

              የተሳሳቱ ርዕዮተ አለማዊ ትርክቶችና ጂኦ ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ ኦርቶዶክሳውያንን በስልት የማጽዳት ዓላማን ያነገበና የተቀነባበረ ጥቃት በምዕመኖቿ ላይ እየተፈፀመ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያስታወቀች ሲሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እስከ ዛሬ የተፈፀሙ ስልታዊ ጥቃቶች እንዲመረመሩ ጠይቃለች፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ፣ በኦሮሚያ 25 ወረዳዎች በምዕመኖቿ ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠችው ዝርዝር መግለጫ፤ የመንግስት አካላት ተጐጂዎችን በአግባቡ የመካስና ፍትህ የማስፈን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ስትልም ወቅሳለች፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ላይ ለሚፈፀሙ ጥቃቶችም ርዕዮተ አለማዊ ትርክቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው ቤተ ክርስቲያኒቱ ያስታወቀችው፡፡
በዚህ ርዕዮተ አለማዊ ትርክቶች መነሻ 97 ሰዎች ከሞቱበት ጥቅምት ወር ጥቃት ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያኒቱና ምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ ነው ያለችው ቤተክርስቲያኒቱ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተፈፀሙ በደሎችም ተመርምረው ፍትህ ሊሰጥ ይገባል ብላለች፡፡
ከሰኔ 22 እስከ 24 ለሶስት ቀናት በቆየው ጥቃትም 67 ምዕመናን በግፍና በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፤ 38 ከባድ (ዘላቂ) ጉዳት እንደደረሰባቸው በመግለጫዋ ጠቁማ፤ 29ኙ ላይ ቀላል ጉዳት ሲደርስባቸው ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ተፈናቅለዋል ብላለች፡፡
ጥቃቱም በዋናነት በገጀራ፣ ቆንጨራ፣ ጦርና ጩቤ፣ ሜንጫ፣ እንዲሁም ዱላና ድንጋይን በመጠቀም መፈፀሙን ያስታወቀችው ቤተክርስቲያኒቱ፤ የሟቾች አስከሬን በጐዳና እየተንገላታ መዋሉን፣ በአራዊት የተበላ አስከሬን መኖሩን፣ ሴቶች መደፈራቸውንና የተፈናቀሉ በብርድና በዝናብ መንገላታታቸውንም አመልክታለች፡፡ ከዚሁ ጥቃት ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አጣሪ ኮሚቴ ባጠናው መሠረት፤ 5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የምዕመኗ ንብረቶች መውደማቸውም ተገልጿል፡፡
መንግስት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጐች መልሶ ከማቋቋም ባሻገርም በአስቸኳይ ሊፈጽማቸው ይገባል ያላቸውን ተግባራትም የቤተክርስቲያኒቱ ኮሚቴ ጠቁሟል፡፡
ተጐጂዎች አሁንም የጥቃት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን ለኮሮና ወረርሽኝ በሚጋለጡበት ሁኔታ ውስጥ መንግስት የዜግነትና ሰብአዊ መብታቸውን  እንዲያስከብር የደህንነትና የኑሮ ዋስትና እንዲሰጣቸውም አበክራ ጠይቃለች፡፡
መንግስት ከጥቃቱ በኋላ ህግ ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቀው የቤተክርስቲያኒቱ መግለጫ አሁንም ጥፋተኞች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል፡፡ በጥቃቱ ተሳትፎ የሌላቸውና በኦርቶዶክስነታቸው ብቻ ታስረው የሚንገላቱ ምዕመኖቿም ጉዳያቸው በጥንቃቄ ታይቶ እንዲፈቱ ጠይቃለች፡፡ በ2012 ዓ.ም ጥቅምት በአንድ ቀን 97 ዜጐች ያለቁበትን ችግር ጨምሮ በጥምቀት በአል አከባበር ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈፀሙ ግድያዎችና ዘረፋዎች፤ ግፎች በደሎች ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርብና ውጤቱም ህዝብ ይፋ እንዲደረግ የጠየቀችው ቤተክርስቲያኒቱ፤ ምዕመኖቿንና ማንነቷን ለጥቃት ተጋላጭ ያደረጉ ሃሰተኛ ትርክቶችም እንዲታረቁ አሳስባለች፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ አብዝቶ እንደሚነገረው “በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ” ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይሆኑ የተሳሳቱ ርዕዮተ አለማዊ ትርክቶችንና ጂኦ - ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረና በተደራጀ ስልት የሚፈፀሙ ኦርቶዶክሳውያንን የማጽዳት እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ እየተገነዘበች መምጣቷን የጠቆመችው ቤተክርስቲያኒቱ፤ ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሳይታረም ከቀጠለም የከፋ ፍፃሜ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋቷን ገልፃለች፡፡
በጥቃቶቹ በእምነታቸው ሰበብ በግፍና በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ምዕመኖቿም “በሰማዕታት መዝገብ” እንደሠፈሩ በመግለጫዋ አስታውቋለች፡፡     

Read 662 times