Saturday, 29 August 2020 10:27

የግል ሆስፒታሎች ለኮሮና ህክምና የተጋነነ ዋጋ ይጠይቃሉ ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(3 votes)

   - በአንድ ሳምንት ከ10ሺ በላይ የቫይረሱ ታማሚዎች ተመዝግበዋል
          - በአንድ ቀን 1829 የቫይረሱ ታማሚዎች ተመዝግበዋል
                  
           ለኮሮና በሽታ ህክምና እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው የግል ሆስፒታሎች ህመምተኞችን የተጋነነ ዋጋ እንደሚጠይቁ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡ አንድ የግል ሆስፒታል ባለቤት በበኩላቸው፤ ለህክምናው የምንጠይቀው ዋጋ ከመንግስት በተሰጠን ተመን መሰረት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉና ሃሌሉያ በተባለው ሆስፒታል ውስጥ ለኮሮና ህክምና አንድ የቤተሰባቸው አባል ተኝቶ እንደነበር የነገሩን አዛውንት ሰው እንደሚገልፁት፤ ሆስፒታሉ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸው ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ ለሄዱት የቤተሰባቸው አባል ለህክምና የቅድሚያ ማስያዣ 200ሺህ ብር እንደተጠየቁ ገልፀው፤ ከ10 ቀናት ህክምና በኋላ ገንዘቡ ማለቁንና ተጨማሪ ክፍያ ልንከፍል እንደሚገባን ተነግሮናል፡፡   በኮሮና ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ የገቡት የቤተሰቡ አባል፤ በተጨማሪም የደም ግፊትና የስኳር ህመም እንደነበረባቸው ጠቁመዋል፡፡ በሆስፒታሉ ይኼ ነው የሚባል የተለየ ህክምና ባይሰጥም፣ እንድንከፍል የተጠየቅነው ግን እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ነው ብለዋል፡፡
የሃሌሉያ ሆስፒታል ባለቤት ወ/ሮ የትናየት እሸቱን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ ሆስፒታሉ ለኮሮና በሽታ ለሚሰጠው ህክምና የሚጠይቀው ክፍያ በመንግስት የዋጋ ተመን መሠረት ብቻ እንደሆነ ጠቁመው፤ በራሳችን ፍላጐትና ፍቃድ የምናደርገው አንዳችም ጭማሪ የለም ብለዋል፡፡
መንግስት የመክፈል አቅም ላላቸው የኮሮና ቫይረስ ህመምተኞች ህክምና መስጠት እንድንችል ፍቃድ ሲሰጠን፤ ለእያንዳንዱ የኮሮና ህክምና ማስከፈል የሚገባንን የዋጋ ተመን ወስኖልናል የሚሉት ወ/ሮ የትናየት፤ ከዚህ ተመን ውጪ አንድ ብር ጨምረን ማስከፈል አንችልም ብለዋል፡፡
ህመምተኛው ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ ማስያዣ 200ሺ ብር እንደሚከፍል የገለፁት የሆስፒታሉ ባለቤት፤ ይህ የህክምና ማስያዥ ገንዘብ ግለሰቡ በሆስፒታሉ ውስጥ በሚኖረው ቆይታ በሚጠቀማቸው የተጓዳኝ ህመሞች ህክምናና በሚይዘው የመኝታ ክፍል ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል ብለዋል - ባለቤቷ፡፡
አብዛኛው ህሙማን ከሆስፒታሉ ሲወጣ ቀሪ ሂሣቡን እንደሚይስመልስ አስረድተዋል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ውጪ ያሉትን የተጓዳኝ ህመሞች ህክምና በራሳቸው በሆስፒታሉ የዋጋ ተመን መሠረት የሚያስከፍሉ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ሆስፒታሉን የኮሮና ታማሚዎችና የልዩ ልዩ ህክምና ቦታዎች በሚል ለሁለት ከፍለው አገልግሎቱን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ በመግለጽም፤ የኮሮና ህክምና ማዕከሉም ቪአይፒና አንደኛ ደረጃ በሚል ለሁለት የተከፈለ መሆኑን ወ/ሮ የትናየት አስረድተዋል:: በቪአይፒ ለሚታከሙ የኮሮና ታማሚዎች፤ ከእነሙሉ የምግብ ወጪያቸው ለአልጋ በቀን 5ሺ ብር እንደሚያስከፍሉም ገልፀዋል፡፡
“የኮሮና ህክምና በባህርይው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ 52 ሃኪሞችና ነርሶቻችንን በሆቴል አስቀምጠን ሙሉ ወጪያቸውን እየቻልን ነው ህክምናውን እንዲሰጡ የምናደርገው፡፡ ከሃኪሞችና ነርሶች በተጨማሪ ለድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችም ጽዳት ሰራተኞች፣ ሹፌሮችና የመሳሰሉት አንድ ህንፃ ተከራይተን ነው ያስቀመጥናቸው” ብለዋል - ወ/ሮ የትናየት፡፡
እነዚህ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ ያስወጣሉ ያሉት የሆስፒታሉ ባለቤት፤ አሁን ከህሙማኑ ላይ የምንጠይቀው ገንዘብ ከእነዚህ ወጪዎቻችን አንፃር እጅግ ዝቅተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሆስፒታሉ ህክምና ሲያገኙ የቆዩ ህሙማን፣ ወደ መንግስት ተቋማት ሪፈር መባል በፈለጉ ጊዜ ሪፈር እናደርጋቸዋለን ብለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፤ በአገራችን በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ 10ሺ 571 ሰዎች በኮሮና ሲያዙ፤ 125 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ህይወታቸውን እንዳጡ ተገልጿል፡፡ ሣምንቱ በአገራችን በአንድ ቀን ከፍተኛ የቫይረሱ ታማሚዎች የተመዘገቡበት፤ በአንድ ቀን 1829 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ በተመሳሳይ ቀንም 25 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

Read 14562 times