Saturday, 29 August 2020 14:10

በህንድ ሐሙስ ብቻ 75 ሺ የኮሮና ተጠቂዎች ተገኝተዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በህንድ ባለፈው ሐሙስ ብቻ ከ75 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ሪፖርት መደረጉንና ይህም በአለማችን ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ቀን የተመዘገበው ከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር መሆኑ ተዘግቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በአንዳንድ አገራት በተወሰነ ደረጃ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም፣ በአብዛኞቹ አገራት በአንጻሩ በስፋት መሰራጨት መቀጠሉን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን፣ ቫይረሱ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ 24.5 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ማጥቃቱን የወርልዶ ሜትር ድረገጽ መረጃ ያሳያል፡፡
ድረገጹ እንደሚለው፤ ቫይረሱ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ በመላው አለም ለሞት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 832 ሺህ የደረሰ ሲሆን፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 17 ሚሊዮን ተጠግቷል፡፡
6 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባትና ወደ 184 ሺህ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት አሜሪካ፤ በተጠቂዎችና በሟቾች ቁጥር አሁንም ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት የቀጠለች ሲሆን ብራዚል በ3.7 ሚሊዮን ተጠቂዎችና በ118 ሺህ ሟቾች፣ ህንድ በ3.4 ሚሊዮን ተጠቂዎችና 62 ሺህ ያህል ሟቾች እንደሚከተሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ስፔን፣ ስዊዘርላንድና ክሮሽያን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ኮሮና ቫይረስ እንደገና በስፋት መሰራጨት መጀመሩ የተነገረ ሲሆን፣ ወረርሽኙ በድጋሚ ሊያገረሽ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት፤ፍቱንነቱ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ወይም መድሃኒት በሚገኝበት ጊዜ በእኩልነትና በሚዛናዊነት ለሁሉም አገራት እንዲዳረስ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ የሩስያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታቲያና ጎሊኮቫ፤ አገራቸው በቅርቡ አገኘሁት ያለችውን አወዛጋቢውን የኮሮና ክትባት ስፑትኒክ 5 ለመግዛት 27 ያህል የአለማችን አገራት ፍላጎት ማሳየታቸውን እንደተናገሩ የተዘገበ ሲሆን፣ ከእነዚህ አገራት መካከልም ቤላሩስ፣ ብራዚል፣ ቬንዙዌላና ካዛኪስታን እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ በነበሩት ወራት ክፉኛ የኢኮኖሚ ጉዳት ካደረሰባቸው አገራት መካከል እንግሊዝ በቀዳሚነት እንደምትቀመጥ የዘገበው ቢቢሲ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በተጠቀሰው ጊዜ በ20.4 በመቶ ያህል መቀነሱንና ስፔን በ18.5 በመቶ የዕድገት መቀነስ እንደምትከተል ጠቁሟል፡፡ በ7ቱ የአለማችን ሃያላን አገራት በሁለተኛው ሩብ አመት የተከሰተውን የአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ቅናሽ በተመለከተ ዘገባው ባወጣው መረጃም፣ በፈረንሳይ የ13.8 በመቶ፣ በጣሊያን የ12.4 በመቶ፣ በካናዳ የ12 በመቶ እንዲሁም በጀርመን የ9.7 በመቶ ቅናሽ መከሰቱን አስነብቧል፡፡  
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአለማችን ቱሪዝም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን እንደሚቀጥል ባለፈው ማክሰኞ ያስጠነቀቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በ2020 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያዎቹ 5 ወራት በመላው አለም አገራትን የጎበኙ አለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር ከግማሽ በላይ መቀነሱንና በቱሪዝም ኤክስፖርት የ320 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መታጣቱን አስታውሷል፡፡ በመላው አለም ከቱሪዝሙ መስክ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባላቸው የስራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ 120 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የስራ ዋስትና አደጋ ላይ እንደወደቀም የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ በመላው አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ1.2 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የዘገበው ኦልአፍሪካን ኒውስ፣ በአህጉሪቱ በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ወደ 30 ሺህ እየተጠጋ እንደሚገኝና ያገገሙት ሰዎች ቁጥርም 950 ሺህ መድረሱን አመልክቷል፡፡ ከ615 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባትና ከ13ሺህ በላይ ሰዎችም ለሞት የተዳረጉባት ደቡብ አፍሪካ፤ በአህጉሩ በቫይረሱ ክፉኛ የተጎዳች ቀዳሚዋ አገር ስትሆን ግብጽ በ98 ሺህ፣ ሞሮኮ በ55 ሺህ ተጠቂዎች እንደሚከተሉ ተነግሯል፡፡
20 የአፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚል ድንበሮቻቸውን አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ዘግተው እንደሚገኙ የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡


Read 3857 times