Wednesday, 02 September 2020 00:00

አሜሪካ ሱዳንን ከሽብርተኝነት ዝርዝር ለመሰረዝ 330 ሚ. ዶላር ካሳ መጠየቋ ዜጎችን አስቆጥቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 44 ሺህ አፍሪካውያን ደብዛቸው ጠፍቶ መቅረቱ ተነገረ

                 የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ፤ ሱዳን ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ መውጣት ከፈለገች በቅድሚያ 330 ሚሊዮን ዶላር በካሳ መልክ መክፈል ይገባታል ማለታቸው ሱዳናውያንን ማስቆጣቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ሱዳንን የጎበኙት ፖምፒዮ፣ሱዳን አሜሪካ ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ ብላ ከለየቻቸው አራት አገራት ዝርዝር ውስጥ ለመውጣት የምትከፍለው 330 ሚሊዮን ዶላር በአሸባሪው ቡድን አልቃይዳ ጉዳት ለደረሰባቸው አሜሪካውያን እንደሚውል መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ልዕለ ሃያሏ አገር ይህን ያህል ገንዘብ በካሳ መልክ ይከፈለኝ ማለቷ የድህነት ኑሮን በመግፋት ላይ የሚገኙትን ሱዳናውያን ክፉኛ ማስቆጣቱን ገልጧል፡፡
አሜሪካ ሱዳንን 330 ሚሊዮን ዶላር እንድትከፍል መጠየቋ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የአገሪቱ ሚኒስትሮች፣ የተቃዋሚ ቡድኖች አመራሮች፣ አክቲቪስቶች እንዲሁም በርካታ ዜጎች ቁጣቸውን መግለጽ መጀመራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ አንዳንዶችም ለ30 አመታት አገሪቱን የገዛውና በህዝባዊ አብዮት ፍጻሜው እውን ሆኖ የተቀበረው አምባገነኑ የአልበሽር መንግስት ለፈጸመው ጥፋት አዲሱ የአገሪቱ መንግስት ተጠያቂ መሆኑ ፍትሃዊ አይደለም በማለት ቅሬታቸውን መግለጻቸውን አስረድቷል፡፡
ፖምፒዮ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በሱዳን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች በሚነሱበት ሁኔታ ዙሪያ መወያየታቸውንና አሜሪካ የሱዳንን የሽግግር መንግስት እንደምትደግፍ ማረጋገጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከሱዳን ሉዓላዊ መማክርት ሊቀ መንበር ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡ አሜሪካ ሱዳንን ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ ካለቻቸው ኢራን፣ ሰሜን ኮርያና ሶርያ ተርታ በዝርዝሯ ውስጥ ያስገባቺው እ.ኤ.አ በ1993 እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ የአንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱዳንን ሲጎበኝ ከ15 አመታት ወዲህ ይህ የመጀመሪያው መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ በአፍሪካ 44 ሺህ ያህል የተለያዩ አገራት ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ደብዛቸው ጠፍቶ እንደቀሩ የጠቆመው አለማቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ ከእነዚህ መካከልም ግማሽ ያህሉ ከአካባቢያቸው በጠፉበት ወቅት በህጻንነት ዕድሜ ላይ እንደነበሩ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡ በአፍሪካ ደብዛቸው ከጠፋ ሰዎች መካከል 82 በመቶ ያህሉ ከናይጀሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ካሜሩን የጠፉ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የጠፋባት አገር ናይጀሪያ መሆኗንና በአገሪቱ 23 ሺህ ያህል ሰዎች መጥፋታቸውንም አስረድቷል::
የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተብሎ በየአገራት የተጣሉ ገደቦችና ክልከላዎች የጠፉ ሰዎችን ለማፈላለግ የሚደረጉ ጥረቶችን አዳጋች እንዳደረጋቸውም ተመልክቷል፡፡


Read 2711 times