Saturday, 29 August 2020 14:50

ከግዙፍ ስሙ ተደብቆ የኖረው ከያኒ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 ኢትዮጵያ የክት ልጇን አጥታለች
                     
              በአገራችን ረዥም ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን በመፃፍ ፈር ቀዳጅ፣ የነበረው የመፅሃፍና የቲያትር ተርጓሚው፣ እንዲሁም የህፃናት መዝሙሮችን ደራሲው፣ ራሱን ከዝናና ከታይታ ደበቆ የኖረው ታላቁ ሰው አረፈ።
ወላጆቹ ካወጡለት አድነው ወንድይራድ ከሚለው መጠሪያ ስሙ ይልቅ አዶኒስ በተሰኘው የብዕር ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው የሥነጽሑፍ ሰው፤ ተምሮ በተመረቀበት የአርክቴክቸር ሙያ በጣና በለስ ፕሮጀክት አማካሪ ሆኖ ሰርቷል።
አዶኒስ የነፍስ ጥሪው ኪነጥበብ ነበረችና ራሱን በኪነጥበብ ሙያ ውስጥ ለማሰገባት በንባብ እጅግ ይበረታ ነበር። ይህንን ሁኔታ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ገልፆት ነበር - “ትምህርቴ ከኪነጥበብ ሙያ ጋር ግንኙነት የለውም፤ ግን ራሴን በዚህ ሙያ ውስጥ ለማስገባት በጣም ብዙ አንብቤአለሁ፤ ወደፊትም አነባለሁ። ራሴን የምቆጥረው በኪነጥበብ ውስጥ ራሱን እንዳስተማረ ሰው ነው”።
አዱኒስ በአገራችን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ታሪክ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፍ የሚታወቀው “ገመና” ቁጥር አንድ የቴሌቪዥን ድራማ ደራሲም ነበር።  የቴሌቪዥን ድራማው ከከተማ እስከ ገጠር የቴሌቪዥን ስርጭት በደረሰበት ስፍራ ሁሉ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አግኝቶ ሲታይ የቆየና የሚሊዮኖችን ስሜት ለመግዛት የቻለ ስራ ነበር።
ከአንድ አመት የአየር ላይ ቆይታ በኋላ ክፍል አንድ ድራማው ሲጠናቀቅ፤ አዱኒስ ክፍል ሁለት “ገመና” ፅፎ ከድራማው ፕሮዱዩሰር ከአቶ እቁባይ በርሄ ጋር በክፍያ ዙሪያ ሲነጋገሩ አለመግባባት ተፈጠረ። ሁኔታው በዚህ ላይ እንዳለም ፕሮድዩሰሩ ገመና ክፍል ሁለት በማለት በሌላ ደራሲ በተፃፈ ድርሰት ድራማውን አሰርተው በቴሌቪዥን መተላለፍ ጀመረ። ይህ ሁኔታም አዱኒስን እጅግ ያስቆጣ ድርጊት ሆነ። ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በወቅቱ ጉዳዩን በጥብቅና ይዘው ለፍርድ ቤት ክርክር ያበቁት የህግ ጠበቃ ሰሞኑን ስለጉዳዩ በሰጡት መረጃ እንዳመለከቱት፤ ፍ/ቤቱ ገመና ቁጥር ሁለት ተብሎ በቴሌቪዥን በመተላለፍ ላይ የሚገኘው ድራማ እንዳይተላለፍ ማገዱንና ይህንን እግድ አስመልክቶ የተሰጠው የፍ/ቤት ውሳኔ ከመዝገቡ ውስጥ ተቀዶ እንዲወጣ መደረጉን ይፋ አድርገዋል።
ጉዳዩ በይግባኝ እስከ ጠቅላይ ፍ/ቤት ድረስ ቢሄድም ድራማው በቴሌቪዥን መታየቱን መቀጠል ይችላል የሚል አስገራሚ ውሳኔ ተሰጠው። ይህ ሁኔታም አዱኒስን በእጅጉ አሳዝኖት ነበር። ጠበቃው እንደሚናገሩት፤ ጉዳዩን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ለመውሰድ ፍላጐት ቢኖራቸውም አዶኒስ “በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት ስለሌለኝ የይግባኝ አቤቱታ እንዳታስገባ” ብሎ እንደከለከላቸውም ያስታውሳሉ። ከ “ገመና ቁጥር 1” የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማው በኋላ  “መለከት” የተሰኘውንና 104 ክፍሎች የያዘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ በመፃፍበሮሆቦት ፕሮሞሽን ፕሮዲዩስ ተደርጐ ለእይታ በቅቶለታል፡፡ ይህም የቴሌቪዥን ድራማም ከፍተኛ ተወዳጅነትን ማትረፉንና፣ ለአገራችን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ውሃ ልክ የነበረ ታላቅ ስራ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ አዱኒስ ስለዚሁ የቴሌቪዥኑ ድራማው ሲናገር፤ “ስሜቴን በደንብ የገለጽኩበት፤ ማለት የፈለኩትን ሁሉ ያልኩበት ሥራዬ ነው” ብሏል፡፡
የሮሆቦት ፕሮሞሽን ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ከበደ ስለአዱኒስ ሲናገሩ፤ “አዱኒስ ለስራው ያለው ተነሳሽነት፣ ለሙያው ያለው ዲሲፒሊን እጅግ ያስገርመኛል፡፡ ዝርክርክ አይደለም፤ ጥንቅቅ ያለ ሰው ነው፤ ስራው በተሻለ ጥራት ተሰርቶ እንዲወጣ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፤ የፃፈው ነገር ተሰርቶ ማየት ይፈልጋል፤ በጣም ብዙ ያነበበ፣ ብዙ የሚያውቅ ግን ብዙ የማያወራ ጐበዝ  ሙያተኛ ነው” ብለውታል፡፡  
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ድራማዎችን በድርሰት፣ “አንድ እድል” የተሰኘውን ፊልም ደግሞ በድርሰትና በዝግጅት “መንትዮቹ” ፊልምን በድርሰት ተሳትፎባቸዋል።
በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከአንድ ዓመት በላይ ለዘለቀ ጊዜ በየሳምንቱ ሲወጣ የነበረውን እጅግ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈውን ኋላም በመፅሃፍና በቲያትር ለአንባቢና ለተመልካች የቀረበውን “የአና ማስታወሻ” የተጐመውም ይኸው ራሱን ደብቆ የኖረው ከያኒ ነው። አዱኑስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ለንባብ ካበቃቸውና ረዘም ላለ ጊዜ ከዘለቁት ሥራዎቹ መካከል የአዶልፍ ሄክማን ታሪክ ላይ የተመሰረተው ትርጉም ስራው ተጠቃሽ ነው። “ፕሮፌሰሩ” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መፅሃፍም ለአንባቢያን አድርሷል።
አዱኒስ በቲያትር ስራዎች ላይም ስሙ የገነነ ነው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ለረዥም ጊዜ ሲታይ የቆየውና ከፍተኛ ተወዳጅነትና ያተረፈውን “ኪሊዮፓትራ”፣ በራስ ቲያትርና በአገር ፍቅር ቲያትር ሙድረኮች ደግሞ “ጣውንቶቹ” የተሰኘውንና በአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ ደግሞ “ቀስተደመና” የተሰኙ ስራዎችን ተርጉሞ ለተመልካች አብቅቷል። ይህ ታላቅ የጥበብ ሰው ከመፅሃፍትና ከቲያትር ትርጉም ስራዎቹ፣ ከመፅሃፍ ድርሰቱና ከፊልም ስራዎቹ በተጨማሪ በርካታ የህፃናት መዝሙሮችን ደርሷል። ገና ያላሳተማቸውና ሰርቶ ያጠናቀቃቸው 15 የሚደርሱ የልጆች የመዝሙር ስራዎች አሉት።
እጅግ ከገነነው ስምና ዝናው ውስጥ ተደብቆ የኖረውና በምንም መልኩ በሚዲያ ወጥቶ የማያውቀው አድነው ወንድይራድ (አዶኒስ) ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር፤ በነፃነት መኖር ስለምፈልግ ነው ራሴን የማላወጣው። በነፃነት መኖር ውስጥ ብዙ ነገር አለ። እኔ ደግሞ በእውቅና ስም ይህንን ነፃነቴን ማጣት አልፈልግም” ብሏል።
የገመና ቁጥር አንድ ድራማን መጠናቀቅ ምክንያት በማድረግ በሸራተን አዲስ በተካሄደ የሽልማት ስነስርዓት ላይ አዱኒስ ተሸላሚ ስለነበረ ስሙ ሲጠራ በርካታ አይኖች ወደ መድረኩ አፈጠጡ። መድረክ ላይ ስሙ የተጠራውን በነዛ ትላልቅ ስራዎቹ የገዘፈ ስም ቢያገኝም ራሱን ሸሽጐ የቆየውን ደራሲ ለማየት በርካቶች አሰፈሰፉ። ነገር ግን መድረክ ላይ መጥታ ሽልማቱን የተቀበለችው በድራማው ላይ ትተውን የነበረችው ፓንደራ የተባለችው ልጁ ነበረች። በጣም አስገራሚው ጉዳይ በዚህ እለት ልጁ እሱን ወክላ ከመድረክ ሽልማቱን ስትቀበል አዱኒስ እዛው አዳራሹ ውስጥ ነበር። ሌላው አዱኒስ ለዝናና ለታይታ ቦታ እንደማይሰጥ የሚመሰክረው ደግሞ በዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ክፍል ውስጥ የነበረው ገጠመኝ ነው። በወቅቱ ዩኒቨርስቲው በገመና ድራማ ላይ ግምገማ ያካሂድ ነበር። አዱኒስ ግምገማው በሚካሄድበት ስፍራ በአካል ተገኝቶ ነበር። ነገር ግን ለግምገማው ከታደሙት ሰዎች መካከል አዱኒስ በአዳራሹ እንደነበር የሚያውቅ አንድም ሰው አለነበረም። ከዝናና ከእውቅና ሸሽቶ ተደብቆ የኖረ ግዙፍ ከያኒ ነበር።
አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ስለዚህ ታላቅ የጥበብ ሰው በሰጠው አስተያየት፤ “ኢትዮጵያ የክት ልጇን አጥታለች፤ አዱኒስ በብዙ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ባልተለመደ ሁኔታ ታይታን የማይወድ፣ ግብዝ ያልሆነ፤ ከእውቅና ይልቅ ለስራው ቅድሚያ የሚሰጥ፤ የማይታበይ ድንቅ ባለሙያ ነበር፡፡ ወደ ህይወቱ መጨረሻ አካባቢ 52 ክፍል ያለው አንድ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማን ጽፎ አጠናቆ ነው ያረፈው፤ ለልጆቹ፣ ለባለቤቱና ለትዳሩ ያለው ፍቅርና አክብሮት እጅግ የሚያስገርም ነው፡፡ ያጣነው በጣም ትሁት፣ ሙያውን የሚያከብርና አስገራሚ ስብዕና ያለው ሰው ነው፡፡ ኢትዮጵያም የክት ልጇን አጥታለች - ለቤተሰቦቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ ለእሱም ሰላማዊ እረፍትን እመኝለታለሁ1 ብሏል፡፡
በመድረክ ቲያትርና በሬዲዮ ድራማ ስራዎቹ ይበልጥ የሚታወቀው ታላቅ ወንድሙ ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ፤ ለአሁን ማንነቱ ትልቁን መሰረት እንደጣለበትም ብዙ ጊዜ ይናገራል። አዱኒስ ባደረበት የሳንባ በሽታ ለጥቂት ቀናት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን የቀብር ስነስርዓቱ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ሐምሌ 20 ተፈጽሟል፡፡ የቀብር ስነስርዓቱ የዝናውንና የተወዳጅነቱን ያህል የደመቀ አልነበረም፡፡ ከኮቪድ -19 ጋር በተያያዘ ይመስላል የአዶኒስ ቀብር በዚህ መልኩ ሊሆን የቻለው፡፡ ይህንን ድንቅ የጥበብ ሰው በከፍተኛ ሀዘን ተሰናብተነዋል ነፍሱ በሰላም ትረፍ፡፡  

Read 516 times