Saturday, 29 August 2020 14:45

ማጮለቅ

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(7 votes)

    ሰመመን ላይ ነኝ፡፡ ደጋግሞ የሚነካካኝ ጣት መሆኑን ስረዳ አቅጣጫውን ተከትዬ ዞርኩ፡፡ እጮኛዬ ናት፡፡
“የኔ ፍቅር ....ንቃ...ንቃ...” በለሆሳስ ድምፅ ጆሮዬ ላይ ተለጥፋ እያቃሰተች ...
“ምን ሆነሻል...” ግራ በመጋባት ስሜት ....ሰውነቴ በላብ ተዘፍቋል፡፡ ሰቆቃ የተሞላበት ህልም እያየሁ ነበር -- የቀሰቀሰችኝ፡፡
በርግጥ ህልሙ፤ ገዳም ውስጥ በሶስት የተወላገደ ሰልፍ ወደ መኪና ለመሳፈር ቆመናል፡፡ ነገሩ ግራ ቢያጋባኝም ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ ነን፡፡ ፊት ለፊታችን የገዳሙ ደጀ ሰላም ይመስለኛል ገዝፎ ይታያል ፤ከመኪናችን ባሻገር፡፡ ሰልፋችን እየተመናመነ መጣ፡፡ ተራዬ ደርሶ መኪና ውስጥ ገባሁ፡፡ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ መኪናችን እንደ አለንጋ እየታጠፈ ዚግዛግ ጫካውን አቆራረጠ፡፡
ረዘም ያለ ጉዞ ካደረግን በኋላ በአሸዋ ደለል በተሞላ አውላላ ሜዳ ላይ ወረድን:: እየተሯሯጥን ወደ መሀሉ ገሰገስን፡፡ ነገር ግን መኃሉ ላይ የተንጣለለ ባህር አገኘን:: ዳርቻው ላይ ባለ ሶስት ሜትር ከፍታ ግድግዳ አገኘንና ሁሉም ሰው እላዩ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፡፡ እኔ ፤ ከስር አሸዋው ውስጥ የተሰገሰጉ ረጃጅም ትሎች ተረከዜና ጣቶቼ ላይ ተጣብቀውብኝ ለመራመድ አልቻልኩም፡፡ አንዳንዴ ስወድቅ እጄ ላይ እንዳይጣበቁ ስታገል እቆይና  ቀና ስል ሰዎቹ ሁሉ #ተነስ...ተነስ ..;.እያሉ ሲጮሁ ይሰማኛል፡፡...ልክ እዚህ ላይ ነው ...የቀሰቀሰችኝ፡፡
“የሆነ ሰው በር ለመክፈት እየታገለ ነው፤ ይሰማሃል? “ አለች -- በተዳከመ ድምፅ፡፡
“ማነው እሱ ..?”  ከማለቴ ፣ አፌን በጣቷ አፈነችኝ፡፡
“ባትሪ በመስኮቱ በኩል ወደ እኛ እያበሩ ነበር፤ አልፎ ...አልፎ...ያወራሉ” አለችኝ ፤ጆሮዬ ስር ተወሽቃ፡፡
“አሁን የኔ ተራ ነው፤ አትጨነቂ” ከማለቴ ከበር ጋር መታገል ጀመሩ፡፡ ልነሳ ስል እላዬ ላይ ተጠምጥማ እንዳልነሳ ለመነችኝ፡፡
“ተይኝ ልነሳበት...ሊዘርፉን እኮ ነው!"
“አይደለም!  ሊገሉህ ነው፡፡ ዘረፋ አይደለም.....ደሞ መጥፎ ህልም አይቻለሁ:: አውቄዋለሁ፡፡ በማሪያም፣ በገብሬል ይዤሃለሁ እንዳትነሳ... እንዳትወጣ:: እቃውን ላልከው ከወሰዱ ይውሰዱት እገዛዋለሁ::” እውነትም አምርራለች... ተጨንቃለች...ድምጽዋ ይሻክራል፤ ውስጧ ጠቁሯል፡፡
ሰዎቹ በየአቅጣጫው ያበራሉ...ይፈልጋሉ... ያጮልቃሉ፤ በሩን ደጋግመው ይጫናሉ፡፡
“እስኪ ስለ ህልምሽ ንገሪኝ?....ምን አየሽ?...”  
“በጣም ያስፈራል..” ሰውነቴን ጨመቀችኝ፤ መዳሰስ አይሉት መቧጠጥ ...ጣቶቿን ደረቴ ላይ  አስደነሰቻቸው፡፡
“ኸረ ገቡ...መሳሪያ እንኳን የለን....በምን እንከላከላለን....” አለችኝ በጭንቀት....
“እሽ ንገሪኝ ... “
“ስማኝ እሽ! ... ገጠር ውስጥ ሶስት ጎጆ ቤቶች ተከራይተን  ይመስለኛል፡፡ ከዛ ዙሪያውን የወዳደቀ እንጨት እየለቀምኩ ሳለ ይቺ አስቀያሚ ጎረቤታችን ...ስሟን ቄስ ይጥራውና ...ታሽሟጥጠኝ ጀመር፤ በህፃን ልጇ አስመስላ፡፡ በገንኩ! ተከንኩ!  ከዛ የለቃቀምኩትን  እንጨት እንጀራ ልጋግርበት እሳት ጫርኩ፡፡ ምጣዱንም ጣድኩና ሲሞቅ ማሰሻ እየተጠቀምኩ እያለ ...የላይኛው፣ ለስላሳው የምጣዱ ክፍል በራሱ ጊዜ ተቀርፍቶ ተነሳ፡፡ ከዛ ምኑን ላስሰው፤ ሸካራ ሸክላ ሆነብኝ፡፡ ከዛ ጣራ ላይ ድንጋይ ይመስለኛል ሲወድቅ ነቃሁ፡፡ ምን ተፈጠረ ብዬ ስጨነቅ ባትሪ አየሁ፡፡ በቀደም እራሱ አትውጣ እያልኩህ ወጣህ....ይገሉብኛል .... እንዳትወጣ፡፡....”   እንባ  እየተናነቃት...
በአዕምሮዬ በርካታ ጉዳዮች ተርመሰመሱ:: የነገሮችን ልክ ለመረዳት ባዘንኩ፡፡ ትውስታዎቼን ለማውጠንጠን ብሞክርም ውቅያኖስ ሆነብኝ፡፡ አንዱን አንስቼ ሌላውን ጣልኩ፡፡ አልቻልኩም:: ስለሆነም በዚህ ውድቅት ሌሊት ለምን ዓላማ ፣ ተልዕኮ እንደመጡ ማወቅ ተሳነኝ፡፡
የሚገርመው ደግሞ ችግር እንኳ ቢፈጠር ምን ማድረግ እንደምችል አለማወቄ ነው:: ምንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ የጥቅጥቅ ጨለማው ድባብ፣ ከስስ ካፊያና ጠንከር ካለ ነጎድጓድ... ብልጭታ ጋር ተዳብሎ ሁኔታው የምጥ ያህል ከብዶኛል፡፡ ሀሳብ ፤ ጭንቀት፡፡ ከፍተኛ ጥርጣሬ፡፡
በቅፅበት ትዝታዎቼ ቀዝቃዛ ስሜት ውስጥ ዘፈቁኝ፡፡ በህይወት፤ የሞግዚትነት ሚና እንደነበረኝ ተሰማኝ፤ “ለራሴ አልኖርኩም እንዴ?...” አልኩ፡፡
“ኸረ ባክህ ልብስ ልበስ፡፡ ድንገት ሰብረው ቢገቡ ራቁትህን... ቀስ ብለህ ...ድምፅ ሳታሰማ ተነስ፤ ልበስ፡፡”  የእንባ ጠብታ ደረቴ ላይ በተከታታይ አረፈ፡፡ ምንጩን ለማግኘት ጣቶቼን ብልክም ትክክለኛ ቦታ ላይ አላረፉም፡፡ ቢሆንም...
“ህልሜን እየቋጠርኩ ነው፡፡ በህይወት የተጫወትኩትን ሚና ደግሜ እየፈተሽኩ ነው፡፡ ሳይቀድሙኝ መቅደም አለብኝ፡፡ የምንም ነገር ሀይል ብርታቱ የሚመነጨው ከትርጉሙ ነው፡፡ እውነቴን ልጨብጣት፤ የህልው መሆን ተስፋ  ምን ድረስ እንደሆነ መረዳት አለብኝ፡፡ በዚህ ነው፤ ማሸነፍ ምችለው፡፡ ...ዋጋን አለማወቅ ነው፤ ተሸናፊነት፡፡ ጠብታ ማር ብዙ ንቦችን እንደምትስበው ሁሉ ብርቱ ህልምም በርካታ ህሊናዎችን ይገዛል፤ ይጠራል፡፡ ዋጋ ባይኖረኝ ኖሮ ሊገሉኝ ይመጡ ይሆን?... አይመስለኝም፡፡"
ከሐሳቤ ስመለስ ሰዎቹን አጣኋቸው፡፡ በበር ባጮልቅም ላያቸው አልቻልኩም፡፡ ዳናቸው ጠፋኝ፡፡
ተጠቃቅሰን ወደ እንቅልፋችን ተመለስን:: ፀጥ፡፡ እረጭ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1151 times