Print this page
Tuesday, 08 September 2020 00:00

ማኬንዜ ስኮት በ68 ቢ. ዶላር የአለማችን ሃብታሟ ሴት ሆናለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      ካይሌ ጄነር በ590 ሚ. ዶላር የአመቱ ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኛ ተብላለች

         የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ የቀድሞ የትዳር አጋር የነበረችው አሜሪካዊቷ ደራሲና በጎ አድራጊ ማኬንዜ ስኮት አጠቃላይ የተጣራ ሃብት 68 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ይህም ግለሰቧን የአለማችን ቀዳሚዋ ሴት ባለጸጋ እንዳደረጋት ብሉምበርግ ከሰሞኑ አስነብቧል፡፡
ማኬንዜ ባለፈው አመት ከአማዞኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ ጋር ባለመግባባት ሳቢያ ትዳራቸውን አፍርሰው መፋታታቸውንና በካሳ መልክ ከቤዞስ የአማዞን የአክሲዮን ድርሻ ሃብት ሩብ ያህል እንደተካፈለች ያስታወሰው ዘገባው፣  የ4 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ በወቅቱ 35 ቢሊዮን ዶላር ይገመት እንደነበርና ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እያደገ መጥቶ አሁን 68 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጧል:: ግለሰቧ በአሁኑ ወቅት የአለማችን 12ኛ ሃብታም ሴት መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ለ116 ድርጅቶች በድምሩ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ያህል የበጎ አድራጎት ድጋፍ ማድረጓንም አመልክቷል፡፡
የአማዞን ኩባንያ የአክሲዮን ዋጋ ባለፉት ሶስት ያህል ወራት በ28 በመቶ ያህል ማደጉን ያስታወሰው ዘገባው ይህም ዋና ስራ አስፈጻሚውን ጄፍ ቤዞስን ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ያፈራ የመጀመሪያው የአለማችን ሰው እንዳደረገው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፤ ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2020 የፈረንጆች አመት የአለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በአልባሳትና መዋቢያ ቁሳቁስ ኩባንያዋ የምትታወቀው አሜሪካዊት ሞዴልና የሚዲያው ዘርፍ ዝነኛ ካይሌ ጄነር በ590 ሚሊዮን ዶላር አንደኛ ደረጃን ይዛለች:: አሜሪካዊው ራፐር ካንያ ዌስት በ170 ሚሊዮን ዶላር የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮናው ሮጀር ፌደረር በ106.3 ሚሊዮን ዶላር፣ ፖርቹጋላዊው የአለም የእግር ኳስ ኮከር ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ105 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ተፎካካሪው አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በ104 ሚሊዮን ዶላር እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የአመቱ 100 የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች በድምሩ 6.1 ቢሊዮን ዶላር እንደተከፈላቸው የጠቆመው ፎርብስ መጽሄት፣ ክፍያው ካለፈው አመት በ200 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ መሆኑንና ይህም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ መሆኑን አክሎ ገልጧል፡፡
ቴለር ፔሪ በ97 ሚሊዮን ዶላር፣ ብራዚላዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ኔይማር በ95.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ሆዋርድ ስተርን በ90 ሚሊዮን ዶላር፣ ሊብሮን ጄምስ በ88.2 ሚሊዮን ዶላር፣ ዋየኔ ጆንሰን በ85 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ክፍያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ6ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ዝነኞች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

Read 2802 times
Administrator

Latest from Administrator