Sunday, 06 September 2020 15:00

የኮሮና ቫይረስ ጽኑ ህሙማን ቁጥር እያሻቀበ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

             - በዓሉ የደስታ እንዲሆን በጥንቃቄ እናክብር
             - የኮሮና ህክምና ማዕከላት በየወረዳው እንዲስፋፉ እየተደረገ ነው
            - መጪው በዓል የበሽታውን ስርጭት ሊያስፋፋ እንደሚችል ተሰግቷል
                     
           የኮሮና ቫይረስ ፅኑ ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣ ሲሆን ባለፈው ሳምንት እስከ 357 ሰዎች ጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል መግባታቸው ታውቋል፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ አንድ መቶ አስራ አንድ ታማሚዎች በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንሚይመለክተው፤ በሣምንቱ ለ139ሺ 122 ሰዎች ምራመራ ተደርጐ፣ 8ሺ 796 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡
የጽኑ ታማሚዎች ቁጥርና በቫይረሱ ሳቢያ የሚከሰተው ሞት ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን የገለፁት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 የጤና ቴክኒክ አማካሪ ቡድን አስተባባሪ ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋ ነው፤ ይህንን ችግር ለማስወገድም የተቋማት ማስፋፊያ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ የህክምና ማዕከላት በስፋት እየታየ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ወልደሰንበት፤ ችግሩን ለማስወገድ በወረዳ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ህክምና መስጫ ማዕከላትን የማስፋፋትና የጽኑ ህሙማን ክፍሎችን የማጠናከር ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ካለፈው ሰኔ ጀምሮ የጽኑ ታማሚዎችና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን የገለፁት ዶ/ር ወልደሰንበት፤ አሁን የገጠመን ችግር የጽኑ ህሙማን ክፍሎች መሙላታቸውና መጨናነቅ መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን ጽኑ ህሙማኑ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ ህክምናዎችን መፈለጋቸውና የጤና ባለሙያዎችን የቅርብ ክትትል የሚሹ በመሆኑ ብዙ ባለሙያዎቻችን በአንድ የተወሰነ ቦታ ላይ እንዲሰሩ በማድረግ የባለሙያ እጥረት እንዲፈጠር መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ እያንዳንዱ ማህበረሰብ የሚፈጽማቸው ጥንቃቄዎችና የበሽታ መከላከል እርምጃዎች እንዲህ አይነት ችግሮችን ለማስቀረት የምናደርገውን ትግል በእጅጉ ያግዛል ያሉት ዶክተሩ፤ በበሽታው ከተያዝን በኋላ የሚገጥመንን ችግር ከወዲሁ በመገንዘብ በጥንቃቄዎቹና መከላከያዎቹ ላይ ልንበረታ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡
ከመጪው የአዲስ አመት በዓል አከባበር ጋር በተያያዘም የበሽታው ስርጭት ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት መፈጠሩን ያመለከቱት ዶክተሩ፤ ህብረተሰቡ ከወዲሁ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግና ራሱን ከበሽታው ሊጠብቅ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡  
በዓሉን የደስታ ለማድረግ በጥንቃቄ ማክበር ይመከራል፡፡

Read 913 times