Sunday, 06 September 2020 15:15

አቶ ልደቱ በፃፏቸው ፖለቲካዊ ሰነዶች ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ሆኗል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የኢዴፓ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው ፍ/ቤት አስቀድሞ በተጠረጠሩበት ጉዳይ  ነፃ ብሎ ቢያሰናብታቸውም፤ በእጃቸው ላይ ተገኙ በተባሉ ፖለቲካዊ ሰነዶች ምክንያት ከእስር ያልተፈቱ ሲሆን የኢሃን ሊቀ መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ ከሁለት ወራት እስር በኋላ ከትላንት በስቲያ ተለቀዋል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌው፤ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ፣ በቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶችን በገንዘብ በመደገፍ ሁከትና ግርግር አስነስተዋል በሚል ፖሊስ ምርመራ እያጣራሁባቸው ነው ማለቱ የሚታወስ ሲሆን ከተደጋጋሚ ቀጠሮ በኋላ ጉዳዩን የሚመለከተው የቢሾፍቱ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ አቶ ልደቱን የሚያስከስሳቸው ጉዳይ አላገኘሁም በማለት፤ በነፃ እንዲሰናበቱ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 25 መወሰኑ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ አቃቤ ህግ፤ በሌላ ጉዳይ እፈልጋቸዋለሁ በማለቱ አቶ ልደቱ አያሌውን በእስር አቆይቷቸዋል፡፡ በብርበራ ወቅት በእጃቸው ላይ የተገኘ “የሽግግር መንግስት ማመልከቻ ሰነድ”  እና “ለውጡ ከድጡ ወደ ማጡ” የሚሉ ርዕስ ያላቸውና ህገ መንግስቱን ለመናድ የተዘጋጁ ፖለቲካዊ ሰነዶች ላይ ምርመራ ማድረግ በመጀመሩ በእስር እንዲቆዩ ማድረጉን አቃቤ ህግ ለፍ/ቤት አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪው አቶ ልደቱ በበኩላቸው፤ የሽግግር መንግስት መመስረቻ ሰነዱን ለመንግስት በይፋ አቅርበው ተቀባይነት የለውም በመባሉ ያስቀመጡት እንደሆነና ተጠያቂነትን የሚያስከትል ቢሆን መንግስት እስካሁን ዝም እንደማይላቸው አስረድተዋል:: ዋስትናቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉም ጠይቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ጉዳያቸውን ሲከታተሉበት የቆየው የምስራቅ ሸዋ ቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጐ፣ ለአቃቤ ህግ ክስ የመመስረቻ 15 ቀን ጊዜ ትናንት ከሰአት ፈቅዷል፡፡
በሌላ በኩል፤ የኢሃን ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት  “በአዲስ አበባ ሁከትና ግርግር መፍጠር” በሚል ከቀረበባቸው ክስ ነፃ ተብለው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ከእስር ተለቀዋል፡፡  

Read 1080 times