Print this page
Sunday, 06 September 2020 15:34

ቤተ ክርስቲያኒቱ ለተጐጂዎች የ3 ቢ. ብር ድጋፍ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ይፋ አደረገች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ቤተ ክርስቲያኒቱ በኦሮሚያ ክልል ጥቃት ለተፈፀመባቸው ምዕመኖች በአጠቃላይ የ3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ይፋ ያደረገች ሲሆን እስከ ዛሬ የተሰባሰበው 40 ሚሊዮን ብር እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ለተጐጂዎች ይከፋፈላል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እርዳታና መልሶ ማቋቋም አብይ ኮሚቴ በኩል በአጭር የሞባይል መልዕክት፣ የቤተክህነት ሠራተኞችን፣ ተቋማትን፣ አድባራትን፣ ባንኮችን፣ የመንግስት ተቋማትን በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያሉ ምዕመናንን በማስተባበር እስከ 3 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ 7ሺ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም እቅድ ማውጣቷን አስታውቃለች፡፡
ድጋፉ ለተፈናቃዮች የሚደርስበት መንገድም የጉዳት መጠንና አይነትን መነሻ ያደረገ መሆኑንና በቀጥታ ለተጐጂዎች በእጃቸው የሚደርስ እንደሚሆንም ታውቋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ በቀጣይም የምዕመኖቿን የኑሮ ዋስትናና ደህንነት ለማስጠበቅ ይረዳል ያለችውን የድጋፍ ተቋም ማቋቋሙም ተገልጿል:: ከዚህ ተቋም ውጪ የሚሰበሰብ ድጋፍም ተገቢነት እንደማይኖረውና ሁሉም ምዕመኖችና ቤተ ክርስቲያኒቱን ማዕከል ያደረጉ ድጋፎች በዚህ ተቋም በኩል ይከናወናሉ ተብሏል፡፡
እስካሁን በተለያዩ መንገዶች የተሰበሰበው የ40 ሚሊዮን ብር ድጋፍም እያንዳንዱ ተጐጂ ስም ዝርዝሩ ተለይቶና የጉዳቱ መጠን ተጠንቶ፣ ድጋፉ በቀጥታ እንዲደርሳቸው መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 9315 times