Print this page
Sunday, 06 September 2020 15:36

በአፋር ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች በጐርፍ ሲፈናቀሉ፤ ከ32ሺህ በላይ አደጋ ተጋርጦባቸዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

የአፋር ክልልን ደጋግሞ እያጠቃ የሚገኘው የጐርፍ አደጋ፣ እስካሁን ከ40ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ያፈናቀለ ሲሆን አሁንም ከ32ሺህ በላይ የሚሆኑት ስጋት ተጋርጦባቸዋል ተብሏል::
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከትላንት በስቲያ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በአማራና በትግራይ ደጋማ አካባቢዎች በሚዘንበው ዝናብ የሚፈጠረው ጐርፍ በ11 የአፋር ወረዳዎች ላይ መጥለቅለቅን እየፈጠረ፣ 67ሺህ 885 ያህል ሰዎችን አጥቅቷል፤ 40ሺህ 731 ደግሞ አፈናቅሏል፡፡
የጐርፍ አደጋው 100 ያህል ት/ቤቶችና የጤና ተቋማትን ከጥቅም ውጪ ሲያደርግ፤ ከ17ሺህ በላይ የቤት እንስሳትም ገድሏል፡፡
የክረምቱ ሁኔታ ቀጣይነት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞም፣ አሁንም ከ32ሺህ 3መቶ በላይ ነዋሪዎች የአደጋ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ሳምንታትም የክረምቱ ዝናብ በኢትዮጵያ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በተለይም በሀገሪቱ ሰሜን ምዕራብ ከ200 ሚሊ ሜትር በላይ የሆነ ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ፤ የምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ምርምር ማዕከል አስጠንቅቋል፡፡
መንግስትና የተለያዩ በጐ አድራጐት ተቋማት፣ ለጐርፍ ተፈናቃዮች እርዳታ እያቀረቡ ቢሆንም በቀጣይም ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡  

Read 8373 times