Sunday, 06 September 2020 15:50

የድህነታችን ሰምና ወርቅ - ከኮሮና ዶፍ አንፃር

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(0 votes)

  ብልህ ገበሬ፣  ክረምት ከመግባቱ አስቀድሞ፤ ሰማይ እርቃኑን ሳለ፤ ጎተራውን ይሰራል:: ሰብሉን ይሰበስባል፣ ለራሱና ለቤተሰቡ ብሎም ለእንስሳቱ በቂ ቀለብ ያዘጋጃል፡፡ የዝናም ልብሱን፣ ዣንጥላውን፣ ባርኔጣውን ይጠቃቅማል፤ የቤቱን ጣሪያ ያጠባብቃል፤ እና የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን ይቀዳድዳል፡፡ ሰማይ ስስ ደመና መልበስ ሲጀምር፣ የጀመረውን ዝግጅት ያፋጥናል፡፡  ሰማዩ መጠቋቆር ሲያመጣ ደሞ ያሉትንና የሌሉትን ነገሮች በመለየት የጎደሉትን ያሟላል፡፡ እናም፣ ፈገግ ባይልም፤ አይቀሬውን ጥቁር እንግዳ፤ ክረምትን፤ እጅ ነስቶ ይቀበላል፡፡
ዝናም መጣል ሲጀምር፣ አይደናገጥም - ተዘጋጅቷላ፡፡  ይሁንና፣ የእለት እንቅስቃሴው ከወቅቱ ጋር  ይቃኛል እንጂ፣ ሥራ ፈትቶ ከቤት አይውልም፡፡ በክረምት፣ መንደር አካላይ በረራዎቹን ሁሉ ሰርዞ ከጎጆው የሚውለው አሞራ ብቻ ነው፡፡ ሰው እንደዚያ ሊሆን አይችልም፡፡ እናም፣ ዝናም ቢጥልም ከቤት መውጣት ግድ የሚሆንበት አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ ያኔ ታዲያ፣ ዣንጥላውን ይዞ፣ ከጓሮው ኮባ ቅጠል ቆርጦ፣ ገሳውን ወይም የማዳበሪያ ከረጢት ብጤ ጭንቅላቱ ላይ ጣል አድርጎ፣ ራሱን ያሰማራል፡፡ ይህን የሚያደርገው ታዲያ፣ ዝናሙ የማያቋርጥ መሆኑን ከገመገመ በኋላ ነው - እንጂ በማንኛውም ሰዓት ብድግ ብሎ ደጁን አይረግጥም፡፡ ለዚህም “የሚያልፍ ዝናም አይምታህ” የሚል መመሪያ አለው:: ከየአቅጣጫው የሚምዘገዘገው የደመና ፈትል ሳይገጥም፣ በቅጡም ሳይጠቁር፣ ሌላ ቀርቶ ፀሀይ ሙሉ በሙሉ ሳትጋረድ፤ ጨረሯ ሳይደበዝዝ፤ እየተሽቀነጠረ የሚወርድ ጠጠር፣ ጠጠር የሚያህል ዝናም ሲያይ አይደናገጥም፡፡ ከተሞክሮው አላፊ መሆኑን ስለሚያውቅ፣ ከበሩ ታዛ ቆሞ ነው ቀጥ እስኪል  የሚጠብቀው::  ህፃናት ግን፣ ክረምትና በጋ ሲደበላለቁ በማየታቸው የተነሳ ተደስተው፣ “ጅብ ወለደ” እያሉ ሜዳ ላይ ወጥተው ሊቦርቁ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴም፣ ከምስጥ ኩይሳ ውስጥ እየተንደረዱ የሚወጡ ክንፋም በራሪ ነፍሳትን (አሸን) አሳደው ለመያዝ እየተሯራጡ ይዝናናሉ:: ውሾቻቸው ነፍሳቱን ከመያዝ አልፈው ሲበሏቸው በማስተዋል ይደሰቱም ይሆናል:: ወፎች ሰማይ ላይ ከፍ ዝቅ እያሉ ነፍሳቱን ሲለቅሙ በማየትም ይፍነከነካሉ:: ትዕይንቱ፣ በቀስተደመና ዝርጋታ ይደምቅም ይሆናል:: ይህም ባይሆን፤ “ዝናቡ አሳድገኝ” እያሉ መጨፈራቸው አይቀርም፡፡
ፌዘኛ ከሚመስለው ዝናብ መለስ እንበልና፣ በረዶና ውሽንፍር የቀላቀለ ዶፍ የሚወርድ ከሆነ፣ ገበሬው በ”ከመኖር መሰንበት” መላ ወደ ቤቱ መለስ ይላል እንጂ ዣንጥላውን ይዞም ቢሆን ከቤት አይወጣም፡፡ ለምን? በመብረቅ መመታት አለኣ፡፡ በጎርፍ መጠለፍ፣ በደራሽ ውሃ መወሰድም ሊኖር ይችላል፡፡ ዣንጥላን በንፋስ ማስገንጠልም ይኖራል፡፡ በአንጻሩ፣ ስስ፤ እኝኝኝኝ  የሚል ካፊያ ከሆነ፣ ሲሻው የዝናም ልብሱን ደረብ አድርጎ አሊያም የስራ ልብሱን ብቻ እንደለበሰ ሮጥ፣ ሮጥ እያለ ወደ ጉዳዩ ያቀናል፤ ገበሬው፡፡ በአጭሩ፣ ገበሬና ክረምት እንዲህ እንዲያ እያሉ ነው የሚኖሩት፡፡ “ገበሬ” ስል “እማ-ወራ” ሴት ገበሬዎችን- የገበሬ ሚስቶችንም ማለቴ ነው::
ክረምት ግን ወቅቱን ሳይጠብቅ ሊመጣ ይችላል፡፡ ከሚጠበቅበት ወር ጥቂት ቀደም ወይም ጥቂት ዘግየት ብሎ መምጣት ብቻ ሳይሆን የበጋውን አንጓ ዘብሮ ሊከሰት ይችላል:: አዝመራ ሳይሰበሰብ፤ ሳይታጨድ፣ ሳይከመር ከተፍ የሚል ዝናም “ወቅቱን ያልጠበቀ” ተብሎ ይታወቃል፡፡ ያኔም ቢሆን፣ ገበሬው ችግሩን የሚቋቋምባቸው፣ የመጣውን አደጋ ጉዳት መጠን የሚቀንስባቸው፣ ዘዴዎች ይኖሩታል:: ይህን ለማድረግ ግን ብዙ መሯሯጥ፣ ብዙ “ጎበዝ፣ ድረሱልኝ” ማለት ይጠበቅበታል፡፡
ይህ ሁሉ ሀተታ የሚያመራው የኮሮናን ክስተት ከክረምት ጋር ለማገናኘት ነው፡፡ ይህ ነው መነሻ ሀሳቤ፡- ከጠቅላላ ህዝባችን ቁጥር ሰማንያ አምስት በመቶው በግብርና (ከብት ማርባትን ጨምሮ) የሚተዳደርና በገጠር የሚኖር ነው፡፡ ቀሪው፤ የህዝባችን አስራ አምስት በመቶ የሆነው፤ የከተማ ነዋሪም በአያሌው መሰረቱ ገጠር ነው:: አዲስ አበባ ውስጥም ይሁን በሌሎች ከተሞች አያቶቻቸው “ከተማ ተወልደው ከተማ ያደጉ” አባቶች ቁጥር ብዙ አይደለም፡፡ ትምህርትና እንጀራ ብቻችንን እያንደረደረ አዲስ አበባ አስገብቶ ያስቀረን (ነው?/የቀረን) ሰዎችም ብንሆን፣ የህልም ኬላችን ከከተማ ይልቅ የመጣንበት የገጠር መንደር ነው፡፡ እና፣ ምሳሌው ያግባባናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ኮሮናን ባልተጠበቀ ዝናም አመሳስዬ የጀመርኩትን ልጨርስ፡፡ “ቻይና ውስጥ ወቅቱን ያልጠበቀ (ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ በፊት ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ) ዝናም ጥሎ ብዙ ሰው በጎርፍ ተወሰደ፣ ሰብል ወደመ፣ ፋብሪካዎች ተዘጉ፣ ሰው ከቤቱ መውጣት ስላልቻለ የኑሮ ምስቅልቅል ገጠመው ...” የሚል ዜና ተሰማ:: ዝናቡ በቻይና ብቻ አልተገደበም፤ ወደ አጎራባች አገሮችም ዘልቆ ተመሳሳይ ጉዳት አደረሰ፣ ሰው ገደለ፣ ሰብል አጠፋ ተብሎ ተነገረ፡፡ “ይሄ ነገር የወዲያ አገር ሰዎች ጣጣ ይሆን እንዴ?” በማለት የዓለም ህዝብ ያለ ስጋት ወሬ ሲከታተል፣ የኮሮና ዶፍ ወደ አሜሪካ ዘለቀ፡፡ ሰብላቸውን ሳይሰበስቡ፣ ጎተራቸውን ሳያጠባብቁ ከተፍ አለባቸው:: ቀጠለ፡- ዝናሙ ዓለምን እንደሚያዳርስ ተጠረጠረ፤ ብዙም ሳይቆይ ታወቀ፡፡
ዝናሙ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት አልቸኮለም፡፡ አገራችን፣ ግን ጥቁሩ እንግዳ እንደማይቀር እርግጠኛ ነበረች፡፡ ቢሆንም፣ “ሳይረግጡ ማንከስ፣ ሳይደርሱ ማጎንበስ” የራሱ ጫና ስላለው ሁኔታዎችን በንቃት ስትከታተል ቆየችና፣ ነገሩ የበለጠ አሳሳቢ እየሆነ ሲመጣባት፣ የኮሮናን ክረምት የምትቋቋምበትን ስልቶች በጥድፊያ መቀየስ ጀመረች፡፡ ለዜጎች የማስጠንቀቂያ “አዋጅ” ተነገረ፡፡ ስንቅ መሰባሰብ ተጀመረ፡፡ ሌላ ቀርቶ የዝናቡ አደጋ ጉዳት ለሚያደርስባቸው ዜጎች ተኝቶ መታከሚያ በርካታ ሊባል የሚችል ቦታ ተዘጋጀ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በታሪኩ ሳይሆን አይቀርም (ከጦርነት ውጪ)፣ ከ”ሕዝቡ” ሁለት የአዋቂ እርምጃ ቀድሞ የመጣውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶችን አደረገ:: መሪዎቹ በአዝማችነት ከፊት ተሰልፈው አርዓያነት ያለው ተግባር መፈፀም ጀመሩ፡፡ ዜጎችስ እንዴት ተቀበሉት?
የኮሮና ዝናብ ኢትዮጵያ ውስጥ መጣል ጀምሯል፡፡ ዝናሙ ገና ቻይና በነበረ ጊዜ መጪውን አደጋ ለማለፍ በቂ የኑሮ ዝግጅት ያላደረጉ ሰዎች፣ ችግሩ ደጃቸው ሲደርስ ስላዩ መጠንቀቅ ጀምረዋል፡፡ አይከፋም፡፡ የዝናም መከላከያ፣ ዣንጥላ፣ የዝናም ልብስ ወዘተ እያዘጋጁ፣ እየሸመቱ፣ እየተጠቀሙም ነው:: አብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ (የገጠሩን ትተን፣ የከተማው ላይ ብቻ ብናተኩር) ግን መንግሥት የሚያሰሟቸውን አዋጆች፣ ማስጠንቀቂያዎች እየተገበሩ አይደለም:: “ከቤት መውጣት ግድ ካልሆነባችሁ በስተቀር ዝናቡ እስኪያልፍ ድረስ ከቤታችሁ ተጠልላችሁ ቆዩ” ቢባሉም ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡ በማንኛውም ሰዓት ዝናብ ሊመታቸው እንደሚችል እየተነገራቸው ስስ ልብስ ለብሰው ከቤት ይወጣሉ፤ ያውም ይህ ነው የሚባል ጉዳይ ሳይኖራቸው፡፡ ግድ የላችሁም፤ ዝናብ አበሰበሰን፣ ጭቃ በጭቃ ሆንን፣ ጎርፍ ደጃችን ድረስ መጣ (ሊመጣ ነው) ወዘተ እያልኩ ከማሰፋባችሁ ወደ ቀለብ ነክ ጭውውት እንዝለቅ፡፡ ለመሆኑ፣ “ሕዝባችን” ለዝናም ጊዜ፣ ለችግር ጊዜ፣ ማለት ቀለብ እጥረት ለሚያጋጥምበት ወቅት (ሬኒ ዴይ እንዲሉ ፈረንጆች) ዝግጁ ነው ወይ? አይደለም፤ ብዙ ሰው እንደሚለው፣ “አብዛኛው ህዝባችን ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ነው!” ግን ለምን ሆነ?
መዋቅራዊ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ ብዙ ሰው ድንገተኛ ችግሮችን ለመቋቋም የሚቸገረው፣ በገቢው ማነስ ብቻ አይደለም፤ ጨርሶ! “ክፉ ጊዜ”ን አስቦ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ስለማይጥር፤ ቀድሞ ነገር “ክፉ ጊዜ”ን ማሰብን ራሱ ስለሚፈራ፤ በዚህ ላይ ደግሞ ከገቢው ላይ ቀንሶ ጥሪት የመያዝ ልምድ/ባህል ስለሌለውም ነው፡፡ ለመታከሚያ የሚሆን ገንዘብ ማጠራቀም፣ የጤና/የህይወት ኢንሹራንስ መግባት ወዘተ ከብዙ ሰዎች የሀሳብ ንፍቀ ክበብ ውጭ ነው፡፡ “መረዳዳት” ብለን የምንመካበት ባህላችንም ከዚሁ፤ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ችሎ ለመኖር ዝግጅት ከማጣቱ፤ ጋር የተያያዘ “ተግባር” መሆኑን ጠቆም አድርጌ ልለፍ፡፡
የገንዘብ አያያዝና አጠቃቀማችንን ከኮሮና ክስተት (ብሎም ከሌሎች አደጋዎች) ጋር አቆራኝቼ አንድ ሁለት ነገር ልበል:: ያ ሁሉ ዝናብ ነክ ወግ መቼም ለዝናብና ለክረምት የሚደረግ ዝግጅትን ብቻ ለማተት አይደለም፤ እንደምትገምቱት፡፡ መደምደሚያዬ፣ ለኮሮና ብቻ ሳይሆን ለብዙ አይነት ችግር ዝግጁ አይደለንም የሚል ነው::
አገራችን ውስጥ በኮቪድ - 19 የተጠቁ ሰዎች መኖራቸው ተነግሮ ለአስራ አራት ቀናት ያህል ከቤት ዋሉ ተብሎ ሲነገር፣ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የከተማ ነዋሪዎች (ሚሊየኖች ያላልኩት ፈርቼ ነው) ለአንድ ቀን የሚበቃ ገንዘብ በኪሳቸው፣ በቦርሳቸው ውስጥ አልነበራቸውም፡፡ ስለ ባንክ ደብተርማ አይነሳም፡፡
ምሳሌ ልስጥ፡- በግንባታ ሥራ ላይ በቀን ሠራተኛነት ተሰማርቶ ቤተሰቡን “ቀጥ አድርጎ” የሚመራ አንድ ጎረቤት አለኝ፡፡ ይህ ሰው፣ በሰላሙም ጊዜ ለክረምት የሚሆን ዝግጅት እንደማይኖረው እገምት ነበር - እንኳን በድንገት ከቤት አትውጡ ተብሎ - ማለቴ ነው:: “ከቤት አትውጡ” የሚለው ጥሪ በሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተሰማ፣ እንዲያየኝ ብዬ በደጁ መንጎራደድ ጀመርኩ፤ ብርቱ ችግር ካለበት እንድድደርስለት አስቤ:: ከቤቱ ወጣ ሲል አየኝ:: እንደ ወትሮው ሰላምታ ሳይሰጠኝ፤  “አረ ጋሼ፣ ጉድ ሆንኩልህኮ...” አለኝ፡፡ ቀጥሎም፤ “ሚስቱ ከቀናት በፊት መውለዷን ነገረኝ፡፡ ከጥቂት ጭውውት በኋላ፣ በእርዳታ መልክ ሳይሆን በ”እንኳን ደስ አላችሁ” ሽፋን አንድ ሶስት ቀን የሚገፋበትን ገንዘብ ሰጠሁት፡፡
ዋናው ወግ ይኼውላችሁ፡- ከብዙ ወራት በፊት፣ ከዚህ ሰው ጋር ስለ ገንዘብ አያያዝ አውርተን ነበር፣ በኔ ጨዋታ አንሺነት:: ታዲያ፣ በየቀኑ ሁለት ስኒ የጀበና ቡና (እየገዛ) እንደሚጠጣ፣ በተጨማሪም፣ ለውሀ ጥም አንድ ሁለት ድራፍት (ቢራ) እንደማይቀርበት፣ ወዘተ አወጋኝ:: ሲያበቃም፣  “አሁን በእጅህ ላይ ስንት ብር አለ፤ ተቀማጭ?” ብዬ ጠየኩትና ደነገጠ:: የመለሰልኝ፣ “ከየት አምጥቼ፤ ኑሮዬ እንደነገርኩህ ከእጅ ወደ አፍ ነው” ብሎ ነበር፡፡
ከዚያ፣ “ሁለት ስኒ ቡና እጠጣለሁ ያልከኝን ትቼ በቀን አንድ ስኒ ቡና ብቻ የምትጠጣ ቢሆን በአንድ አመት (ማለት፣ 365 ቀናት ውስጥ) ስንት ብር እንደምታድን አስበህ ታውቃለህ?” ብዬ ጠየኩት፡፡ መልሱን እኔው ልንገራችሁ፤ አስቦ አያውቅም፡፡ አንድ ስኒ ቡና በአምስት ብር ሂሳብ፣ 1825 ብር መሆኑን ስነግረው፣ ሊያምነኝ አልቻለም፡፡ ሞባይሌን ሰጠሁትና በራሱ ጣት ቁጥሮቹን በቀስታ እየደነቋቆለ መልሱን አገኘ:: አይኖቹ እንደፈጠጡ፣ እስቲ ብር 1825ን ለ14 ቀን አካፍል አልኩት፡፡ አካፈለ፡፡ መልሱ ስንት ሆነ መሰላችሁ? በቀን (በቀን) 130 ብር:: ምን ለማለት ነው? አስቦበት ቢሆን ኖሮ ከቤት አትውጡ፣ “ከኮሮና ዝናም ተጠለሉ፣” ሲባል ተጣብቦም ቢሆን ለ14 ቀናት ከቤት ሊውል ይችል ነበር፡፡
ከሞላ ጎደል፣ ኑሯችን እንደዚያ ነው - ከኮሮና ከምንማራቸው ነገሮች አንዱ ይኸው ለክረምት ያለመዘጋጀታችን ነው፡፡ ለዝናሙ የሚያጋልጠንም፣ መሳሳም መተቃቀፋችን ብቻ አይደለም፡፡ ሰምና ወርቁን እየለየን እንማር!


Read 1051 times