Sunday, 06 September 2020 16:15

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)


              ሴትየዋ ሁሉም ነገር ላይ መዋሸት ይቀናታል፡፡ ከልጇ ጋር መርካቶ ወይም ሌላ ቦታ አሊያም መንገድ ላይ እያለች ስልክ ተደውሎ፡-
“የት ነሽ?” ስትባል
“ቤተ ክርስቲያን፣ ለቅሶ ቤት ወዘተ…” ማለት ልማዷ ነው፡፡
 ከስራም ስታረፍድ ወይም ስትቀር፡-
“ምን ሆንሽ ነው?” ሲሏት፤እውነቱን አትናገርም፡፡
“ታምሜ ነው፤ ሞቼ ነበር” ትላለች፡፡
ብዙ ነገሯ ያልገባው ትንሹ ልጇ አንድ ቀን፤
“እማማ” አላት
“አቤት”
“እኔም ሳድግ እንዳንቺ እሆናለሁ”
“እንዴት እንደኔ?” ግራ ተጋብታ፡፡
“ሰዎች ስልክ ደውለው የት እንዳለሁ ሲጠይቁኝ፣ያልሆነ ቦታ እየተናገርኩ አታልላቸዋለሁ--”…
እናት ደነገጠች፡፡ ልብ ባላለችው መንገድ የልጇን “ነገ” እያጨለመች መሆኗ አሳሰባት:: ልጇ እንደሷ “ዋሾ” እንዳይሆንባት በመጨነቅ፡-
“ውሸትማ ጥሩ አይደለም…እኔ’ኮ ስቀልድ ነው” አለችው፡፡
“ውሸት መጥፎ ነው?” ሲል አፋጠጣት፡፡
“በጣም! በጣም መጥፎ ነው፣ ከመዋሸት መሞት ይሻላል” አለችው፡፡
ማሙሽም ደንግጦ ምን ብሎ እንደጠየቃት ታውቃለህ? መጨረሻ ላይ እነግርሃለሁ፡፡
*   *   *
ወዳጄ፡- መጥፎም ሆነ መልካም፣ ማህበራዊ፣ ቤተሰባዊም ሆነ ግለሰባዊ የአስተሳሰብ ባህል በሂደት እንጂ በፕሮፓጋንዳ ወይም በጦርነት ለመቀየር መሞከር ያስቸግራል፡፡ በፕሮፓጋንዳ ወይም በሃይል የቀየርነው ከመሰለን ፕሮፓጋንዳው፣ በፀረ-ፕሮፓጋንዳ ሲተካ ወይም የሃይል ሚዛን ሲለወጥ የተደበቀው ገጽታ ይገለጣል፣ ይቀሰቀሳል፡፡ አብዛኛው የአፍሪካና የደቡብ አሜሪካ ማህበረሰቦች ወደ ስልጣኔ ባደረጉት ግስጋሴ ላይ እንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡
በኛም አገር በጣሊያን ወረራ ወቅትና በስልሳ ስድስቱ አብዮት ማግስት፣ ለዝበው የነበሩ ወጐችና ልማዶች ከተኙበት ተነስተው ዳግም ነፍስ ሲዘሩ ተስተውሏል፡፡ ኢሬቻ አንደኛው ነው፡፡ በአንፃራዊነት ከፍተኛ ማህበረ-ሰብዓዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ወግና ልማዶች፣ ዘመናዊነት የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ስርዓትና አዲስ ስነልቡና፣ ምንም ግለሰባዊ ኑሮንና እሽቅድምድምን የሚያበረታታ ቢሆንም፣ ወደ ዓለም አቀፉ የግንኙነት ስርዓትና የስልጣኔ ባህል አብሯቸው ሊዘልቅ ችሏል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሽግግር ጃፓንን በመሳሰሉ የሩቅ ምስራቅ አገሮች በጉልህ ይታያል፡፡ በኛም አገር እንደ ዕቁብና ዕድር የመሳሰሉት ማህበራትና አንዱ በሌላው ላይ የማያተርፍባቸው የመረዳጃ ተቋማት በምሳሌነት ይጠቀሳሉ:: ይሁን እንጂ እነሱም ቢሆኑ በከፍተኛ ፍጥነት እየተንሰራፋ ያለው ዘመናዊነት ይዞት በሚመጣው ምቹ ኑሮና የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ ኑሮን በማቅለልና ጊዜን በአግባቡ እንድንጠቀምበት በማድረግ በባንክና ቁጠባ፣ የማይክሮ ፋይናንስ እንዲሁም የማህበራዊ ዋስትናን በሚያስፈጽሙ መሰል ተቋማት መተካታቸው አይቀርም፡፡
ወዳጄ፡- ሰኮንድ በማትሞላ ጊዜ ውስጥ ትልቅ የለውጥ እመርታ ሊፈጠር እንደሚችል ሁሉ በዘመናት ጉዞ እየደበዘዙ፣ እየከሰሙ በአዳዲስ የሚተኩ ነገሮችም ብዙ ናቸው፡፡ ከቁሳዊ ለውጥ ይልቅ የማህበራዊ ስነልቦና ለውጥ አዝጋሚ ነው፡፡ ባህላዊ እምነቶችና ልማዶች በተወራራሽነት ወደ ኑሮ ዘይቤነት ለመቀየር ዘመናትን ፈጅተዋል፡፡ የማህበራዊ ማንነት መግለጫ የሆኑት እነዚህ ባህላዊ ዕሴቶች፣ አንደኛው በሌላኛው ውስጥ እየሟሙና እየተዋለዱ ስለሚቀጥሉ፣ በሽክርክሩ ውስጥ ማንኛው ከየትኛው እንደሚቀድም እንኳን ለመለየት ያስቸግራል፡፡ የማያደራድረው ዕውነት ግን ሁሉም ከመኖር አለመቅደማቸው ነው፡፡ Existence first!
ወዳጄ፡- የአስተሳሰብ ለውጥ የባህል፣ የባህልም ለውጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው:: ማህበረሰባዊና ግለሰባዊ ባህሪ ከሁለቱ ይመነጫል፡፡ በተለያየ አካባቢና ባህል ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች መካከል የሚታየው የልማድ ተመሳሳይነትና ልዩነት በግለሰቦችም መሃል አለ፡፡ ለመመሳሰላቸውም ሆነ ለልዩነታቸው ምክንያት ደግሞ ኑሯቸው የፈጠረው አስተሳሰብ ወይም ልምድን መሰረት ያደረገ የዕውቀት መራራቅ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ለምሳሌ፡- ተወልደን ካደግንበት ቀዬ ርቀን ለረዥም ጊዜ ሌላ ቦታ ቆይተን ስንመለስ፣ ትተነው የሄድነው ወግና ልማድ ሳይለወጥ፣ እንደነበረ አይጠብቀንም፡፡ አንድ ቦታ በቋሚነት ስንኖር ግን በተለይ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የማንጠቀም ከሆነ፣ በራሳችንም ሆነ ባካባቢያችን ላይ የሚከናወነውን ለውጥ ፈጥነን ለመረዳት ያዳግተናል፡፡ ወንዙ መሙላቱን ወይም መጉደሉን እንጂ ወራጁ ውሃ በፍጥነት እየተቀየረ እንደሚያልፍ ልብ አንልም፡፡
ለምሳሌ እኔ ተወልጄ ያደኩባት ከተማ አሁን የለችም፡፡ ያለው ስሟ ብቻ ነው ብል ያስኬዳል፡፡ በኔ ዘመን የነበረው ወግና ልማድ ተረት ሆኗል፡፡ እኔም ሌላ ቦታና ሌላ ባህል በመውረሴ፣ ሌላ ሰው ሆኛለሁ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ እዛው ብቆይ ግን አብረን እየሳቅን፣ አብረን እያዘንን ስለምንኖር፣ አንዳችን ላንዳችን ባይተዋር አንሆንም፡፡ ትተናቸው የመጣናቸውን አካባቢዎች፣ ሰዎችና ነገሮች ከረዥም ጊዜ በኋላ መልሰን ስናገኛቸው እንግዳ የሚሆኑብን ለዚህ ነው፡፡ ሰዎች ረዥም ጊዜ ከኖሩበት፣ ሃብትና ንብረት ካፈሩበት፣ ወልደው ከዳሩበት፣ ዕድር ከተሰበሰቡበት፣ ዕቁብ ከጣሉበት፣ ማህበር ከደገሱበት፣ ታቦት ካነገሱበት፣ ጁምዐ ከሰገዱበት፣ ክፉና ደጉን እንዳመጣጡ ከጐረቤቶቻቸው ጋር እየተቀበሉ ሲያስተናግዱ ከነበሩበት ቀዬ ያለ ውድ በግድ ሲፈናቀሉ “ሞት” የሚሆንባቸው ለዚህ ነው፡፡ እስር ቤት እንኳ ረዥም ዓመታት አሳልፈው ሲለቀቁ “አንወጣም እንቢ”ብለው ያስቸገሩ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ወዳጄ፡- መኖር መልመድ ነው!!
የመልመድን ነገር ካነሳን አይቀር አንድ የድሮ ቀልድ ትዝ አለችኝ፡፡
ሁለት የድሮ ባለስልጣናት (አለቃና አማካሪያቸው) በአገሪቱ ስለተፈጠረው የኑሮ ውድነት ይወያያሉ፡፡
“ጤፍ ተወደደ ምን ይበጃል?”
“እንግዲህ የተገኘውን መብላት ነው፡፡ ምን ምርጫ አለ”
“የተገኘውን ማለት?”
“በቆሎውንም፤ ዘንጋዳውንም ከተገኘ ሩዙንም እየጋገሩ መሰልቀጥ ነዋ!”
“ጤፍ የለመደ ሆድ እንዴት…?” በማለት አማካሪ ለማሳመን ሲሞክሩ፣ ዋናው ተቆጥተው ምን አሉ መሰለህ?! “የማይለመድ ነገር ምን አለ? ግድ ሲሆን ህመም እንኳ ይለመዳል፡፡ እኛ ውስኪና ጮማ ለምደናል አይደል?” አሉ ይባላል፡፡
በነገራችን ላይ “ሆዴ ልመድ ሆዴ ልመድ/ቂጣ በጐመን ጉመድ” የምትለውን የበገና እንጉርጉሮ ታውቃታለህ?... ያኔ የተናቀችው ቂጣ በጐመን አሁን የኢንቨስተሮች “ፌቨራይት” ሆናለች፡፡
***
ወደ መጀመሪያው ጨዋታችን ስንመለስ እናት ልጇን፡-
“ከመዋሸት መሞት ይሻላል” ስትለው ማሙሽ ደንግጦ “ስንት ጊዜ ልትሞቺብኝ ነው?” በማለት ነበር የጠየቃት”…
እውነት ተናግሮ የመሸበት የሚያሳድር ልምድ እንደሌለን አላወቀም፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!
ሠላም!


Read 286 times