Saturday, 12 September 2020 12:29

ቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶች መንደፏን አስታወቀች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ አካባቢዎች በእምነት ተቋማቶቿና በምዕመኖቿ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን መንደፏን የጠቆመች ሲሆን በቅርቡ በኦሮሚያ ጥቃት ለተፈፀመባቸው ተጐጂዎች የ3 ቢሊዮን ብር እርዳታ እያሰባሰበች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ የተቋቋመ የእርዳታና መልሶ ማቋቋም አቢይ ኮሚቴ የ3 ቢሊዮን ብር እርዳታ አሰባሰብ ሂደትን አስመልክቶ ረቡዕ እለት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ በቀጣይ ኮሚቴው የእርዳታና ማቋቋሚያ ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር “ከእንግዲህ በቤተ ክርስቲያኒቱና ምዕመኖቿ ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችንም እንደሚነድፍ ተመልክቷል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለሚቃጡ ጥቃቶች የህግ ሂደቶችን ተከትሎ የመከላከል እንዲሁም አጥፊዎችን በቀጥታ ወደ ህግ የማቅረብ ስራ ይከናወናል ተብሏል፡፡
በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በቤተክርስቲያኒቱ ምዕመኖች ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች 67 ምዕመናን መገደላቸውንና ከ10ሺህ በላይም መፈናቀላቸው የተገለፀ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በመጀመሪያ ዙር የእርዳታ ማድረስ ለ2171 ተጐጂዎች በንግድ ባንክ የሂሳብ መዝገብ ተከፍቶላቸው ለበአሉ 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲደርሳቸው መደረጉ ተነግሯል፡፡
በቀጣይም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ካሉ በጐ አድራጊዎች፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሠራተኞችና ተቋማት እንዲሁም በአጭር የስልክ መልዕክት ከምዕመኖችና በጐ አላማውን ከሚደግፉ ዜጐች የ3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ በማሰባሰብ ተጐጂዎችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራ እንደሚሠራ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
መኖሪያ ቤት ለፈረሰባቸውም መኖሪያ ቤት ገንብተው የሚያስረክቡ በጐ አድራጊዎችን በማስተባበር ጭምር በተለያየ መንገድ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት መልሰው እንደሚገነቡም ተገልጿል፡፡  

Read 1114 times