Saturday, 12 September 2020 12:31

የኮሮና ቫይረስ ከመጋቢት እስከ ነሐሴ በስድስት ወር 61ሺ 700 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

  - በመዲናዋ በነሐሴ ወር በ3 ሳምንት ብቻ በኮሮና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ5 ወራት ከሞተው በእጥፍ ይበልጣል
  - በቀጣዮቹ ሳምንታት በርካታ ጽኑ ህሙማን ወደ ህክምና ማዕከል ሊገቡ እንደሚችሉ ተሰግቷል
  - በሽታውን ለመቆጣጠር ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነሐሴ 30 አብቅቷል
                
            በአገራችን በኮሮና ቫይረስ መያዙ የተረጋገጠው የመጀመሪያው ሰው የተመዘገበው ከዛሬ 181 ቀናት በፊት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር፡፡ ከዛሬ 6 ወራት በፊት የቫይረሱ ስርጭት እጅግ አነስተኛ በሆነ ቁጥር ሲጓዝ ቆይቶ ከሰኔ ወር 2012 ዓ.ም በኋላ ቁጥሩ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ሄዷል፡፡
አለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ሰሞኑን ይፋ ያደረገው አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሽታው በአገሪቱ መገኘቱ ከተረጋገጠ ወዲህ ባለፉት ሳምንታት የስርጭቱ መጠን እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ካለፈው ሐምሌ ወር ወዲህ የታየው የቫይረሱ የስርጭት መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የጠቆመው  የድርጅቱ መረጃ፤ ይህም የሚያሳየው ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል ያደርግ የነበረውን ጥንቃቄ እየቀነሰ መምጣቱን ነው ብሏል፡፡  የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ የሚያወጡት ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ61ሺ 700 በላይ የደረሰ ሲሆን ከ960 በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ወደ 23ሺ የሚጠጉት ደግሞ ከቫይረሱ ማገገማቸው ታውቋል፡፡
አገሪቱ ካለፈው ሐምሌ መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ የምርመራ መጠኑን እያሳደገች መሄዷንና በአሁኑ ወቅት በቀን በአማካይ ከ20ሺ ሰዎች በላይ እየመረመረች ሲሆን  ጠቅላላ የተመረመሩ ሰዎች ቁጥርም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፤ በከተማዋ የኮሮና ቫይረስ የስርጭት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፡፡ በተለይም በተጠናቀቀው የነሐሴ ወር የቫይረሱ ስርጭት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ በነሐሴ ወር በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሐምሌው የስርጭት መጠን በእጥፍ ይበልጣል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘው የሞት መጠንም በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ በሐምሌ ወር በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 191 የነበረ ሲሆን በነሐሴ ወር ውስጥ በኮቪድ 19 ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በሶስት እጥፍ አድጐ 446 ሰዎች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የነሐሴ ወሩ የሞት መጠን በአምስት ወራት ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ካጡት ሰዎች በእጥፍ እንደሚበልጥ የጤና ቢሮው መግለጫ አመላክቷል፡፡
በአገሪቱ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ሰዎች የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደሆነ ያመላከተው የጤና ቢሮው መግለጫ፤ በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙትም በአዲስ ከተማና ልደታ ክፍለ ከተሞች ነው ተብሏል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሪፖርታቸው ላይ እንደገለፁት፤ በአገራችን በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት ሰዎች ውስጥ ከስልሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ በከተማዋ በበሽታው የተያዙትን ህሙማን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ተቋማት በስፋት ያሉ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት አብዛኛዎቹ ሆስፒታሎች በህሙማን በመጨናነቃቸው ሳቢያ በቫይረሱ ተይዘው በጽኑ ያልታመሙ ሰዎች በራሳቸው ቤት ራሳቸውን አግልለው ለመቆየት የሚችሉበት አሠራር ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የግል የጤና ተቋማትም ለኮሮና ቫይረስ ህመም ህክምና መስጠት እንዲችሉ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዚህ ወቅት ወደ ኮሮና ህክምና ማዕከላት የሚገቡ ህሙማን ቁጥሩ እያሻቀበ ሲሆን በተለይም ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ የጽኑ ህሙማን ክፍሎች በኮሮና ታማሚዎች እየተጨናነቀ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ በቫይረሱ በጽኑ የሚታመሙ ሰዎችን ተቀብለው ህክምና ከሚሰጡት የጤና ማዕከላት በተጨማሪ ቀለል ያለ ህመምና ምልክቶች ያለባቸው ኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸውን ሰዎች ተቀብለው ህክምና የሚሰጡ ማዕከላት በስፋት እየተከፈቱ እንደሆነም የጤና ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ቀጣዮቹ ሳምንታት ህብረተሰቡ በስፋት ተሰባስቦ በዓልን በጋራ የሚያከብርባቸው ጊዜያት ከመሆኑ አንፃር በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ አይቀሬ መሆኑን ያመለከቱት የህብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶ/ር ተስፋዬ አብርሃም፤ ከእነዚህ ሳምንታት በጽኑ ህመም ተይዘው የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ አይቀሬ ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል።
በአገራችን የበሽታው የስርጭት መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣው ከፋሲካ በዓል ግርግርና ከአርቲስት ሃጫሉ ሞት ጋር በተያያዘ ያለጥንቃቄ በተደረገው እንቅስቃሴ ነው ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ፤ እንዲህ አይነት መዘናጋቶችና ያለ ጥንቃቄ የሚወስዱ እንቅስቃሴዎች ለቫይረሱ ስርጭት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የበሽታውን መስፋፋትና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ ለኮሮና ታማሚዎች ህክምና መስጠት የሚያስችል የህክምና ተቋማት በየወረዳው እንዲኖር ለማድረግም እየተሰራ መሆኑን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ገልጿል፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን፣ የምርመራ አቅምን በማሳደግ በየወሩ ከ400ሺ በላይ ሰዎችን ለመመርመር ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ይህም በቫይረሱ መያዛቸው የሚረጋገጥ ሰዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊያንረው እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መረጃ አመላክቷል፡፡
በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጤና ባለሙያዎችም ከባድ ስጋት ሆኖ የከረመ ሲሆን በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በቫይረሱ የሚያዙ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ከየክልሎች በተለይም ከአማራ፣ ከሱማሌ፣ ከደቡብ ክልል፣ ከጋምቤላ ክልልና ከድሬደዋ መስተዳድር ያገኛቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙና በተለያዩ የጤና ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፡፡ በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ የጤና ባለሙያዎችም እንዳሉ ይኸው መረጃ አመላክቷል፡፡
ቫይረሱ በአገራችን መገኘቱን ተከትሎ፤ መንግስት ለአምስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ት/ቤቶች እንዲዘጉ፣ ሰዎች በጋራ የሚሰበሰቡባቸው ፕሮግራሞች እንዲሰረዙና ከአራት በላይ ሰዎች በአንድ ቦታ ላይ ተሰባስበው መቀመጥ እንዳይችሉ የሚያግድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱ የሚታወቅ ሲሆን ይኸው አዋጅም ነሐሴ 30/2012 ዓ.ም አብቅቷል፡፡ የህብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶ/ር ተስፋዬ አብርሃም ይህንን ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ እጅግ አስፈላጊና ውጤቱም ጥሩ ቢሆንም በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ይህንን ማድረጉ ፈታኝና እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን አመልክተው፤ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የመከላከል እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ መንግስት አሁን ት/ቤቶች እንዲከፋፍቱ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑም አግባብ ያልሆነ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
በመጪዎቹ ሳምንታት ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ሃይማኖታዊ በዓላት መኖራቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ተስፋዬ በተለይም የመስቀልና የእሬቻ በዓላት ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡     
ቫይረሱ በአገራችን መገኘቱ ከተረጋገጠበት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የስርጭቱ መጠን እጅግ በከፍተኛ መጠን እያሻቀበ መሄዱን መረጃዎቹ ያመለክታሉ፡፡ ከህይወት የሚበልጥ የለምና በዓሉንም ሆነ ሌላውን በጥንቃቄ ብቻ እናድርግ፡፡ ማስክ ሳናደርግ ከቤታችን ከመውጣት እንቆጠብ፡፡  


Read 8213 times