Print this page
Sunday, 13 September 2020 00:00

ግዴታዊ ፈቀቅታ! (ዙግዝዋንግ)

Written by  አበባው ከበደ ታፈሰ (የአለም ቼስ ፌዴሬሽን ኢንስትራክተር)
Rate this item
(3 votes)

     "--ኢትዮጵያን ወድቃ ለማየት፣ የመበተን ዜናዋን ለመስማት የሚናፍቁ፤ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ዕኩያን እዚህም እዛም ጎዶሎ አጀንዳቸውን ይዘው፤ እንቅልፍ አጥተው ያለመታከት ሴራ ሲሸርቡ ይታያል፡፡ ምኞታቸውም እውን እስኪሆን ድረስ የጥፋት እጃቸውን ወዲህም ወዲያም ይዘረጋሉ፤ የጭካኔ በትራቸውንም ያለ ምህረት በንጹሃን ላይ ይሰነዝራሉ፡፡ እኛም ተመቻችተን በትሩን ተጋድመን እየተቀበልን ነው፡፡--"
                    

               ፈላስፋው ፍሬድሪክ ኒቼ በ‘አንታይ ክሪስት’ መፅሐፉ  መግቢያ ላይ “ይህ መፅሐፍ ለጥቂቶች፣ የዛራቱስቱራን ፍልስፍና ለሚረዱት ብቻ፣ ከነዚህም ውስጥ አንዱ፤ ምናልባትም በህይወት ለሌለ የተዘጋጀ ነው…” ሲል አንባቢው ላይ ዕቀባ ጥሏል፡፡ እኔም ጽሁፌን ያዘጋጀሁት የማየት ውክልና የተሰጠውን የንባብ ህግ ሳያዛቡ፣ ገንቢ ፅሁፎችን ብቻ ለመገብየት ለተሰናዱ፤ ዛሬ ጆሮ ላበቀሉት ሳይሆን ለትላንት  ጆሮዎች፣ በማስተዋል መርጠው ለሚያደምጡ፣ ዘግነው በግርድፉ ለሚሰለቅጡት  ሳይሆን፤ ለይተው አላምጠው ለሚውጡቱ ነው፡፡
የቼስን ለቋንቋ ዕድገት አበርክቶ  (another  word a day) ከሚል መጽሐፍ ላይ “words having origin in chess“ በሚል ርዕስ ከሰፈሩት ትንታኔዎች፤ የተመረጡ የቼስ ቃላቶች፤ ተነባቢ በሆኑ መፅሄቶችና ጋዜጦች፣ በዓለም አንኳር ክስተቶች ውስጥ ለተፃፉ ጽሑፎች ማድመቂያ ሆነው ከተሰደሩት ውስጥ (ዙግዝዋንግ)ን ለዋናው ሃሳቤ ርዕስ አድርጌ የመረጥኩት በምክንያት ነው፡፡
በአንድ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ስንገኝ፣ እጅ ከመስጠት ባልተሻለ መልኩ ስንፍጨረጨርና ባላንጣችን ወደ ፈለገው አቅጣጫ አስገድዶ ሲዘውረን፤ ያ ክስተት ነው እንግዲህ - ዙግዝዋንግ፡፡ አንዳንዴ ከገሀዱ ዓለም ወጥተን ራሳችንን በቼስ መጫወቻ ፒሶች መስለን ይቺን ውብ ፕላኔታችንን እንደ ቼስ ቦርድ ስንቆጥር፤ ያን ጊዜ የደስታ ማማ ላይ እንወጣለን፡፡ በዚህኛው ዓለም ውስጥ ሁሉም እንቆቅልሾች ይፈታሉ፤ በርግጥም አካፋን አካፋ ማለት በቼስ ዓለም  ቀላል ነው፤ ለምን ቢባል ውሸትና ማስመሰል በቼስ ውስጥ ዕድሜያቸው አጭር ነውና:: ይህ የቼስ ቃል ዙግዙዋንግ! ዛሬን ፍንትው ብሎ እንዳይ የረዳኝ መሰለኝ፤ መቼም ቢሆን የሚታየውን ለማየት አልጥርም፤ የሚነገረውንም ለማድመጥ ዳተኛ ነኝ፤ ይልቁንም ድብቁን እንጂ … ራሴን ሳውቀው እንዲህ ነኝ፡፡ ቼስ ከሰው ልጆች የህይወት እንቅስቃሴ እንደተቀዳ በብዙው ይታመናል:: ይሁንና የአለማችን ታላቁ ግራንድ ማስተር ጋሪ ካስፓሮቭ፤ ህይወት ከቼስ እንደተኮረጀ (how life imitates chess) በተሰኘው ጽሁፉ ለመሞገት ሞክሯል፡፡ ነገር ግን ማን ቀዳማይ፤ ተከታይስ ማን ሆነና፤ በርግጥ ፊተኛው ከኋለኛው እንደሚማር ባምንም፡፡
የመጀመሪያውን የቼስ ኮምፒዩተር ‘ፕሮግራም’ ያዘጋጀው ሻሎን፣ ‘ሻሎን ናምበር’ በተባለው ጽሑፍ ላይ እንዲህ ሲል አትቷል፡- “… በአንድ የቼስ ጨዋታ ውስጥ 10 ኃይል 120  ያህል አማራጭ እንቅስቃሴዎች መካሄድ ይችላሉ፡፡ የሚደንቀው በ’ዩኒቨርሳችን’ ያሉት አተሞች ቁጥር 10 ኃይል 75 ብቻ ነው”  (በሌሎች ጽሑፍች ላይ 10 ኃይል 80 አተሞች በዩኒቨርሳችን ላይ እንደሚገኙ ተጽፏል) በዚህ እጅግ ረቂቅ የአዕምሮ ፍትጊያ ውስጥ ውስብስብ ሚስጥሮች በብሩህ አዕምሮዎች ያለ ስህተት ይተነተናሉ:: በዚህ ፅናትን በሚጠይቅ ደም-ዐልባ ውጊያ ውስጥ ፍትህ ይበየናል፣ የጠንክሮ መስራት ውጤት ይበረታታል፣ በቼስ ዓለም አንድነት የድል ብስራትን ያበስራል፣ መናናቅ በዚህ ስፍራ የለውም፤ በዚህኛው ዓለም ሁሉም ለአንዱ፤ አንዱም ለሁሉም ያስፈልጋልና:: አገራችን ዛሬ በብዙው ጎድላለች፣ እንደ እሬትም እየመረረች ነው፣በኢትዮጵያችን ውስጥ መኖር፤ የምርጫ ማጣት አየሆነ ያለ ይመስለኛል፤ ግልብ ካልሆንኩ፡፡
እንደ አለመታደል ሆኖ፤ በተተበተብንበት ችግር ጥልቀትና ስፋት ልክ መፍትሄ ማምጣት የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ አለመከሰቱ፤ ዝሆን የሚያህለውን ችግራችንን ዘንግተን ጭራውን አጀንዳ አድርገን እንድንናጥ ሆነናል፡፡ ማሪዮ ፑዞ “God father” በተሰኘው መጽሐፉ … በታላቁ ዶን ኮርሎዎኒ ላይ በተቃጣበት የመግደል ሙከራ ሳቢያ የመሪነት ስፍራውን የተረከበው ትዕግስት-ዐልባው ሶኒ ኮርሎዎኒ፤ አፍታም ሳይቆይ በቤተሰቡ ጠላቶች በተቀነባበረ ሴራ አሰቃቂ ሞትን ሞቷል፡፡ ቤተሰቡን ወደ ትላንት ክብሩና ታላቅነቱ ለመለሰው ብርቱው ሚካሄል ኮርሎዎኒ፤ ከቀድሞው፣ የዶኑ አማካሪ፣ ሄገን እንዲህ የሚል ትችት ቀረበበት፤ “…አንተ በብዙው አባትህን መስለሃል፤ ነገር ግን እንድ ነገር ይቀርሃል፤ ይኸውም፡- ሰዎችን እንዴት አይሆንም! እንደሚባል ዛሬም አላወቅክም…” የሚል፡፡ ማይክም ፈጥኖ ወደ አባቱ አመራ፤ እንዲህም ሲል አባቱን በትህትና ጠየቀው “…ለመሆኑ እንዴት ነው፣ ሰዎችን ‘ኖ’ የምትለው?”  ዶን ኮርሎዎኒም “…አየህ! ሰዎችን፣ በተለይም የምትወዳቸውን ሰዎች ‘ኖ’ አትላቸውም፤ እራሳቸው ‘ኖ’ እንዲሉ ታደርጋቸዋለህ እንጂ! ለዚህም በብዙ መቸገር አለብህ፡፡ ቢሆንም እኔ የትላንቱ ዘመን ፍሬ ነኝ፣ አንተ ደግሞ አዲሱ ትውልድ፤ ስለዚህ የራስህን መንገድ ተከተል…” ብሏል፡፡ ወቅቱ በየትኛውም የሃላፊነት ስፍራ ላይ ያኖራችሁ መሪዎቻችን፤ አይሆንማችሁ እንደ ኮርሎዎኒ ሕዝባችሁን ሊያስደስት በሚችል ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡  
ለመሆኑ ጥሩ ምንድን ነው? መጥፎስ? ደስታስ የቱ ይሆን? ሀዘንስ ምን ይሆን? … ምንድን ነው የወል ያለን? አገራችን እንደ ‘ኒዩክለስ’ ሆና በዙሪያው እንድንከብ የሚያደርገን።  ይህኛው ዕኩይ በሚለው፤ ያኛው ሀሴትን ሲያደርግ፤ እርሱ ውጉዝ የሚለው፤ ለዚህኛው ክቡር የሚሆነው እስከ መቼ ነው?  ፈረንጆቹ  የጫማን ተለዋውጦ መደረግ ይጠቁማሉ፤ አንደበት ግብርን አልገልጽም ሲል (the shoes is on the wrong way!)፡፡ እስቲ ከደንብ ውጪ አለዋውጠን ያደረግነውን ጫማ፤ እንደ ወጉ የግራውን በግራ፣ የቀኙን በቀኝ እናጥለቀው፤ እውነት እዛም እዚህም እውነት እንዲሆን:: መብረር ስንችል ስለ ምን መንገድ ለመንገድ ስንንፏቀቅ እንታያለን፡፡
ኢትዮጵያን ወድቃ ለማየት፣ የመበተን ዜናዋን ለመስማት የሚናፍቁ፤ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ዕኩያን እዚህም እዛም ጎዶሎ አጀንዳቸውን ይዘው፤ እንቅልፍ አጥተው ያለመታከት ሴራ ሲሸርቡ ይታያል፡፡ ምኞታቸውም እውን እስኪሆን ድረስ የጥፋት እጃቸውን ወዲህም ወዲያም ይዘረጋሉ፤ የጭካኔ በትራቸውንም ያለ ምህረት በንጹሃን ላይ ይሰነዝራሉ፡፡ እኛም ተመቻችተን በትሩን ተጋድመን እየተቀበልን ነው፡፡
ዊሊያም ሼክስፒር፤ “እንዲህ በሏቸው ለእነዛ አዲስ  ወላጆች፡- የልጃቸውን ስም ለመሰየም አያሌ መጽሐፍትን ላገላበጡ፣ ከሰበሰቧቸውም በርካታ ስሞች የተሻለውን ለመምረጥ ከወዳጆቻቸው ጋር በብርቱ ለመከሩ፤  እንዲህ በሏቸው፡- ጽጌረዳን በየትኛውም ስም ጥሯት፣ ጽጌሬዳ ያሰኛትን ያንን ጥዑም-መዐዛዋን ግን ልትነጥቋት አትችሉም”  ብሏል:: እኔም የኢትዮጵያ  ‘ፎቢያ’ ያለባችሁ እኩያን  እላችኋለሁ፤  ኢትዮጵያን በየትኛውም ስም ጥሯት፤ ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን አገር ናት!  ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከከች አገር ናት!  አሳንሰህም እያት፤ የሰው ዘር መገኛ ታላቅ አገርነቷን ልትነፍጋት አትችልም!!!
 ቸር እንሰንብት፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንን ሕዝቦቿን ይባርክ!


Read 2384 times