Print this page
Monday, 14 September 2020 00:00

“የኢትዮጵያ ልክ - ከግቢ እስከ አገር” እና የቴሌ “333” ጥሪ

Written by  አበበ ገ/ህይወት
Rate this item
(4 votes)

    “ሃሳብህና ተግባራዊነቱ ወሳኝና ልዩነት የሚፈጥር ነው ብለህ ካመነክ፣ ሙሉ ኃላፊነቱን በፍጹም ለሌላ ሰው አትስጥ፡፡ ራስህ አድርገው፡፡”
                
             ባለፈው ሰሞን በጠቅላይ ሚኒስትራችን አማካኝነት “የኢትዮጵያ ልክ - ከግቢ እስከ ሃገር” በሚል ርእስ የቀረበውን ዶክሜንተሪ በተመለከተ ከአንድ ወዳጄ ጋር ተጨዋውተን ነበር፡፡ እኛ የተገናኘነው ፕሮግራሙ አርብ እለት ማታ ቀርቦ ቅዳሜ ከሰአት በኋላ ነበር፡፡ እኔና ወዳጄ ከተወያይተንባቸው ነጥቦች አንዱና በብዙ ሰዎች ሊነሳ የሚችል ነጥብ ብለን ያሰብነው፣ ፕሮግራሙ ለምን በፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ወይም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች አልቀረበም የሚል ነበር::  ውይይታችን አጭር ነበር፡፡ ጉዳዩ መደበኛ የህዝብ ግንኙነት ስራ ስላልሆነ ገለፃው በእሳቸው መደረግ እንደሚገባው ደመደምን::
በሌላ በኩል፤ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ጉዳዩ የመነጋገሪያ ርእስ ሆኖ መሰንበቱን ደረጀ በላይነህ በተባሉ ጸሃፊ ቀርቦ ስመለከት ትኩረቴን ሳበው:: ፀሃፊው ጉዳዩን ምክንያታዊ በሆነ አቀራረብ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ በእኔ እምነት በአቶ ደረጀ ከቀረቡት ምክንያቶች በተጨማሪ ፕሮጀክቶቹ የታላቅ አገራዊ ሃሳብ/ አስተሳሰብ ንዑስ ክፍሎች በመሆናቸው በውስጣቸው ብዙ ነገሮችን ያካትታሉ፡፡ ስለሆነም በትልቁ አገራዊ ሃሳብ (Big picture) ውስጥ- ተነሳሽነት (Initiative)፣ ጥልቅ ስሜት (Passion) ቁርጠኝነት (Commitment) - የመሳሰሉ መሰረታዊ ነጥቦችንና የሃሳብ መገለጫ የሆነውን ድርጊት (ተግባር) የያዙ መሆናቸው ነው፡፡
ሌላው ዋና ነጥብ ግን በአቀራረብ ረገድ ሊኖር የሚገባው የታሪክ ነጋሪነት (Story telling) ክህሎት ነው፡፡ ይህ ክህሎት ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች በተለይ ከጥልቅ ስሜት ጋር ሲዋሀድ ግልፅ የአቀራረብ ልዩነት ይፈጥራል:: በሌላ በኩል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ በማድረግ የመጀመሪያ አይደሉም፡፡ ማንዴላ (ማዲባ) ስልጣን እንደያዙ ታላቅ ፈተና የሆነባቸው በሃሳብና በቀለም የተከፋፈለችውን ደቡብ አፍሪካ አንድ አድርጎ መምራት ነበር፡፡ በሃገሪቱ የሚታየውን የመጠላላትና የዘረኝነት ስሜት ለማርገብ ስፖርትን እንደ አንድ መሣሪያ ለመጠቀም ወስነው ይሰሩ ነበር፡፡
የአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫና የዓለም የራግቢ ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ እንዲዘጋጁ ለማድረግ ሌት ተቀን ደክመዋል፡፡ ዓላማቸው ተሳክቶ የአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫንና የዓለም ራግቢ ዋንጫን ቡድኖቹ ማሸነፍ የቻሉት፣ እሳቸው ውድድሮቹ በሀገሪቱ እንዲዘጋጁ ከማድረግ አንስቶ በቡድኖቹ የልምምድ ቦታዎች፣ የውድድር ስታዲየሞች በመገኘትና በማበረታታት፣ የቡድን አምበሎችንና ተጠሪዎችን የአመራር ክህሎት በማስተማር፣ በተጫዋቾቹ ላይ የአሸናፊነት መንፈስ እንዲፈጠር በማድረግና የህዝቡን ስሜት ማነሳሳት በመቻላቸው ነበር፡፡
ታላቅ ዓላማ የያዘውን ስፖርትን ለሃገር አንድነት የመጠቀምን የፕሮጀክት እቅድ ያልተረዱ የራሳቸው የስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የራግቢ ቡድኑ የነጮች የበላይነትን የሚያሳይ የጭቆና ተምሳሌት ነው በማለት ሊያፈርሱት ጫፍ ደርሰው ነበር፡፡ ማዲባ ጉዳዩን በቅርብ ይከታተሉ ስለነበር ሴራውን አከሸፉት፡፡
ፖለቲከኞች "ማንዴላ ዋና ሥራቸው ስፖርት ብቻ ሆነ፣ ሌላውን ሥራቸውን እርግፍ አድርገው ትተውታል" በማለት ሲወቅሷቸው፤ የስፖርት ተንታኞችና ኤክስፐርቶች ደግሞ ቡድኖቹ ውጤት ሊያመጡ የማይችሉበትን ምክንያቶች በመቀባበል ሲደረድሩና ሲተቹ ከረሙ፡፡ ውጤቱ ከእነሱ ግምት ውጪ ሲሆን ደግሞ ሚስጢሩን ጠይቆ ከመረዳት ይልቅ ሌላ ሌላ ነገር ሲያወሩ ከረሙ፡፡
ማዲባ ይህንን ተግባር የፈጸሙት የነጭ የበላይነትን እንደማይቀበሉ፣ ለጥቁር የበላይነትም እንዳልታገሉ፣ በአንጻሩ ግን ለመላው ደቡብ አፍሪካውያን ነጻነትና ዲሞክራሲን ለማምጣት እንደሚሰሩ፣ ለዚህም ዓላማ በፅናት እንደሚቆሙ፤ አስፈላጊ ከሆነም እንደሚሰዉለት ለራሳቸው የገቡትን ቃል ከዳር ለማድረስ ነበር፡፡
“The Invincible”  (“የማይረታው”)  የሚለው የማዲባ ፊልም ይህንን ታሪክ በግልፅ ያሳያል፡፡
ሌላው ምሣሌ ደግሞ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ታላቅ ፈርጥ ስቲቭ ጆብ ነው፡፡ የአፕል ኩባንያ አዲስ የፈጠራ ሥራዎችንና ምርቶችን ሲያስተዋውቅ፣ ከቴክኖሎጂው የፈጠራ ሃሳብ እስከ ተግባራዊነቱ ድረስ ባለው ቀጥተኛ ተሳትፎ ምክንያት ለሃሳቡና ለተግባራዊነቱ ከነበረው ጥልቅ ስሜት ጋር ተያይዞ የቴክኖሎጂውን ውጤት ተጠባቂ፣ አቀራረቡን ደግሞ ተናፋቂ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በገበያው ላይም ታላቅ ተፅእኖ ይፈጥር እንደነበረም ይታወሳል፡፡ ስቲቭ ጆብ የሽያጭ ባለሙያ ወይም የገበያ ክፍሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አልነበረም:: የኩባንያው ተባባሪ መሥራች፣ ከፍተኛ ባለድርሻና ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንጂ፡፡  የጆብ ራዕይ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ እንዴት የተሻለች ዓለምን መፍጠር እንደሚቻል ማሳየት ነበር፡፡ ይህንን እዉነታ ለማሳየት በጥልቅ ስሜት ተሞልቶ በሚያደርጋቸዉ አቀራረቦች ዓለምን አስደምሟል፡፡ “The Presentation Secrets of Steve Jobs”  የሚለው መጽሃፍ ይህንን ያሳያል፡፡
ማንዴላም ሆኑ ጆብ ታላላቅ ሥራ ማከናወን የቻሉት፡-“ሃሳብህና ተግባራዊነቱ ወሳኝና ልዩነት የሚፈጥር ነው ብለህ ካመነክ፣ ሙሉ ኃላፊነቱን በፍጹም ለሌላ ሰው አትስጥ፡፡ ራስህ አድርገው፡፡” የሚለውን የኖረ አባባል ተግባራዊ በማድረጋቸው ነው::
ሃሳቡን ለማጠቃለል፤ እኔ ዶክሜንታሪውን የተረዳሁት፤ አነስተኛ ከሚመስሉ የፕሮጀክቶች ክንውን ጀርባ፣ በጥልቅ ስሜት የታጀቡ ታላላቅ አገራዊ አሰተሳሰቦች መኖራቸውን ነው፡፡
በእግረ-መንገድ ፤- የቴሌ  “333”  ጥሪ
ቦታው አያት አደባባይ አጠገብ የሚገኘው ሂል ቦተም በመባል የሚታወቀው የመዝናኛ ማዕከል፣ ወሩ ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ዕለቱ ደግሞ ዓርብ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ከቤቴ መጽሃፍ፣ ጋዜጣ ወይም መጽሄት ይዤ እወጣና አነብባለሁ፡፡ የዚያን ዕለትም የሆነው እንደዛው ነው፡፡ ከሬስቶራንቱ ጀርባ ከሜዳ ቴኒስ መጫወቻ ትይዩ ተቀምጫለሁ፡፡ በመሳሪያ ብቻ የተቀናበረ ሙዚቃ ይሰማኛል፡፡ የቀይ አሸዋ በተነጠፈበት የቴኒስ ሜዳው ላይ ሁለት ወጣቶች ከአሰልጣኛቸው ጋር ይለማመዳሉ፡፡
አስተናጋጁ ያቀረበልኝን ሻይ ለመጠጣት እጄን ወደ ጠረጴዛው ስዘረጋ (Chicken Soup for the Soul) “የዶሮ መረቅ ለነብስያችን” የሚለውን በጃክ ካንፊልድና በማርክ ቪክቶር ሃንሰን የተፃፈውን ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጥኩትን መፅሀፍ አየሁ፡፡ መፅሀፉ በተለያዩ ሰዎች የተፃፉ አጫጭር እውነተኛ ታሪኮች ተቀናብረው የቀረቡበት ነው፡፡ ከቤት ስወጣ መጽሐፍ መደርደሪያው ላይ ፊት ፊት ስላገኘሁት ነው ይዤው የወጣሁት፡፡ መጽሐፉን ገለጥ አድርጌ "ስለ መጽሐፉ ሰዎች ምን ይላሉ?” የሚለውን በወፍ በረር እይታ ቃኘሁት፡፡ ወደ ማውጫው ዘለቅሁና በሰባት ንዑስ ክፍሎች የተከፈሉትንና በእያንዳንዱ ንዑስ ክፍል ስር የሚታየውን የታሪኩን ርዕስ፣ የጸሐፊውን ሥምና የማውጫውን ገጽ ገለጥ- ገለጥ እያደረኩ ተመለከትኩ፡፡
እያንዳንዱ እውነተኛ ታሪክ ከንዑስ ክፍሉ ጋር የሚጣጣም ታሪክ ይዟል፡፡ ስለ ፍቅር፣ ራስን ስለ ማክበር፣ ስለ ቤተሰብ፣ ስለ ግንዛቤ፣ ህልምን ስለ መኖር፣ ችግርን ስለ መጋፈጥ፣ ስለ ጥበብ የተጻፉ ታሪኮች በማውጫው ተዘርዝረዋል፡፡
ከመጽሐፉ አጠገብ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጬው የነበረው የእጅ ስልኬ አቃጨለ:: አነሳሁት፡፡ ቁጥሩን አየሁት፡፡ መልዕክቱ ቀጥሏል፡፡ የቴሌ መልዕክት ነው፡፡ ይህን ቁጥር ብዬ አይኔን ጨፍኜ ለማስታወስ ሞከርኩ:: የመጽሀፉን ማውጫ አየሁት፡፡ ገጽ 333 የሚል የለውም፡፡
‘333’ የሚል ቁጥር ከስልክ ጥሪው በፊት ለማየቴ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ የማውጫውን ገጽ ብቻ ሳይሆን ርዕሶቹን ማየት ጀመርኩ፡፡ ቢንጎ! አገኘሁት፡፡ ገጽ 189 ላይ “የ333 ቁጥር ታሪክ” በቦብ ፕሮክተር ይላል፡፡ ግጥምጥሞሹ ገረመኝ፡፡
ቦብ ፕሮክተር ታዋቂ ጸሐፊ፣ ጥልቅ አሳቢና የህይወት ክህሎት አሰልጣኝ ነው፡፡ “ምስጢሩ” (“The Secret”) በተሰኘው የሮሃንዳ ባይረን መጽሐፍና ፊልም ላይ ስለ መሳሳብ ኃይል ብዙ ሃሳቦችን ጽፏል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የ”333 ቁጥር ታሪክ” በአንድ የስልጠና ፕሮግራም ላይ በተገኘ ጊዜ ያጋጠመውን ነገር ያሰፈረበት አጭር ጽሁፍ ነው፡፡
ታሪኩ በአጭሩ እንዲህ ይነበባል፡-
በሳምንቱ መጨረሻ ከቶሮንቶ ከተማ በስተሰሜን ሴሚናር እየሰጠሁ ነበር፡፡ ዓርብ ዕለት ምሽት ነፋስ ቀላቅሎ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ እኛ ካለንበት በስተሰሜን አቅጣጫ “ባሪ” በመባል በምትጠራው ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የብዙ ሰዎችን ህይወት አጥፍቶ ነበር:: በተጨማሪም በሚሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት አውድሟል፡፡ እሑድ ዕለት ከስልጠናው ቦታ ወደ ቤቴ በመመለስ ላይ እያለሁ፤ ባሪ ከተማ ስደርስ መኪናዬን አቁሜ ወረድኩ፡፡ በአውራው መንገድ ጠርዝ ላይ ቆሜ ዙርያ ገባውን ቃኘሁ:: በጣም የተደበላለቀ ነገር ይታያል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ የፈራረሱ ቤቶችና ጎማቸው ወደ ላይ የተገለበጡ መኪናዎችን ተመለከትኩ፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ ምሽት የቴሌ ሚዲያ ኮምኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነው ሞክሽዬ ቦብ ቴምፕልተን እኔ በተጓዝኩበት መንገድ እየተጓዘ ነበር፡፡ እኔ መኪናዬን አቁሜ እንደተመለከትኩት ሁሉ እሱም እንደዛው አድርጓል፡፡ ልዩነታችን እሱ ለጉዳዩ የነበረው ትኩረት ከኔ የተለየ መሆኑ ብቻ ነበር፡፡
ቴምፕልተን ሁኔታውን ካየ በኋላ ለእነዚህ ጉዳት ለደረሰባቸው የባሪ ከተማ ነዋሪዎች በኦንታርዮና በኪዮቤክ የሚገኙ የራድዮ ጣቢያዎችን ተጠቅመን እርዳታ ማድረግ አለብን ብሎ አሰበ፡፡ በሚቀጥለው ምሽት እኔ በቶሮንቶ ከተማ ሌላ ሴሚናር እሰጥ ነበር፡፡ ቴምፕልተንና ሌላኛው የሥራ ባልደረባው መጥተው ለባሪ ከተማ ነዋሪዎች እርዳታ ለማድረግ ማሰባቸውን በቁርጠኝነት ገለጹልኝ፡፡ በሚቀጥለው አርብ በራድዮ ጣቢያው የሚሰሩትን የሥራ ሃላፊዎች ለስብሰባ ጠራቸው፡፡ ቴምፕልተን ስለ ሁኔታው ካስረዳቸው በኋላ ልሙጥ ነጭ ወረቀት አወጣና 333 ብሎ ፃፈበት፡፡ በመቀጠልም እንዴት አድርገን በሚቀጥሉት 3 የስራ ቀናት ውስጥ የሚተገበር፣ ለ3 ሰዓታት በሚደረግ ገቢ የማሰባሰብ የሬዲዮ ፕሮግራም 3 ሚሊዮን ዶላር በመሰብሰብ  ለባሪ ከተማ ነዋሪዎች መስጠት እንችላለን ብሎ ጠየቀ?
ክፍሉ በጸጥታ ተዋጠ!
ከቆይታ በኋላ አንዱ እንዲህ በማለት ሃሳቡን ገለጸ፡፡ ቴምፕልተን እየቃዠህ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ የምንችልበት መንገድ የለም አለ፡፡ ቴምፐልተንም የእኔ ጥያቄ ለማድረግ ብንፈልግ? የሚል ነው አለ፡፡ ሁሉም በእርግጥ ማድረግ እንፈልጋለን ግን እንዴት? የሚል ስሜት ታየባቸው:: ቴምፕልተን 333 በሚለው ቁጥር ስር አግድም አንድ መስመር ካሰመረ በኋላ የአግድሙን መስመር ቁልቁል እኩል ከፈለው (T) በአንደኛው ጎን “ለምን እንደማንችል” በሌላው ጎን “እንዴት እንደሚቻል” ብሎ ጻፈ፡፡ ቀጠል አደረገና “ለምን እንደማንችል” የሚለው ጹሁፍ ላይ ትልቅ የኤክስ (X) ምልክት  አደረገበት፡፡ ለምን እንደማንችል መነጋገር ጊዜ ከማባከን በስተቀር ምንም ጥቅም የለውም አለ፡፡
አሁን እንዴት ይቻላል የሚለው ስር ማንኛውንም ሃሳብ መዘርዘር ይቻላል አለ:: እንዴት እንደምንችል ጥርት ያለ ሃሳብ እስካላመጣን ድረስ ከዚህ ስብሰባ አንወጣም አለ፡፡
ሌላ ፀጥታ!
አንዱ ተሰብሳቢ ለምን በመላው ካናዳ በራድዮ የሚሰራጭ የእርዳታ ፕሮግራም አናዘጋጅም አለ፡፡ ሌላኛው ተሰብሳቢ መላውን ካናዳ የሚሸፍን የሬድዮ ጣቢያ ስለሌለን ይህንን ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም አለ፡፡ እኛ ያሉን ጣቢያዎች ሁለት ማለትም በኦንታርዮና በኪዩቢክ ብቻ ናቸው፡፡
ቴምፐልተን ይህን ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ የምንችልበት ምክንያት ሁለት ጣቢያዎች ስላሉን ነው አለ፡፡ ይልቅ ተቃውሞው ዋጋ የሚኖረው በራድዮ ጣቢያዎቹ መካከል ባለው የከፋ ፉክክር ምክንያት ነው፡፡ አሁን በሚታየው የአስተሳሰብ አድማስ ልዩነት የራድዮ ጣቢያዎችን አስተባብሮ ለአንድ አላማ ማሰራት ፍጹም የሚሞከር አይመስልም፡፡ በድንገት አንዱ ብድግ አለና በመላው ካናዳ በብሮድካስቲንግ የሙያ ዘርፍ ታዋቂ የሆኑትን ሃርቪ እና ሊሎይድን ለምን ፕሮግራሙን እንዲመሩት አናደርግም፡፡ እነሱ በቲቪ እንጂ በራድዮ ላይ ስለማይሰሩ የተፈራው የራድዮ ጣብያዎች ፉክክር አይኖርም አለ፡፡
በቀረበው የመነሻ ሃሳብ መሰረት በተከታታይና በፍጥነት ብዙ ፈጠራ የታከለባቸው ሃሳቦች ይጎርፉ ጀመር፡፡ በሚቀጥለው የስራ ቀን ሰኞ በመላው ካናዳ ከሚገኙ ጣቢያዎች ውስጥ 50 የራድዮ ጣቢያዎች በስርጭቱ ለመሳተፍ ተሰማሙ፡፡ ማክሰኞ እለት በሃርቪ እና በሊሎይድ የፕሮግራም መሪነት፣ ለ3 ሰዓት በተደረገው የገቢ ማሰባሰብያ የራድዮ የስርጭት ፕሮግራም፣ 3 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ፡፡ ዓርብ፣ ሰኞና ማክሰኞ ለ3 የስራ ቀናት በተደረገ የተቀናጀ ሥራ የታቀደውን ገንዘብ ለማሳባሰብ ተቻለ፡፡
ሃሳቡን ማንም ያቅደው፣ ዝግጅቱን ማንም ያስተባብረው፣ ፕሮግራሙን ማንም ይምራው ዋናው ቁምነገር የባሪ ከተማ ነዋሪዎች የእርዳታውን ገንዘብ ማግኘታቸው ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው አንድ ነገር ለማከናወን ትኩረታችን “ለምን ማድረግ እንደማይቻል“ ከሚሆን ይልቅ “እንዴት ማድረግ ይቻላል“ የሚለው ከሆነ ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ነው በማለት ቦብ ፕሮክተር የ “333 ታሪክ” ን ያጠናቅቃል፡፡
እንደገና ወደ ቴሌው 333 ጥሪ፡-
የቴሌው የጥሪ ቁጥር 333 እና በመጽሐፉ የተጠቀሰው የ “333 ቁጥር ታሪክ” ሁለቱም የሚያነሱት ሃሳብ ስለ እርዳታ ማሰባሰብ ነው:: በመጽሐፉ የቀረበው ታሪክ ላይ የተጠቀሱት 3 ቁጥሮች እያንዳንዳቸው ግልጽ መልዕክት ይዘዋል፡፡ 3 ሚሊዮን ዶላር፣ በ3 የስራ ቀናት ውስጥ፣ ለ3 ሰዓታት በሚተላለፍ የእርዳታ ጥሪ ስርጭት የሚሉ ሃሳቦችን ወክለዋል፡፡ ለጊዜው የቴሌ 333 ቁጥሮች ምን እንደሚወክሉ መረጃው የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ገቢ የማሰባሰብ ስራዎች በግልጽ ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ፣ ተነሳሽነትን፣ ፈጠራንና ቁርጠኝነትን የሚያንጸባርቁ ከሆኑና የተገኘውም ውጤት በግልፅ የሚቀርብ ከሆነ እንደ ተጠቀሰው ታሪክ ልዩነት መፍጠር ይቻላል፡፡


Read 1010 times