Print this page
Tuesday, 15 September 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ለምን ኢትዮጵያን እናስቀድማለን?
                               (ሙክታሮቪች)


             ኢትዮጵያን የምንል ሰዎች ከኢትዮጵያ የተለየ ጥቅም ስለምናገኝ አይደለም:: ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንደ ታሪኳ ቀና ብላ በአለም ላይ ብትደምቅ ብትበለፅግ፣ ለእኛ የተለየ ድርሻ ይኖረናል ብለን አይደለም። የሁላችንም ጥቅም ጎልቶ ስለሚታየን ብቻ ነው። "ተዉ አንድ እንሁን፣ ተዉ ቂም በቀል አንፈልፍል፣ ተዉ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ማንም ኢትዮጵያዊ ያሻው ቦታ ላይ ሠርቶ የማፍራት፣ መርጦ የመኖር ነፃነትና መብቱ ይጠበቅለት" ማለታችን፣ ማረፊያ መውደቂያ ስላጣን አይደለም፣ የአባት የእናት የዘመድ አዝማድ የትውልድ ቦታ አጥተን አይደለም:: "አንድ እንሁን አንለያይ; የምንለው መነሻ የሌለን ወፍዘራሽ ስለሆን አይደለም። የሀገርና የፖለቲካ ትርጉም ስለገባን ነው። የዜግነት ፅንሰ ሀሳብ የሚመሰረተው በሁሉ እኩልነት ላይ መሆኑ ስለገባን ነው። "የእኔ ብሄር ብቻ ያስተዳድር" በሚል የሚጀመር ፖለቲካ በየትኛውም መስፈርት ኋላቀር ፖለቲካ መሆኑ ስለገባን ነው።
ለምን ይህን አቋም መረጥን?
የሀገር ፍቅር በጥቅም ስለማይመዘን ነው::
ትሥሥራችን እያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ የዘለቀ ስለሆነ ነው::
ሀገር ከመንደር ስለሚሻል ነው::
ሠርተን፣ ለፍተን በላባችን አፍርተን፣ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንኖርባት ሰላማዊ ሀገር ለመፍጠር ነው:: ደስታም ስኬትም፣ ዝናም ክብርም፣ ሀብትም ፍቅርም፣ ትዳር ጥሪትም፣ ዕምነት ተስፋም፣ ሰርግ ቀብርም...ሁሉም በሀገር እንደሚያምር ስለገባን ነው:: መስከናችን፣ ዝም ማለታችን ለሀገር የሚበጅ ከሆነ ግዴለም ይሁን ብለን እንጂ እውነት ከኛ ጋ መሆኗን አጥተን አይደለም።
.የብሔርተኝነት መንገድ ለሰጥቶ መቀበል የማያመች፣ መነጋገር የሌለበት፣ እኛ እና እነሱ በሚል ግጭት ቀስቃሽ ቁርሾና ጥላቻ በመፈልፈል ህዝብን ከህዝብ ስለሚያጋጭ ነው የምንርቀው። ብሔርተኝነት ታሪክንና የድሮ በደልን እየቆሰቆሱ በቂም ማያያዝን እንደ ርእዮተ አለም የሚጠቀም፣ በፍርሃትና በስጋት ህዝብን እያመሰ ድጋፍ የሚሰበስብ የጥቅመኞች መንገድ ስለሆነ ከግል ጥቅም ሀገርን መርጠን ነው የራቅነው።
በብሔር እየተቧደኑ ደም መፋሰስ ያረጀ ያፈጀ፣ ኋላ ቀር፣ እንስሳዊ ባህሪ ስለሆነ ነው የራቅነው:: መጫረስ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያቀዱልንና ማዳከም ማልፈስፈስና አቅመቢስ ማድረግ የፕሮጀክታቸው ግብ ስለሆነ ነው ብሔርተኝነትን የምንጠየፈው። የብሔር ፅንፈኝነት አሸናፊ የማይኖርበት ሁላችንንም መቀመቅ ይዞን የሚወርድ የጋራ ውድመት መንገድ ስለሆነ ነው የምንርቀው።
ማንም ማንንም ለፍቶ ካቀናው ሀገር፣ ተወልዶ ካደገበት ከተማ፣ ከአባቱ ርስት በዋዛ ሲነቀል ዝም ስለማይል፣ መተላለቅ ደጃችን ላይ መሆኑን ፈርተነው ነው ከልዩነት አንድነትን የምንመርጠው። ማንም በማንም ላይ የበለጠ ጀግና ስላይደለ የእልህ ፖለቲካ ያዳክመናል ብለን ነው ጎሰኝነትን የራቅነው። ማንም በየትም ቦታ መኖር መክበርና ወልዶ መሳም አለበት ብለን ስለምናምን ነው፣ የብሔር ፖለቲካ ዘመናዊውን አለም የማይመጥን አደገኛ ስለሆነ ነው የማንከተለው።
ይህ ማለት ብዝኃነትን የምንክድ ሆነን አይደለም። አንድነት ልዩነትን ማሰሪያ አማራጭ የለሽ መፍትሄ እንጂ ጨፍላቂነት እንዳልሆነ እናውቃለን።
አንድነት የልዩነት ማሰሪያ ብርቱና ወርቃማ ገመድ መሆኑን እናውቃለን።
ልዩነት የአንድነት ጌጥ መሆኑን እናውቃለን።
ሀገር በአንድነት ላይ ተመስርታ ልዩነትን ማቀፍ እንዳለባት እናምናለን።
ከልዩነት መነሳት ወደ አንድነት ሳይሆን ወደ የባሰ መከፋፈል እንደሚወስደን ስለገባን ነው፣ አንድነትን የምናስቀድመው እንጂ ልዩነት አይኑር ብለን አይደለም።
በሀይማኖትና በጎሳ የሚለያዩን በችግር ጊዜ ከእኛ ጋ እንደማይሆኑ ስለሚገባን ነው የማንፈልጋቸው። የግጭትና ሞት ነጋዴ ስለሆኑ ነው የምንርቃቸው። የሰው ህይወት መጥፋት ስለሚያመን ነወ የማንወዳቸው። በሞት ስለሚያተርፉ ነው የማንከተላቸው።
ኢትዮጵያንና ህዝቦችዋን የምናስቀድመው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሰው መሆኑ ተከብሮ፣ እኩል ሆኖ፣ በተከበረችና በበለፀገች ሀገር ላይ ብሔሩ፣ ቋንቋውና ታሪኩ እንደሚከበርና እንደሚበለፅግ ስለምንተልም ነው አንድነትን የምንሻው። የስርዓት ችግር ስርዓቱን በማረምና በማዘመን ይታረማል ብለን ስለምናምን ነው፣ ወደ ኋላ ከማየት ወደ ፊት እያየን፣ ነገአችንን በመመካከር በእኩልነትና በነፃነት ላይ ሀገር እንገንባ የምንለው። ከትናንት ተምረን ነገን እናሻሽል በማለት ነው፣ የትናንቱን ታሪክ መጥፎ መጥፎውን ብቻ ሳይሆን መልካሙንም እንያዝ የምንለው።
እኛ ይህን ነው የምናስበው። በዚህ እሳቤ ሀገር ያድጋል እንጂ ማንም አይጨፈለቅም። ማንም አይዋረድም። የአለም ሀገራት የሚሄዱበትም መንገድ ይህ ነው።
.ኢትዮጵያ ከእነ ህዝቦችዋ፣ ከእነ ልዩነቷ ለዘላለም በአንድነቷ ትኑር!

Read 722 times
Administrator

Latest from Administrator