Print this page
Monday, 14 September 2020 00:00

“የተጀመረው የብሔራዊ መግባባት መድረክ ተስፋ ሰጪ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 30 በተካሄደው የብሔራዊ መግባባት ሁለተኛ የውይይት መድረክ ላይ “ብሔራዊ መግባባት በኢትዮጵያ፡- ዘላቂ ሠላም፣ ሀገራዊ አንድነትና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር” በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት የ“ነፃነት እኩልነት ፓርቲ” ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር አደም ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በብሔራዊ መግባባት ሂደቶች ዙሪያ ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

          በፓርቲዎች መካከል የተጀመረው የብሔራዊ መግባባት መድረክ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች በመፍታት በኩል ምን ያህል ተስፋ ሰጪ ነው?
ግልጽ ሊሆን የሚገባው ነገር አሁን በፓርቲዎች መካከል የተጀመረው ውይይት የብሔራዊ መግባባት መድረክ አይደለም፡፡
በፓርቲዎች መካከል ያሉ ዋልታ ረገጥ የሆኑ የፖለቲካ አመለካከቶችን ለማቀራረብ ያለመ፣ ለዋናው ብሔራዊ መግባባት መድረክ የሚደረግ የዝግጅት ምዕራፍ ነው፡፡ ዋናው የብሔራዊ መግባባት መድረክ የሚባለው በንድፈ ሃሳብም በተግባርም ባለድርሻዎቹ የፓርቲ ተወካዮች ብቻ አይደሉም፡፡ ስለዚህ መድረኩ ዋናው የብሔራዊ መግባባት መድረክ አይደለም፤ የፓርቲዎች ውይይት ነው፡፡ ግን ለዋናው ብሔራዊ መግባባት በእጅጉ መነሻ የሚሆን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን እየተካሄደ ያለው ውይይት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
ህወኃት በሌለበት እንዲሁም አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች በእስር ላይ ባሉበት ይህ መድረክ ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን ይችላል?
ብሔራዊ መግባባት በብዙ ሀገሮች በተለያየ መንገድ ተሞክሯል፤ እንደየሀገሩ ሁኔታና የተሞከረበት አግባብም ውጤታማ የሆነም ውጤታማ ያልሆነም አለ። በኛ ተጨባጭ ሁኔታ እኔም በጽሑፉ እንደጠቆምኩት፤ ውጤታማ የብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በመጀመሪያ በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሠሩ ካሉ እነሱን መልቀቅ ያስፈልጋል፤ በጊዜያዊነት ይቅርታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሊሰጣቸው ይገባል፤ የሚዲያ ቅስቀሳና የማንቃት ተግባር ያስፈልጋል፤ በሂደቱ ወቅት ማንም በፖለቲካ አመለካከቱ ሊገለል ወይም የተለየ ዘመቻ ሊከፈትበት አይገባም፡፡ እርቅ ማምጣት ካለብን በሀገሪቱ ከዳር እስከ ዳር ያሉ ሃይሎች በሙሉ ሊሳተፉ ይገባል፡፡ ማንንም ማግለል ተገቢ አይሆንም፡፡ ስለዚህ መንግስት በጣም ሆደ ሰፊ መሆን አለበት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆን አለባቸው፡፡ የራስን ፍላጐት ብቻ በማየት በዚህ አጋጣሚ ተጠቅሜ ወይ ስልጣኔን አራዝማለሁ አሊያም ወደ ስልጣን እመጣለሁ የሚል ወገን ካለ አላማው ውጤታማ መሆን አይችልም፡፡
በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ብሔራዊ መግባባት የሚያስፈልግበት  ምክንያት ምንድን ነው?
በሁለት የሚከፈሉ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው ያልተቀረፉ የታሪክ ቁርሾዎች ይኖራሉ፡፡ በሀገሪቱ ግንባታ ታሪክ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ላይ መነጋገርና አንድ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው የምርጫ ጉዳይ፣ የብሔር ጥያቄ፣ የክልልነት ጥያቄ፣ የህገመንግስት ማሻሻያ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ አለ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የብሔራዊ መግባባት ሂደትን መጀመር በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በእነዚህ ላይ የብሔራዊ መግባባትን ጀምሮ ቢቻል ከምርጫ በፊት በተለይ ዋነኛ በሚባሉት ጉዳዮች ላይ መግባባትና መቀራረብ ብንችል እጅግ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ብሔራዊ መግባባት በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ አይደለም፤ በየጊዜው ሊካሄድ የሚገባው ሂደት ነው፤ በቋሚነት ምናልባት በየ5 አመቱ ሊሆን ይችላል፡፡ የብሔራዊ መግባባት ውይይቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ይሄን ማድረጉ ችግሮች ተጠራቅመው ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ለመከላከል በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አንዳንድ ሀገሮች እንዲህ ያለ ተሞክሮ አላቸው፡፡
ብሔራዊ መግባት በመንግስት በኩል በአቋራጭ ወደ ስልጣን መውጫ መንገድ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ ከዚህ እሳቤ ለመውጣት ሊደረግ የሚገባው ብሔራዊ መግባባት ምን አይነት ነው ይላሉ?   
ብሔራዊ መግባባት ሂደት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ብቻ የሚሳተፉበት አይደለም። ሌሎች ባለድርሻዎችም የሚካተቱበት ነው። የሲቪክ ማህበራት የመሳሰሉት ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከድርድርና ከሌሎች አማራጮች ይልቅ የብሔራዊ መግባባት ሂደት የበለጠ ችግሮችን ለመፍታት ተመራጭ ነው የሚል እምነት አለኝ። ከዚያ በተረፈ ብሔራዊ መግባባትን አቋራጭ የስልጣን መወጪያ መንገድ ተብሎ የሚገለፀው ትክክል አይመስለኝም፡፡ ስልጣን መፈለግም በራሱ ችግር አይደለም፤ በትክክለኛው መንገድ ከሆነ ነገር ግን ብሔራዊ መግባባትን ከስልጣን መፈለግ ጋር ማገናኘት ተገቢ አይሆንም፡፡ ብሔራዊ መግባባት ዋና አላማው ስልጣን መከፋፈል ሳይሆን ሀገርን ማዳን ነው፡፡ ነገሩ ትንሽ እውቀትና ዝግጁነት ይፈልጋል፡፡ ሂደቱን በደንብ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ የብሔራዊ መግባባት መድረክ ላይ ያለፉ አወዛጋቢ ትርክቶችን ማንሳት ተገቢ አይደለም የሚል ትችት ሲቀርብ ይስተዋላል። የሔራዊ መግባባት አጀንዳ ከምንድን ነው መጀመር ያለበት ይላሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ የብሔራዊ መግባባት ሂደት ልጀምር ያለ ሀገር፤ ሁሉንም አይነት ትርክት ለመስማት ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ እነዚያ ያልተግባባንባቸውን ትርክቶች አንስተን ተወያይተን መፍትሔ ካላመጣንባቸው ታዲያ ምንድነው የውይይቱ ጥቅም? ነገር ግን ታሪክ ሲነሳ አላማው ወሳኝ ነው፡፡ ያለፈን ቁስል አንስቶ ልዩነትን ለማስፋት ከሆነ ተገቢ አይሆንም ነገር ግን “በብሔር በሃይማኖት ተበድያለሁ፤ ያ በደሌ ተስተካክሎ የአንድ ሀገር እኩል ዜጋ እንሁን” ከሆነ አላማው ያ ሃሳብ በሚገባ ቀርቦ መሰማት አለበት፡፡ ያንን ለመስማትም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ውይይቱ ያስፈለገውም ለዚሁ አላማ ነው፡፡ ማንኛውም ሃሳብ ሲነሳ ክልከላ ወይም ገደብ ሊደረግበት አይገባም፡፡ ግን ሃሳብ ስናነሳ በማስረጃና ለመግባባት በሚጠቅም መንገድ መሆን አለበት፡፡ ብሔራዊ መግባባት ላይ ቁልፉ ነገር መተማመን መፍጠር ነው፡፡
ከምርጫው በፊት ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ የሚቻል ይመስልዎታል?
ብሔራዊ መግባባት እንደ አጀንዳው ስፋት ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን እስከ ምርጫው ባለው ጊዜ ቢያንስ ወሳኝ በሚባሉና ለምርጫው ጥሩ መደላድል በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ መወያየትና መግባባት ይቻላል፡፡ ሌላው በሂደት ውይይት ሊደረግበት ይችላል፡፡ የብሔራዊ መግባባት ሂደት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅበትም አይደለም፡፡ ተደጋጋሚ ውይይት በየጊዜው ማድረግ ይጠይቃል፤ የሚያልቅ ጉዳይም አይደለም፡፡  
ከመንግስት በኩል ለብሔራዊ መግባባት ምን ያህል ቁርጠኝነት አለ ብለው ያስባሉ? አሁን የተጀመረው ሂደት ልባዊ ይመስልዎታል?
እኔ እንደዛ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም አሁን ያለንበት ሁኔታ ያን አይነት ቁርጠኝነት የሚያስፈልገው ነው። አሁን እየገጠመ ያለው ችግር ሀገርን የማስቀጠልና የዜጐች የህልውና ጉዳይ ነው። ብዙዎች በቁርጠኝነቱ ላይ ይጠራጠራሉ፡፡ ስጋቱን እኔም በተወሰነ ደረጃ እጋራዋለሁ። በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ነው የሚል አመለካከት መንግስት ዘንድ ካለ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን መጀመሩ በራሱ ለኔ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ይሄ ውይይት እንዲጀመርም ተነሳሽነቱን የወሰዱት ጠ/ሚኒስትሩ መሆናቸውም ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
በዚህ ውይይት እነማን ቢሳተፉ ነው ውጤታማ የሚሆነው ይላሉ?
የብሔራዊ መግባባት ሂደቱን ቅቡልነት ከሚወስኑት አንዱ እነማን ናቸወ የሚሳተፉበት የሚለው ነው፡፡ በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እነማን ይሳተፉ የሚለው ወሳኝ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡ ከልሂቃኑ እነማን ይሳተፉ ተብሎ ሲመረጥም በጣም ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያራምድ ሳይሆን ከሁሉም የተካተቱበት መሆኑን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ መስፈርቶች ወጥተው በዚያ መስፈርት ነው ተሳታፊዎች ሊመረጡ የሚገባው፡፡ የተሳታፊ ብዛትን በተመለከተ ተወያየቶ መወሰን ከአሳታፊነት አንፃርም ገምግሞ መወሰን ያስፈልጋል። ለምሣሌ እኔ ባቀረብኩት ጽሑፍ እንደጠቀስኩት፤ በኬንያ በተደረገው መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩት 8 ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ 4 ከመንግስት 4 ከአንድ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ ነበሩ የተሳተፉበት፡፡ ሌሎችን አላሳተፉም፡፡ የኛ ሁኔታ ከዚህ ይለያል፡፡ በህዝብ ቅቡልነት ያላቸውን ሰዎች ሁሉ አሰባስቦ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ የካድሬዎች ስብሰባ ከሆነ ለብሔራዊ መግባባት የተባለው ተለውጦ የበለጠ ልዩነት ሊፈጥር ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሰብሳቢውም በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ብዙ ሀገሮች ላይ ብሔራዊ መግባባት የሚሠናከለው የሀገሪቱ መሪዎች ራሳቸው ሰብሳቢ ሲሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በኛም ሀገር ሁኔታ ሰብሳቢው ወሳኝ ነው፡፡ ገለልተኛና ሁሉም የሚያምነው ሰው መምረጥ ወሳኝ ነው፡፡
አዲሱን አመት እርስዎም ሆኑ ፓርቲያችሁ በምን ተስፋ ነው የምትጀምሩት? ምንስ ይመኛሉ?
የባለፈው አመት ለብዙዎቻችን ከባድ አመት ነበር፡፡ የፖለቲካ ችግርም ነበር የኮሮና ወረርሽኝም ችግርም ሌላው አስጨናቂና አመቱን ከባድ ያደረገ ችግር ነው፡፡ የጐርፍ አደጋም የብዙዎችን ህይወት አመሰቃቅሏል። በግጭቶች የበርካቶችን ህይወት አጥተናል። ዓመቱ ያም ሆኖ ግን ስኬቶችም ተመዝግበዋል፡፡ የአባይ ግድብ አንዱ ነው፡፡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሞልተናል፡፡ በዚህ መንግስትንም ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ በ2013 ደግሞ ሁሉም ነገር ሠላም እንዲሆን እመኛለሁ፤ የተፈናቀሉ በአስቸኳይ ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትና ዳግም መፈናቀል የማይኖርበት አመት እንዲሆን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡ ከፖለቲካ አንፃር፤ በአጭር ጊዜ ብሔራዊ መግባባት ውስጥ ገብተን ብዙ ችግሮችን እንፈታለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ይህም እንዲሆን እመኛለሁ፡፡  

Read 1727 times