Print this page
Saturday, 12 September 2020 14:11

የዓመቱ ምርጥና ድንቅ ስኬቶች፣ … ለአሳፋሪና ለአሳዛኝ ጥፋቶች

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(5 votes)

ብዙ የስኬት ማሳያዎች አይተናል፡፡ ስራዎችን ለውጤትም ብቃትና ፈተናዎችን የማብቃት አቅም እንዳለን 2012 ይመሰክርልናል፡፡
የዘረኝነት አስተሳሰብንና መዘዞችን መከላከል አለመቻላችን ሃጥያታችንን ይመሰክርብናል - የእውቀት የስነምግባር እጦታችንን
የወዳጅነት አደባባይና ለሎች መንፈስ አዳሽ ማዕከላት፣ የስኬት ማሳያዎች ናቸው፡፡
ለብዙ ኢንቨስትመንትና ለብዙ ፋብሪካ፣ ለመኖሪያ ቤትና ለትልልቅ ግንባታ እንድንተጋ ያነቃቁናል፡፡
በተቃራኒው፣ ባለፉት 10 ዓመታት እንደሰማነው፣ “የኢትዮጵያ ከተሞችን 40% ወይም ቢያንስ ቢያንስ 30% ፓርክ በፓርክ እናድርጋቸው” በሚል ዲስኩር ከተዘፈቅን፣ ለውድቀት መቸኮል ይሆናል

                 በክፋትና በጭካኔ ሳቢያ፣ የብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ፣ የሚሊዮኖች ኑሮ መናጋቱ ያሳዝናል፡፡ ያሳፍራልም፡፡ ዘረኝነትን የመሳሰሉ የረከሱ አስተሳሰቦችን መመከት፣ የጥፋት ሰበቦችን መከላከል አቅቶናልኮ፡፡ ዘረኝነትን ለመግራትና ለመግታት መቸገራችን፣ ያሳፍራል፡፡ በእውቀትና በስነምግባር እጦት ምንኛ እንደተራቆትን (ማለትም፣ የቱን ያህል ወደሃጥያት፣ ወደ እጦት እንደወረድን) ይመሰክርብናል፡፡
ግን ደግሞ፣ እጦታችን፣ እርግማን አይደለም፡፡ አደጋዎችን መመከትና የጥፋት ሰበቦችን መከላከል እንደማያቅተን፣ ቅንጣት አያጠራጥርም፡፡ ፈተናዎችን የማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወትን የማሳመር ድንቅ ውስጣዊ አቅም አለን፡፡ ካወቅንበትና ከተጋንበት፣ ምን ያቅተናል? ወረርሽኝን መከላከል ብቻ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚን ማዳን እና ማሳደግ፣ የሕዳሴ ግድብን ለውጤት ማብቃት እንዴት ይሳነናል? በጭራሽ! በእውቀትና በስነምግባር፣… ሃሳባችንን ማጥራት መንገዳችንንም ማቃናት እንችላለን፡፡ በተግባር አይተናል፤ አሳይተናልም፡፡
ለእውነታ በመታመን እውቀትን ስንጨብጥ፣…
ለሕይወት ዋጋ ሰጥተን በቀና የጥረት መንገድ ስንጓዝ፣
ኑሮን ለማሻሻል አልመን፣ አለማን ለማሳካት በጥበብ ስንተጋ፣
እነዚህ ቅዱስ የስነምግባር መርሆች በጽናት ይዘን ስንሰራባቸውና የግል ኃላፊነትን በኩራት ስንጨብጥ፣ ውጤት እንደምናፈራ፣ 2012 ይመሰክርልናል፡፡
ማሳያ ሞልቷል፡፡ እውነታውን ለመረዳት አይከብድም - መረጃዎች ሞልተዋል። ለማስረዳትም አይቸግርም - ማስረጃዎች ሞልተዋል፡፡
የስራ እድሎችን ለመክፈት፣ ኑሮን ለማሻሻልና ኢኮኖሚን ለማሳደግ የሚጠቅሙ፣ በርካታ የስራ ፍሬዎችንና ስኬቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሕዳሴ ግድብ ለወግ ለማዕረግ ሲደርስ፣ ከታሪክ ጋር አብረን እያየን ነው - ታሪክን እየፈጠርን፡፡ ለጣና ሐይቅ ክብር የሚመጥን አዲስ ሐይቅ፣ ገና ከጅምሩ ሲፈጠር በእውን ማየት፣ አስደናቂ ታሪክ ነው፡፡
አስቡት፤ በርካታ ምዕተ ዓመታት አልፈዋል። ሕዳሴ ግድብ አልነበረም፡፡ አዲስ ሐይቅም አልታየም - የተራቆተ ጋራ ሸንተረር እንጂ፡፡ ወደፊት ደግሞ፣ እርቃኑ የሚታይ ጋራ ሸንተረር አይኖርም - የተንጣለለ ሐይቅ እንጂ፡፡ እኛ፤ ይህንን ድንቅ ታሪክና ተዓምረኛ ክስተት ለማየት በቅተናል፡፡
የተራቆተውን ጋራ ሸንተረር ስናይ ቆይተን፣ የግድብ ግንባታው፣ ደረጃ በደረጃ፣ ቀን በቀን መልክ ሲይዝ፤ ጋራ ሸንተረሩ በውሃ ሲሸፈንና ሐይቅ ሲወለድ ምስክር ሆነናል፡፡ ምስክር ተመልካች መሆን ቀላል እድል አይደለም፡፡
ነገር ግን፤ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ የስኬት ታሪክ ምስክር ከመሆንም በላይ፣ የድንቅ ስራ ተሳታፊ፣ የስኬት ታሪክ ባለድርሻ ሆነዋል፡፡
ሌሎች ምርጥና ድንቅ የስራ ፍሬዎችንም እያነሳን እናያለን፡፡ 2012 እንደ መሰክቷልን፣ ካወቅንበትና ከተጋንበት፣ ድንቅ ውጤት ማፍራትና ለስኬት መብቃት እንችላለን፡፡ የሚገታን ሃይል የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ካወቅንበትና ከተጋንበት፣ ከባባድ ፈተናዎችን መመከት እንደምንችልም፣ 2012 ይናገርልናል። ለወረርሽኝ አልተሸነፍንም፡፡  የኮረና ቫይረስ ማዕበል አላጥለቀለንም፡፡ በዚህም የብዙ ሰው ሕይወት፣ ከአደጋ ድኗል፡፡
አዎ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ያሳዝናል፡፡
ነገር ግን፣ ከባሰ አደጋና ከብዙ ጥፋት ተርፈናል፡፡ ለምን? የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን በአስተዋይነት ጥረዋል፡፡ ለጥንቃቄ በመትጋታቸውም፤ ወረርሽኙን መግራት ችለዋል፡፡ ሕይወትን አትርፈዋል፡፡ ይሄ፣ ትምህርት ሊሆነን ይገባል። ሌሎች የአስተሳሰብ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ በሽታዎችን ለማሸነፍ፣ እንጠቀምበት፡፡
የቫይረሱን ምንነትና የበሽታውን ባሕርይ፣ እንዲሁም መከላከያ ዘዴዎችን በግልጽ ማወቅ፣ አንዱ ቁምነገር ነው፡፡ በተገቢው መንገድ (በስነምግባር)፣ እውቀትን በተግባር የመተርጐምና በእውን የመፈፀም ጽናት ደግሞ፣ ሁለተኛው ቁምነገር ነው፡፡
በእርግጥ፣ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተፈጠረው ሁከትና አመጽ፣ ወረርሽኙን አባብሶብናል፡፡ በሐምሌ ወርም፣ ብዙ ሰዎች ተዘናግተዋል፡፡ የመንግስት ተቋማትና በርካታ የሚዲያ ምንጮችም ተዝረክርከዋል፡፡ ኢቲቪን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ የወረርሽኝ መረጃዎችን ሳይዘግብ፣ የኬንያ፣ የኢራቅ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የብራዚልና የሌሎች አገሮች የወረርሽኝ ዘገባዎችን በተከታታይ ቀናት ሲያሰራጭ ሰንብቷል - በሐምሌ አጋማሽ። እነዚህ ስህተቶች ቢኖሩም፤ የአገሪቱን ስኬት አላጨለሙም፡፡
አስታውሱ፡፡ በበርካታ አገራት ከተከሰተው የመደናበር ስህተት አምልጠናል፡፡ “አገርና” ኢኮኖሚን ሁሉ ዝጉ፣ ስራንና ኑሮን ገዝቱ፣ ቤታችሁንም ቆልፋችሁ ተቀመጡ” ብለው ያወጁ መንግስታት ጥቂት አይደሉም… በተለይ በአውሮፓ ምድር፡፡
“ሲሉ ሰምታ…” እንዲሉ፣ ከህንድና ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ፣ በርካታ ድሃ አገራትም በጭፍን ገብተውበታል፡፡ “ይዘጋ፤ ይከርቸም” በሚል የሆይሆይታ ግርግር ሳቢያ ተደናብረዋል። የጭፍን ኩረጃ ሰለባ ሆነዋል፡፡ “ወደ ስራ አትሂዱ፣ ገበያ አትውጡ፣ በየቤታችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ”…ብለው አውጀዋል -በጭፍን ኩረጃ የተደናበሩ መንግስታት፡፡
ውዥንብር ከመፍጠር ውጭ፣ ምን አመጡ? ለቫይረስ ስርጭት የሚያጋልጥ ግርግርና አመጽ ከመፍጠር ውጭስ ምን አተረፉ?  የሰዎችን ስራ ዘግቶ፣ ኢኮኖሚውን አጨልሞ፣ የእለት ጉርስ ማሳጠት፣…እንዴት መፍትሔ ይሆናል? እንዲያውም፣ በኮረና ቫይረስ ላይ ተጨማሪ የጤና ጠንቅና በሽታ ከመፍጠር አይተናነስም። በዚያ ላይ፤ ለአመታት የማይሽር የኢኮኖሚ ስብራትም ነው፡፡
በዘወትሩ ደካማ ኢኮኖሚና በነባሩ የድህነት ኑሮ ላይ፣ “ኢኮኖሚን ዘግተን፣ ኑሮን ቆልፈን እንቀመጥ” የሚል የጭፍንነት ሃሳብና የተደናበረ ውሳኔ ሲታከልበት፤ የድጡ ወደማጡ ይወርዳል። የዛሬን የኑሮ አማራጭ ይዘጋል፤ የነገንም ተስፋ ያጨልማል፡፡ የኢኮኖሚ ውድቀት ደግሞ፣ በአመት በሁለት አመት አይሽርም፡፡ የበርካታ ዓመት ከባድ እዳ ነው - ከውድቀት ማገገምና ማንሰራራት ቀላል አይደምና፡፡
ከዚህ ጥፋት ድነናል፡፡ “ይዘጋ፣ ይቆለፍ” እያሉ የቀሰቀሱና የጮኹ ጠፍተው አይደለም። ብዙ ነበሩ፡፡ ደግነቱ፣ መንግስት፣ በጭፍን ኩረጃና በሆይሆይታ አልተደናበረም፡፡ ይሄ፣ ከዓመቱ የእውቀትና የጥበብ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
በጭፍን ኩረጃ የመደናበር መዘዝ ብዙ ነዋ። አንደኛ፣ የቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል አላገዘም፡፡ ውጤት አልባ ኪሳራ ነው፡፡ የተደናበሩ መንግስታት፣ ውዥንብርና ግርግር ነው ያተረፉት፡፡ ሁለተኛ ነገር፣ የሚሊዮኖችን የእለት ጉርስ ዘግተዋል፤ ኑሮን አጐሳቁለዋል፤ ኢኮኖሚን ሽርሽረዋል፡፡ ሦስተኛ ነገር፣ ለዓመታት የማይገላገሉት እዳ ፈጥረዋል፡፡
ከእንዲህ አይነት ጭፍን ኩረጃ ድነናል፤ ከመደናበር አምልጠናል፡፡ ይሄ ቀላል ነገር ነው? አይደለም፡፡
“ወረርሽኝን መከላከል” ማለት፣ “በጥንቃቄ ኑሮን መቀጠል” ማለት እንጂ፣ መደናበር ማለት አይደለም፡፡ ኢኮኖሚን ዘግቶ ስራን ማቋረጥና ኑሮን ይባስኑ ማጐሳቆል ማለት አይደለም፡፡
“ኑሮን ለማሻሻል መትጋት” ማለት፣ “ከወረርሽኝ እየተጠነቀቁ መስራት” ማለት እንጂ፣ መፍዘዝ ማለት አይደለም “ስለኮረና ቫይረስ ሰምተው እንዳልሰሙ መሆንና በጭፍን መዝረክረክ” ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ መንግስታት ግን ተዝረክርከዋል፡፡ “ኢኮኖሚን አንገድልም፤ ስራን አናግድም፤ ኑሮና አናጐሳቁልም” ብለው፤ በጥንቃቄ ከመስራት ይልቅ፣ ከጥንቃቄ ተዘናግተው ተዝረክርከዋል፡፡
በዚያው ልክ፣ “ቫይረሱን እናጠፋለን፤ ለወረርሽኙ ቀዳዳ አንከፍትም” ብለው፤ ኢኮኖሚያቸውን ያንኮታኮቱ፣ የሚሊዮኖችን ስራ ዘግተው፣ የኑሮ ገቢን አሳጥተው ለተመጽዋችነት የዳረጉ መንግሥታትም በርካታ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ፣ ለእነዚህ መንታ ስህተቶችና ጥፋቶች አልተዳረገችም፡፡ ከመፍዘዝም ከመደናበርም አምልጣለች፡፡ ኢትዮጵያ በዝርክርክነት ለወረርሽኝ ማዕበል ተመቻችታ አልተጥለቀለቀችም፡፡ በጭፍን ኩረጃ እየተደናበረች፡፡ በአዋጅ የአገርን ኢኮኖሚ አልገደለችም፤ የሚሊዮኖችን ኑሮ ለባሰ ጉስቁልና አልዳረገችም፡፡
በእርግጥ፣ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮትያ የደረሰው፣ ከበርካታ አገራት በኋላ ስለሆነ፣ እድለኞች ነን፡፡ ስለቫይረሱ ምንነትና ስለመከላከያ መንገዶች መረጃ ለማግኘት፣ እውቀትም ለመጨበጥ ረድቶናል፡፡ ለመዘጋጀት ጊዜ አግኝተናል፡፡
ቱሪስት በሚበዛበት ወቅት፣ ወረርሽኙ አለመጀመሩም አግዞናል፡፡ የአየሩ ፀባይም፣ በበልግ የመጋቢትና ሚያዝያ ዝናባማ ወራትም ጭምር፣ የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት አለማጣታችም ረድቶናል፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ የእውቀትና የስነምግባር መንገድ ነው፤ ወረርሽኝን ለመመከት ያስቻለን - ከመደናበርና ከመፍዘዝ የፀዳ ቀና መንገድ። ይሄ፣ መልካም ውጤት ነው፡፡ ሌሎች ፈተናዎችን ለማሸነፍና ጥፋቶችን ለመግታትም ጥሩ ትምህርት ሊሆነን ይችላል፡፡ ድርብ ጥቅም እንዲሉ ነው፡፡
የተጀመሩ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ፣ የተወጠኑ ሃሳቦች በተግባር ሲከወናኑ ማየትም፤ ጥቅሙ ድርብ ነው፡፡ ለግንባታ የዋለ ሃብት፣ ለአገልግሎት ይበቃል፡፡ ተጨማሪ ሃብት ለማፍራትና የስራ እድል ለመፍጠር ይጠቅማል፡፡ ከዚህም አልፎ፣ የስራ መንፈስን ያነቃቃል፤ የስኬት ተስፋን ያደምቃል፡፡ ለእድገት ያነሳሳል፤ ኑሮን ለማሻሻል ብርታት ይሰጠናል፡፡
ለዚህም ነው፤ ግንባታዎችንና ስኬቶችን ማየት ሊያስደስተን የሚገባው፡፡ የተለያዩ የዘይት ማምረቻ የግል ፋብሪካዎች እየተገነቡ መሆናቸው፤ በአዲስ አበባ በሚድሮክ ኢትዮጵያ የተቋቋመው የዳቦ ማምረቻ በአጭር ጊዜ ስራ መጀመሩ፣ እና ሌሎችም ስኬቶችና የግል ኢንቨስትመንቶች እሰየው ያሰኛሉ፡፡
የባንኮች ትርፋማነትም መልካም ነው፡፡ በባንኮች የተጀመሩ ትልልቅ ሕንፃዎች፣ ከእለት እለት፣ ከሳምንት ሳምንት እየተመነደጉ፣ ሽቅብ መጥቀው፣ ግንባታቸው በፍጥነት እየተጠናቀቀ፤ አምረው ተውበው ግርማ ሞገስ ሲላበሱም አይተናል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግዙፍ ሕንፃም፣ በተወጠነለት መልክና ማዕረግ ለአዲስ ዓመት ጐልቶ ደምቆ ለመታየት በቅቷል፡፡
በታላቁ ቤተመንግስት ከተሰራው የአንድነት ፓርክ በመቀጠል፣ የእንጦጦ እንዲሁም የወዳጅነት አደባባይ ተብሎ የተሰየመው መንፈስ አዳሽ ማዕከል፤ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ተመርቋል፡፡
ካወቅንበትና ከተጋንበት፣ አደጋን መከላከልና ወረርሽኝን መግታት ብቻ ሳይሆን፣ መገንባትና ማሳካት፣ መስራትና ማደግ እንደሚቻል የሚመሰክሩ የ2012 ክስተቶች ጥቂት አይደሉም። በምረቃው በዓል የቀረበው የክብር ዘብ ወታደራዊ ትዕይንትና የሰልፍ ሙዚቃ ጭምር፣ መንፈስን ያነቃቃል -ብቃትንና ስነሥርዓትን አድምቆ የሚያሳይ ነውና፡፡
ነገር ግን አትርሱ፡፡ እነዚህ ሁሉ መልካም የግንባታ፣ የስኬት፣ የብቃት ስራዎች፣ “ማሳያ” መሆናቸውን ለአፍታ መዘንጋት የለብንም፡፡
አዎ፤ ራሳቸውን የቻሉ ስኬቶች ናቸው፡፡ ጥቅም የሚሰጡ ውጤቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን፣ ከቀጥተኛ አገልግሎታቸው በላይ፣ የስኬት ማሳያ መሆናቸው ይልቃል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንደተናገሩት፤ ለመልካም ዓላማ ግንባታ መጀመር በፍጥነት ማጠናቀቅና ለውጤት ማብቃት እንደምንችል፤ እውን ማሳያዎች ናቸው፡፡
ፕ/ት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉትም፤ ዜጐች በእውቀትና በትጋት፣ ኑሯቸውን የሚያሻሽሉበት የኢኮኖሚ እድገት ነው ዋናው ዓላማ፡፡ ኑሮን የሚሻሻል ልማትና እድገትን በጽናት እውን ማድረግ እንደምንችል፤ የወዳጅነት አደባባይ ግንባታ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል - ፕ/ት ሳህለወርቅ፡፡
አዎ፣ ነፍስ አዳሽ ማዕከላት ያስፈልጋሉ፤
ተገንብተው አምረው ሲመረቁም ያስደስታል። መንፈስን ከማደስ ጐን ለጐን ለቱሪዝም ገቢም ይጠቅማሉ፡፡ ነገር ግን፤ ዋና ግብ አይደሉም፡ ማሳያ ናቸው፡፡
አዲስ አበባን ወይም አገሪቱን ከዳር እስከዳር፣ “የፓርክ ከተማ” ወይም “የመናፈሻ አገር” እንዲሆኑ አይደለም፡፡ ደግሞም አይቻልም። ቢቻልም እንኳ፣ ስኬት ሳይሆን የለየለት ውድቀት ይሆናል፡፡
ከተሞችን ሁሉ ፓርክ በፓርክ ለማድረግ የሚሰብኩ ግን ብዙ ናቸው፡፡ ከምር እቅድ የሚያወጡ “ወገኞች” እና “የውደቀት ጠንሳሾች” በየቦታው ሞልተዋል፡፡ ቢሮክራቶች፣ የውጭ መንግስታት፣ አበዳሪ ተቋማት፣ “ፈንድ” የሚያሳድዱ ምሁራንና የእርዳታ ድርጅቶች… ብዙ ናቸው፡፡
የከተማው 40% መሬት፣ ለፓርክ፣ ለመናፈሻ፣ ለጫካና ለዱር አራዊት ብቻ እንዲከለል ይሰብካሉ፡፡ “ቢያንስ ቢያንስ 30%“ እያሉም ይዝታሉ፡፡ ከዚያም አልፈው፤ ከምር ሕግ አርቅቀው ያውጃሉ፡፡ እንዲያውም፤ የኢትዮጵያ ከተሞች፣ ይህንን ለመተግበር በጉባኤው ሲወስኑ፣ ለፓርክ ቅድሚያ ሰጥተው የከተማ መሬት ለማዘጋጀት ቃል ሲገቡና ሲያጨበጭቡ አይተናል - በቀድሞው የከተማ ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት፡፡
ይሄ የአገርን ውድቀት ከመደገስ አይለይም። የዜጐችን ኑሮ ለባሰ ጉስቁልና የመዳረግ እሽቅድምድም ነውና፡፡ ከዚህ እንጠንቀቅ፡፡
መንፈስ አዳሽ ማዕከላት፣ ለትጋት የሚያነቃቁ፣ ኑሮን ለማሻሻል የሚያነሳሱ፣ የስኬት ማሳያ ናቸው፡፡ በዚያው ልክ፤ ለስራ የሚተጋና ኑሮውን የሚያሻሽል ሰው፣ መንፈስ አዳሽ ማዕከላት ያስፈልጉታል፡፡ የማይሰራና መኖሪያ የሌለው ሰው፣ መናፈሻ አይፈይድለትም፡፡
በሌላ አነጋገር፤ የፋብሪካዎችና የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችን ለማሳለጥ፣ የስራ እድል ለመፍጠር፣ የመንፈስ አዳሽ ማዕከላት ግንባታ የስኬት ማሳያ ይሆነናል፡፡ የመንግስት ተቋማትና የከተማ አስተዳደሮች፣ ይህንን በፍጥነት ተገንዝበው፣ የቀድሞውን የውድቀት መንገድ መግታትና የተቃና የብልጽግና መንገድን ለመጥረግ መትጋት ይገባቸዋል፡፡ አለበለዚያ፤ የስኬት ማሳያዎች በከንቱ ባክነው ይቀራሉ፡፡ መባከን የለባቸውም፡፡ ለብልጽግና የሚያነሳሱ ማንቂያዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ በአጭሩ፤
የግል ኢንቨስትመንቶች እና አዳዲስ ፋብሪካዎች በብዛት ያስፈልጋሉ፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን፣ የሰዎች የስራ ገቢ እያደገ፣ የመኖሪየ ቤት የግብይትና የቢሮ ግንባታም ይሳለጣል፡፡ ከዚህ ውጭ ብልጽግና የለምና፡፡

Read 9663 times