Saturday, 12 September 2020 15:04

የተጨማደዱት

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

 በሁለት ወራት ልዩነት ውስጥ እግዜር ጨብጦ በዞሮዶባ ሰፈር ስርቻ የጣላቸው ገፀ ባህሪዎች መሃል ሁለቱ ሞቱ፡፡ ከስርቻው ወደ ቁሻሻ መጣያው ቅርጫት ተወረወሩ፡፡ መላው ተስፋ ቆራጭ ማህበረሰብ ደነገጠ። «ተረፍን» የሚሉት ስለ ራሳቸው እጣ-ፈንታ ማሰላሰል ያዙ፡፡ ተጨማድዶ እስከ መጨረሻው መቀጠል አይቻልም፤ መዘርጋት ካቃተው መሞቱ የማይቀርለት ነው፡፡
ማታ የጠጡትን አረቄ ለማብረድ እንደ ሁልጊዜውም ከጠዋቱ ሦስት ሰዐት ላይ በጠላ ቤት የስራ ገበታቸው ላይ ይገኛሉ። የጠላ መጠጣቱን ስራ እዛው ገበታ ላይ ሆነው ሲያገባድዱ… ወደ አረቄ ይሸጋገራሉ። አንቶቭ መሞቱ የተሰማው ከትላንት ወዲያ ነበር። የተቀበረው ደግሞ ትላንት። አረቄያቸውን አቋርጠው  የካ ሚካኤል ድረስ በዘጠኝ ሰዐቱ ጠራራ ፀሐይ መሔድ ስላልቻሉ ሳይቀብሩት ቀሩ፡፡
አንቶቭን የቀበሩት አብረውት ያልጠጡት ናቸው፡፡ ብር እየተቀበሉ አረቄ ለአስር አመት የጋቱት ጋሽ ባይሣም ለቀብሩ አልተገኙም። ሰውን ያጠጣሉ እንጂ እሳቸው ግን አይቀምሱም። ሟቹ፣ ሞቱን ቀስ በቀስ እየጋቱ ያጨማደዱት እሳቸው መሆናቸውን አያምኑም፡፡ ፖሊስም ያልያዛቸው ለዚህ ነው። ቀስ በቀስ የሚገድል መግደያም ሆነ ገዳይ በህግ አይጠየቅም። አንዳንድ መንግስትም ዜጎቹን ቀስ በቀስ ነው የሚገድላቸው፡፡ ኑሮ በማስወደድ፣ በፕሮፓጋንዳ፣ ዘራፊ እያሰማራባቸው፣ እያፈናቸው… የተስፋ መፈናፈኛ በማሳጣት ነው የሚገድላቸው፡፡
ሚስትም አንዳንዴ ባሏን ቀስ በቀስ ነው የምትገድለው፡፡ ነፃነቱን በ«ብር አምጣ» ጭቅጭቅ አሯሩጣ፣ በ«ጊዜ ቤት ግባ» ንትርክ ልቡን ተርክካ፣ በ«ወንድ ነህ አይደለህም» ፈተና ፈትፍታ፣ በ«ትወደኛለህ አትወደኝም» ቤተ-ሙከራዋ አሰልችታ፣ በ«አርግዣለሁ መሰለኝ» ማስደንገጫ ወግራ… ቀስ በቀስ ሸርሽራ ትገድለዋለች። በህግ አትጠየቅም፡፡ የቀስ በቀስ ገዳዮችን ጉዳይ በደል የሚመለከት ፍርድ ቤት በህሊና ግዛት እንጂ በህገ መንግስት አንቀፆች ላይ የለም፡፡ ቢኖርም ተግባራዊ አይደረግም፡፡
አንቶቭ (አንተነህ) እና በድሉ የሞቱት በአረቄ ነው፡፡ አረቄውን የሸጡላቸው ጋሽ ባይሣ ናቸው። አረቄውም ጋሽ ባይሳም መኖር ቀጥለዋል፤ ጠጪዎቹ ደግሞ ቀስ በቀስ መሞታቸውን፡፡ ጥያቄው የሚቀጥለው ሟች ማነው የሚል ነው፡፡
በአንቶቭ ቀብር ማግስት ስካር የበለጠ እየታወሰ፣ ሃዘናቸው እየተዘነጋ የሄደበትን ቅፅበት ተጠቅሞ አንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሚከተለውን ጥያቄ ስካር ባጎሳቆለው ገፅታቸው ላይ ወረወረባቸው፡፡
«ቀጥሎ ከዚህ ቤት የሚሞተው ማነው?» አላቸው፡፡ ግራ ሲጋቡ ቀጠለላቸው፤
«ቀጥሎ ማን እንደሚሞት በትክክል ለገመተ ሰው አንድ ጠርሙስ አረቄ እገዛለታለሁኝ» አለና፣ ያቀረበው ጥያቄና ውርርድ እሱን እንደማይጨምር፣ እንደማይመለከተው አይነት ከእነሱ መሃል ሟቹን እንዲጠቁሙት ይጠብቅ ጀመር፡፡ ትንሽ ተደናግጠው ከቆዩ በኋላ፣ ይሉኝታ የተሞላው ገጣሚ ከመሃላቸው፣ በእጅጌው አፉን እየሸፈነ «ኧረ ግፍ ነው! ትላንት አንቶቭ ተቀብሮ ዛሬ አንተ እንደዚህ ዓይነት ነገር ታወራለህ? አይደብርህም እንዴ?» ብሎ ምራቁን ከበሩ ውጭ ተፋ፡፡ ጥያቄው ያስፈራው እሱን ቢሆንም፣ ሟቹ ከእርጥብ አፈር ስር ሆኖ እንዳይሰማውና ተነስቶ እንዳይመጣ የፈራ ይመስል፣ የራሱን አፍ በእጁ በመክደን የጠያቂውን አፍ ዝም ለማድረግ ተወራጨ፡፡
«ለምን ትፈራለህ? እኔ ነኝ የምሞተው ብትል… እና አሁን እዚህ ቤት የተሰበሰበ ሰው በአጠቃላይ አንተ ተከታዩ ሟች መሆንህን ከተስማማበት፣ በህይወት እያለህ አንድ ጠርሙስ አረቄ  ባለቤት ሆንክ ማለት ነው»
«ኧረ ራስህ ሙትና አረቄው ራስህ መቃብር ላይ ይዝነብልህ!» አለ ገጣሚው ግልፍ ብሎት፡፡ ብዙ ራዕይ ያለው ገጣሚ ነው፡፡ የአረቄ ዘመኑን ባያክሉም በቁጥር በዛ ያሉ ግጥሞችን ፅፏል። በቅርቡ የግጥም መፅሐፍ ሊያወጣ እንደሆነ ደጋግሞ ያወራል። ያወራል፤ ጠጪዎቹም ይሰሙታል፡፡ በአረቄ የተጨማደደና  ከፈጣሪ ጠረጴዛ ተገፍቶ የተጣለ፣ የተሰረዘ፣ የተደለዘ ወረቀት ቢሆንም፣ ታርሞ ከዋናዎቹ የድርሰት ገፆች መሃል  አንድ ቀን ተመልሶ እንደሚጠረዝ ተስፋ ያደርጋል። ቀስ በቀስ እየሞተ ቢሆንም፣ አንድ ቀን ግን፣ ቀስ በቀስ ህይወት እንደሚዘራ ያምናል። የሚያሳዝነው፣ ተስፋው ያለው በአፉ ላይ ብቻ መሆኑና አፉ ደግሞ በአረቄ ሽታ የተሞላ መሆኑ፣ እምነቱን ቅዠት እንደሚያደርግበት ስለማይገባው ነው፡፡ አፉ የሚያወራውን ተስፋ ልቡ ማመን ካቆመ ቆይቷል፡፡
ጥያቄውንና ሽልማቱን ያነሳባቸው ልጅ ከሁሉም በእድሜ ወጣት ነው፡፡ ስሙ ንጋት ይባላል፡፡ አረቄውንና የሦስተኛ አመት የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ሳይፎርሽ ይከታተላል ይባልለታል፡፡ ጥሩ ተማሪና ጥሩ ጠጪ ነው፤ እስካሁን፡፡ የመሞትና የመኖር እጣዎቹን በአንድ ላይ ይዞ ቅልልቦሽ ይጫወታል፡፡
ሰይጣንና እግዜርን በአንድ ላይ ይዞ መቀጠል እስከ መቼ እንደሚያዛልቅ አይታወቅም። እሱ ግን ሁለቱንም በአንድ ላይ ይዟል፡፡ ተስፋና ሞትን፡፡ ብርሃንና ጨለማን እየደባለቀ፣ የህይወቱን መንገድ ይጠርጋል፣ አልያም ያቆሽሻል፡፡
«ሰማህ አርቲስቱ!» አለ ንጋቱ ለገጣሚው፤ «በነገርህ ላይ ማንም የማይሞት የለም፤ በምራቅም ሆነ በአረቄ ትንታ ትሞታለህ። በአረቄ የተለከፍን እስከሆንን ድረስ ግን ማን ከመሃከላችን ቀጭኗን  ገመድ ስቶ እንደሚፈጠፈጥ ብንገምትና ያሸነፈውን በድምፅ ብልጫ አወዳድረን ብንሸልም ምን አለበት?»
«እንጃልህ! መንገዴን እኔም ሆንኩኝ አንተ… ማናችንም አናውቀውም፡፡ በእግዚአብሔር ስራ አትግባ» ገጣሚው የአረቄ መለኪያውን አንስቶ በረጅሙ ለጋ፡፡
«እኔ አውቃለሁ» አለ በወሬኛነቱ የሚታወቀው ሰዐሊ ድንገት ጣልቃ ገብቶ። ወሬን በስዕል መግለፅ ባለመቻሉ፣ ስዕል ከሰራም ሆነ ከሸጠ ብዙ አመታት አስቆጥሯል። ከሞያው፣ የሰዐሊ አለባበስና  የፂም አቆራረጥ ብቻ ቀርተውታል፡፡ በግራ ጆሮው ሎቲ ያንጠለጥላል፡፡
«ማነው?» አሉ፤ ሰዐሊው የደረሰበትን ሟች ማንነት ለማረጋገጥ ጓጉተው። ሰዐሊው ወደ ኋላ ለጠጥ ብሎ ሳቀ፡፡ ለአፍታ የፈጣሪን የመግደል ወይንም የማዳን ስልጣን የተላበሰ መሰለ፡፡ ስሙን ጠርቶ «ትሞታለህ» ያለውን ሰው በቅፅበት መድፋት የሚችል መሰለ፡፡ «ስምዖን ነው» አለ ሰዐሊው፡፡
ቤቱ ውስጥ ብዙ ሳቅና ትንታ አመለጠ። ስምኦን የሚለው ስም በሰዐሊው ስም አወጣጥ መሰረት ቢሆንም፣ ሟች የተባለው ግለሰብ ትክክለኛ ስም ፋሲል ነው፡፡ ሰዐሊው ለእያንዳንዱ ጠጪ የሚያወጣው የራሱ ስያሜ አለው፡፡ ስምዖን፣ ጳውሎስ፣ ገማልያል፣ ሉቃስ … ወዘተ፡፡ የሚያወጣላቸው ስሞች በሙሉ ከመፅሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ናቸው፡፡ ስሙን የሚያወጣላቸው ደግሞ ገና የመጀመሪያ ቀን በተዋወቃቸው ቅፅበት ነው፡፡
የስምዖን (ፋሲል) ሟች መሆን በሰዐሊው አማካኝነት ሲመሰከር ቤቱ አንድ ላይ የሳቀው፣ የስሙ ባለቤት አንዴ መጠጣት ከጀመረ ወይንም መጠጣት በጀመረ ቁጥር ማቆም የማይችል  በመሆኑ ምክኒያት ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም ጋር ጠብ ጭሮ አንባጓሮ ፈጥሮ፣ ተደባድቦ፣ መሬት ላይ ተንከባሎ፣ በፖሊስ ተቀጥቅጦ ቤቱ ሁሌ ስለሚገባ ነው። ስምዖንም አሁን አብሯቸው እዛው ጠላ ቤት ውስጥ ይገኛል፡፡ እሱም እንደ ሁሉም፣ ከሁሉም ጋር ሳቀ፡፡ ገና ስካሩ ወደ እብደት አለም አላስገባውም፡፡ ከሁለት ሰዐታት ቆይታ በኋላ ግን አይስቅም፡፡ ሳቁ እሰው ፊት ላይ ምራቁን ወደ መትፋት ይቀየራል፡፡
«ምን ትስቃላችሁ? በትንቢቴ ሁላችሁም ትስማማላችሁ ወይንስ አትስማሙም? ከተስማማችሁ አንድ ጠርሙስ አረቄ ጀባ በሉኝ»
ሳቃቸው ቀጠለ፡፡ ሰዐሊው አናቱ ላይ ያስቀመጣትን ባርኔጣ ወደ ግንባሩና ወደ መሃል አናቱ ይገፋታል፡፡ ከገፋት በኋላ መልሶ ያስተካክላታል፡፡ ወሬ ሲያወራ እጁን በሃይል ያንቀሳቅሳል፡፡ በእጁ የሚያወራ በኮፍያው ደግሞ የሚያደምጥ ይመስላል፡፡
«አይ አንስማማም… እኔ አልስማማም» አለ፤ ከሳይንስ ግቢ አንዱን የሳይንስ ዘርፍ እያጠና ሳለ ራሱን አረቄ ቤት ውስጥ ለአምስት አመታት ተቀምጦ ያገኘ አንድ የአምስት ኪሎ ግቢ የቀድሞ ተማሪ፡፡ ከአርቲስቶች ጋር በፍፁም አይስማማም። የሁሉንም ነገር መፍትሄ የሚፈልገው በሂሳብ አማካኝነት ነው፡፡ ሂሳቡ ሁሉንም ሃሳብ ሊፈታለት ሳይችል ሲቀር በጣም ይቆጣል፡፡ ሲቆጣ ንግግሩ ይተሳሰርና ፣ በጎጃም መንገድ በአማርኛ መጓዝ ጀምሮ የነበረው ሰውዬ አንደበቱን ምፅዋ ገብቶ ያገኘዋል፡፡
«ጎሊያድ ለምንድነው የማትስማማው?» ብሎ ሰዐሊው ጠየቀው፡፡ ጎሊያድ ብሎ ቢጠራውም ከሀገሩ ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ ይዞ የመጣው ስም ግን አብርሓ ነው። ከአብርሓ አጠገብ ዘወትር የማይለይ አንድ ልጅም አለ፡፡ ስሙ አፅብሓ ነው፡፡ ሰዐሊው ግን ዳዊት ብሎ ነው የሚጠራው፡፡
«ፋሲል በተጨባጭ ለመሞት… አይመጥንም» አለ ጎሊያድ፡፡ «ለመሞት አልደረሰም» ማለት እንደፈለገ ሌሎቹ ይገባቸዋል፡፡ አማርኛ ሲያበላሽ ሁሌ ይቀልዱበታል፡፡ እሱም፣ እነሱ በአማርኛቸው ሲኩራሩ «ወሬ፣ የወፍ ቋንቋ» ይላቸዋል፡፡
«በሳይንስ ያልተደገፈና ስሜታዊ ስለሆንክ አልስማማም» አለ ጎሊያድ፡፡
አሁን የተሰበሰቡበት ጠላ ቤት፣ ከሌሎች ጠላ ቤቶች በንፅፅራዊ እይታ እንደ ሸራተን ወይንም እንደ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የሚቆጠር ነው፡፡ ምሁራን፣ ጥበበኞች፣ አሰላሳዮች፣ አስተማሪዎች… ወይንም ነን ባዮች የሚሰበሰቡበት ስፍራ ነው። ነገር ግን ሁሉም በሞያ ዘርፋቸው ስኬታማ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ስኬታማ ቢሆኑማ አይጨማደዱም ነበር፡፡
«ከመሃላችን ቀድሞ ሱስ ያቆመ መጀመሪያ ይሞታል» አለች ብቸኛዋ የሴት አረቄያም እመሃላቸው ተሸጉጣ፡፡ ለቤተኞቹ ልዕልታቸው ነች፡፡
«ልክ ናት» አለ አንዱ ከመሃላቸው ተደባልቆ ቢጠጣም፣ የማህበረሰብ ደረጃው ሊደባልቀው ያልቻለ፣ ቅላፄው ከየትኛው ጠረፍ እንዳመጣው የማያስታውቅ ጎረምሳ፡፡ የተናገረችው ነገር ገብቶት ሳይሆን፣ ብቸኛ ከሆነችው የሴት ሰካራም ፈርጥ ጋር መቀራረብ ስለፈለገ ነው። የሆነ ነገር ለፈለፈ፡፡ ሁሉም ፀጥ ብለው አደመጡት፡፡ በደረጃ የሚለያዩት ባይግባቡም ይደማመጣሉ፡፡ ጎረምሳው ለማስረጃ አንድ ታሪክ ጠቀሰ፡፡
«እኔ አንድ የማውቀው አጎቴ ነበረ፡፡ ሲጋራ ለአርባ አመታት አጭሷል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ዶክተር ሲጋራ እንዲያቆም አስጠነቀቀው። ካላቆምክ ትሞታለህ ተባለ፡፡ አቆመ፡፡ … በአንድ ጊዜ ማቆም ለካ አደገኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በፍጥነት የሚከንፍ መኪናን ፍሬን በአንዴ ግጥም አድርጋችሁ ብትይዙት፣ አሽከርካሪው በመስኮት ነው ተወርውሮ የሚወጣው፡፡ አጎቴም በአንዴ ላቁም ሲል ታመመ…፡፡ ከዛ የሸሚዙ ኮሌታ ሰፋው… ጥቂት ቆይቶ ሞተ…»
«ውሸታም» አለው፤ አብርሓ/ጎሊያድ። «ገና ለገና አያውቁም… ብለህ ነው? ሰው ሲያወራ የሰማኸውን መጥተህ ታወራለህ አንተ!»
ጎረምሳው ግራ ገባው፡፡ ጎሊያድ ተቆጣ። ጎሊያድ ሲቆጣ ዳዊት ይስቃል፡፡ የጎሊያድ ሰሜናዊ ደም ፈልቷል፡፡ የጎሊያድ ደም ሲፈላ የዳዊት (አፅብሓ) ደግሞ ይዝናናል፡፡ ሲዝናና ይስቃል፡፡
«ባለፈው እዛ ውቤ ቤት አረቄ ስንጠጣ፣ አንዱ ጠጪ የሚያወራውን ጥግ ላይ ተወሽቀህ ስትሰማ አልነበረም…?»
ያኛው አመድ በፊቱ ላይ ተነፋበት፡፡ ፊቱን በበርኖስ ፈትገው የለቀቁት መሰለ፡፡ ያስቀዳውን ጨልጦ እየተሳደበ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ወጥቶ ሄደ፡፡
ሴቷ ጠጪ «መጀመሪያ ከመሃላችን የሚሞተው… እስካሁን ሞቶ እንደነበር አምኖ የተቀበለ ነው» አለች፡፡ ልዕልት ‘ተናኘ ወርቅ’ እያሉ እንዲጠሯት ታበረታታለች፡፡ አጭር ልብ ወለድ ትፅፋለችም ይባልላታል፡፡ ከምትፅፈው ይበልጥ ለአጭር ልብ ወለድ የሚሆኑ ገድሎች በወንዶች ላይ ፈፅማለች፡፡
ናጋት አብርሓን በጥያቄ አፋጠጠው፡፡
«በግልፍተኝነት ምክኒያት መጀመሪያ የምትሞተው አንተ ትመስለኛለህ፡፡ አሁን በስድብ ጎሽምጠህ ያባረርከው ሰውዬ ተመልሶ መጥቶ ጩቤ አንገትህ ላይ ቢሰካብህ ሞትክ ማለት አይደለም?»
ጎሊያድ አሰላሰለ፡፡
«በአረቄ አስከሬን የሚሆን በዚህ ጎጆ…ማለቴ ቤት ውስጥ ማነው ነው ጥያቄው! አንተም እንደ አርቲስቶቹ ምን ትወላውላለህ?»
ንጋቱ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ በመሆኑ፣ ሳይንሳዊ ወንድማማችነት ያስተሳስረናል ብሎ አብርሓ ያምናል፡፡
«ወንድሜ ጎልያድ፤ አርቲስቶቹ ምን እናድርግህ?» አለው ወሬኛው ሰዐሊ፡፡
«ምንም አታደርጉልኝም፡፡ ትልቅ ጉድጓድ በምህንድስና ዲዛይን የሚቆፍርልኝ ቢኖር፣ ሁላችሁንም ከትቼ እንዳትወጡ አፉን እለስነው ነበር»
«ሳይንስ ላንተ አረቄ ነው፤ ያውም አረቄ ማውጣት ሳይሆን መጠጣት» አለው ሰዐሊው፡፡
«ይሄንን ተራራና ሜዳ በድማሚት አፈንድቼ…. የምትስሉትንና የምትገጥሙበትን እንዳላሳጣችሁ»
ተጯጯሁ፡፡ ለጥል ተገባበዙ፡፡
በያዥ በገራዥ "ተዉ-ተዉ" ተብለው ሲረጋጉ ንጋቱ አዲስ መፍትሄ አመጣ፡፡
«ሁላችንም አስቀድሞ ይሞታል ብለን የምናስበውን ሰው ስም በቁራጭ ወረቀት ላይ እንፃፍ… የፃፍነውን በዚህ ሲጋራ መተርኮሻ ወረቀት ላይ አጣጥፈን እናስቀምጥ፡፡ በአብዛኛው ሰው የተመረጠው ስም ሽልማቱን ያገኛል» አላቸው፡፡ ተስማሙ፡፡ ወረቀት በጣጥሰው እስኪሪብቶ እየተቀባበሉ ፃፉ፡፡ ከመፃፋቸው በፊት ግን ሁሉም በትካዜ ተመስጠው፣ ጠጉራቸውን እያከኩ ቆዩ፡፡
የሲጋራ መተርኮሻው እንደተቆላ ቡና ከተነቀነቀ በኋላ እየተገላበጠ ተነበበ፡፡ ቁርጥራጮቹ የተለያየ ስም ሰፍሮባቸው ተገኙ። በሁለት የተለያየ ሰው የተመረጠ አንድ አይነት ስም አልነበረም፡፡
«ራሱ በፃፈው ወረቀት ላይ የራሱን ስም ያሰፈረ አለ?» ብሎ ንጋቱ ጠየቀ፡፡ ሁሉም የስካር ቤቱ አባሎች በአሉታ ጭንቅላታቸውን ነቀነቁ፡፡
«የራሱን ስም የፃፈ ቢኖር ኖሮ… የአንደኛ እጣ ተሸላሚ በጠፋበት በፈንታው ይሸለም ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ለጥያቄዬ መልስ ማግኘት አልቻልኩም… ስለዚህ፣ ሽልማቱ በተቀማጭነት ይያዛል» ጠርሙስ አረቄ መግዣውን ብር ወደ ኪሱ መለሰ፡፡
ሲጠጡ ዋሉ፡፡ ሲጣሉና ሲታረቁ፡፡ ተሳክረው፣ ከምሽቱ አራት ሰዐት ላይ በአቶ ባይሳ ዱላ እየተነዱ… ከአረቄ ቤቱ ወጥተው ተበታተኑ፡፡
አብርሓ ቀኑን ሙሉ «ይሄኔ በሳይንሳዊ መንገድ የህክምና ላቦራቶሪ ሄደን ብንመረመር ኖሮ ያለጥርጣሬ ማን ቀድሞ እንደሚሰዋ እናረጋግጥ ነበር» እያለ ሲነተርካቸው ዋለ። እነሱም «መሰዋት ለትግል ነው፤ ለአረቄ ‘መሞት’…‘ማረፍ’ ነው የሚባለው» እያሉ በአማርኛው ሲያሾፉበት ቆዩ፡፡ ቀኑ ሲያልቅ ወደማይቀረው አልጋቸው ሄደው ወደቁ፡፡
 *  *  *
በዛው እለት ምሽት የአቶ ባይሳ የመጨረሻው ወንድ ልጅ ራሱን በገመድ አንጠልጥሎ ሞቶ ተገኘ፡፡ የተንጠለጠለው አረቄ ጠጪዎቹ ሲቀመጡ የዋሉበትን አግዳሚ ወንበር እንደ መወጣጫ ተጠቅሞ ነበር፡፡ በዛች እለት ምን ገጥሞት ወይንም በምን ተስፋ ቆርጦ እንደሆነ ባይታወቅም፣ ከስራ ገበታው አቋርጦ ወጥቶ፣ ሲሰክር ውሎ፣ ማታ አምሽቶ ነው የገባው አሉ፡፡
ጥያቄው በአረቄ ነበር የሰከረው ወይ? የሚል ነው፡፡ ቢያንስ አረቄ ቤት መሞቱ፣ አንድ ጠርሙሱን አረቄ ያሸልመው ይሆን?... አባቱ የአረቄ ሃብታም ናቸው፡፡ አንድ ጠርሙስ አረቄ ቢሸለም ምን ያደርግለታል?
የተጨማደዱት፣ በቀደመው ቀን ሲወራረዱ የዋሉበትን ነገር በቀጣዩም ቀን በሌላ አረቄ ቤት ገፉበት፡፡ አዲሱ ውርርድ ግን ‘ቀጥሎ ማነው የሚሞተው’ ሳይሆን፣ ‘መቼ ነው ለቅሶው አልቆ አረቄ ቤቱ ስራ የሚጀምረው’ የሚለው ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡

Read 864 times