Monday, 21 September 2020 00:00

ግድ የላችሁም፤ ዘፈኖቻችን ይፈተሹ!

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(0 votes)

  ዘፈንና ፖለቲካ እንዳይፈቱ ሆነው የተገመዱ ናቸው - በአገራችን፡፡ ሲመስለኝ፣ ሲመስለኝ፤ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ምስቅልቅል “ዘፈን” ትልቅ ድርሻ ነው ያለው። እንደምታውቁት፣ ለለውጡም የነበረው አስተዋጽኦ ጉልህ ነበር፡፡
ልጨምርበት፡- በብልጽግና እና በኦነግ፤ ብሎም በሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች  መካከል ያሉትን የአመለካከት ልዩነቶች የሚያጦዙት፤ ሌሎች ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ዘፈኖች (ዘፋኞች)ም ናቸው፡፡  በ”መደመር” እና “ባለመደመር” መካከል ያለውን መገፋፋትም በሉት መጓተት - እንዲሁ ጎራ ለይተው “ጃስ!” የሚሉትም እነዚሁ የኪነጥበብ ሥራዎችና የዘርፉ ሰዎች ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ከለውጡ ወዲህ ራሱ እጅግ በጣም ብዙ አዳዲስ “የትግል” ዘፈኖች ለምሳሌ፣ የኦሮምኛ፤ ተመርተው በቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ፣ በዩቲዩብ ወዘተ አማካኝነት ለህዝብ ፍጆታ ቀርበዋል፡፡ የአብዛኛው ለማለት መረጃ ቢያጥረኝም፣ የብዙዎች ዘፈኖች ጭብጥ ነባር ተብለው በሚታውቁት የኦሮሞ ትግል ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያቀነቅኑ ናቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉት የቁጭትና ደም የመመለስ ጥሪዎችም አሉባቸው፡፡ ምን ያህሉ ጽንፍ የረገጡ (ለክሊፕ ጠመንጃ የጨበጡ) ስለመሆናቸው ባላውቅም፤ ታሪክን ታክከው ሙግት በሚካሄድባቸው ርዕሶች ላይ የተሰሩ ለመሆናቸውን ግን እርግጠኛ ነኝ። ከድርድርና ከምክክር ይልቅ ጦርነትን፣ ከመደገፍ ይልቅ መቃወምን ማቀንቀን እንደ ጀግና የሚያስቆጥር ብቻ ሳይሆን ብዙ ላይክና ቪውም የሚያስገኝ በመሆኑም ሳይሆን አይቀርም ያልኳችሁ አይነት ዘፈኖች የበረከቱት፡፡ የሌሎቹም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች የትግል ዘፈኖች ቢፈተሹ ይፋ ያልተነገሩ አዋጆች ይኖርባቸዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ፣ የባህል ሚ/ር፣ በክልል ደረጃ የባህል ቢሮዎች እንዲሁም ሙዚቃ የሚመለከታቸው ሌሎች ጽ/ቤቶችና ማህበራት በጉዳዩ ላይ ጥናት ቢያካሄዱበት ጥሩ ይሆናል እላለሁ፡፡
ዘፈን፣ ለማመን ከምንፈልገው በላይ የሰዎችን አመለካከት ለመቃኘት ከፍተኛ ጉልበት ያለው የኪነጥበብ ዘርፍ ነው - ብዙዎቻችሁ ከኔ ጋር እንደምትስማሙት። በዘፈን ምን የማይባል ነገር አለ? በዘፈን ታሪክ ይነገራል - ታሪኩ ትክክል ይሁንም አይሁንም! በጥሩ መልኩ፣ ባህልም ይስተጋባበታል፣ ለልማትም ጥሪ ይደረግበታል፡፡ ያልተጠቀምንበት ሀብት መሆኑ ይሰማኛል፤ በበኩሌ፡፡
ትዝ ይለኛል፤ አሊ ብራ በ1968 እድገት በህብረት ዘመቻ ላይ በነበርኩበት ወቅት - #እሹሩሩሩ ያ ብርቱካኔዎ፣ ደማ ዋለላ ቤን ሲፉዴን ገላ!”ን እና ሌሎች ኦሮምኛ ዘፈኖችን እንደለቀቀ - ትልቅ የባህል አብዮት ተነስቶ ነበር፡፡ በወቅቱ፣ ቋንቋውን የማያውቁ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ፤ ዳር ከዳር፤ ዜማውን አጥንተው አብረውት ዘፍነዋል - ጨፍረውበታል፡፡ በዚህም ምርጥ ዜማዎችን ያሰማን (የያኔው ወጣት፣ የዛሬው አንጋፋ አርቲስት) - በዜማና በግጥሞቹ ብርታት ህዝቦችን አስተዋውቋል፡፡ ልጨምርበትና፣ አሊ ብራ አንዴ ስለ ማንነቱ፣ አንዴ ስለ ትምህርት፣ አንዴ ስለ ፍቅርና ውበት እየዘፈነ፣ ሙዚቃ ሊኖራት የሚገባትን ከፍታ ያመላከተ ጀግና ነው፡፡ ለዚህ ብቃቱ፤ ባለበት ባርኔጣዬን ከፍ አደርግለታለሁ! የአሊ ዘፈኖች ሲነሱ፤ ሁሌም ወደ አይምሮዬ የሚመጣው ኢብራሂም ሀጅ አሊ ነው - አብሮ አደጉ የሆነው ጋዜጠኛው ሙዚቀኛ። ስለ ሥራዎቹ ሲያወራ ያፈዛል!
ወደ ተነሳሁበት ስመለስ፤ ያለፉት አራት አመታት፤ በተለይም የአሁኑ ዘመን፤ ሁኔታ አስደንጋጭ ነው፡፡ ዘፈኖች በአብዛኛው ፖለቲካ ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ደራሲዎቹም ሆኑ ዘፋኞቹ በአያሌው ወጣቶች በመሆናቸው ደግሞ በአይምሮአቸው የተጫነውን ፍቅርም ሆነ ጥላቻ የሚያቀነቅኑት በእልህ ነው። “አንድ ኢትዮጵያ” የሚሉትም ሆነ “አገሬ ጨቁናኛለች” የሚሉ ዘፋኞች፣ ፍሬ ነገሮችን ከማስጨበጥ ይልቅ ወደ ብሽሽቁ ያደላ ነው አካሄዳቸው፡፡ አንደኛው የሌላውን ብሶት ወይም መልዕክት “እህ!” ብሎ አያዳምጥም፡፡ እንዲሁ፣ ማዶ ለማዶ ሆኖ በመጯጯህ ነው አመታት ያለፉት፡፡ ዘፈኖቻችን ቁርጥ እኛኑ ነው የሚመስሉት፤ መቼም! እኔ የምለው፤ ፖለቲካን ግብ ነው ብሎ ያሳሳተን ማነው?
የዘፈን ቃላት ላይም ትንሽ ለማለት ያህል - ለብዙ አመታት ምንነታቸው በውል ያልታወቀ ቃላት የዘፈን ማጣፈጫ፣ ቡድን ማጠናከሪያ፣ ቅራኔ ማክረሪያ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ዛሬም አየር ላይ ናቸው፡፡ ሞተራቸው ወርዶ መፈታታትና መጠራረግ ከሚያስፈልጋቸው ቃላት መካከል “ነፍጠኛ”፣ “ጠላት፣ ”ባዕድ፣ “ባንዳ” እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ግጥሞቹ በአንድ ወቅት የሆነ ቡድን ላይ ተነጣጥረው የተዘፈኑ፣ በሌላ ጊዜ ልክ እንደ ጠመንጃ ሌላን ቡድን ለማጥቃት የሚተኮሱ ናቸው፡፡ በቃላቱ ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ አይቻልም፡፡  እንኳን በህዝቡ ዘንድ አንድ አይነት ፍቺ ሊኖራቸው ቀርቶ ዘፈኑን የገጠመው ሰውና ዘፋኙ እንኳ የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡
የዘፈን ተደራሽነት ስፋት ሲታሰብ፣ ዘፋኞች ላይ ትኩረት ማድረግ፤ ግጥም ደራሲዎችን ሰብስቦ ማነጋገር፣ ማስተማር፤ እንዲሁም፣ ሀላፊነት እንዲሰማቸው (እንዲወስዱ) ማድረግም ይገባ (ነበር)ል ያሰኛል፡፡ አንዳንዴ ሳስብ፤ አገራችን በዘፋኞች ምላስ ጫፍ ላይ ተንጠልጥላ ያለች ሁሉ ይመስለኛል። በሬዲዮና በቴሌቪዥን፣ እንዲሁም፣ ፌስቡክን ይዞ በበርካታ ሶሻል ሚዲያ አማካኝነት የሚያጋጥሙን የሀሳብ ግጭቶች፤ “ዘይትና ውሃ” የሆኑ አመለካከቶች፤ በግጥም መልክ ቀርበው፣ በዜማ ተውበው አድማጭ ተመልካችን “ሸፍት ሸፍት አለኝ” ሲያሰኙ ነው ውለው የሚያድሩት፡፡ ደግነቱ፣ ወጣቱ እንዳይሰማማ፤ የጎሪጥ እንዲተያይ፤ ሙላቱን ሳይሆን ጉድለቱን እንዲያጠና ሆኖ የተሰራ በመሆኑ፤ ሁሉም በራሱ ቋንቋ ዘፈኖቹን በተረዳበት መንገድ ይረገረጋል እንጂ ጣት ቀስሮ፤ “ምን አልክ አንተ!?” አይባባልም። አንዱ የሌላውን የሚሰማ ቢሆን ኖሮማ ካለንበት ሁኔታም የከፋ ችግር ውስጥ ልንወድቅ እንችል ነበር - ብዬ አስባለሁ። ጎበዝ፤ ያጋልኩትን ላብርድ፡፡ በቀጣይ አንቀጾች ደግሞ ገራገሩን እያነሳሳሁ፣ ዘፈን በታሪካችን ውስጥ ያለውን ሥፍራ ላስታውሳችሁ፡፡  
በአድዋ ጦርነት ወቅት ዘፈኖች - ቀረርቶና ሽለላ፣ ጌረርሳ (ኦሮምኛ)) እንደ ልዩ ትጥቅ ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡ ያኔ ወጣት ወደ ጦርነት የሚሄደው “ለአቅመ ጦርነት ደርሻለሁና አዝምቱኝ” ብሎ ወላጆቹንና አዝማቾችን ለምኖ ነበር፡፡ ወጣቱ፣ ከአገር በፊት ልሙት ብሎ ወደ ዳር ድንበር የሚገሰግሰው በውዴታ ብቻ ሳይሆን በልመናም ነበር ማለቴ ነው፡፡ እስቲ ይህቺን ግጥም አጣጥሙልኝ፡-
“አስከትለኝ - ልጅ ነው አትበልና
ግንድን የሚያያይዝ - ጭራሮ ነውና! …" ኧ ተተተተተ! ማለት አሁን ነው! ያስብላል አይደል? ቀጣዩን ደሞ ተመልከቱልኝ! “ትጥቅ የለኝም ብሎ መቅረት የለም፤ ትጥቅማ ጣሊያኖቹ ይዘው (ልን) መጥተዋል!” ነው መልዕክቱ፡፡
“ጣሊያን ቢደነድን ቢሰፋ ደረቱ
እንመልሰዋለን በገዛ ጥይቱ!” … (ፓ!)
በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ጊዜም ቀስቃሽ ዘፈኖች ነበሩ፡፡ እነ ጥላሁን ገሠሠ፣ እነ አለማየሁ እሸቴ፤ ለምሳሌ፤ በእነ መንግሥቱ ነዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሰሞን፤ እንትን ብለው የዘፈኑት ፖለቲካ ነው ተብሎ (ወይም ስለነበረ) ታሰሩ፤ ተቀጡበት ሲባልም ሰምተናል፤ አንብበናልም፡፡ እንዲህ እንደ አሁኑ፣ ፍጥጥ ግጥጥ ያሉ ባይሆኑም የብሶት መግለጫ ዘፈኖች ነበሩ ማለቴ ነው፡፡ አይ ጊዜ! አንዳንዶቹኮ፣ “ፖለቲካ” የተባሉት ቅኔ አዋቂ - ወርቅ አቅላጭ፣ ውስጠ ወይራ ፈላጭ ተፈልጎ የሚያጎላቸው ናቸው እንጂ ግልጽ የነበሩ አይደሉም፡፡ “ኡ ኡታ አያስከፋም፣ ሲለዩ ተዋዶ … ከዚህ የበለጠ ከየት ይምጣ መርዶ?” በሾርኔ የሠራዊቱን ብሶት እንዲገልጥ ታስቦ የተዘፈነ ነበር የሚሉን ውስጥ አዋቂዎች ናቸው፡፡ (እህህህህህ!)
ከሙገሳ ዘፈኖች መካከል ጃንሆይ ስለ ራሳቸው ያስዘፈኑትን ላቅምሳችሁ፡-
“ኃይለሥላሴ ሀዋርያ
የሰላም መሪ ባለሙያ!
ባንዲራውን ይዞ የሚገሰግሰ”ው
አንድም ንጉሥ የለም - እሱን የሚደርሰው!” ልብ አላችሁልኝ? እንዲህም በማሰኘት ነው ጃንሆይ፤ የንጉሦች ንጉሥ (ንጉሠ ነገሥት) መሆናቸውን ሲያስጠኑን የኖሩት - በመዝሙር ክፍለ ጊዜ ሳይቀር፡፡  
አሁን ደግሞ ፈገግ የምትሉበትን ልንገራችሁ፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን ወርደው እያለ፤ ነገር ግን የደርግ መንግሥት በኦፊሴል ሳይተካ፤ ድምጻዊ አያሌው መስፍን ያወጣው “ጉንፋን” የሚል፤ ለውጥ አቀጣጣይ፤ ዘፈን ነበር፡፡ እነሆ ግጥሙ፡-
“የጥንቱ ህመሜ የአምናው ኢንፊሉዌንዛ
ሊለቀኝ ነው መሰል? ዘንድሮ እንደዋዛ! …" በመሃከል ያሉ ስንኞች፤ ወደ ፈረንጅ አገር ገንዘብ አከማችቶ፣ ሊሸሽ ሲል ተያዘ … (ንንንንንቶ) ምናምን ብሎ ያጋልጣቸውና፤ ዘፈኑን እንዲህ ብሎ ይዘጋል፡-
“አይመልስህ እንጂ ከተመለስክማ
ይህን ተናግሬ ምን ተረፍኩ እኔማ?” (ሃ! ሃ! ሃ!) አያሌው ይህን ዘፈን ሲለቅ፤ ወደ ደርግነት ያልተቀየረው ሰራዊት፣ ጃንሆይን “አንቱ” እያለ ነበር የሚያነጋግራቸው፡፡ ለውጡ ግን የማይቀር መሆኑ ያስታውቅ ነበር፡፡ ለዚህ ነው “አይመልስህ እንጂ …!” ያለው፤ አራዳው አያሌው - “ጃንሆይ ድንገት ወደ ስልጣናቸው ይመለሱ ይሆን?; ብሎ ፈርቶ! ፍጥነቱን ግን አያችሁልኝ አይደል? ይኸው ዘፋኝ፣ ቀደም ሲል ለ80ኛ ዓመት ልደታቸው የለቀቀው ዘፈን ነበረው፤ እንዲህ የሚል፡-
በኤጄርሳ ጎሮ ብርሃን ወረደ
ሀምሌ አስራ ስድስት ቀን ጠቅል ተወለደ!
80ኛውን ልደት በዓሉን
እናከብራለን አብረን ሆነን!” ትዝብቴ ይህ ነው፡- ዘፋኝ ሁሉ በፈለገው ጊዜ የፈለገውን ይላል - ተጠያቂነት የለበትም፡፡ በአድማጭ ዘንድ የሚፈጠረው ስሜት ግን አገዳዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ እንድታውቁልኝ የምፈልገው፤ አላማዬ ግለሰብ ዘፋኞችን ነጥሎ መውቀስ አይደለም፡፡ ላድርገው ብልስ አያሌው በአገር ጉዳይ ምኑ ይወቀሳል?
"ዘር መለየት ይቅር አንድ ነው ደማችን!" ብሎ የዘፈነ አገር አቃፊ አርቲስት ነው፡፡
ደርግ ዙፋኑን ከተቆናጠጠ በኋላ ስለነበሩ ዘፈኖችማ ስንቱ ይወራል? የደርግ በካሪ መፈክር የነበረው “ኢትዮጵያ ትቅደም!” ፈጣን ተቀባይነትን ያገኘው በዜማ ተከሽኖ በመሰራጨቱ መሆኑ ለከረረ ክርክር የሚበቃ “ሀቅ” አይሆንም ብዬ አምናለሁ፡፡
“ያለ ምንም ደም
እንከኗ ይውደም
በቀና መንፈስ - ኢትዮጵያ ትቅደም!”
ተማሪ፣ አስተማሪ፣ ወዛደር ገበሬ
በህብረት እናንሳ (??) የአገሪቱን ፍሬ!" … በሲዳምኛም፤ ይኸው መልዕክት - “ኢትዮጵያ ሎጲቶ አልቢራ” ተብሎ መዘፈኑ ትዝ ይለኛል፡፡
“ኢትዮጵያ ትቅደም!” ትልቅ የምስራች ነጋሪ፣ ትልቅ ተስፋ ሰጪ አዋጅ ነበር። ይታያችሁ፤ ደም ሳይፈስ እንከኖቿ ወድመው፣ ዜጎች በቀና መንፈስ ተጋግዘው ኢትዮጵያችን ስትቀድም፡፡ ይህን ዘፈን ሲሰማ የወጣቶች ልብ በደስታ ይንዷዷ ነበር - የኔን ጨምሮ፡፡ ያኔ “ኢትዮጵያ” ነበር ያለችው - ከነችግሮቿ፡፡ በብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ተለይታ አትጠራም ነበር፡፡
አለፍ፣ አለፍ ልበልና … ከዚያ ደግሞ፣ የእድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ  ሰሞን (መሰለኝ) “ተነሳ ተራመድ!” መጣ - ለአገራችን ልማት የተሟላ ፕሮፖዛል የያዘው መዝሙር (ሀሁ - ኢትዮጵያ ትቅደም)!  የአዝማቹ ግጥሞች መልዕክት፡- “እኛ ተነስተን ከተራመድንና ክንዳችንን ካበረታን፣ ለአገራችን ብልጽግናን እናስገኛለን፤ ለወገናችንም መከታ እንሆናለን” የሚል ነው፡፡ እኔ የምለው? “ብልጽግና” ከ45 ዓመታት በፊት፣ የደርግም ህልም ነበር ማለት ነው! መቼ ይሆን፤ ይሄ “ህልም!” እውን የሚሆነው? ለማንኛውም እነሆ ግጥሙ፡-
ተነሳ ተራመድ - ክንድህን አበርታ
ለአገር ብልጽግና - ለወገን መከታ!
እንበል ሀሌሉያ - ታላቅ የምስራች
ከብዙ እስር ዘመን - ኢትዮጵያ ተፈታች…
ወንዞች ይገደቡ - ይዋሉ ለልማት
በከንቱ ፈሰዋል - ለብዙ ሺ አመታት!
ይውጡ ማዕድናት - ለአገራችን ጥቅም
ህዝቧም ታጥቆ ይስራ በተቻለው አቅም … ሀሁ - ኢትዮጵያ ትቅደም … እያለ፣ እያለ ይቀጥላል፡፡
… አብዮቱ “ያለምንም ደም” ብሎ ቢጀምርም - አገሪቱ ደም በደም ለመሆን ውላ አላደረችም፡፡ ለስልጣን የሚደረግ ፉክክር ብዙ ጭንቅላቶቸን አጋጨ፣ አፈጣፈጠ፡፡ መንግሥትን በሚደግፉና መንግሥትን በሚቃወሙ ቡድኖች መካከል መታኮስ መጣ፡፡ ለአገራችን ፖለቲካ እንግዳ የነበሩት ፓርቲዎች (ኢሕአፓ፣ ሰደድ፣ መኢሶን፣ ኢጭአት፣ ወዝ ሊግ፣ ምናምን) እርስበርሳቸው ተነቃቀፉ፣ ተጨፋጨፉ። አገርም በውጪ ወራሪ ተወጋችና ደማች። … “ወራሪን እንደግፍ? ወይስ የአገርን ሉዓላዊነት እናስቀደም?” በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ሳይስማሙ ቀርተው የተገዳደሉ ፓርቲዎችም ነበሩ፡፡ እዚህ ላይ፣ አሁን ያሉ ነገሮች ያኔም እንደነበሩ ልብ ይሏል። “የጠላትህ ጠላት ወዳጅህ ነው” ብለው ለጊዜው ህብረት ፈጥረው የነበሩ ቡድኖች የጋራ ጠላት ወደሚሉት ኃይል አቅጣጫ አብረው ሲጓዙ ስትራቴጂያዊ ወዳጅ ብለው ያሰቡት “ትንሹ ጠላት” ከመንገድ ያስቀራቸውም አሉ፡፡ … በዚያው የታሪክ ወቅት፣ አካባቢያቸውን ነጻ ለማውጣት የሚዋጉ ሀይሎችም ነበሩ - የትግራይ ህዝቦች ነፃነት ግንባር፣ የኤርትራ ህዝቦች ነፃ አውጪ ግንባር፣ የምዕራብ ሶማሌ (ሶማሊ አቦ) ነፃ  አውጪ (ነበር መሰለኝ) … እያለ ይቀጥላል፡፡ ታዲያ፤ ሁሉም ፓርቲዎች፣ ነፃ አውጪዎች የየራሳቸውን ህዝብ መቀስቀሻ፣ አባሎቻቸውን ማጀገኛ ዘፈኖች ነበሯቸው፡፡ ትዝ ይለኛል፤ በ1970 ሶማሌ አቦ የሚባለው ቡድን የሬዲዮ ጣቢያ ከፍቶ ያስተላልፍ በነበረ ጊዜ - አንድ በጥገኝነት አብሮን ይኖር የነበረ ሰው (የአማርኛ አቻ ትርጉሙ - “አርነት ሆይ ወተት ነሽ - ያለ ጠመንጃ አያገኙሽ;)፡-
“ቢሊሱማ ያ አነኒ
ቀዌ መሌ ኢናርገኒ!”
የሚል የኦሮምኛ ዘፈን ሲሰማ እንዴት፣ እንዴት ያደርገው እንደነበር መቼም አልረሳም፡፡ በርከክ ይልና ብትሩን፤ ሲለው ወደኔ፣ ሲለው ወደ ሰማይ ደግኖ በምናቡ ይተኩስ ነበር፡፡ በቃ እንደዚያ ነው የሚያደርገው፤ ስሜት ቀስቃሽ ዘፈን። ጭንቅላቱን ለአንድ ሀሳብ (ፓርቲ አላማ) ያስገዛ ሰው፤ እሱን የሚወክሉትን ዘፈኖች ሲሰማ አበረታች ዕፅ የወሰደ ያህል መነቃቃቱ፣ በስሜት መንሳፈፉ፣ መጦዙ አይቀርም፡፡  
ልቀጥል፡፡ ትግራይን ነፃ ለማውጣት ተጋድሎ ያደረጉት ወጣቶችም እጅግ ብዙ የቅስቀሳ ዘፈኖች እንደነበሯቸው እናስታውሳለን፡፡ እነ ብአዴን - ም ገበሬውን አንደርድረው ወደ ጫካ የሚያስገቡበት ድራማዊ ዘፈኖች ነበሯቸው፡፡ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ራሱ ሰምተን የወደድናቸው ብዙ የድል ዝማሬዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፣  አቶ ህላዌ ዮሴፍ ግጥሙን የፃፉት ይህ የሚያባባ ዘፈን አይረሳም፡-
“እንዳያልፉት የለም - ያ ሁሉ ታለፈ
ታጋይ የህዝብ ልጅ - በደሙ፣ በላቡ ደማቅ ታሪክ ፃፈ!” … በበኩሌ፣ መዝሙሩን እነዚያ የወጣትነት ዘመናቸውን በረሃ አሳልፈው የመጡ የፓርቲ ከያኒያን፤ ጎፈሬያቸውን ችቦ አስመስለው፣ ቁምጣ፣ ሸበጥና ሽርጣቸውን “መለያ እንዳደረጉ” ሲዘምሩት፣ እንባዬ በጉንጬ ላይ ኮለል ብሎ ነበር የወረደው፡፡ “ይኸኔ በየጉድባው የወደቁ ጓዶቻቸውን ያስቡ ይሆናል” ብዬ ነው ራሴ በፈጠርኩት ሀሳብ ለእንባ የበቃሁት፡፡ አቤት የባከኑ ዜማዎች ብዛታቸው! በማን ይሆን፤ መቼ ይሆን፤ ሪሳይክል የሚደረጉት?
“ወደ ገደለው” ልመለስ፡- ግድ የላችሁም፣ ዘፈኖቻችን ይፈተሹ፡፡ እንግዲህ ሁሉም አገር የራሱ ፖለቲካዊ ባህሉን የሚያራምድበት መንገድ ይኖረዋል አይደል? በኛ አገር ዘፈን ከባድ (ጅምላ ጨራሽ) መሳሪያ ነውና ነው ይፈተሽ - ከተቻለ አንዳንዱም ይምከን - እላለሁ፡፡ በድጋሚ እላችኌለሁ፡- ዘፈን የሰዎችን አመለካከት ለመቃኘት ከፍተኛ ጉልበት አለው፡፡ ባለፈው ስርዓት ላይ ካነጣጠሩ የትግል ዘፈኖች የተወሰኑትን አንዴ አናስብ እስቲ፡- ፋሲል ደሞዝ ከጎንደር “አረሱት!” እያለ በአንድ ፊት አንጀት የሚያርስ፣ በሌላ ፊት አንጀት የሚጠብስ የእንጉርጉሮ ጥይት ተኝቶ እነ እንትና ላይ እያርከፈከፈ አማራውን በስሜት ሲንጠው፤ ወዲህ መሀል፣ መሃሉን ቴዲ አፍሮ “አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?” እያለ ከልጅ እስከ አዋቂ (የማንነት ጥያቄን ድንበር ጥሶ) አስተቃቅፎ ያስጮኽ ነበር፡፡ ቆፍጣናው ሃጫሉ ሁንዴሳም በቋንቋው “… ጂራ ጂራ፣ ጂራ; (አለን - ግን አለን አንባልም፣ ለስሙ ነው ያለነው እንደ ማለት) አፉን ከድኖ ሲያንጎራጉር እንዳልቆየ … በህይወቱ ቆርጦ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ መድረክ ላይ ወጥቶ  (የመንግሥት ሹማምንት የፊት ወንበር ይዘው እያዩ፣ እየሰሙት) ከዳር እስከ ዳር እየተውረገረገ፤ እንጣጥ ብሎ እየዘለለ፤ ቤት ሳይሆን ቤተ መንግሥትን በሚመቱ ግጥሞቹ ታዳሚውን በደስታ አስፈነደቀ (መድረኩን የጦር ሜዳ አድርጎ ለውጡን በጥበብ ሲመሩ የነበሩ ሀይሎችን) አስደነገጠ፡፡ ይህን ልብ ያለ በዘፈን አይቀልድም! ዘፈን ውስጥ አገርን የሚበትን ወይም አንድ የሚያደርግ አቅም አለ፡፡ ዘፋኝም አንድ ሰው አይደለም - ከብዙ ሚሊዮኖች ጋር መዛመድ የሚችል፤ ሚሊዮኖችን በፉጨት ሊያዘምት፣ ከዘመቻ ሊያስመልስ የሚችል ነው፡፡ ስለዚህ፣ ዘፈኖቻችን ይፈተሹ፣ የዘፈን ገጣሚዎችና ዘፋኞቻችንም ለውይይት ይጠሩ በማለት ሀሳቤን እቋጫለሁ፡፡ የዘፈን ምርጫ አለኝ - የጥላሁን ገሠሠ፡-
ያቅታል እንጂ - ቁምነገር መስራት
በጣም ቀላል ነው ሰውንስ ማማት!
ቸብ፣ ቸብ፣ ቸብ፣ ቸብ!

Read 5237 times