Saturday, 26 September 2020 00:00

ግርታ የሚፈጥረው የአሜሪካ ምርጫ

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

  በዓለም የሀገር አስተዳደር ዘይቤ ውስጥ ጎልተው የሚታወቁት ሁለት አይነት ሥርዓቶች ናቸው። የሕዝብ ተወካዮች (ፓርላማ) እና ፕሬዚዳንታዊ አስተዳደር የሚሏቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች አስተዳደርን፤ እንግሊዝ ጣሊያንና ሕንድን የመሳሰሉ ሃገሮች ይጠቀሙበታል። በዚህ የአስተዳደር ዘይቤ ወሳኝ ሥልጣን ያለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ነው፡፡ በ1987 ዓ.ም በወጣው የአገራችን ሕገ መንግሥት መሠረት "ጠ/ሚኒስትሩ፤ ርዕሰ መስተዳድር፥ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው።” እኒህ ሰው የአገሪቱ መሪ ለመሆን በመኖሪያ አካባቢያቸው ባለ የምርጫ ክልል ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። አባል የሆኑበት የፖለቲካ ድርጅት የምክር ቤቱን አብላጫ ወንበር ከተቆጣጠረ፣ የዚያ ፓርቲ መሪ፣ የጠ/ሚኒስትርነቱን እርካብ ይቆናጠጣል።  
ከዚህ አንጻር ጀርመን፥ ጃፓንና እስራኤልን የመሣሠሉ ሀገሮች ፕሬዚዳንትና ንጉሥ ቢኖራቸውም፣ በአብዛኛው የሚታወቁት ግን ጠ/ሚኒስትሮቻቸው ናቸው፡፡ ለዚህም የጀርመኗ አንገላ ሜርክል፥ የእስራኤሉ ቤንያሚን ናታንያሁና የጃፓኑ ሺንዞ አቤ ይጠቀሳሉ፡፡ ርዕሰ ብሔሮቹ በተለይም መሣፍንታዊ ባህል ባላቸው እንግሊዝ፥ ጃፓንና ሰሜን አውሮፓ፣ የሀገር አንድነት ምልክት ሆነው ከመታየታቸው በተጨማሪ፣ የአመራር ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ፣ ምክር ቤትን የመበተንና ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ጊዜያዊ ጠ/ሚኒስትር በመሾም፣ የፖለቲካውን ትኩሳት የማብረድ ሚና ይጫወታሉ፡፡  
በአንፃሩ ደግሞ ፕሬዚዳንታዊ የሚባለውን አስተዳደር በመከተል በዋናነት አሜሪካ ተጠቃሽ ስትሆን ሩሲያ፥ ፈረንሣይ፥ ናይጄሪያና የመሣሠሉት ሀገሮችም ይጠቀሙበታል። በእነዚህ አገራት አብዛኛው ሥልጣን ያለው በፕሬዚዳንቱ እጅ ሲሆን እንደ ሀገሩ የአስተዳደር ባህል ጠቅላይ ሚኒስትር ያላቸው አገራት አሉ፤ የሌላቸው ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ይኖራቸዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ አመራረጥ በአሜሪካ
በዚህ ፅሁፍ የምናተኩርበት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አመራረጥ፣ በስኬቱ ተወዳዳሪ የለውም። ሥርዓቱ ከእንግሊዝ ነፃነቷን ካወጀችበት ከ1768 ጀምሮ ነው በሥራ ላይ የዋለው፡፡ ይህ አካሄድ ከዕንከን የፀዳ ነው ባይባልም፣ ሀገሪቱን ግን የዘመናዊነት ምሳሌ አድርጓታል።
በመጪው ጥቅምት ወር ማገባደጃ ላይ አሜሪካውያን በታሪካቸው ለ58ኛ ጊዜ መሪያቸውን ይመርጣሉ፤ ድምፅ መስጫ ጣቢያ በመሄድ አለያም በፖስታ! ለዘንድሮ ውድድር የቀረቡት ለአራት ተጨማሪ አመታት አሜሪካን መምራት የሚፈልጉት የኒው ዮርኩ ዶናልድ ትራምፕና በቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት የደላዌር ግዛቱ ሴናተር ጆ ባይደን ናቸው።
ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚፈስበት የአሜሪካ ምርጫ፤ የራሱ እንግዳ የሆኑ ባህርያት አሉት። ሲጀመር ዜጎች በቀጥታ ፕሬዚዳንቱን አይመርጡም። ይህ እንዴት ሆነ? ሰባት አንቀፆች ያሉት የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ ስለ ምርጫ በሚጠቅስበት አንቀፅ ሁለት የመጀመሪያ ክፍል ላይ “እያንዳንዱ ክፍለ ግዛት በሕዝብ ተወካዮችና ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ባሉት መቀመጫዎች ቁጥር ልክ የመራጭ ጉባኤ አደራጅቶ ፕሬዚዳንት ያስመርጣል” ይላል።
በዚህም መሰረት እያንዳንዱ ግዛት በሸንጎ (ኮንግረስ) ውስጥ ባለው ውክልና ልክ መራጮች አሉት። ያገሪቱ ሸንጎ ባሉት ሁለት ምክር ቤቶች አወቃቀር ምክንያት ማንኛውም ክፍለ ግዛት ከሶስት በታች መራጭ ሊኖረው አይችልም። ምክር ቤቶቹም፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፦ አባላቱ በየሁለት አመቱ ይመረጣሉ። የተወካዮቹ ቁጥር በግዛቶቻቸው በሚኖረው ሕዝብ ብዛት ይወሰናል። ካሊፎርኒያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ስላለው በተወካዮች ምክር ቤት 53 መቀመጫ ይዟል። ትንሹ ደግሞ ዋዮሚንግ ነው። የሕዝቡ ብዛት ከግማሽ ሚሊየን ብዙም ስለማይዘል በአንድ መቀመጫ ተወስኗል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላላ አባላት 435 ሲሆኑ አንድ ተመራጭ 700 ሺህ ሰዎችን እንዲወክል ታስቦ የተሰላ ነው። ያን ያህል የሕዝብ ብዛት የሌላቸው ግዛቶች፣ የግድ አንድ ተወካይ ይኖራቸዋል። ርዕሰ ከተማይቱ ዋሺንግተን ዲሲ ከሜሪላንድና ከቨርጂኒያ ግዛቶች መሬት ተሸንሽና የተዋቀረች በመሆኗ ልዩ አስተዳደራዊ ክልል ናት። ስለዚህ ድምፅ አልባ ናት። በምርጫ ወቅት ብቻ ሶስት የመራጮች ድምፅ አላት። 

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሰኔት) ፦ ጠቅላላ አባላቱ 100 ሲሆኑ ትንሽ ትልቅ የለ ሁሉም ሁለት ተወካዮች አሏቸው። ሀገሪቱ 50 ግዛቶች ስላሏት የአባላቱ ቁጥር ዕቅጩን 100 ነው። የዚህ ምክር ቤት አባላት ለስድስት አመታት ያገለግላሉ፥ በተጨማሪም የሚወክሉት የምርጫ አካባቢን ሳይሆን ግዛቶቻቸውን በመሆኑ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት የበለጠ ክብርና ተሰሚነት አላቸው። የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ግዛቶች ትናንሾቹን እንዳይጫኑ ውክልናውን ለማመጣጠን የተዘረጋ ሥርዓት ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ግዛት በምክር ቤት ቢያንስ አንድ፣ በሕግ መወሰኛ ደግሞ ሁለት ተወካይ ስላለው፣ ምን ጊዜም የተወካዮቹ ቁጥር ከሶስት ሊወርድ አይችልም። ይህ ወደ መራጮች ጉባኤ ይወስደናል።
የመራጮች ጉባኤ (ኤሌክቶራል ኮሌጅ)
የምርጫ ጉባኤ እሳቤው የመጣው ብዙ ሕዝብ ያላቸው ግዛቶች አነስተኞቹን እንዳይደፈጥጡና ሀገሪቱ እየተሰራች በነበረበት በ1780ዎቹ የፊላዴልፊያው የሕገመንግሥት ማርቀቂያ ክርክር ላይ ወደ ስምምነት ለመድረስ የተጠቀሙበት የድርድር ፖለቲካ ውጤት ነው።
የአስመራጮቹ ሁኔታ ግራ የሚያጋባ ይመስላል። በየአራት አመቱ የፈረንጆች ሕዳር በገባ ከመጀመሪያው ሰኞ ቀጥሎ ባለው ማክሰኞ ይካሄዳል (አይ ቀን አወሳሰን!)። በዛን ቀን ዜጎች ድምፅ የሚሰጡት በቀጥታ ለመረጡት ዕጩ ሳይሆን እነሱ የፈለጉትን ሰው ለሚመርጥላቸው ወኪል ነው። “እኔ የምፈልገው እገሌን ነውና እሱን ምረጥልኝ” ነው የሚሉት። ብዙ ሰዎች የማይረዱትም ይህን መሰሉን አካሄድ ነው። በቀጥታ ፕሬዚዳንቱን መምረጥ እየተቻለ የምን ዙሪያ ጥምጥም ነው? አሰራሩን ከመተቸት አልፈው ሀገሪቱ የሕገመንግሥት ማሻሻያ እንድታደርግ የሚጠይቁ እንዳሉ ሁሉ የሚደግፉትም በርካቶች ናቸው። የደጋፊዎች መከራከሪያ ፦  ላለፉት 230 ዓመታት ያላንዳች መስተጓጎልና ውዝግብ፣ አገሪቱ በየትኛውም የዓለም ክፍል ተደርጎ የማያውቅ የሥልጣን ሽግግር እንድታካሂድ አስችሏታል፤ ትብብርንና ሰጥቶ የመቀበል ፖለቲካን አጠናክሯል፤ ትንንሾቹ ግዛቶች እንደ ትልልቆቹ ሁሉ ተሰሚነት እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን አመቻችቷል።
በሌላ ጎኑ ግን በዚህ አይነቱ ሥርዓት ሳቢያ፣ በሀገሪቱ ታሪክ ለአምስት ጊዜ ያህል፣ አብዛኛው ሕዝብ የመረጠው ሳይሆን አናሳ ቁጥር ያገኘው እጩ፣ ፕሬዚዳንት ሆኗል። ባለፉት ሃያ አመታት እንኳ ሁለት ጊዜ አብላጫ ሕዝብ የመረጠው ዕጩ ተሸንፏል። የዛሬ አራት አመት ሂላሪ ክሊንተን ዶናልድ ትራምፕን በሶስት ሚሊየን ድምፅ ቢበልጡም ቅሉ፣ በዚሁ አሰራር ሳቢያ በመሸነፋቸው በታሪክ የመጀመሪያዋ አሜሪካዊት ፕሬዚዳንት ከመሆን ተደናቅፈዋል።
ታዲያ በሶስት ሚሊየን ድምጽ እየበለጡ መሸነፋቸው እንዴት ዲሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል? ዲሞክራሲያዊ የሚያሰኘው ነገር የአብላጫና የአናሳ ጉዳይ ሳይሆን ተወዳዳሪዎቹ ለተስማሙበት የጨዋታ ሕግ መገዛታቸው ነው። ለዚህም ነው ሂላሪ ለትራምፕ ስልክ ደውለው መሸነፋቸውን ተቀብለው፣ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
የምስጢሩ ቁልፍ
የሆነስ ሆኖ ምንድነው የመራጮች ጉባኤ? ጉባኤው እንደ ሀገሩ ሸንጎ ሁሉ 535 በተጨማሪ ደግሞ የዋሺንግተን ዲሲ አስተዳደር 3፣ በድምሩ 538 አባላት ያለው ተቋም ነው። አንድ ዕጩ በፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ 270 ድምፅ ማግኘት አለበት። ይህ ጉባኤ በየግዛቱ እንደ ሕዝቡ ቁጥር ተመጥኖ የተሸነሸነ ሲሆን ትልልቅ የሚባሉት ካሊፎርኒያ  55፤ ቴክሳስ 38፤ እንዲሁም የኒው ዮርክና የፍሎሪዳ ጉባኤዎች እያንዳንዳቸው 29 አባላት አሏቸው። ትንንሾቹ ደግሞ ዴላዌር፥ ዋዮሚንግና ቨርሞንትን የመሣሠሉት ዝቅተኛው ሶስት አባላት አሏቸው። በዚህ ደንብ መሰረት፤ በተመጣጣኝ ውክልና ድምፅ ከሚያከፋፍሉት ሜይንና ኔብራስካ በስተቀር በ48ቱ ግዛቶች አብላጫ ድምፅ ያገኘ አሸናፊ ነው።


ሰንጠረዡን ለማብራራት ያህል አሸናፊና ተሸናፊ የሚለው መላ ምት ከመሆኑ ውጪ ሌላው በሙሉ እውነታ ነው። እርግጥ ጥሩ በተባለ ጊዜ እንኳ ድምፅ መስጠት ከሚችለው ከ60 በመቶ በላይ ባይወጣም፣ ምሳሌው ግን የግዛቶቹ ነዋሪዎች ሁሉ እንደሚመርጡ ታስቦ የቀረበ ነው። ለምሳሌ ቴክሳስ ካለው 29.1 ሚሊየን ሕዝብ 15 ሚሊየን ለአሸናፊው፣ ቀሪው 14.1 ሚሊየን ለተሸናፊ ቢሰጥ፣ አሸናፊው የምርጫ ጉባኤውን 36 ድምፅ ጠቅልሎ ይወስዳል። ይህ ማለት 14.1 ሚሊየን ሕዝብ በዜሮ ወጣ ማለት ነው። ከሰንጠረዡ እንደሚታየው አንድ ዕጩ ወሳኝ በሆኑት 12 ግዛቶች የሚኖሩ ወደ 97 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ከመረጡት ተፎካካሪው በተቀሩት 38 ግዛቶች ያሉትን ጨምሮ ከ200 ሚሊየን ሕዝብ በላይ ድምፅ ቢሰጠው እንኳ የሚሰማው የለም። የትም ፍጪው 270ውን አምጪው!
ሩብ በሚሆነው ሕዝብ ብቻ ተመርጦ ምርጫ ማሸነፍ የሚቻልበት ዕድል እንዳለ ዩቲዩብን በመሣሠሉ መድረኮች እየቀረቡ ስሌቱን የሚያሳዩ አሉ። እርግጥ ይህን ያህል የከፋ ነገር እስከ ዛሬ ባይገጥምም፣ ተቺዎች ግን እነዚህን መላ ምቶችን እያስቀመጡ ሥርዓቱ ፀረ ዲሞክራሲያዊ መሆኑን ለማሳየት ይጠቀሙበታል። ለዚህም ይመስላል ማይክል ሙርና ዴቪድ ዋሰርማን የተባሉ የፖለቲካ ተንታኞች፤ በቀጣዩ ሕዳር ምርጫ ትራምፕ በአምስት ሚሊየን ድምፅ ተበልጠው በድጋሚ ሊያሸንፉ ይችላሉ የሚሉ መላ ምቶችን መሰንዘር የጀመሩት።
በምርጫ ወቅት ዕጩዎች በርካታ ጊዜአቸውንና ገንዘባቸውን የሚረጩት ጥቂት ሞገደኛ ግዛቶች ላይ ነው። ሊገርም ቢችልም ከፍተኛ ድምፅ ያላቸው ላይ ጊዜ የሚያጠፋ የለም። ካሊፎርኒያና ኒው ዮርክ  የዲሞክራት፤ ቴክሳስና ጆርጂያ የሪፐብሊካን ደጀን ናቸው። ይህንን መቀየር የአንድ ወይም የሁለት ትውልድ ጊዜ የሚፈጅ ተግባር በመሆኑ ዕጩዎች ወሳኝ ድምፅ ያላቸውን ፍሎሪዳና ፔንሲልቫኒያና የመሣሠሉ ውላቸው የማይታወቅ ግዛቶችን መራጮች ሲቀሰቅሱ ይከርማሉ። 
ምንም እንኳ ካለው የቴክኖሎጂ እድገትና ከሁለት መቶ አመታት በላይ የዘለቀው ልምድ ተጨምሮ በምርጫው ዕለት አሸናፊው ቢታወቅም፣ ይፋዊ በሆነ መንገድ የመራጮች ጉባኤ ድምፁን የሚሰጠው በታህሳስ ወር ነው። በደንቡ መሰረት ጉባኤው የሕዝቡን ፍላጎት ማንፀባረቅ እንዳለበት ቢታመንምና እስካሁን እንደታየውም ያንን መንገድ ቢከተልም፣ ላፈንግጥ ቢል ግን ሕጉ አይከለክለውም።
ይህ አይነቱ የምርጫ ሥርዓት የሕዝቡን ትክክለኛ ስሜት የሚገልፅ አይደለም በሚል የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግ ሲወተወት ቆይቷል። በድድርነቱ የሚታወቀው የአሜሪካን ሕግ ማሻሻል እንዲህ ቀላል አይደለም። በዋናነት ደግሞ አሰራሩንም የሚደግፉ በርካቶች ናቸው።
የዚህ ተቋም ሁኔታ አሁን የፓርቲ ቅርፅ ይዟል። ዲሞክራቶች ሲኮንኑት ሪፐብሊካኖች ያደንቁታል። ባለፉት ጊዜያት ከተከናወኑ ሶስት ምርጫዎች ሁለት ጊዜ አናሳ ቁጥር ያለው ተመራጭ አሸናፊ ሆኗል። አሸናፊዎቹ ጆርጅ ቡሽና ዶናልድ ትራምፕ ሪፐብሊካኖች ነበሩ።
እንደ ፖለቲካ ተንታኞቹ፣ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ አብዛኛው ህዝብ ሳይመርጣቸው ፕሬዚዳንትነቱን የሚያሸንፉ ከሆነ፣ ሥርዓቱን ከመኮነን ይልቅ ጥበቡን የተካኑትን ሰው ማድነቅ ይገባል። ይህ ግር የሚል የምርጫ ሥርዓት መነጋገሪያነቱ እንደሚቀጥል ቢጠበቅም፣ በታሪክ እንደታየው ግን ከእነ እንግዳነቱ ለአሜሪካውያን ከሁለት ክፍለ ዘመን በላይ ሰላምና ብልፅግናን አቀዳጅቷል፡፡

Read 481 times