Saturday, 26 September 2020 00:00

በሙስና ሀብት ክፍፍል የተነሳ ባልና ሚስቱ ሳይፋቱ ቀሩ!

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(0 votes)

 ይህን ታሪክ የነገረኝ መኖሪያው ወደ ሰበታ አካባቢ የሆነ አንድ ወዳጄ ነው፡፡ ጊዜው...? በትንሹ አንድ አመት አልፎታል፡፡ ታሪኩ እውነተኛ ነው፡፡ የመረጃዬ ምንጭ የሆነው ወዳጄ፤ ብዙ የባልና ሚስት ሽምግልና ላይ የተቀመጠ፣ አመለ-መልካም፣ ጨዋ፣ ፍርድ አዋቂ አዛውንት ነው፡፡ በዚህ ፀባዩ ብዙ ባልና ሚስት ጉዳያችንን እይልን የሚሉት ነው፡፡ ስለሱ የሚያውቁ ሰዎችም፤ “...ግድ የላችሁም፤ አቶ እንትና ይሸምግላችሁ” እያሉ የብዙ ሰዎችን ችግር ፈቷል፡፡
ይሄ ወዳጄ እንደ ነገረኝ፤ “እንፋታ...” ተባብለው ወደ ሽማግሌ የሚመጡ ባልና ሚስቶች በአብዛኛው መጨረሻቸው ፍቺ ነው፡፡ አሁን ታሪካቸውን የምነግራችሁ ጥንዶች ግን ለመፋታት ቢያስቡም ሳይፋቱ ቀርተዋል፡፡ ለምን ይሆን?
እንዲህ ቀለል አድርጌ የማወጋችሁን አስደናቂ ታሪክ፣ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ግራና ቀኝ እየተገላመጠ ነው፡፡ እንደ ትልቅ ምስጢር የያዘውን ጉዳይ፣ እንደ ኑዛዜ ነው የነገረኝ። “ምናልባት ከሞትኩ፣ በተጠርጣሪነት የምታስይዝልኝ እገሌን ነው” በሚል ስሜት፡፡  
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ጥንዶቹ ከአንድ ሁለት ስብሰባ በኋላ፣ "መፋታት ይሻለናል፣ እንለያይና ንብረታችንን ተከፋፍለን ልጆቻችንን እናሳድግ” ሲሉ ይወስናሉ። ቢላቸው፣ ቢለምናቸው ውሳኔያቸውን ለማጠፍ አልፈቀዱም፡፡ ጨክነዋል፡፡
ይሄኔ ወዳጄ፤ “እንግዲህ የማትታረቁ ከሆነ ሌላ ሽማግሌ ይጨመርና ወደ ንብረት ክፍፍሉ እንግባ” አላቸው፡፡
ባል ሆዬ፤ “ለምን ተብሎ?!” ሲል አፈጠጠ፡፡ “እኔና እሷ እንተዋወቃለን፤ የተጣላነው በሀብት ሳይሆን በሌላ ነገር ነው፡፡ ልጆቻችን የጋራ ናቸው፤ የቱንም ያህል ገንዘብ ወደ እኔም መጣ ወደ እሷም ሄደ ለውጥ የለውም፡፡ ስለዚህ፣ አንተው ማስታወሻ ያዝና አፈራርመን” አይነት ነገር ይላል፡፡ ሚስትም፣ “ይኸው ነው፣ በቃ!” በማለት የባለቤቷን አቋም ደገፈች፡፡
ሽምግልና የተቀመጠው ጓደኛዬ፤ ፍቺን በሚመለከት ያለው ተሞክሮ የዚህ አይነት አልነበረምና ግር ይለዋል፡፡ ለማንኛውም፣ ደብተር ይሰጡትና ንብረት ለመመዝገብ ይዘጋጃል፡፡ ባል፣ መዝገብ መያዙ ራሱ ብዙም አላስደሰተውም፡፡ “እንዲያውም መመዝገቡን ተወው፡፡ በኔ በኩል የሚያስፈልጉኝን የተወሰኑ ነገሮች ብቻ እወስድና፣ የቀረውን ለእሷ እተውላታለሁ፡፡ ልጆቻችን ያደጉ ስለሆኑ ከኔም ሆነ ከእሷ ጋር መኖር ይችላሉ፡፡ ካሻቸው ራሳቸውን ችለው ቤት መከራየት አያቅታቸውም...” ምናምን እያለ ሂደቱን ማቅለል ያዘ፡፡
ሚስት አልተደናገጠችም፡፡ ዝም ብላ የባሏን ውሳኔ ትጠባበቃለች፡፡ ንብረት አደላዳይ ሆኖ የተቀመጠው ወዳጄ፤ ሸሚዙን ጠቅልሎ፣ ብዕሩን ነጭ ወረቀት ላይ ደግኖ ከባልየው የሚወጣውን ቃል ለማስፈር ይጠባበቃል፡፡
“እኔና እገሊትዬ ስንጋባ ምንም አልነበረንም” አለ ባል፡፡ “ከባዶ ተነስተን ነው ሀብት ንብረት ያፈራነው፡፡ ስለዚህ በብረታብረትና በሲሚንቶ አንጣላም (መኪና እና ቤት ማለቱ ነው)፡፡ ... ለመንቀሳቀሻ አንድ መኪና እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ ፒካፕዋን ከወሰድኩ ይበቃኛል፡፡ አንድ ስድስት ክፍሎች ያሉት፣ በወር አስር ሺህ ብር የምናከራየው ቤት አለን፡፡ ተከራዮቹ የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ ብንሰጣቸው ይለቁልናል። እና እኔ እዚያ እኖራለሁ፡፡ በቃ ይኸው ነው። አንድ ቤት ውስጥ እንኖር የነበርን ሰዎች፣ ባለ ሁለት ቤት ሆንን እንጂ የምንለያይ አይመስለንም፡፡ ቅድም እንዳልኩት ልጆች በመካከላችን አሉ ... “ ብሎ ትንፋሽ ወሰደ - ባል፡፡
ጓደኛዬ በጡረታ ከመገለሉ በፊት ባገለገለባቸው መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ቃለ ጉባዔ ፀሀፊነት ስቶት የማያውቅ፣ ትልልቅ ፋይሎችን ተሸክሞ ወደ ቤቱ የሚያመጣ፣ መቸክቸክ የማይሰለቸው ነውና - የሰውየውን ንግግር ቃል በቃል መከተብ ይዟል፡፡  
ባል፣ ንግግሩን ካቆመበት ቀጠለ፡፡ “ጥሬ ብር ... እንኳን ብዙ የለንም፡፡ አንድ መቶ ሺ ብር ያህል ከሰጠችኝ እወስዳለሁ። የባንክ ገንዘባችን ሁሉ የሚቀመጠው በእሷ ስም ነው፡፡ ... ሌላው አንድ ሁለት የባንክ ቤት ሼሮች አሉን፡፡
እነሱ በኔ ስም ነው ያሉት። ስለዚህ፣ ችግር የለም፤ ውልና ማስረጃ እንሄድና ወይም ድርጅቱ ቢሮ ሄደን ፋይል እናስወጣና አንዱን ሼር፣ ያውም የመረጠችውን፤ በስሟ አዞርላታለሁ...” ብሎ ሚስቱን ትክ ብሎ ተመለከታት፡፡
ውይይቱ ሲጀመር ቀይ የነበረችው ሴትዮ ጠቁራለች፡፡ የደም ስሮች ከግራና ከቀኝ ጆሮዎቿ ከፍ ከፍ ብለው እንደተነረቱ ተጋድመዋል፡፡ ከናፍሯ እንደ ጠፍር ደርቀዋል፡፡ ለመናገር አልፈለገችም፡፡ ባልዋን በግልምጫ ብድግ አድርጋ አፈረጠችው፡፡ እሱ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ሁሉ ነገር ለአፍታ ፀጥ-ረጭ አለ፡፡ ምን ተከሰተ?
“ጨረሰክ?” አለችው ሴትየዋ፣ ባልዋን አትኩራ እያየች፡፡ አይኖቿ በጥላቻ ቀልተዋል። የተወሰኑ የዓይኖቿ የደምስሮች በንዴት ሳይበጣጠሱ አልቀረም፡፡ “ግንባርህን እንዳልበረግድልህ!” አለችው። ከዚህ በፊት ስትለው ለቀልድ ነበር፤ ዛሬ ግን የምሯን ልትበረግደው እንደምትችል የጠረጠ ይመስላል፡፡
ሚስት - እስከ ጠረጴዛው አጋማሽ ድረስ አንገትዋን ወደፊት ስባ፣ ደረቷን አስከትላ፣ ከፊት ለፊቷ ወደ ተቀመጠው ባልዋ እያስጠጋች እንዲህ አለች፤ “መልስልኛ፤ ደጉ ባሌ! መልስ ስጠኛ፣ የኔ ቸር! ለኔ አምስት መቶ ካሬ ሜትር ግቢ ያለው ባለ አንድ ፎቅ ቤት ሰጠኸኝ፤ ላንተ ባለ ስድስት ክፍል ቪላ ቤት ወሰድክ፡፡ ላንተ አንድ ፒካፕ መኪና ወሰድክ፣ ለኔ ራቭ ፎርና ቶዮታ አውቶሞቢል ተውክልኝ፡፡ እንዴት ያለህ ጥሩ ሰው ነህ ጃል?! አንተን የመሰለ ቅን ሰው እንዴት ለመፍታት ወሰንኩ እባክህ?!” አለችው፣ አፍጥጣ እያየችውና አንገቷን እየሰበቀች፡፡
ባል ፀጥ!
አሸማጋዩ ጓደኛዬ አንድ ሶስቴ ትንፋሹን ከዋጠ በኋላ “ ... ምነው ችግር አለ እንዴ?” ብሎ ሰውየውን ተመለከተው፡፡
ሚስት ተናግራ አልወጣላትም፡፡ ባሏ ላይ አብዝታ ልትሳለቅበት ቆርጣለች፡፡ እናም ንግግሯን ቀጠለች፡-
“እሺ እባክህ ... ! ትዳር የጀመርነው ከዜሮ ነው ነው ያልከው?  እንዴት ታሪክ አስታዋሽ ነህ እባክህ! ከሆነ አይቀር፣ የካልሲህን ቀዳዳ ሰፍቼ፣ ሸሚዝህን አስገልብጬ፣ ወርቄን ሽጬ ሱሪ ገዝቼልህ ... የሰው ቤት ሰርቼ.. ዲግሪ እንዳስያዝኩህም ተናገራ!”
“ገበና ባንገላለጥ ምን ይመስልሻል፤ ወ/ሮ እንትና?” አላት ባልየው፤ እሱም ንዴት ንዴት እያለው፡፡ “ከምን ውስጥ አውጥቼ እንዳገባሁሽ አንቺም አይጠፋሽም!” ብሎ በተቀመጠበት ተናጠ - አፀፋ መመለሱ ነው።
“እኔ የምለው...” አለች ሚስት፡፡ “ሁለት ቤት ብቻ ጠቅሰህ ዝም ያልከው፣ የማዶው ቤትስ? የእንትን መስሪያ ቤት ተከራይቶት ያለው የፉሪው መሬትስ? በእህትህ በሚጡ ስም የገዛኸው መጋዘንስ? ህ? እ ... በወንድምህ ስም ያለው የአስጎብኚ ድርጅትስ? በአጎትህ ልጅ ስም ያለው ሥጋ ቤትስ? በላ - ሚዛናዊው ባሌ፡፡ ንገረኛ ...! ልቀጥልልህ? ስታየኝ ጅል እመስልሃለሁ? ሁሉንም ነገር ዘክዝኬ ላውጣልህ? ... ቆይ ኧረ ...!”
ጓደኛዬ፤ “ቆይ አንዴ ... ይሄ ነገር!” ብሎ ከወንበሩ ይነሳና ሁለቱንም ዝም እንዲሉ ይመክራቸዋል፤ ግራ ቀኝ እየተገላመጠ፡፡ ከዚያም “ግድ የላችሁም፣ ተመካከሩና በሌላ ቀጠሮ እንገናኝ” ይላቸዋል፡፡
ሁለቱም፣ አላመነቱም፡፡ “እሺ፣ እሺ” ብለውት፣ ሳምንት በዚያው ቀን እዚያው ሆቴል ለመገናኘት ተስማምተው፣ ለቀጠሮውም ስልክ የመደወሉን ሃላፊነት ባልየው ወስዶ ተለያዩ፡፡
ጓደኛዬ ይህን ታሪክ የነገረኝ የቀጠሮው ቀን ካለፈ ከስምንት ወራት በኋላ ነበር - አንድም እየሳቀ፣ አንድም እየተጨነቀ፡፡ የተጨነቀው “አደገኛ የሆነ ምስጢር መስማት ሊያስገድል ይችላል” ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡
ጓደኛዬ ምስጢር ብሎ የያዘውን ነገር የቋጨው ግምቱን አጋርቶኝ ነው - እንዲህ በማለት፡- “... ከዚያልህ ብጠብቅ፣ አይደውሉም… ብጠብቅ አይደውሉም፡፡ ጥፍት ብለው ቀሩ፡፡ አንድ ቀን ግን አየኋቸው። የት ይመስልሀል? ሰርግ ቤት፡፡
እኔ ታድሜ የነበረበት ሰርግ ላይ ሶቶ ተያይዘው ወደ አዳራሽ ሲገቡ አላያቸው መሰለህ? እኔስ ምኔ ሞኝ፣ ጠጅ የምጠጣበትን ብርጭቆ አፌ ላይ ደቅኜ ፊቴን አዞርኳ፡፡ ..  ለካስ፣ ሀብታቸውን እንዴት ብለው እንደሚከፋፈሉ ጠፍቷቸው፣ ምስጢራቸውን ጠብቀው፣ አብረው መኖራቸውን ቀጥለዋል፡፡”
የኔን ወግ ጣል ላርግበት፡፡  “በሙስና ሀብት ክፍፍል የተነሳ ባልና ሚስቱ ሳይፋቱ ቀሩ ያልኩት፣ ከእንግዲህ በኋላም እንደማይፋቱ ስለገመትኩ ነው፡፡ ሰሞኑንማ ምንም ቢባባሉ አይጣሉም፡፡ ሽማግሌ ባለበት የገንዘብ ክፍፍል ነገር ቢነሳ ... “ያኛው ክፍል የዱቄት በርሜል ውስጥ ያለው አንድ ሚሊዮን ብርስ? ጓሮ ጎመን የተተከለበት ጉርድ በርሜል ውስጥ ያለው ሁለት ሚሊዮን ብርስ...?” ሊባባሉ ሁሉ  ይችላሉ፡፡
ይህን ታሪክ ያስታወስኩት በሰሞኑ የአዲስ ብር ምንዛሪ የተነሳ ነው፡፡ ይሄኔ በዚህም የተነሳ ሊፋቱ ያሉ ባልና ሚስት የሽማግሌ ቀጠሯቸውን ሰርዘው ስለ ብራቸው እያሰቡ ይሆናል፡፡ አደራ ታዲያ፣ ይህ ድፍረት የተሞላበት ወግ የሚያነጣጥረው ቅጥ ባጣ ሙስና በተዘረፈ ሀብት ላይ ነው እንጂ በሥራ በተገኘ አዱኛ ላይ አይደለም፡፡   ባለታሪኩ የክፍለ ከተማ ይሁን የወረዳ መሃንዲስ እንደነበር ሰምቻለሁ... በኋላ መሬት አስተዳደርም ነበር  አሉ፡፡ ወዳጄ ይሄን ታሪክ ቢያነበው ያብዳል፡፡ “ልታስገድለኝ ነው?” ብሎ ይጮህብኛል፡፡ እንግዲህ እችለዋለሁ። በነገራችሁ ላይ.... ልክ እንደ ብር መሬትም ወደ ባንክ ይግባ የተባለ ቀን፣ እዚህ አገር ጉድ ይፈላል!!Read 411 times