Thursday, 01 October 2020 11:31

ብራችንን የሚወክል ምልክትም ያስፈልጋል!

Written by  ዮናስ ብርሃኔ
Rate this item
(0 votes)

  ሀገራት የየራሳቸው መገበያያ ገንዘብ እንዳላቸው የሚታወቅ ሲሆን ከተወሰኑ መወራረሶችና መመሳሰሎች በቀር ገንዘቦቻቸውን የሚጠሩበት የየራሳቸው ስያሜዎችም አሏቸው፡፡ ብር፣ ዶላር  ፓውንድ፣ የን፣ ፔሶ፣ ወዘተ፡፡ ይሁንና ሁሉም ገንዘቦች የራሳቸው መለያ ምልክት (sign) የላቸውም፡፡ ከዚያ ውስጥ አንዱ የኛው - የሀገራችን ብር ነው፡፡
“ብር” የሚለው ቃል ራሱ መቼና ከምን የመጣ ነው? እንደሚታወቀው በአለማችን ላይ ከነበሩ ቀደምት ስልጣኔዎች አንዱ የአክሱም ስልጣኔ ሲሆን በኃያልነትም ቢሆን በዘመኑ ከነበሩት ሰፊ ግዛት የመሰረቱ አራት ገናና መንግስታት አንዱም የአክሱም ስርወ - መንግስት ነው፡፡ የራሳቸው መገበያያ ገንዘብ የነበራቸው ደግሞ አክሱማውያንና ሮማውያን ናቸው፡፡ ከወርቅና ከብር በተሰሩ ሳንቲሞች ነበር የሚገበያዩት፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ከሶስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነገስታቱ ምስል የተቀረፀባቸው እጅግ በርካታ የወርቅና የብር ሳንቲሞች በሀገር ውስጥም በባህር ማዶም ተገኝተዋል። “ብር” የሚለውን ቃል ታሪካዊ ዳራ የምናገኘው እዚህ ላይ ነው።
እናም ታላቁ የታሪክ ምሁር ፕ/ር ሰርገው ሃብለስላሴ፣ መጠነ ሰፊ የሆነ ጥናትና ምርምር ባደረጉበት “Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳሰፈሩት፤ በሶስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድንጋይ ላይ በተቀረጸ አንድ የግዕዝ ጽሑፍ ላይ “Birur” -- (ብሩር) የሚል ቃል ተገኝቷል፡፡ ይህም ከብር የተሰራ ሳንቲም ወይም ባጭሩ ገንዘብ ማለት እንደሆነ ይጠቅሱልናል፡፡
ዛሬም ድረስ የምንጠቀምበትን “ብር” የሚለውን ቃል ስር መሰረት ወይም ታሪካዊ አመጣጥ በተመለከተ ይህን ያህል ካልን ዘንዳ አሁን ደግሞ (እኛ) ብር’ራችንን የሚወክል ምልክት ብናበጅለትስ ወደሚለው ሃሳብ መምጣት እንችላለን፡፡ ይህንን ማንሳቴ ደግሞ ብናደርገው (አዲስ ነገር መሆኑ ብቻ ሳይሆን) የራሱ የሆነ ጠቀሜታ ወይም የሚጨምረው እሴት (Value) ስላለው ነው።
ሌላው ቢቀር እንደ €፣£፣$፣ ያሉትን የትልልቆቹን ገንዘቦች ምልክት እናውቃቸዋለን፡፡ የኛው ብር ግን የለውም። ብራችን ምልክት እንደሚያስፈልገው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ አነሳሴ ደግሞ ብራችንን የሚገልጽ ምልክት ቢኖረው የሚለውን ጥቆማ ለመወርወር ብቻ አይደለም፤ የራሴን አማራጭ እነሆ ለማለትም ነው፡  
እንዲህ ሲሆን ቤሳ ይመረቃል እንጂ “ቤሳ-ቤስቲን” የለኝም አይባልም፡፡ (ምን ማለት ነው የሚል ካለ፤ “ወላሃንቲ የለኝም” የሚለው ላይ እናንጠልጥለውና) ቤሳውን እንወርውርለት፡፡ በአጤ ምኒልክ ዘመን የነበረ ሳንቲም ነው፡፡ በመሃል ያለውን ውድቅት ሊመለስ እንደውም ማሪያቴሬሳ እና ጠገራ ብር ይበረከትለታል፡፡ በሺህ አመት የሚሰፈር ዳፍንት ነው፡፡ በዳፍንቱም የተነሳ ንግዱ ጠፋ፣ የገንዘብ ነገር ከሰመ፡፡ ህይወትም ጨለመ፡፡
በዚህ ሁሉ ጽልመት መሃል ለወሬ ነጋሪ የተረፈች አንዲት የገንዘብ ድምጽ ብትኖር ለደቂቃ እስጢፋኖሳውያን የተሰጠች “ጥሌ የሚሏት ቤሳ” ነች፡፡ ይህም በዚያን ዘመን (በ15ኛው መ.ክ.ዘ) ጥሬ ገንዘብ እንደነበር የሚያመለክት መሆኑን የሚዘክሩት አንጋፋው የታሪክ ተመራማሪ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፤ “ድሌ” (ሰሌዳ) ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ከሆነ “ቤሳ” ከማለት ይልቅ “ጠገራ” (ጥፍጥፍ ነሐስ) ብሎ መተርጐሙ ይሻል ነበር ይሉናል፡፡
ሰላም ይስጥልን!     


Read 413 times