Thursday, 01 October 2020 11:32

የክትባት ጊዜ ቀርቧል፡፡ “አይዞን፣ አይዞን!” እንበል - ለጥቂት ጊዜ እንጠንቀቅ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  በአሜሪካ፣ ብዙ ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ክትባት እየተመረተ ነው” ብሏል የዎልስትሪት ጆርናል ጋዜጣ የቅዳሜ እትም፡፡
እስከ ጥር ወር - 400 ሚሊዮን ክትባት አምርቶ ለማስረከብ፣ ትልቁ የሕንድ ኩባንያ፣ በስራ ተጠምዷል” - ይላል ብሉምበርግ መጽሔት፡፡ 5 ኩባንያዎች፣ ክትባት በብዛት እያዘጋጁና  እያመረቱ  ነው፤ ከክትባት ሙከራ ጐን ለጐን - ይሄ ደግሞ የሳይንስ መጽሔት ዘገባ ነው፡፡
ዘገባዎቹ ጥያቄን ያጭራሉ፡፡ መልዕክትንም ያስተላልፋሉ፡፡ “አይዞን” የሚል ነው መልዕክታቸው፡፡ ቸሊና - በአስገራሚ ድምጿ ያዜመችው ዘፈን ነው፡፡ “አይዞን” እያለች መዝፈኗ - ደግ አደረገች፡፡ እውነቷን ነው፡፡ ፈተና ባይጠፋም፣ ጽናት ካለ፣ ውጤት አለ፡፡
በፈተናዎች ሳይበገሩ ለማሸነፍ፣ በሁሉም ጉዳይ ላይ ጽናትን አለመዘንጋት፣ መቼም ቢሆን ብርታትን አለማጣት፣ ትልቅ ኃይል ነው፡፡ ኃያልነቱ ለዛሬም ለዘንድሮም ይሰራል። እናም “አይዞን”! ማለታችን ይጠቅማል፡፡ አዎ፤ ኮረና ቫይረስ የሕይወትና የጤና ፈተና፣ ሆኖብናል፡፡ ስራችንን አናግቶ፣ ኑሮአችንን አክብዶብናል። ሸክሙ ያስጠላል። በየደቂቃው በየሰዓቱ ፋታ የማይሰጥ፣ የጥንቃቄ ብዛት ይሰለቻል። ከወር ወር መቋጫ የሌለው መምሰሉም ያታክታል፡፡
ግን፣ “አይዞን” እንበል፡፡ ብዙ ተጉዘናል፤ ሸክማችን ቢከብድ ለትንሽ ጊዜ ነው፡፡ ለጤናችን እየተጠነቀቅን፣ ለኑሮም እየተጋን፣ ክትባት ጋ ለመድረስ ተቃርበናል፡፡ የስራ ትጋታችን -ለኑሮአችን ፋይዳ፣ ጥንቃቄያችንም ለጤናችን ትልቅ ዋጋ እንዳላቸው ለአፍታም አንዘንጋ፡፡ መጨረሻው ያምርልናል፡፡ ደግሞም፤ አትርሱ፡፡
ሳይወጡ ሳይወርዱ፣ እዚያው በዚያው፣ የሚታፈስ ወርቅና እንቁ የለም፡፡ ሳይውሉ ሳያድሩ፣ ለትልቅ ደረጃ አይደረስም፡፡ ረፋድ ላይ ተመኝተው፣ ከመኝታ በፊት እቅፍ ውስጥ የሚገባ ስኬት፣ ወይም በአፍታ ልዩነት - በፌሽታ የሚቀበሉት ውጤት አይኖርም፡፡
ሳይጥሩ ሳይፈተኑ፣ ሳይነሱ ሳይራመዱ፣ እንደዋዛ፣ መዳፍ በመዘርጋት ብቻ የሚሸመጠጥና የሚቀመስ ጣፋጭ ፍሬ የለም፡፡ ቢኖር እንኳ፣ ወይ እዳ ነው፤ ወይም ውስጡ መራራ ነው፡፡
ወርቅም እንቁም፣ ስኬትም ውጤትም፣ ጣፋጭ ፍሬም የፍቅር ጣዕምም፣ ደስታም ፌሽታም፣ ማንኛውም ውድ ነገር፣ በየጐዳናው ወዳድቆ አይገኝም፡፡ የግል ማንነት ክብር፣ የሕይወት ትርጉምና እርካታም በየሜዳው ወዳድቀው አይገኙም፡፡ ውድ ነገሮች፣ ውድ ዋጋ አላቸው፡፡ ዋጋቸውም፤ የአእምሮ፣ የአካልና የመንፈስ ብርቱ ጥረት ነው። በአጋጣሚ የሚደነቀር ጋሬጣ እና ነባር ድርብርብ ችግር፣ ክፉ መሰናክልና ጊዜያዊ እንቅፋት እየደጋገመ ይፈራረቅበት ይሆናል፡፡ ተስፋንም ይፈታተናል፡፡ ግን፣ አትጠራጠሩ። እያንዳንዷ የጥረት ጠብታ፤ ዋጋ አላት፡፡
ዋጋ፣ አለው፤ መታገስ አይደለም ለከንቱ
እንቁ፣ ሲታሽ፣ ነውኮ የሚደምቀው ውበቱ፡፡
ከቤቲ ጂ ዘፈን የተወሰደ ነው፡፡ እውነት ነው፡፡ ነፍስ ከስጋ ጠልቆ እንዲሰማችሁ፣ ደምቆም እንዲታያችሁ ብትፈልጉ፣ ዘፈኑን ከነውበቱ፣ ቤቲ ጂ ስታዜመው አድምጡ፡፡ ምን ይጠየቃል?
የዛሬ ጥረትና ጥንቃቄ፣ የዛሬ ንባብና እውቀት፣ ለነገ ለከነገወዲያ፣ ዋጋ ያወጣል። ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ማንኛውንም የእለት ተእለት እንቅስቃሴያችሁን ተመልከቱ። አንድም ነገር ከዚህ ውጭ አይደለም። ከትናንት ጥረት ፈልቆ የወጣ ነው - ዛሬ የመጣው ውጤት፡፡
ካቻምና ተከላችሁ፣ አምና ተንከባክባችሁ፣ ዘንድሮ አብቦ ለፍሬ የበቃላችሁ ነው። ከትናንት በስቲያ ተወጥኖና ተጠንስሶ፣ ትናንት ተብላልቶና ስራው ተጋምሶ ነው፤ ዛሬ ለምረቃና ለቅምሻ የሚደርሰው፡፡
ጥቃቅን የምንላቸው ነገሮች፣ ይህን እውነት ይመሰክራሉ፡፡ እጅግ ውድ እና ብርቅ ፀጋዎች ደግሞ፣ የዚያኑ ያህል ክቡር ዋጋ ይጠይቃሉ፡፡ ረዥሙን ጉዞ በጽናት የሚዘልቅ፣ የአእምሮ፣ የአካልና የመንፈስ ብርቱ ጥረትን ይፈልጋሉ - ውድ እና ድንቅ ውጤቶች፡፡
በእርግጥ፣ አንዳንድ እፁብ ድንቅ ግኝቶች፣ በድንገትና ባጋጣሚ እንደቀልድ የተገኙ ውጤቶች መስለው ይታዩናል፡፡ አንዳንድ ፈጠራዎችም፣ እንደቀላል፣ በምኞት ፍጥነት፣ በአንድ አፍታ፣ በአንዳች ምትሃት፣ እንደዋዛ የተፈጠሩ ስኬቶች ይመስሉናል፡፡

ውድ ጸጋ፤ በምኞት አይሆንም
የክትባት ፈጠራዎችን ተመልከቱ፡፡ ምንኛ ውድ እንደሆኑ አስቡት፡፡ ዋጋቸው ተዘርዝሮ የሚያልቅ፣ ውድነታቸው ተለክቶ የሚዘለቅ አይደለም፡፡ የሚሊዮኖችን ሕይወት ማትረፍ ቀላል ነው? ብዙ ሚሊዮኖችን፣ ከህመምና ከስቃይ፣ ከሀዘንና ከጭንቀት ማዳንስ? ይህም ብቻ አይደለም፡፡
በኑሮና በገንዘብ የሚመነዘር የክትባት ፋይዳስ? ዘንድሮ፣ የስንቱ አገር ኢኮኖሚ፣ ውርጭ እንደመታው ሚስኪን፣ ምንኛ ተኮራምቶ እንደደቀቀ ተመልከቱ፡፡ የስንቱ ሰው ኑሮ ብርድ ብርድ እንዳለውና ብሶበት እንደተጐሳቆለ አስቡት፡፡ ጠቅላላ ኪሳራው፣ ከ5 ትራሊዮን ይበልጣል መባሉ አይበዛበትም፡፡ ከዚህ የኮረና ቫይረስ የሚያድን፤ ከአደንዛዥ የኢኮኖሚ ውርጭ የሚገላግል ነው - ውጤታማና ፍቱን ክትባት፡፡
አስገራሚ ነው፡፡ እንዴት ቢባል፣ በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረስ ክትባት፣ እጅግ ውድ እና ድንቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ ያን ያህል ከባድ ዋጋ የሚጠይቅ አይመስልም፡፡ የትሪሊዮን ዶላር ሃብት አይፈጅም፡፡
ይድነቃችሁ ብሎ ደግሞ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የክትባት አይነቶች ተሰርተው፣ እየተሞከሩና እየተፈተኑ ነው - ፍቱንነታቸውን ለማረጋገጥ፡፡  
ለወትሮው፣ የክትባት ፈጠራ፣ ብዙ ገንዘብን ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ አመታትንም የሚፈጅ አታካች ስራ ነው፡፡ ሰላሳ ዓመት ቢሞላውም፣ የኤችአይቪ ክትባት እስከዛሬ ድረስ፣ ገና አልተሰራም፡፡ የኮረና ቫይረስ ክትባትስ?
 የቫይረሱ “የጂን መዋቅር”፣ ወይም (ፍጥረተ - ኮረና)፣ በዝርዝር ተጠንቶ፣ በኢንተርኔት የተለቀቀው፣ ቅዳሜ ጥር 2 ቀን ነው፡፡ ከዚያስ? ውሎ ማደር የለም። “ሞደርና” በተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ፣ ወዲያውኑ፣ የቅዳሜና የእሁድ እረፍት ተሰረዘ፡፡
ቀድሞም ቢሆን፣ የኩባንያው ግቢ ስራ መፍታት አያውቅም፡፡ ከጥር 2 ወዲህ ግን፣ የንብ ቀፎ መስሏል፡፡ የምርምር መሳሪያዎች ያለ እረፍት ይሾራሉ፡፡ ተመራማሪዎች፣ ፋታ በሌለው ስራ፣ ቀን ከሌት ይፈራረቃሉ። በእርግጥ ቁጥራቸው ጥቂት ነው፡፡ በመቶዎች ሳይሆን በደርዘን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ግን፣ ለእንዲህ አይነት ስራ፣ ከእነሱ ጋር የሚስተካከል፣ በዓለም ዙሪያ ቢታሰስ፣ እፍኝ አይገኝም፡፡
“ሞደርና”፣ እንደ ትልልቆቹ መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች፣ ገናናም አንጋፋም አይደለም፡፡ ከወራት በፊት፣ እስከነመፈጠሩም አይታወቅም ነበር። ለነገሩ፣ ለዓይነት ያህል፣ አንዲት ፍሬ መድሃኒት፣ ወይም  አንዲት ብልቃጥ ክትባት እስከ ዛሬ ሰርቶ አላሳየም፡፡ ግን፣ “ኮረና ቫይረስን ለመሳሰሉ የጤና ጠንቆች፣ በፍጥነት ክትባት ሰርተን እናደርሳለን” ባይ ነው ኩባንያው፡፡ በፍጥነት ማለት፣ በስንት ዓመት? የሞደርና ምላሽ፣ ;2 ወር; የሚል ነበር፡፡
“እውቀቱ አለን፤ አዲስ መላ ፈጥረናል፣ አዲስ ቴክኖሎጂ አዘጋጅተናል፤ በሁለት ወር ውስጥ ክትባት መስራት እንችላለን።” በማለት ለበርካታ ዓመታት ተናግረዋል - የሞደርና መስራቾች፡፡ ግን በቀላሉ የስራ ኮንትራት አላገኙም፡፡ ገበያና ደንበኛ አልጐረፈላቸውም፡፡ “ብዙ ያመነን ሰው አልነበረም” ይላሉ የሞደርና ዋና ኃላፊ ስቴፈን ባንሰል፡፡
 መናገርና መስራት ይለያያል፡፡
የሞደርና ሰዎች ተሳስተዋል። ንግግራቸውና ተግባራቸው አንድ አልሆነም። ;በሁለት ወር ማድረስ እንችላለን; ብለው ነበር፡፡ ለኮረና ቫይረስ ክትባት ሰርተው ለማዘጋጀት የፈጀባቸው ጊዜ ግን፣ ሁለት ወር አይሞላም፡፡ በ42 ቀናት ውስጥ ሰርተውታል፡፡ በቤተሙከራ የተፈተሸና ውጤት ያስገኘ ክትባት፣ በሞደርና ተዘጋጅቶ ለእንስሳት ሙከራ በቃ፡፡ እንስሳት ላይ ስኬታማ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ፈቃደኛ ሰዎች ላይ ሙከራ ተጀመረ፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው በ63 ቀናት ውስጥ ነው፡፡
በፈቃደኝነት የተከተቡ ሰዎች ላይ የታየው ለውጥ፣ ሁለት መልክ አለው፡፡
አንደኛ ነገር፣ ክትባቱ በጐንዮሽ ያመጣው ጣጣ፣ የፈጠረው ችግር የለው - “Safe” ነው። ሁለተኛ ነገር፣ በሰውነታቸው ውስጥ፣ አዲስ የበሽታ መከላከያ አቅም ተፈጥሯል - ይህም፣ በደም ምርመራ ታይቷል፡፡ እሰዬው ነው፡፡ ግን፣…
ግን ስራው አለቀ ማለት አይደለም። ከቀዳሚው የእንስሳት ሙከራ በኋላ፣ በሁለተኛው ምዕራፍ፣ የክትባት ሙከራ የሚካሄደው፣ በጥቂት ፈቃደኛ ሰዎች ላይ ነው - ከ20 እስከ 150 በሚደርሱ ፈቃደኛ ሰዎች፡፡ አዎ፣ በተከተቡት ሰዎች ላይ የጤና እክል አለመፈጠሩ፣ መልካም ውጤት ነው፡፡
ሰውነታቸው ውስጥ፣ አዲስ የበሽታ መከላከያ አቅምም ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን፣ ቫይረሱን የመከላከልና የማምከን አቅም ምን ያህል ነው? ክትባቱ፣ ለምን ያህል ጊዜ ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነም አብጠርጥሮ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
በፍጥነት የሚረጋገጥ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ ግን፣ የአንድ ጀንበር ቀላል ስራ አይደለም፡፡ በእርግጥ፣ ቀላልና ፈጣን አቋራጭ ዘዴ አለ፡፡
የተከተቡ ሰዎች፣ ለኮረና ቫይረስ በተጋለጡ ማግስትና ሳምንት፣ ውጤቱን ማየት ምን ይከብዳል? ዘገየ ቢባል፣ በሁለት በሦስት ሳምንት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለዚህም ፈቃደኛ ሰዎች ሞልተዋል፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን ቀላልና ፈጣን ዘዴ ለመጠቀም፣ በአቋራጭም ስኬታማ ለመሆን የደፈረ ኩባንያ የለም፡፡ የሚደፍር ቢገኝም፣ ብዙዎቹ መንግስታት አይፈቅዱም፡፡ በዚያ ላይ፣ የውግዘት መዓት ይወርድበታል፡፡ ለምን?
የክትባትን ፋይዳ ለማጣጣል አይደለም - ጉዳዩ፡፡ ክትባት የሚሊዮኖችን ህይወት ይታደጋል፡፡ ነገር ግን የክትባቱን አስተማማኝነት ለመፈተን፣ ሰዎችን ለአደገኛ ቫይረስ መዳረግ፣ ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ አደገኛ መንገድ ሊሆን ይችላልና፡፡ “ህዝብ ለማዳን” በሚል ሰበብ፣ ሰዎችን እንደበግ ለመስዋዕትነት መንዳት ክፉ መንገድ ነው፡፡ ሰዎችን እንደማገዶ የማንደድ ቀዳዳ መፈጠር የለበትም፡፡
ለዚህም ነው፣ የክትባት ስራ፣ “በቀላልና በፈጣን አቋራጭ መንገድ” የማይጓዘው። ሞደርና ኩባንያ፣ በሐምሌ ወር፣ በ30ሺ ሰዎች ላይ የክትባት ሙከራ ማካሄድ የጀመረውም፣ በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የኮረና ቫይረስ ተጠቂ እንዲሆኑ አይደረግም፡፡
ግን፣ እንደማንኛውም ሰው፣ አንዳንዶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ለቫይረስ የሚጋለጡበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ውጤቱም ከጊዜ ወደጊዜ ይታያል፡፡ የክትባቱ አስተማማኝነት የሚረጋገጠው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በርካታ ሳምንታትን ይፈጃል ማለት ነው፡፡ ግን እንደድሮ አመታትን አይፈጅም፡፡ ለምን?  
ሞደርናንና ተፎካካሪውን ተመልከቱ። ክትባት ለመስራትና ቀዳሚ ለመሆን ከሞደርና ጋር ይፎካከራል - የጀመርኑ “ባዮኤንቴክ” ኩባንያ፡፡ ገናና ወይም አንጋፋ የመድሃኒት ኩባንያ አይደለም፡፡ እንደ ሞደርና ነው - ትንሽ ኩባንያ፡፡ እስከዛሬም፣ አንዲት ቅንጣት ክኒን፣ ጠብታ ክትባት አላመረተም፡፡ ለገበያ አላቀረበም፡፡
እንዲያውም፣ እስከመኖሩም አይታወቅም ነበር፡፡ እንደሞደር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን፣ አዲስ እውቀት በመታጠቅና የአዲስ አቅጣጫ ፈርቀዳጅ በመሆንም ይመሳሰላሉ። የአዲስ ቴክኖሎጂ ፈጣሪና ተጠቃሚ ናቸው - ሞደርናና ባዮኤንቴክ፡፡
አጀማመራቸውም አይለያይም - ከዩኒቨርስቲ ምርምር የፈለቁ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የባዮኤንቴክ መስራቾች የጉንተንበር ዩኒቨርስቲ ሁለት ተመራማሪዎች ናቸው - ባልና ሚስት፡፡ የሞደርና መስራቾችም እንዲሁ፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን ናቸው። ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ መምህርነት ይጀምራል - የሞደርና ጽንስ፡፡ የዩኒቨርስቲ ምርመራቸውና ግኝታቸውን፣ በፅሁፍ ላይ ብቻ የሚቀር እንቶፈንቶ አይደለም። እውቀታቸውና የቴክኖሎጂ ፈጠራቸው፣ በይስሙላና በታይታ መክኖ የሚቀር እርባና ቢስ ወግ አይደለም፡፡ እናም፣ ግኝታቸውንና የፈጠራ ስራቸውን፣ ወደ ተጨባጭ የቢዝነስ ደረጃ ለማሳደግና ለማበልፀግ ተስማምተው ኩባንያቸውን መሰረቱ፡፡ የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ “የእውቀት እና የፈጠራ ባልደረባ” የነበሩት መምህራን፣ የሞደርና ኩባንያ “የቢዝነስ ባልደረቦች” ሆነው አዲስ ጉዞ ጀመሩ - የዛሬ 10 ዓመት፡፡
በበርካታ ዓመታት ጥረት የገነቡት እውቀት፤ በምርምር የደረሱበት ግኝትና የፈጠሩት ቴክኖሎጂ፣ እዚያው በዚያ፣ ወዲያውኑ ለፍሬ አልደረሰም፡፡ ነገር ግን፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ያፈራል፡፡ ይሄውና በክትባት ስራ እየታየ ነው፡፡  
በቀድሞው የዩኒቨርስቲ ጥረት ላይ፣ በቢዝነስ ዓለም የ10 ዓመት ጥረት ተጨምሮበት ነው፤ ዛሬ ለዚህ የበቁት፡፡ ዛሬ ኩባንያቸው፣ 30ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኩባንያ ሆኗል፡፡ የመስራቾቹ የሃብት ድርሻም ተተኩሷል፡፡ በየግላቸው የቢሊዮን ዶላር ባለድርሻ ሆነዋል፡፡ ያው፤ የጥረታቸው ፍሬ ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት ሰርተዋል፤ ደክመዋል፡፡
አለም ያወቃቸው ግን ዘንድሮ ነው። የኩባንያቸው ስም በዓለም ዙሪያ የተሰማውም ዘንድሮ ነው፡፡ እና፣ ዘንድሮ ድንገት፣ በአንዳች ተዓምራዊ ቅጽበት ወደ ቢሊዮነርነት የደረሱ ቢመስሉን ይገርማል? ግን ለዓመታት የደከሙለት ስራ ነው ዛሬ ለፍሬ የበቃላቸው፡፡ የዛሬ 10 ዓመት፣ ወዲያው ወዲያው ውጤት ስላላገኙ፣ እዚያው በዚያው፣ የእለት ተእለት ጥረትና ድካማቸው  ከስር ከስር አብቦ ስላላፈራ፣ ተስፋ ቢቆርጡ ኖሮ አስቡት፡፡ “አይዞን፣ አይዞን” እያሉ በብርታት ባይተጉ ኖሮ ይታያችሁ፡፡
ደግነቱ ከትጋት አልተዘናጉም፡፡ “ዋጋም የለው፣ ልፋታችንም ከንቱ ድካም ነው” ብለው በምሬት አልተሸነፉም፡፡
ዋጋ አለው፤ ጽናታችን ከንቱ አይደለም በከንቱ…እያሉ ቢተጉ ነው፣ ይሄውና፣ ውለው አድረው ለድል የበቁት፡፡ አዲስ ክትባት መስራትም ሆነ ቢሊዬነር መሆን የቻሉት። በእርግጥ ጥቂት የቢሊዩን ዶላር ሃብት፣ ከክትባት ፋይዳ ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነው፡፡
በወረርሽኙ ሳቢያ፣ ዓለም፣ የቢሊዮን ዶላር ሺ እጥፍ ከስሯል፣ በርካታ ትሪሊዮን ዶላር ቀልጦ ቀርቷል፡፡
ስኬታማ ክትባት፣ ዓለምን ከዚህ ከባድ ኪሳራና ከትልቅ የኑሮ ጉስቁልና ይገላግላል። ሚሊዮኖችን ከሞትና ከስቃይ ያድናል። አንዳንዶቹ የክትባት ዓይነቶች ደካማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እስካሁን እየተመረተ የተከማቸውም በዚያው ይቀራል፡፡ ገሚሶቹ የክተውባት ዓይነቶች ግን ይሳካላቸዋል፤ ምርታቸው ይቀጥላል፤ለኛም ይደርሱልናል። ለጥቂት ጊዜ፣ በጽናት ራሳችንን ከበሽታ ከተጠነቀቅን፣ ሳንሰላችና ሳንዘናጋ ከቆየን፣ ከወረርሽኝ ማዕበል አምልጠን፣ ለክትባት እንበቃለን፡፡
የእስከ ዛሬው የጥንቃቄ ጥረት፣ ዛሬ ደርሶ፣ ለክትባት ተቃርቦ፣ መበላሸት የለበትም፡፡ ወደ ተሟላ ፍሬ መድረስ አለበት፡፡ ሳይንስ መጽሔት እንደዘገባው፣ በርካታ ኩባንያዎች፣ ብዙ ሚሊዮን ክትባቶችን እያመረቱ ነው፡፡ እስከ ጥር ወር ድረስ፣ ቢሊዮን ያህል ክትባቶች ተመርተው ይዘጋጃሉ፡፡ በርካታ ሚሊዮን ክትባቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው አትጠራጠሩ፡፡ ነገር ግን አንድ ሚሊዮን ክትባት ብቻ ቢመጣ እንኳ፣ አብዛኛው የኮሮና ቫይረስ ጉዳት ተቃለለ ማለት ነው፡፡ የክትባት ጊዜ ቀርቧል፡፡ እዚህ ደርሰን አንዘናጋ፣ አንድከም፡፡ ;አይዞን፣ አይዞን; አንበል፡፡    


Read 4585 times