Thursday, 01 October 2020 12:19

የድንኳኑ ኑሮ

Written by  ደ.በ
Rate this item
(5 votes)

 ከላንጋኖ ሀይቅ ወደ ሰሜን መለስ ብሎ የተሠራው ካምፕ፤ ቀን ቀን ስለሚሞቅ ድንኳኖች የተተከሉት የግራር ዛፎችን ጥላ እያደረጉ ነው፡፡ ከዚያ ሌላ ምግብ ማዘጋጃና የተለያዩ ቢሮዎች ከፊሉ በጣውላ ተሠርቷል፡፡ ጐማ ተገጥሞላቸው እንደ ተሳቢ በየሥፍራው እየተሳቡ የሚወሰዱ ቅንጡ ቤቶችም አሉ፡፡
ጉልማና ጓደኞቹ በድሪልንግ ሥራ ተቀጥረው ከመጡ አመታት ስላለፋቸው ሙቀቱም ከከተማ መውጣቱም ብዙ ስሜት አይሰጣቸውም፡፡ በሣምንት የምትኖራቸውን የእረፍት ቀን፤ ቡልቡላ ወይም ዝዋይ ከተማ ብቅ ብለው ተዝናንተው ይመለሳሉ፡፡ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የጂኦተርማል ሃይል ፍለጋ በሚካሄደው ቁፋሮ ይሳተፋሉ፡፡ አሉቶ የተባለው ተራራ አናት ድረስ በጠንካራ መኪኖች እየወጡ፣ ሌሊቱን በፈረቃ ሲሠሩ ያድራሉ፡፡ ድንኳናቸው ትዳራቸውና ቤታቸው ነው፡፡ አንድ ታጣፊ አልጋ ወይም ፍራሽ፣ የልብስ ሻንጣ፣ ምናልባት ቴፕ ሪኮርደር ይኖራቸዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ነጠላ ጫማ፡፡ አንዳንዶቹ ክራር ጊታር፣ ሌሎቹ የእጅ ሥራ መስሪያ ሊኖራቸው ይችላል፡፡
ጉልማ ግን የሚታወቀው በጨዋታው ነው፡፡ ሰውነቱ ሞላ ያለ ሆኖ፣ ብዙ ጊዜ ሲሞቀው ከደረት በላይ እርቃኑን ይሆንና ከታች ሽርጡን ይሸርጣል፡፡ ድንኳኑም ከሻንጣና ከነጠላ ጫማ፣ አንዳንዴም ከክበብ ከሚያዳምጣቸው የቢራ ጠርሙሶች በቀር ሌላ ሀብት የለውም፡፡ ብቻ በተለየ ሁኔታ ሁልጊዜ ከትራስጌው የማትለይ የሁለት ወጣት ጥንዶች ፎቶግራፍ አለች። የመኝታውን አቅጣጫ በቀየረ ቁጥር ይቀይራታል፡፡
“ምንድነው?” ለሚለው ሰው መልስ የለውም፡፡ በሣቅ ያሳልፋል፡፡ የሁሉም ጥያቄ፣ የሁሉም እንቆቅልሽ ነው፡፡ ቀይ ቆንጆ ልጃገረድ ጠይም ድንቡሼ ልጅ ፎቶግራፉ ላይ ይታያሉ፡፡ አለባበሳቸው ግን ለየቅል ነው፡፡ ሴቷ ዘመናዊ ልብስ፣ ዘመናዊ ጫማ አድርጋለች፤ ወንዱ ካኪ ሱሪና ሸሚዝ፣ ከሸራ ጫማ ጋር አድርጓል፡፡ ብዙ የሚወደድ ፎቶግራፍ አይደለም፡፡ ምናልባት የሚማርከው የልጅቷ ውበት ነው፡፡
አንዳንዴ ጐረቤት ያለው ፀጋአብ ክራር ሲጫወት ሆዱ ይባባና…”ትንሽ እረፍት ስጠን?” ይላል፡፡ በዚያ ላይ ሲያንጐራጉር - ለብቻ ነው፡፡ ሳቂታ ተጨዋች ስለሆነ በእርሱ ድንኳን ሰው አይጠፋም፡፡ አንዳንዴም ካርታ ይጫወታል፡፡ ወደ ከተማ ለመዝናናት ሲወጡ ከሁሉም ይልቅ ወደ ጨዋታ የሚያይለው እርሱ ነው፡፡ ሌሎቹ ወደ ግራና ወደ ቀኝ ተበትነው አቻቸውን ሲፈልጉ፣ ጉልማ በሙዚቃ ተጠምዶ ቢራውን ይጐነጫል፡፡ ሌላ መዝናኛ የለውም፡፡ ላንጋኖ ሀይቅ ሲሄዱ ግን በዋና አንደኛ ነው፡፡ ዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች መዝናኛው አጠገባቸው ስለነበር ብዙዎቹ የጂኦተርማል ሠራተኞች ዋና ለምደዋል፡፡ ጉልማ ግን ይለያል። ልምምዱን በተከታታይ ስለሚያደርግ የተሻለ ችሎታ አለው፡፡ አንዳንዴም በአዲስ አበባና ከሌሎች ከተሞች ለመዝናናት የመጡ ሰዎች የትውልድ ስፍራውን ሲጠይቁት፤ አዲስ አበባ፣ ለዚያውም ዘነበወርቅ መሆኑ ይደንቃቸዋል፡፡ ከውሃ ጋር ያደገ ይመስላል፡፡ አስተዳደጉ ግን ከውሃ ጋር ሳይሆን ከወላጅ እናቱ ጋር ጉልት ቁጭ ብሎ፣ ሽንኩርትና ቃሪያ እየሸጠ ነው፡፡
የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ሲያልፉ ሲያገድሙ ብዙ ጊዜ ያዩት ነበር፡፡ ግን ደንታ የለውም፡፡ እያደገ ሲሄድ ወላጅ እናቱ ጉሊት እንዳይመጣ ከለከሉት፡፡ ይሁን እንጂ በትምህርቱ ጥሩ የሚባል ተማሪ ነበር። ጓደኞቹ የሚቀኑበት በትምህርቱና ስነ ከምትባል ቆንጆ ልጅ ጋር ትምህርት ቤት ሲመላለስ ነው፡፡ ስነ፤ የሀብታም ልጅ ብቻ ሳትሆን ትምህርት ወዳድ ስለነበረች አብረው በማጥናት፣ አንዳንዴም በመጫወት አብረው ያሳልፋሉ፡፡ በኋላ በኋላ ግን የስነ ቤተሰቦች ደስተኛ አልነበሩም፡፡ አቀማጥለው ያሳደጓት ልጃቸው ድንገት ከደሀ ልጅ ጋር በፍቅር ብትወድቅ፣ ክብራቸው እንዳይነካ ሠጉ። እናም ወደ ፈረንጅ ሀገር ላኳት፡፡ ጉልማ ብቻውን ቀረ፤ ከደብተሩና ከመጻሕፍቱ ጋር። ትምህርቱን ጨርሶ በነርስነት ተቀጠረ። በኋላ ሥራው ስላልተስማማው፣ አዲስ አበባ ለድሬሰርነት የወጣውን ማስታወቂያ አንብቦ፣ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ውስጥ ተቀጠረ፡፡ እናም ዝዋይን አልፋ ካለችው የቡልቡላ ከተማ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ባለው ፕሮጀክት ተመደበ፡፡ የበረሃ ሕይወት፣ የድንኳን ኑሮ ጀመረ፡፡
“ዋና ለምን ታበዛለህ?” አለው ጓደኛው፤ አንድ ቀን፡፡
“ዋና፣ ለጤና! ሲባል አልሠማህም!” አለና ሲጋራውን ለመለኮስ አሽሞነሞናት። ከዚያም ለኮሰና በአንደኛው የከንፈሩ ጠርዝ ሠካት፡፡ መለሰና ወደ ሌላው ጠርዝ ወሰዳት። ሲጋራ በማጉላላት፣ የወይን ጠርሙስ በማቀማጠል የታወቀ ነው፡፡
“ለምታጤሳት ነገር ለምን ጣጣ ታበዛለህ?”
“ሙሽራዬ ናታ! ... ወደ ከንፈሬ ስትመጣ፣ አምሮባት ተኳኩላ መሆን አለበት፡፡ ዝም - ብሎ ማንደድ ወግ ይመስላችኋል!“
“ጉደኛ ነህ!”
“ጉደኛ እናንተ ናችሁ! ... ሁሉን ነገር በጥሬው!...”
“አንተስ?”
“እኔማ ሁሉን ነገር በብስሉ ነው፡፡ ይህ ቦርጭም የለጋስነት ምልክት ነው!” ብሎ ሆዱን መታታ፡፡ ከወገብ በላይ እርቃኑን ነበር፡፡
“ዋና የምትዋኘው ይህንን ለመቀነስ ይሆናል!”
“አይደለም ባክህ የጭንቅላት ጭነት ለመቀነስ ነው”
“ምን ሀሳብ አለብህ!...ሠርተህ ለሆድህ፣ ሠርተህ ለቢራ ነው፡፡ ሚስት የለህ ድስት የለህ!”
ከት ብሎ ሳቀባት፡፡
“ካገባህ ስድስት ወር ሳይሞላህ…እንዲህ መናገር ጀመርክልኝ!...በል ቀበሌ እንዳይሰማህ!...ወገኛ ቀበሮ!…”
ብድግ አለና፤ “ይልቅ ክበብ ሄደን ሻይ እንጠጣ ወይስ እዚሁ ይምጣልን?”
“ማነው የሚያመጣልህ?”
“ከበደን አይቸዋለሁ… ሚንስ ቤቱ?”
ሲጠሩት ከበደ ከተፍ አለ፡፡ ከታች ሽርጥ ለብሷል፤ ከላይ ሳሳ ያለ ቲ-ሸርት፡፡
“ስንት ሻይ ነው?”
“እኛ ስንት ነን?”
“ላንተ አንድ አይበቃህም ብዬ ነው” ተሳሳቁ፡፡
ከሻንጣ ውስጥ ተለቅ ያለች ብልቃጥ ነገር አወጣና፣ የሻይ ቅመም በእጁ መዳፍ አደረገ።
“ላድርግልህ?”
“አልፈልግም!”
ለራሱ አደረገና ፉት አለ፡፡
"ቅመማ ቅመም ትወድዳለህ፡፡ ባለሞያ ሴት ይመስል፣ ሁሉን ነገር በቄንጥ ነው፡፡"
“የተማርኩትን ነዋ!”
ፀጋአብ ክራሩን ገረፈ፡፡ የሁለቱም ጆሮ ብድግ ብድግ ብሎ ቆመ፡፡
“ሠይፈ፤ አንተም ክራር ይመስጥሃል መሠለኝ!”
“አዎ አባቴ ትዝ ይለኛል፡፡ አባቴ ክራር በጣም ይወድድ ነበር፡፡ አንዳንዴ የማይጨው ጦርነትና ዘመቻን ሲያስታወስ ልጅነቱ ትዝ እያለው ያለቅሳል!”
“ታዲያ እንባ ያወረሱህ እሳቸው ናቸዋ!”
“እኔ እንኳ ውስጤ እንጂ ዐይኔ አያለቅስም!”
ገረፈው ክራሩን፡፡ “ሂድ! ሂድ! ሂድ!” አለው፡፡ “ውጣ! ውጣ! ውጣ! ውጣ!” አለው፡፡ ለብቻው የክራሩን ዜማ ተከትሎ የሚመጣበት ድምጽ ነው፡፡ ቢሆንም እጅ አይሰጥም፤ ብድግ አለ፡፡
“ወደ ዋና ቦታ ልሄድ ነው፡፡”
“ሥራ አትገባም?”
“Day off ነኝ!”
ወደ ከተማ በሚወጣ መኪና ተሳፈረ፡፡ ለአስቤዛ ከሚወጡት ጋር ሄዶ፣ በቡልቡላ ወደ ላንጋኖ ይሄዳል፡፡ በቃ! ሻንጣውን አንጠልጥሎ ወደ መኪናው፡፡ ሊገባ ሲል፣ ሌላ መኪና መጣ፡፡ አራት ወጣቶች ወረዱ፡፡ አንዱ የሠፈሩ የዘነበወርቅ ልጅ ነው፡፡
ማመን አልቻለም፡፡
ተሳሳሙ፡፡
“እንዴት መጣህ?”
“አድራሻህን አጠያይቄ መጣሁ! አትደንግጥ፣ ሀገሩ ሠፈሩ ሰላም ነው፡፡”
 አላመነም፡፡ ወደ ካፌ ይዞት ሄደ፡፡
“ወዳንተ መኖሪያ ብንሄድ ይሻላል!”
ከንፈሮቹ ደረቁ፣ አናቱ ሲነድድ ተሰማው።
“ምንድነው?”
“የምሥራች ይመስለኛል!”
“ንገረኛ!”
የቴፕ ሲዲ አውጥቶ ሰጠው፡፡
“ምንድነው?”
“አዳምጠው!”
አብሮት የተጣጣፈ ወረቀት አለ፡፡
“በሕይወት ካለ በእጁ ስጡት፣ ከሌለ መቃብሩ ላይ ወስዳችሁ ክፈቱለት!”
“ስነ … ናት!?” ፎቶግራፉን ብድግ አድርጐ፣ ደረቱ ላይ ለጠፈና ማልቀስ ጀመረ።
“ጨርሰህ አዳምጠው!”
“እመጣለሁ አንለያይም፤ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ያንተ ነኝ!...”
የተለያዩበትን ቀን አስታወሰ፡፡
ቤተሰቦቿ ወደ ካናዳ እንድትሄድ ያስገደዷት ሰሞን ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተያይዘው ሄዱ፡፡ ብስራተ ገብርኤል!!
“እምልልሃለሁ… ማልልኝ!...የትም ሀገር ብሄድ፣ አልከዳህም! አንተም እንደማትከዳኝ ማልልኝ!”
ተቃቅፈው ተላቀሱ፡፡ ፎቶግራፍ ተነሱ። እርሷ ወደ ካናዳ በረረች፡፡ አሁን ይኸው ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ድምጽዋ መጣ።
“የምን ዋና ነው?...አሁንማ ሃሳቤ ወደቀ!..ልዕልቴን አገኘሁ!”
ፀጋአብ ክራሩን ሲገርፍ፣ ልቡ አብሮ አላለቀሰም፡፡

Read 2178 times