Saturday, 03 October 2020 12:43

ፖሊስ በእሬቻ በዓል ላይ የሽብር ተግባር ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መኖራቸውን ደርሼበታለሁ አለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  በእሬቻ በዓል ላይ  የሽብር ተግባር የመፈጸም ተልዕኮ የተሠጣቸው ቡድኖች መኖራቸው እንደተደረሰበትና የፀጥታ ኃይሉ ጥብቅ ክትትል እያደረገ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማና በነገው እለት በቢሾፍቱ የሚከበረውን የእሬቻ በዓል አስመልክቶ የብሔራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤  የጥፋት ኃይሎች በበዓሉ በሚታደሙ ሰዎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ለማድረስ ሽብር ፈፃሚ ሀይሎችን በመመልመልና በማሰልጠን እንዲሁም በማስታጠቅ እያሰማሩ መሆኑ ተደርሶበታል። ከሰሞኑም ለዚህ እኩይ ተግባር ከተሰማሩት ውስጥ ውስን የጥፋት ቡድኖች  በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ለዚህ እኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ የሚጠቀሙበት የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ገንዘብ በቁጥጥር ስር መዋሉን አመልክቷል።
ይህ የጥፋት ሀይል የተለያዩ የሽብር ውዥብሮችን በመንዛት ሀገር የማፍረስና የማተራመስ እኩይ ተግባሩን ቀጥሎበታል ያለው የብሔራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴው ቡድኑ በሀገራችን ለዘመናት የዳበረውን የመቻቻልና የአብሮነት እሴት ለመናድ እያደረገ ያለው አፍራሽ ዝግጅት ለማምከን መላው የጸጥታ ሀይል ከህዝቡ ጋር በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል። በየደረጃው ያለው የጸጥታ ሀይል ፀረ-ሰላም ሀይሎች እየሰሩ ያሉትን አገር የማፍረስ ሴራ የማስቆም፣ የመቆጣጠርና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሀላፊነቱን  እንደሚወጣም መግለጫው አመልክቷል።
ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን የሀገሪቱን ህግ በማክበርና በማስከበር የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባና  ከዚህ ያለፈ ህገወጥ እንቅሰቃሴዎችን ግን በየደረጃው ያለው የጸጥታ ሀይል በዝምታ እንደማይመለከተውና ህግን በተከተለ መንገድ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ  ብሔራዊ የፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴው ገልጿል።

Read 7153 times