Saturday, 03 October 2020 12:46

የዘንድሮ ኢሬቻ በአል “በከፍተኛ ጥንቃቄ” ይከበራል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

  በኮቪድ -19 እና በፀጥታ ችግር ስጋት የተነሳ የዘንድሮ የኢሬቻ በአልን በከፍተኛ ቁጥር በጋራ ተሰባስቦ ማክበር እንደማይቻል የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አስታውቋል፡፡
ህብረቱ መስከረም 23 እና 24 በአዲስ አበባ (ሆራ ፊኒፊኔ) እና በቢሾፍቱ (ሆራ አርሰዲ) የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ስነስርዓት አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ በዓሉ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚከበር ነው ብሏል፡፡
ለወትሮ ከ4 እስከ 6 ሚሊዮን ታዳሚዎች ይገኙበት የነበረው የሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በአላት በየዓመቱ ዘንድሮ በቁጥር የተገደበ ባይሆንም ከወቅቱ የፀጥታና የኮቪድ ስጋት አኳያ ሰዎች ወደ በአሉ ማክበሪያ ስፍራዎች በከፍተኛ ስብስብ መምጣታቸው አይመከርም ተብሏል፡፡
በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ በዓላቱ ማክበሪያ የሚመጡ ታዳሚዎችም በየአካባቢያቸው ባሉ ማክበሪያ ቦታዎችና በየቤታቸው እንዲያከብሩ ነው አባገዳዎች ያሳሰቡት፡፡
በአዲስ አበባና አካባቢዋ ያሉ ወጣቶችም በኢሬቻ ሲታደሙ በዓሉ ለምስጋና ማቅረቢያ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ፣ ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና መልዕክቶች በፀዳ መልኩ እንዲያከብሩም አባገዳዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የበዓሉ ታዳሚዎች ወደ ሆራዎች በሚጓዙበት ወቅትም ከፍተኛ መሰባሰቦችን በመቀነስ፣  የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ በማድረግና ሳኒታይዘር በመያዝ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ አባገዳዎች መክረዋል፡፡
ኦሮሞ ከተፈጠረ ጀምሮ ኢሬቻ በየአመቱ በመስከረም ወር መጨረሻ ሣምንት እንደሚከበር ያስታወሱት አባገዳዎች፤ የዘንድሮ ኢሬቻ በዘመነ ኮቪድ 19 በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚከበር ይሆናል፤ የስርአቱ ፈፃሚዎችም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በፀሎት እንዲያከብሩት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ (ሆራ ፊኒፊኔ)፣  ነገ መስከረም 24 ደግሞ በቢሸፍቱ (ሆራ አርሰዲ) የሚከበር ሲሆን በተጨማሪም በየአካባቢው ባሉ ማክበሪያ ስፍራዎች ይከበራል ተብሏል፡፡   

Read 10997 times