Wednesday, 07 October 2020 17:56

በአፍሪካ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር በ13 በመቶ ሲቀንስ፣ ሟቾች በ7 በመቶ ጨምረዋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በአለማችን 34.3 ሚ ተጠቂዎች፣ 1.02 ሚ ሟቾች፣ 26 ሚ. ያገገሙ ተመዝግበዋል

           በአፍሪካ እስካለፈው ሃሙስ በነበሩት 7 ቀናት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ13 በመቶ ያህል ሲቀንስ፣ የሟቾች ቁጥር በአንጻሩ፣ በ7 በመቶ መጨመሩን የአለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ በአፍሪካ አጠቃላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ1.4 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ወደ 36 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል፤ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡ በአህጉሪቱ በኮሮና ቫይረስ የሚጠቁ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፣ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በ43 የአፍሪካ አገራት ወደ 44 ሺህ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና 27 ሺህ 360 ያህል ባለሙያዎች የተጠቁባት ደቡብ አፍሪካ በቀዳሚነት እንደምትቀመጥም አመልክቷል፡
በአህጉሪቱ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችና በሌሎች ተያያዥ ቀውሶች ሳቢያ በአቪየሽኑ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ 5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከስራ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉና አገራት ከዘርፉ ሊያገኙት የሚችሉት ገቢ በ37 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚቀንስ አለማቀፉ የአቪየሽን ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
አፍሪካ የተሰጋውን ያህል በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አለመጎዳቷን የጠቆመው የአለም የጤና ድርጅት፣ በአህጉሪቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እምብዛም ላለመጨመሩ በምክንያትነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ጉዳዮች መካከልም፣ ተፋፍገው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን፣ የአየር ንብረቱ ሞቃትና እርጥብ መሆን እንዲሁም አብዛኛው የአህጉሪቱ ህዝብ ወጣት መሆኑ እንደሚገኝበት አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ሰዎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የበሽታውን ምልክቶች እንደማያሳዩ የአለም የጤና ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በአለማቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ34.3 ሚሊዮን በላይ፣ የሟቾች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን 20 ሺህ በላይ፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 26 ሚሊዮን መጠጋቱን ዎርልዶ ሜትር ድረገጽ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡ አሜሪካ በ7.46 ሚሊዮን፣ ህንድ በ6.3 ሚሊዮን፣ ብራዚል በ4.8 ሚሊዮን ተጠቂዎች ከአለማችን አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተጠቁባቸው ቀዳሚዎቹ ሶስት አገራት ሲሆኑ፣ አሜሪካ 212 ሺህ፣ ብራዚል 145 ሺህ፣ ህንድ 99 ሺህ ያህል ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት ተዳርገውባቸዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ የአለማችን አገራት በድጋሚ ማገርሸቱንና ከዚህ ቀደሙ የከፋ አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት መፈጠሩን ተከትሎ፣ ከሰሞኑ አገራት ያላሏቸውን የተለያዩ ገደቦች ማጥበቅና አዳዲስ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማውጣት መጀመራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ 240 የሚደርሱ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርምሮች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ የዘገበው ቢቢሲ፣ 40 የሚሆኑት በክሊኒካል ሙከራ ላይ፣ 9 ያህል ክትባቶች ደግሞ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ሙከራ እየተደረገባቸውና መጨረሻ ደረጃ ላይ ናቸው።
የአለም የጤና ድርጅት ከቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በድህነት ውስጥ ለሚገኙ አገራት 120 ሚሊዮን ያህል የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን እንደሚሰጥ ከሰሞኑ ያስታወቀ ሲሆን፣ የአንዱ ክትባት ዋጋ ከአምስት ዶላር ያነሰ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡



Read 2836 times