Friday, 09 October 2020 00:00

በ5 አመታት 2.5 ሚ. ልጃገረዶች ያለዕድሜያቸው ሊዳሩ ይችላሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያለዕድሜ ጋብቻን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያባብሰው እንደሚችልና በመጪዎቹ አምስት አመታት ጊዜ ውስጥ በመላው አለም 2.5 ሚሊዮን ያህል ተጨማሪ ልጃገረዶች ያለዕድሜያቸው ሊዳሩ እንደሚችሉ አለማቀፉ ግብረሰናይ ድርጅት ሴቭ ዘ ችልድረን አስታውቋል፡፡
ወረርሽኙ በመላው አለም ድህነትን እያባባሰ እንዲሁም ልጃገረዶች ከትምህርት ገበታቸው እንዲቀሩና ወደ ትዳር እንዲገቡ ጫና እያደረገ  እንደሚገኝ የጠቆመው ድርጅቱ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ልጃገረዶች ያለዕድሚያቸው ይዳሩባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት አካባቢዎች መካከል ደቡብ እስያ፣ አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ እንደሚገኙባቸውም አመልክቷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአለማችን የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ቁጥር እያሳደገው እንደሚገኝ የጠቆመው ድርጅቱ፣ ከአስር ልጃገረዶች አንዷ የአስገድዶ መድፈር ወየም ወሲባዊ ትንኮሳ ሰለባ መሆኗንም አክሎ ገልጧል፡፡
ባለፉት 25 አመታት በመላው አለም 78.6 ሚሊዮን ያህል ያለዕድሜ ጋብቻዎችን ማስቀረት መቻሉን ያስታወሰው ድርጅቱ፣ አሁን አሁን ግን ድርጊቱን በማስቀረት ረገድ የሚታዩ ለውጦች አዝጋሚ እየሆኑ መምጣታቸውና በአለማችን በየአመቱ 12 ሚሊዮን ያህል ልጃገረዶች ያለ ዕድሜያቸው እንደሚዳሩም አስታውቋል፡፡
ያለ ዕድሜ ጋብቻ፤ የልጃገረዶችን መብቶች የሚጥስና ለድብርት፣ ለዘላቂ ጥቃት፣ ለአካል ጉዳተኝነት ብሎም ለሞት የሚዳርግ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፣ የአገራት መሪዎች ያለ ዕድሜ ጋብቻና የጾታዊ እኩልነት መዛባትን ለመከላከል ተጨማሪ ገንዘብ በመመደብ የበለጠ ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል፡፡

Read 3317 times