Saturday, 28 July 2012 10:53

የ”እኛ ተማሪነት” ዘመን ሌላኛው ገፅታ

Written by  ቻላቸው ታደሰከ ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ
Rate this item
(0 votes)

እንኳን ጥብቅ የሥራ ሥነ ምግባር በሚጠይቀው የሶሻሊዝም ሥርዓት ውስጥ የነበርን ተማሪዎች ይቅርና፣ እናንተ እንኳን ከትምህርት ቤታችሁ አልፋችሁ የከተማችሁን ቆሻሻ ስታፀዱ አላየንምን?

አንተነህ ይግዛው የተባለ  ፀሐፊ የ”እኛ ተማሪነት” በሚል ጭብጥ ላይ በተባ ብዕሩ የፃፈውን ባለሦስት ክፍል ትዝታውን ሰሞኑን አስኮመኮመን፡፡ የፀሐፊውን ችሎታ ሁሌም የማደንቀው ነው፡፡ በዚህ ፅሁፉ የእኛን ተማሪነት ዘመን ከአሁኑ ጋር በንፅፅር ለማየት ሞክሯል፡፡ በሦስተኛው ፅሁፉ ግን በአብዛኛው የተጋነኑ፣ መሰረታዊ የሃሳብ መምታታት የሚታይባቸውና ለአሁኑ ዘመን ተማሪዎች የተሳሳተ መልእክት የሚያስተላልፉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በወቅቱ ከነበረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አውድ (context) ውጭ የተቀመጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ፀሐፊውን ግልብ ድምዳሜዎች ላይ እንዲደርስ አድርገውታል፡፡

ሁለተኛውን ፅሁፉን ካነበብኩ በኋላ ቀጣይ ክፍል እንደሚኖረው ቃል በመግባቱ በቀጣዩ ፅሁፍ እንዲዳስሳቸው የተወሰኑ ነጥቦችን ከትዝታዬ ቆንጥሬ ወደ ሞባይሉ መልእክት ልኬለት ነበር፡፡ የተካተቱት ሃሳቦች ግን የተጠቀሱበት አግባብ ቁንፅል፣ የተዛባና ስሜታዊነት የሚታይባቸው በመሆናቸው ይህንን ምላሽ ለመፃፍ አስገደደኝ፡፡

በነገራችን ላይ የእኔና የፀሐፊው የተማሪነት ዘመን በ1970ዎቹና 1980ዎቹ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ስለሆነም በቀድሞው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የሚወድቅ ዘመን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከሥርዓቱ ባህሪያት አንፃር የትምህርት ሥርዓቱ አፈፃፀምና የመምህራንና ተማሪዎች ግንኙነት፣ በሁሉም ቦታዎች ከሞላ ጐደል ተመሳሳይነት ነበረው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ፀሐፊው ያነሳቸው ጉዳዮችም ተራ ገጠመኞች አይደሉም፡፡ የእኛን ዘመን የትምህርት ሥርዓትን እንዲወክሉ ታስበው የቀረቡ እንጂ፡፡ ስለሆነም እኔን ጨምሮ በየትኛውም ቦታ የተማረ የወቅቱ ተማሪ አስተያየቱን መስጠቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

ፀሐፊው በእኛ ዘመን የተማሪዎች “ጉልበት ብዝበዛ” እንደነበር በሰፊው አትቷል፡፡ የእኛ ትውልድ የመማሪያ ክፍሎቹን በ”ወረፋ አቧራ እየቃመ የማፅዳት ግዴታ” እንደነበረበትም ፅፏል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት የትምህርት ቤት ቅጥር ግቢያችንን “ቆሻሻ መልቀም” ተማሪዎችን መቅጫና በተማሪው ጉልበት የመጠቀም “ኢፍትሃዊ ስትራቴጂ” ነው በማለት ኢፍትሃዊ የሆነውንና ውሃ የማይቋጥር ድምዳሜውን ሰንዝሯል፡፡

ፀሐፊው የመማሪያ ክፍላችንንና የትምህርት ቤት ቅጥር ግቢያችንን ማፅዳታችን እንደ ጉልበት ብዝበዛ አድርጐ መቁጠሩ  አስገርሞኛል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች “ኃላፊነት” (duty) እንጂ በላያችን ላይ በግዴታ የተጣሉብን አልነበሩም፡፡ እናንተ የዛሬው ዘመን ተማሪዎች ሆይ! መቼም በሲቪክሰና ሥነ-ምግባር ትምህርታችሁ “ኃላፊነት” የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ በደንብ የምታውቁት ይመስለኛል፡፡ የፀሐፊው አባባል ራስን በመቻልና በሥራ ወዳድነት መንፈስ ላይ በረዶ የሚቸልስ በመሆኑ ብዙም ግምት ልትሰጡት አይገባም፡፡

ፀሐፊው ተማሪዎችን ለጉልበት ብዝበዛ የዳረጋቸው የፅዳት በጀት ባለመመደቡ እንደሆነም ይገልፃል፡፡ ሥራው የተማሪዎች የሚያኮራ ኃላፊነትና በጐ ነገር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የበጀት ጥያቄ ማንሳቱ ደግሞ አስቂኝ ነው፡፡ በቂ ትምህርት ቤቶች መክፈት አልቻል ብሎ በርካታ ብሩህ አዕምሮ የነበራቸው የገበሬ ልጆች ገበሬ ሆነው በቀሩበት በዚያ ዘመን ለፅዳት የበጀት ጥያቄ ማንሳት፣ የእኛን ዘመን ከነባራዊ ሁኔታው ውጭ እንድታዩትና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ የሚያደርግ ነው፡፡

እንኳን ጥብቅ የሥራ ሥነ ምግባር በሚጠይቀው የሶሻሊዝም ሥርዓት ውስጥ የነበርን ተማሪዎች ይቅርና፣ እናንተ እንኳን ከትምህርት ቤታችሁ አልፋችሁ የከተማችሁን ቆሻሻ ስታፀዱ አላየንምን? በተደጋጋሚስ በተራቆቱ ቦታዎች ላይ ችግኝ ስትተክሉ አልነበረምን? ይህ ታዲያ የጉልበት ብዝበዛ ነው? ይህንን መሰለ የማህበረሰብ አገልግሎት (community service) መስጠት የትምህርት ቤቶች አንዱ ተልእኮ መሆኑን ፀሐፊው አልተገነዘበም፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በለንደን ከተማ የኦሎምፒክ ችቦውን በሁለተኛነት ተቀብሎ በአደባባይ በክብር የሮጠው ወጣት፣ ለዚህ የተመረጠው በሚኖርበት አካባቢ ባበረከተው የማህበረሰብ አገልግሎት መሆኑን ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት በአሁኑ ወቅት እጅግ የሚያኮራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የእኛ ትውልድ የትምህርት ቤቶችን ቅጥር ግቢ የሚያፀዳው በየጊዜው በሚወጣ ሁሉንም አሳታፊ በሆነ ፕሮግራም እንጂ የተወሠኑ ተማሪዎችን ለመቅጣት ታስቦ አልነበረም፡፡ ለማንኛውም የራስን መማሪያ ክፍልና የትምህርት ቤትን ቅጥር ግቢ ማፅዳት በብዙ የሃገራችን ክፍሎች ዛሬም ተማሪዎች የሚያከናውኑት መደበኛ ኃላፊነታቸው ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ ፀሃፊው መምህራኖቻችን ወደ ክፍል ሲገቡ ከመቀመጫችን በመነሳት መቀበላችንን እንደ “ጭቆና” አድርጐ ማቅረቡ ነው፡፡  ይህ እኮ በየትኛውም ሀገር አሁንም ያለ እጅግ አኩሪ የተማሪዎች እሴት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ እሴት በሀገራችን እየተሸረሸረ በመሄዱ ፣አንዳንድ የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች እንደማትተገብሩት ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ማህበረሰባችሁ ይወቅሳችኋል፡፡ ይህ ድርጊት በመሰረተ ሃሳቡ “ጭቆና” ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ዘመን የወቀሳ በትር ለምን ያርፍባችኋል? እውነታው የእውቀት አባትን ከመቀመጫ ተነስቶ መቀበል ምንጊዜም የአክብሮት መገለጫ የሆነ ተግባር እንደ ኋላቀር አስተሳሰብ ከቶውንም  ሊታይ አይገባም፡፡

ሌላው አስገራሚው ነገር በእኛ ዘመን በየቀኑ ብሎም ሰኔ 30 ላይ ትምህርት ሲዘጋ ከ”እስር ቤት” የተፈታን ያህል እፎይታ ይሰማን እንደነበር መግለፁ ነው፡፡ መደሰቱ እንደተጠበቀ ሆና የፀሐፊው መልእክት ችግር ግን የደስታችን ምክንያት ትምህርት ቤቶቻችንንና መምህራኖቻችንን ከመጥላት የመነጨ እንደሆነ አድርጐ ማቅረቡ ላይ ነው፡፡ ይህ እጅግ ቁንፅል የሆነና የተዛባ ድምዳሜ በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ ፀሐፊው በቁንፅል የተወው ሌላ ሐቅ አለ፡፡ ይኸውም መስከረም ላይ እንደገና ትምህርት ስንጀምር ይሰማን የነበረው ደስታ ነው፡፡ ክረምቱ አልፎ መስከረም ሁለት በአብዮታዊ ሰልፍ ላይ ከወላጆቻችን ጋር ተሰልፈን፣ ከ“ቆራጡ መሪ ጋር ወደፊት!” የሚለውን መፈክር ሰማያዊ ካኪ የለበሱ “ጓዶች”ን ተከትለን አስተጋብተን፣ መስከረም ሦስት ላይ በትምህርት ቤቶቻችን ቅጥር ግቢ ስንገናኝ የሚሰማን ደስታ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ ወርቅ ስታገኝ ከተሰማት ደስታ በሦስት እጥፍ ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡

ይህ እንግዲህ ለትምህርት ቤታችን ከነበረን ፍቅር የመነጨ ነው፡፡ ከትምህርት ቤት ስንወጣ የሚሰማን ደስታ ደግሞ ተፈጥሯዊና ከወላጆቻችንና ከቀሪው ህብረተሰብ ጋር ለመገናኘት የነበረን ፍላጐት እንጂ በጥቅሉ ትምህርት ቤቶቻችንን “እስር ቤት” አድርገን ከመቁጠር አልነበረም፡፡ ይህ አባባል የፀፊውን የግል አመለካከት ያንፀባርቅ እንደሆን እንጂ የበርካታ ተማሪዎችን ትዝታ ሊወክል አይችልም፡፡ የጠዋት ሰልፍ ላይ ሰንደቅ አላማችንን ለመስቀል የነበረን እሽቅድድምና አንዳንድ ጊዜም ፀብ ምን እንደሚያሳይ ለእናንተው ለአንባቢያን እተወዋለሁ፡፡

በነገራችን ላይ “ጓድ” የሚለው የእኛ ዘመን የባለስልጣናትና የፓርቲ አባላት ሶሻሊስታዊ መጠሪያ ማዕረግ ነበር፡፡ መምህራኖቻችንም የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢ.ሠ.ፓ) አባል ከሆኑ “ጓድ መምህር…” እየተባሉ ይጠሩ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ የ”ጓድ”ን ነገር ካነሳሁ አይቀር ባለፈው ዓመት የኢቲቪ ጋዜጠኞች የአሁኖችን ባለስልጣናት “ጓድ” ብለው ሲጠሩ ሰማሁ ልበል? የእኔ ጆሮ ችግር ወይንስ የጋዜጠኞቹ የአፍ ወለምታ? ሆን ብለው ያደረጉት ከሆነም መቼስ “አቤት መመሳሰል!” ብሎ ማለፍ ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል?

ሌላው አቶ አንተነህ ያነሳው ነጥብ በዚያ ዘመን የነበርን ተማሪዎች በተለያዩ ሰበቦች በመምህራን የምንገረፍበትን ሁኔታ ነው፡፡ በእርግጥ እኔም እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ግርፋትን በተደጋጋሚ ቀምሻታለሁ፡፡ በዚያች ደቡብ ጐንደር ውስጥ በምትገኘው ትንሿ ሽሜ ማርያም ትምህርት ቤት ውስጥ እራሳችን በትእዛዝ በምንቆርጠው የባህር ዛፍ ለበቅ (stick) እንገረፍ ነበር፡፡ በትምህርት መስነፍ፣ የቤት ሥራ (home work) አለመስራት፣ ማርፈድ፣ ያልተገባ ሥነ-ምግባር ማሳየት ለግርፋት ይዳርጋሉ፡፡

እስከ ስምንተኛ ክፍል አብራኝ የተማረችው ውዴ ተሾመ፣ ክፍል ውስጥ በድንገት ስለምትስቅና የቤት ሥራዋን ስለማትሰራ በአብዛኛው ሙሉ ክፍለ-ጊዜዎችን መምህራን እያስተማሩ ወለል ላይ ተንበርክካ እንድታሳልፍ ትገደድ ነበር፡፡ ቅጣቱ ግን ለትምህርት የነበራትን አመለካከት የተሻለ ማድረግ አልተቻለውም፡፡ ውዴ፤ ቅጣቱን ብትለምደውም ድርጊቱ ግን ፍፁም ኢፍትሃዊና ያልተመጣጠነ መሆኑን አልደብቃችሁም፡፡ በ1970ዎቹ መጨረሻ አብራችሁኝ የተማራችሁ ጓደኞቼ ሁሉ እውነት ከመካከላችሁ የእርሻ መምህራችን የነበሩትን የጋሽ ሙሉዬን እጅ ያልቀመሰ ይኖራል?

የዛሬው ዘመን ተማሪዎች ደግሞ አስተማሪዎቻችን ለምን በዚያ መንገድ እንደሚቀጡን መጠየቃችሁ አይቀርም፡፡ ግሩም ጥያቄ ነው፡፡ ፀሐፊው አቶ አንተነህ ግን ለዚህ ጥያቄ መልስ እንደሌለውና ምክንያቱንም እንደማያውቁ ገልፆላችኋል፡፡ በዚህ የጐልማሳነት እድሜው ትዝታውን ካካፈላችሁ በኋላ፣ በወቅቱ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ ተነስቶ የራሱን ግምቶች ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ስለዚህ በቁንፅል ትዝታዎቹ ግራ ተጋብታችሁ እንዳትቀሩና የእኛን አስተማሪዎች “ጭራቅ”፣ ትምህርት ቤቶቻችንን ደግሞ “ዓለም በቃኝ ከርቸሌ” አድርጋችሁ እንዳትስሏቸው የእኔን መላ ምት አካፍላችኋለሁ፡፡

ሁሉም ባይሆኑም ይገርፉን የነበሩትን መምህራን በሦስት መደብ እከፍላቸዋለሁ፡፡ በመጀመሪያው መደብ የሚገኙት ቀደም ሲል ኢህአፓ እና መኢሶን የተባሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች አባላት ወይም ደጋፊዎች የነበሩ ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ በመሆኑም በወታደራዊው መንግሥት እስራትና አስከፊ ግርፋት የደረሰባቸው ይመስሉኛል፡፡ ከፍ እያልን ስንሄድም ይህንኑ በጭምጭምታ እንሰማ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ የተወሰነ የሰብዕና መቃወስ አድርሶባቸውና ሥርዓቱንም አምርረው በመጥላታቸው ምክንያት ቁጭታቸውን በእኛ በተማሪዎቻቸው ላይ የተወጡት ይመስለኛል፡፡

በሁለተኛው መደብ የሚገኙት ደግሞ በሥርዓቱ አምነውበት በጥብቅ ሶሻሊስታዊ ሥነ         ስርአት የተገነባ፣ ወለም ዘለም የማይል፣ ሥራ አክባሪና ፍፁም ታዛዥ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር የሚመኙ ይመስለኛል፡፡ በወታደራዊ ዲስፕሊን የተገራ፣ የራሱን ጉዳት እንደ ጉዳት የማያይ፣ ሶሻሊስታዊ ትውልድን በሃይል በመቅረፅ ለሀገራቸው በጐ ነገር ያደረጉ የሚመስላቸው ነበሩ፡፡ ይህ ዘመን ሶሻሊስታዊ ሥርዓትን መገንባት የሚቻለውና የማንኛውንም ሰው አስተሳሰብ መግራት የሚቻለው “ግርፋት” በሚባለውና ከላይ እስከ ታች በተዘረጋው መንገድ እንደሆነ አድርገው ያመኑ በርካታ “ጓዶች” የነበሩበት ዘመን ነው፡፡

በሦስተኛው መደብ ያሉት ደግሞ የፖለቲካ መነሻ ባይኖራቸውም አሁንም በዚህ በእናንተ ዘመን እንዳለው ሁሉ በግል ባህሪያቸው ምክንያት ተማሪዎቻቸውን በተደጋጋሚ የመግረፍ አባዜ የተጠናወታቸው ነበሩ ለማለት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ግን በሁሉም ጐራዎች የሚገኙ መምህራኖቻችን ግርፋት፤ ተማሪዎች ለትምህርት ትኩረት እንዲሰጡ ይገፋፋቸዋል ብለው የሚያምኑ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከግርፋቱ ጀርባ አንድ በጐ አላማ ነበር ማለት ነው፡፡

ይህንን ሁሉ የምላችሁ በወቅቱ የነበረውን የመምህራን ባህሪ በሀገሪቱ ከነበረው የፖለቲካ አውድ (context) አንፃር እንድታዩት ስለምፈልግ ነው፡፡ ይህንን ካደረጋችሁ የእኛን አስተማሪዎች በፈናው እንደ አስፈሪ ፍጡር ከመቁጠር ትቆጠባላችሁ፡፡ በነገራችሁ ላይ ማህበረሰባችን ልጆችን በግርፋት የመቅጣት ጐጂ ልምድ እንዳለው ከእናንተ የተሰወረ አይመስለኝም፡፡ መቼም አሁን አሁን በከተማ አካባቢ ያላችሁ ተማሪዎች በአስተማሪዎቻችሁ የመገረፋችሁ እድል እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም በወላጆቻችሁ ዘንድ ግን በስፋት እንደሚታይ ለእናንተ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡ ለዚህ ነው በወቅቱ የነበረውን የመምህራን ባህሪ ከማህበረሰቡ ነባራዊ ሁኔታ ነጥሎ የተመለከተው የፀሃፊው ፅሁፍ የተሟላ ግንዛቤ እንዳይኖራችሁ አድርጓል የምላችሁ፡፡

ይህን ስላችሁ ግን መምህራን ምንጊዜም የማህበረሰቡ ልማድ ተገዢ መሆን አለባቸው ለማለት አይደለም፡፡ መምህራን የማህበረሰቡን ጐጂ ልማድ በመለየት ልማዱን ለማስቀረት ቀዳሚ ሚና መጫወት እንዳለባቸው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በትምህርት ሥርዓታችን ችግር ምክንያት ይህንን የለውጥ ሂደት ሊመሩ የሚችሉ መምህራን አገራችን በብዛት እንዳላፈራች የምታውቁት ነው፡፡ በእኛ ዘመን የነበረው እውነታም ይኸው ነው፡፡

ለማንኛውም ፀሐፊው የእኛን ዘመን ግርፋት በዓለም አቀፍ ህጐች ከተከለከለው ኢ-ሰብአዊ ግርፋት (torture) ጋር ለማመሳሰል ሲሞክር ታዘብኩት፡፡ ቅጣት እንደነበር ባይካድም የትምህርት ቤቶቻችን ዋነኛ መገለጫ ግን አልነበረም፡፡ አሁን በትልልቅ ኃላፊነት ላይ የምታዩዋቸው ጐልማሳዎችን ያፈሩት የእኛ ዘመን መምህራን ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት አብዛኛዎቻችን በቀድሞ መምህራኖቻችን ላይ ዛሬ አሉታዊ አመለካከት እንደሌለን እምነቴ ፅኑ ነው፡፡ ጐበዝ ተማሪዎችን በግላቸው የሚሸልሙ መምሀራን በርካታ ነበሩ፡፡

ስለሆነም የፀሃፊው አቀራረብ በግነት እና እውነታውን ሸራርፎ በማቅረብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ትምህርት ቤት ውስጥ መኖር ስለሚገባው ነፃነት የተሳሳተ ትርጉም እንድትሰጡት የሚያደርግ ነው፡፡  በነገራችሁ ላይ የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች ወላጅ አምጡ ተባልን ብላችሁ አስተማሪ ታስፈራራላችሁ የሚባለው እውነት ነው?

በእኛ የተማሪነት ዘመን በጣም የምንወደው “ትምህርት በሬዲዮ” መሆኑን አቶ አንተነህ የነገራችሁ እውነት ነው፡፡ የሬዲዮ ትምህርትን የወደድነው ግን ፀሃፊው በተሳሳተ መንገድ እንደገለፀው ከአስተማሪዎቻችን “ንዝንዝ” ስለሚታደገን አልነበረም - በይዘቱና በአቀራረቡ ማራኪነት እንጂ፡፡ ለዚህ ማስረጃው ደግሞ ትምህርት ፕሮግራሞች በሬዲዮ ሲደገሙ በየሱቆችና በመኖሪያ ቤታችን ተኮልኩለን ስንከታተል የነበረበት አጋጣሚ ብዙ መሆኑ ነው፡፡

የሬዲዮ ትምህርትን ሳነሳ አንድ የድሮ ገጠመኝ ትዝ አለኝ፡፡ ከእለታት በአንድ ክፉ ቀን፡፡ በትንሿ ሽሜ ማርያም ትምህርት ቤታችን በጧት ደርሰን ተሰለፍን፡፡ ከድሮው በተለየ ሁኔታ የትምህርት ቤታችን ዳይሬክተር ጋሽ አለማየሁ ከፊት ለፊታችን ኮስተር ብለው ቆሙ፡፡ የእለቱ ተረኛ አሰላፊ መምህር እያሉ የእርሳቸው መምጣት ግራ አጋባን፡፡ ከዚያም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “የሞዛምቢኩ ፕሬዝዳንት ጓድ ሳሞራ ማሼል፤ በትናንትናው እለት በአውሮፕላን አደጋ በሞት ስለተለዩን ሰንደቅ አላማችን ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል” አሉ፡፡ የህዝብ መዝሙሩ አጋማሽ ላይ ስንደርስ ባንዲራችን ከመስቀያው አጋማሽ ቦታ ላይ ደርሶ ቆመ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ መዝሙሩን ባንዲራው በቆመበት ሁኔታ ጨረስነው፡፡ አሳዛኝ ትእይንትም ሆነ፡፡

ወዲያውም በሬዲዮ የሐዘን ማርሽ ተለቀቀ፡፡ ለህብረተሰብ ትምህርት ምስጋና ይግባውና ሞዛምቢክ በደቡብ ምስራቅ አፍሪካ እንደምትገኝና ዋና ከተማዋም ማፑቶ መሆኑን ጠንቅቀን እናውቅ ነበር፡፡ በጊዜው የሁሉንም የአፍሪካ ሀገሮች ዋና ከተማዎች በሙሉ የማያውቅ ተማሪ የሰነፎች ሁሉ ሰነፍ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ አይገርምም?

ለማንኛውም በዚያ እለት በትምህርት ቤታችን ውስጥ ከባድ ሐዘን ሆነ፡፡ በእርግጥም ሁኔታው በመላው ኢትዮጵያ ተመሳሳይ እንደሆነ አልጠፋንም፡፡ ጓድ ሳሞራ የህብረተሰባዊት እናት ሀገራችን የቁርጥ ቀን ወንድም እንደነበሩ ሲነገረን አይኖቻችን እንባ አቀረሩ፡፡ የሐዘናችን ምክንያት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ባንዲራችን ዝቅ ብሎ እና ግርማ ሞገሱ ተገፎ ሲውለበለብ በማየታችን ይሁን ወይንም በጓድ ሳሞራ ሞት ምክንያት ማንም በእርግጠኝነት መናገር አይችልም፡፡

መምህራኖቻችንም ስለ ደመወዝ እድገት መዘግየት ይሁን የጓድ ሳሞራ ሞት በአብዮቱ ውስጥ ስለሚፈጥረው ክፍተት በቅጡ ለይተን ባንሰማቸውም እጆቻቸውን ወደ ኋላ አጣምረው፣ በቡድን በቡድን ሆነው ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው ያወሩ ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ተክዘን ዋልን፡፡ ያን እለት ከምንወደው የሬዲዮ ትምህርትም በላይ ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መኖራቸው ተገለጠልን፡፡

እናንተ የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች ለመሆኑ በእናንተ ዘመን የትምህርት ቤታችሁ ባንዲራ ዝቅ ብሎ ተውለብልቦ ያውቃል? የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ያረፉ እለት ባንዲራችሁ የት ነበር? ለመሆኑስ ባንዲራችሁ በየቀኑ በክብር ይወጣል፤ ይወርዳል? ወይስ የባንዲራ ቀን ላይ በዓመት አንድ ጊዜ ነው?

በዚያን ዘመን በእኔ እምነት ሬዲዮ ሁለት መሰረታዊ አገልግሎቶች ነበሩት፡፡ ቀን ቀን “ትምህርት በሬዲዮ” ፕሮግራምን በነፃነት ለመኮምኮም ያገለግላል፡፡ ማታ ላይ ደግሞ የቪኦኤ (VOA) አማርኛ ድምፅን በድብቅ ለመከታተል፡፡ በእርግጥ በነሐሴ ወር ላይ የፍልሰታ ፆም ስትደርስ ስድስት ሰዓት መሙላቱን ለማወቅ ጉልህ ሚና ተጫውቷል - ሬዲዮ፡፡ ይህንን የማታውን የሬዲዮ ጥቅም መጋራት ግን የጥቂቶች እድል ነበር፡፡ የሬዲዮ ባለቤት መሆን ትልቅ የሃብት መለያ መሣሪያ ነበርና፡፡

ቪኦኤን የማዳመጥ እድሉ የነበረን ተማሪዎች በዳይሬክተራችን መቀመጫ ጀርባ ካለው ግድግዳ ፎቶግራፋቸው የተሰቀለውን “ቆራጡ” መሪያችንን ሲያብጠለጥላቸው መስማታችን ከሌሎች ጓደኞቻችን በተለየ ሁኔታ ብዥታ ፈጠረብን፡፡ አራተኛ ክፍል እያለሁ በዳይሬክተራችን ቢሮ ያየሁትና ሰውዬው ዘንድሮ “ትግላችን” በሚል አርእስት ባሳተሙት መፅሃፍ ጀርባ ላይ ያወጡት ፎቶግራፍ አንድ ለመሆኑ ጥርጣሬ የለኝም፡፡

በነገራችሁ ላይ በዚህ በእናንተ ዘመን በትምህርት ቤታችሁ ውስጥ እንደኛው ዘመን ሁሉ የተሰቀለ ፎቶግራፍ አለ የሚባለው መቼም ቀልድ መሆን አለበት፡፡ እውነት ከሆነ ግን “አቤት መመሳሰል!” ብለን እናልፈዋለን፡፡

የኋላ ኋላ ደግሞ ሬዲዮ ስጐረጉር ከኤርትራና ትግራይ በኩል የሚሰራጩ የሸማቂዎች ድምፆች መኖራቸውን ደረስኩበት፡፡ እነርሱ ሲጨመሩበት ቀን ቀን በምንማረው የፖለቲካ ትምህርት ክፍለ ጊዜ እነዚህን ድምፆች ማዳመጣችን ከፊታችን ላይ የሚታወቅብን እየመሰለን መደንገጥ ጀመርን፡፡ ይህንን ሁሉ ግን እንኳን ለምንወዳቸው የህብረተሰብ መምህራችን ለጋሽ ገበየሁ ይቅርና ለክፍል ጓደኞቻችንም የምናወራ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ለብዙ አመታት አብረን የተመላለስን ልጆች ብቻ ይህን ጥብቅ ሚስጢር በተዘበራረቀ አኳኋን እናወራው እንደነበር ግን ትዝ ይለኛል፡፡

 

 

Read 2277 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:00