Friday, 09 October 2020 11:04

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


                  "የታከለ ሲንድረም" ተጠቂዎች
                      (ጋሻው መርሻ)

          ተወልጀ ባደኩበት እስቴ፣ ፋርጣ፣ ደብረታቦር፣ ጋይንት፣ ስማዳ፣ እብናት፣ በደራ እና ፎገራ አካባቢ አንድ ታዋቂ አስለቃሽ አለ። ስሙ ታከለ ይሰኛል። ታከለ ታዋቂ ሰው የሞተ እንደሆን በቅሎውን ሸልሞ፣ አጭር ምንሽሩን በወገቡ ሻጥ አድርጎ፣ ፎጣውን ጭንቅላቱ ላይ በቄንጥና በዘርፍ ነስንሶ አስሮ፣ ጉሮሮውን ሞራርዶ፣ ጃሎ እያለ ህዝቡን ያስለቅሳል። መቸም አፉን ሲከፍተውና ስለ ሟች ሲተርክ እንኳን ዘመድ አዝማድ ለአልፎ ሒያጅ ባዳ እንኳን ያፈዛል። ታከለ ይመጣል ከተባለ ለቅሶው እንደ ጉድ በሰው ይጥለቀለቃል።
ታከለን ለመስማት ብሎ የሚመጣው ህዝብ ጎርፍ ነው። ታዋቂ ሰዎች ሲሞቱ ታከለ ጠቀም ያለ ክፍያ ተከፍሎት በተጠቀሱት ወረዳዎችና በሌሎችም እየተዟዟረ ያስለቅሳል። የባህር ዳሩ ፓፒረስ ሆቴል ባለቤት አቶ ጠብቀው ባሌ የሞተ እለት ታከለና ሌሎች እሱን መሰል ሰዎች፣ ለቅሶውን ሰርግ አስመስለውት ነበር። በዛች ቀን የእስቴ ከተማ መስሪያ ቤቶች ሳይቀሩ ስራ ዘግተው ነው የዋሉት። በእርግጥ ሰውዬው ለወረዳው ያደረገው አስተዋጽኦ፣ መስሪያ ቤት ዘግቶ ቢቀብሩት ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም። ከትምህርት ቤት እስከ ቤተ ክርስቲያን፣ ከመስጊድ እስከ ድልድይ ሲገነባ ነበር የኖረው።     "እኛ እንጀምረው እንጂ ጠብቀው ይጨርሰዋል" ይባል ነበር።
የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ የአቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ አባት፣ አቶ ምህረቴ አየለ (አገሬው ለምን እንደ ፈረንጅ እንደሚጠራቸው ባላውቅም፣ አየለ ምህረቴ ይላቸው ነበር። የተከበሩ ባለሃብትና ትልቅ ሰው ነበሩ) የሞቱ ቀን እንዲሁ የታከለ አስለቃሽነት ለጉድ ነበር። እኛም ለቅሶውን ለመታደም ብለን ትምህርት ቤት ዘግተን መሄዳችን ትዝ ይለኛል። በዛች ቀን ያለቀ ጥይት አንድ ደከም ያለ መንግስት ያወርድ ነበር። ታከለ ይከፈለው እንጂ የትም ቢሆን እየሄደ ህዝቤን ሲያስለቅስ ይውላል። መንግስት ያስለቀሰውን ያህል ወይም በለጥ ያለውን ታከለ አስለቅሷል ብል አላጋነንኩም።
በአማራ ፖለቲካ አካባቢም ይህ የታከለ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አሉ። "የታከለ ሲንድረም" ተጠቂዎች እላቸዋለሁ። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ማስለቀስ እንጂ ከለቅሶው ምን ትርፍ ይገኛል ብለው አያሰላስሉም። ለጠላት ትልቁ ሙዚቃ የባላንጣ ለቅሶ መሆኑን የተረዱ አይደሉም፡፡ እርግጥ ነው ህዝብ እየተበደለ መበደሉ አልገባህ ሲለው፣ ከተኛበት ለመቀሥቀስ ቁስሉን መነካካትና ማከክ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ህዝቡ ቁስል እንዳለው ከተረዳና ካወቀ በኋላ፣ ቁስሉ እንዳያመረቅዝ የህክምና ክትትል ማድረግ እንጂ ዳር ዳሩን እያከኩ ማስለቀስ ግን ዘላቂ የትግል ሥልት ሊሆን አይችልም። የህዝቡን 1000 ችግር በውብ ቃላት ቀባብቶ መንገር ቀላል ነው፤ ከባዱ ለአንዱ ችግር መፍትሄ መስጠት ነው፡፡ “መገንባት ነው ከባዱ፣ ጊዜ አይፈጅም ለመናዱ” ያለው ዘፋኝ ማን ነበር...?  የኦሮሞ ብሔርተኞች አብዝተው የቀሰቀሱትና በውሸት ያሰለፉት ወጣት፣ ስልጣን ይዞ እንኳን ራሱን የመቃወሙ ምሥጢር፤ አብዝተው ቁስሉን ማከካቸው ነው። ቁስሉ የማይሽርበት ደረጃ ድረስ ከታከከ በኋላ አገግም ብትለው እንኳ ገግሞ በጄ አይልህም።
አንዳንድ የታከለ ሲንድረም ተጠቂዎች፣ የተማሩና እድሜያቸው የገፋ ከመሆኑ አንጻር፣ አሁን ያለው ውዝፍ ትግል የእነሱ በዘመናቸው ያለመታገል ያመጣው ብልሽት መሆኑን አውቀው እንኳን አይታገሉም ወይም አፍረው ዝም አይሉም። አንዳንዱ የምናምን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ብሎ ፕሮፋይሉን ደርድሮ፣ ገብታችሁ ሥታዩት፣ ከሁለት መሥመር ዘለፋ ያለፈ ጽፎ አያውቅም። ምኑን እንደሚመራመረው ፈጣሪ ይመርምረው። በአማራ ፖለቲካ ውስጥ የራስን የማሳነስና ሌላውን የማግዘፍ ክፉ አባዜ የተጠናወታቸው "ትንንሾች" እዚህም እዚያም ለጉድ ናቸው። ትልልቅ የሚሆኑት ትንንሾች አድገው ቢሆንም ቅሉ እነዚህ ግን ራስን በማሳነስ ምን ትርፍ እንደሚያገኙ አይታወቅም። በእርግጥ የአማራ ፖለቲካ በሰው ድርቅ የተመታ ነው። ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም በደንብ ማሰብና ማሰላሰል የሚችለው ገና ፖለቲካውን በሚገባ አልተቀላቀለም።
በዓለም ላይ የተበተነው ምሁር እንኳን በዓመት አንድ አርቲክል በሚችለው ቋንቋ በአማራ ጉዳይ ላይ ቢጽፍ የት በደረስን ነበር። እዚሁ ሶሻል ሚዲያ ላይ ከተማሪዎቹ ጋር ሲሰዳደብ የሚውለው ምሁር ቁጥሩ ብዙ ነው።
ይህን ጉዳይ ዝም ብለን እንዳንተወው እንኳን የአንዳንዶች ጩኸት ከህወኃት ጋር የተናበበ መሆኑ ስጋት ላይ ይጥላል፡፡ እነ ዳንኤል ብርሃኔና  ሰናይት መብራሕቱ፣ የአማራ አክቲቪስት ለመሆን ትንሽ ነው የቀራቸው። እንደኛዎቹ ሁሉ ታከለን ሊሆኑ ምንም አልቀራቸውም። ድሮ ድሮ ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ ነበር ቁርበት አንጥፉልኝ የሚለው፤ የዛሬው ጅብ ግን እዚሁ መሆኑ ነው ነገሩን “ጠርጥር ከገንፎ ውሥጥ ይኖራል ስንጥር” ብለን በሃገሬኛ አባባል እንድናስረው ያስገደደን! ጅቡም የልብ ልብ አግኝቶ በቁርበት ፈንታ ራሳችሁ ተነጠፉልኝ ለማለት እየዳዳው ነው። የሚያነጥፈው እንጂ የሚነጠፍለት ባይኖርም ቅሉ!Read 453 times