Saturday, 28 July 2012 11:20

የንቃት ማስታወሻ አጭር ወግ

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(0 votes)

አዳም ከቤተሰቦቹ እንደተወለደ በቅጽበት ውስጥ ከጥንጡ ጭንቅላቱ ጋር የተዋወቀ አዲስ ንቃት ነበር፡፡ ያ ንቃት ዘላለምን የመተወን አቅም የለውም፤ ህይወት ሆኖ መቆየት ግን ይችላል፤ ህይወትን ተጣብተዋት የሚያዳክሟትና አወራጭተው ትርጉሟን ከሚያሳጧት ብስባሽ ባህሪያቶች ጋር ግን ምንም ህብር የለውም…እነዛ መንጠቆዎች ምንአልባት አስመሳይነት፣ ውሸት፣ መናቅ፣ መበደል…ልንላቸው እንችላለን፡፡ አይደለም…አዳም የእናቱን መሀፀን ጥሎ ሲኮበልል ያጋጠመው ንቃት፡፡ መቼም በማንም ሊተረጐም የማይችለው አይነቱ ነው፡፡ ራሱ አዳም ተመልሶ በአዲስ ንቃት ካልተረጐመው (ውስጡ ተመልሶ ገብቶ ካልኖረበት) እስከመቼም አያገኘውም፡፡

እናም ምንም ድካም ሳይጠይቅ በቀላሉ የሚኖርበትን ድንግል ንቃት እንደያዘ ህይወትን ከናቱ ጡትና ካባቱ ፍቅር ጋር አስተጋብሮ እያምሰለሰለ ወደ ሌላኛው…የሩጫ አለም የንፋስ ነፍስ ውስጥ ያለ ተነቃናቂ፣ ተንቀሳቃሽ፣ ተቅበዝባዥ ንቃት ውስጥ ሰረገ፡፡ በዛው ዘመኑ ውስጥ ቤተሰቦቹ ፍፁም ይቆጣጠሩት ነበር፡፡ የትም እንዳይሄድ፣ ከማንም ጋር የራሱ በሆኑ አማረኞች እንዳያወራ፣ ነገር ግን እነሱ (መንጋው) እንደሚያወሩት እንዲያወራ አድርገው እያሳደጉ ስውሩን…ለልጅ ብቻ የሚቆፈረውን መቃብር በሀይለቃላቸው ቆፈሩበት፡፡ የመጀመሪያው የንቃት ሀይል ፍፁም አደገኛነቱ ለትዝታ እንዳይመች ተደርጐ በፈጣሪ መሰራቱ ነው፡፡ ሁለተኛውና ይሄኛው ንቃት ግን ቆሻሻን መለቃቀም ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሊያይና ሊያስተውል የሚችለው የቆሸሸውን ብቻ ነው፡፡ ቆሻሻነቱን የሚያውቀው ደግሞ የለቃቀማቸው እይታዎችና ቃላቶች ውስጡ ገብተው ምቾቱን ሲነጥቁት ነው፡፡ የተረበሸው ትዝታው ላይ ባለ አቅም ማጣት በዘማቾቹ ሲደሰቅ የማያውቀውን እየሆነ የማያውቀውን እያወቀ መኖሩን ቀጠለ…

አዳም አስተዋይ ልጅ ነው፡፡ አስተዋይ ያደረገው ከቤት ሳይወጣ መጽሐፎችን ብቻ በማንበብ ጊዜውን እንዲያሳልፍ በወላጆቹ ስለታዘዘ ነው፡፡ መጽሐፍ አንብቧል፡፡ መጽሐፍት ደግሞ ችግራቸው መቅረጽን ብቻ ነው የሚያውቁት…በየትኛውም አመክንዮ ውስጥ ይከቱና የሆነ ሰው ያደርጋሉ፡፡

…መፅሐፍት “ምንም” መሆን አይችሉም (ያለምንክንያት አልተፃፍንም ምናምን አይነት መፈክር አላቸው)  እናም አዳም ከሚያነባቸው ገፆች ውስጥ አድሮ ወደ ሆነ…ወደ አዲሱ የንቃት አለም የቀላቀለው የነፃነትን ጥልቅ ሚስጥር የተገነዘበ እለት ነው፡፡ ምንድን ነው ነፃነት? ብሎ ጠየቀ፡፡ መልሱ ምንአልባት የትም ቦታ ነበር፡፡ አንዳንድ ያልተገሩ፣ ስርዓት አልበኛ መልሶች ደግሞ አሉ፤ በግድ አስገድደው፣ ምክንያታቸውን በደንብ ሳያስረዱ ዘው ብለው ከስሜት ጋር የሚቀላቀሉ…ታዲያሳ፤ የነፃነት ትርጉማቸው ሄዶ ያለምንም ተጨባጭ ማብራሪያ ከአዳም ስሜት ውስጥ ተተረጐመ፡፡ አዳም እንደመሰለው መኖር እንዳለበት ያስረዳውና የፈጠረው ሶስተኛውና በቤተሰቡ የአኗኗር ስሌት የተመተረው የንቃት ረቂቅ ውስጥ ሰፈረ፡፡

ምንአልባት፤ ይሄኛው ንቃት ውስጥ ያሉ የመኖር እንቅስቃሴዎች ትዝታ የመሆን አቅማቸው ሃያል ነው፡፡ የአዳም ትዝታ ምንድን ነው? ለቤተሰቦቹ ነፍሱን አስጐንብሶ ሰጥቶ ያለፍቃድ ሲከረከረሙት በነሱ ቃላት ህይወቱን ማስዋብ፣ ሊሄዱበት ሲሉ እረስተውት ያመለጡዋቸውን ቅንጥብጣቢ ልምዶች በግዳጅ ለሚድኸው ማንነቱ ለዘላለም አበድረውት እሬት እሬት እያሉት የግሉ በሆኑት ደቂቃዎቹ ውስጥ ከቷቸው መኖር፣ ብቻውን ያለወንድም ያ ለእህት ያለጓደኛ አይቷቸው በማያውቅ ፀሐፊዎች የህይወት ቅኝት መቃኘት፣ የራሱ የሆነ ሙዚቃ ሳይኖረው በሌሎቹ አንደበት ተደግፎ እንግዳ ድምፆችን በነፍሱ እየጮኸ ሁሌ ለራሱ በራሱ እንግዳ መሆን…፡፡ ያሁኖቹ ትዝታዎች እንደመጀመሪያው ንቃት ሳይታወሱ ነገር ግን እየፈጠኑ የሚሄዱት አይደሉም፤ አሁን ሁኔታዎችን ማየት ጀምሯል…አዳም፡፡

የአዳም ነፍስ የሚያምመው በቀኖች ውስጥ ነው፤ ቀኖቹ የሚደግፉት የሚመስለውን መገለጥ እየተንደረደረ ይዞ መኖር ነው ህይወቱ፡፡ ስለዛም አዳም መቼም ጓደኞች ያዘ፡፡ ቀኑ ነው ያመጣቸው…ጓደኞቹን፡፡ ስለሁሉም ነገር ሊያወሩለት ሲሉ አመናቸው፡፡ ማውራት ሲጀምሩ መከተል …አብሯቸው የተሸከመውን በሚኖሩት ህይወት ውስጥ ለማቅለል…የነፃነት ባለቤት እንደሆኑ አምኖ ለአፍታ የቀድሞ ህይወቱን ጠላው፡፡ በመሆኑም ቀኑ ላበደረው፣ አዲስ አይነት ህይወት ይዘው ለመጡት ጓደኞቹ ቀሪውን የንቃት ጊዜውን ሊያሳልፍ ወደደ፡፡

ያቺ የእሳት ነፍስ ተምሳሌት ያላት ህይወት እጅግ ትበርዳለች፤ ማንዘፍዘፏም ሲያይል ቃላትን ከምላስ ጀርባ ትደብቅና ማየትን ብቻ በተሻለ መልኩ ታስለምዳለች፡፡ በመጀመሪያ አዳም ጓደኞቹ የሚያደርጉትን ነገር በሙሉ ተመለከተ፤ አዲስ ነው፡፡ ይሁን አለ፡፡ በጣቶቹ መሀል ሲጋራ ከቶ በከንፈሩ መማገድ ጀመረ፡፡ ቤተሰቦቹ ይህችን ሙድ አላሳዩትም፤ በፊትስ ጨካኝ ስለነበሩ ለሱ መልካም ማድረግ ስለሚደብራቸው እንደሆነ ገመተ…ሲጋራ ገዝተው ያልሰጡት፡፡ እነዚህ ጓደኞቹ ግን ይወዱት እንደሆነ መጠራጠር አልፈለገም፡፡ ሁሉም ነገራቸው የሚያድገው በነፃነት ነው አለ፤ ፀጉራቸው የትም ድረስ ሄዶ አየሩን ሲኮሰኩሰው ቢመለከት ሃያል መስለው ታዩት፡፡

በአንደኛው ቀን ከዛው እሳት ንቃቱ ሳይነቃነቅ ትክዝ ብሎ ሲጋራውን እየማገ አንዲት ቀጭንና ጠንካራን ጥያቄን ጠየቀ…እኔ የማን ነኝ? አለ፡፡ የመብትን ትርጉም ቀለል አድርጐ ሲጋራ እየማገ ተረጐማት፡፡ እኔ የራሴ ነኝ አለ፡፡ ይህን ባለ ቅጽበት የቤተሰቦቹ ግዙፍ እብደትን መሀይምነት ፍንትው ብሎ ታየው፡፡ ምን አይነት ቀሽሞች ናቸው አለ፡፡ ሲጋራው እንዳያልቅበት አድርጎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቤተሰቦቹን ናቃቸው፡፡

ቀስ በቀስ በአዳም አፍ ላይ የማይሰለቹ ጭሶች በተደጋጋሚ መታየት ጀመሩ (እነዛ ጭሳች የሚያልቀሱ መሰለኝ)፡፡  አንዳንዶቹ ከፅዕረ አርያም ይደርሰኛል ሲሉ፤ በእሳት የሚማግዱት፣ አንዳንዶቹ የህይወትን ርዝመት የማሳጠር አቅም አለው እያሉ የሚጎተተውን ህይወታቸውን የሚያፈጥኑበት፣ ሌሎች በጭስነቱና ውስጡ ስላለው ነፍስ ስለተነገረለት ዝና ሲሉ የሚያጨሱትን … ዕፀ ፋሪስ፡፡ አዳም ረቂቅነቱን ከዕፀ-ደብዳቤ ግዙፍ መፅሀፍ ደጃፍ ደርሶ ሳይተረጉም ለአመታት የተነጠቀውን፣ ለሱም እንግዳ የሆነውን ሳቁን ሊያስመልስ ማጨስ ጀመረ፡፡ እያጨሰና እየሳቀ ብዙ አመታትን ከጥርሱ መግጠጥ ባላለፈ አሰለፋቸው፡፡

ቤተሰቦቹ የትስ ቢፈልጉት አዳም አጠገባቸው ጠፍቶ ነበር፡፡ የበፊቱ ቁጣቸውን ሲሰነዘሩ ቃላቸው አየር ላይ ውልክምክሙ እየወጣ ተንደፋድፎ ድራሹ ይጠፋል፡፡ የበፊቱ ፊታቸው ቅርፁን ሳይለውጡ አይኑ ስር ቢደቅኑበት አዳም እየረገመው … እየገረመው… እየገረመው… ይስቃል፣ ምን እያደረጉ ነው? እያለ፡፡

የሆነ መጨረሻ የሚባል ቦታ ጋር ሲደርስ አዳም ከቤቱ ወጥቶ መንገድ ለመንገድ መሄድን መረጠ፣ ማምለጥ ፈለገ፣ ቤተሰቦቹ ካልተለወጡ እሱ ሲለወጥ፣ እነሱ መሳቅ ካልቻሉ እሱ ብቻውን ሊስቅ፣ እነቡ መቀበል ካልቻሉ እሱ እነሱ የማያውቁትን መሆን አማረውና ጥሏቸው ወጣ፡፡ ወጥቶም ፍፁም ሌላ ፍፁም አዲስ ከሆነ ሰዎች ጋር ተዋወቀ፡፡ እነዛም ሰዎች አዳምን ሲመለከቱት ንፅህናው አየለባቸው፡፡ ንፁህነትን ሁልጊዜ  አይወዱት … ንፁህነት ግን እንዴት ይጠላል? ምን አልባት ጠልተውት ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ወደ ሌላ ነገር ሊለውጡት አማራቸው፤ የበለጠ ነፃ ለማድረግ ይሆናል አላማቸው፡፡

ከራሷ ለምድር የተደበቀ ከመሰለ የሰፈር ስራስር ውስጥ ወስደው ከአንድ የተጨማለቀ ጨለማ ከከበበው ቤት ውስጥ ከተቱት፡፡ መከራን መልመድ ምን እንደሆነ መናገር የማይችለውን ንፁህ ክንዱን ብቻ እንዲያበድራቸው ጠየቁት፣ አዳም የኔ ነፃ ነበር … ክንዱን ሰጣቸው፤ አንዳች መርዝ ነገር በክንዱ በመርፌ አድርገው ለቀቁበት፡፡ አዳም…አዳም…አዳም፡፡

የቤቱ ሰራተኛ መጥቶ በቶሎ እንደሚወጣ ነው የምትናገረው፣ ቤተሰቦቹ የሚሰሙት ደግሞ ናፍቆት የምታባለዋን ህላዌ ነው፡፡ አዳም ግን አለኝ የሚለውን ንብረቱን እያወጣና ሸጦ እየጨረሰ ነበር፡፡ ልብሶቹ እየተሸጡ ባለቁ ቁጥር የአዳም ክንድ ላይ ያለው  የመርፌ ማስረጊያ የደም ስር ቱቦ ወንፊት ወደ መሆን ይቀየር ጀመር፡፡ ክንዶቹ አልቅሰዋል እኮ … አልቅሰዋል … አዎ አልቅሰዋል፡፡

ከመርዛማው ፈሳሽ ጋር ያስተዋወቁት የነፃነት ጓደኞቹ አሁን አብረውም የሉም፤ አብረው መሆኑን ጠልተው ሳይሆን ፈርተውት ነው፡፡ አዳም አስፈሪ ሰው ሆነ፡፡ በግድ በግንባሩ ቆዳ ተቆጣጠረ፤ በግድ ያየውን ነገር መጥላት ጀመረ … ሳይፈልግ መጥላት ጀመረ፤ በግድ አለማፍቀርን አፈቀረ፡፡ ፍፁም አደገኛ ሰው ሆነ… ፍፁም… ይህ ንቃት…

የቤቱ ውስጥ ንብረት በሙሉ ቢያልቅ ያለውን ልብስ ሙሉ በሙሉ አውልቆ ሲያደርጉት እንዳየ ልብሱን ከበንገድ ዳር አንጥፎ በሀልይ እየጮኸ ይለምን ጀመር፤ ወንድ ልጅ ሲከፋው የማይወደው በሙሉ ያለውን እየጣለበት ያልፋል፡፡ አዳም እየራቀ ይሄድና … እየራቀ ይሄድና …

ዛሬ አዳም ቢለምን፣ የሚለምነው በገዛ የህይወት ታሪኩ ተደናቅፎ ከወደበቀት አፈር ውስጥ ያሉትን ምስጦች ነው፡፡ … ሬሳዬን አትብሉት፣ መኖሬ ይቆይልኝ እያለ … ነፃነት የማያውቁትን፣ ቤተሰቦቼን የመሰሉ ምስጦች አለ አግባብ ካለው… ከጥቃቅኑ ሲቀናንሱበት ነው የሚማረረውና የሚለምነው፡፡ የቀብሩ ቀን ማንም አልመጣም፡፡ ማንም መጀመሪያ አልነበረም ነበር … ርቆ ነበር የተፈጠረው … ከሁሉም ርቆ፡፡

የወንድ ልጅ ጉዞ ወዴት ነው? ይሄን ግለቱን የሚያቀጣጥለው ሀይልስ ማርገብገቡን የሚያቆመው መች ይሆን? ቤተሰብነት ትርጉሙ ምንድን ነው? እንደ አዳም ህይወት የሚመላለሱ ሌሎች ነፍሶች ጥያቄያቸው የሚገምረው ትዝታ መሆን ከሚጀምረው ሁለተኛዋ ንቃት ላይ ነው… ጥያቄው የተመለሰላቸው የሚራመዱበትን ይፈጥሪሉ፤ ጥያቄውን ያላገኙ ወይም በግድ ህይወት የመለሰችላቸው ደግሞ ስለ አዳም እያለቀሱ፣ አዳምን እየሆኑ፣ ከአዳም ጎን ያንቀላፋሉ፡፡

 

 

Read 4008 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:28