Print this page
Wednesday, 14 October 2020 00:00

ኮሮና በመላው አለም ከ760 ሚ. በላይ ሰዎችን ሳያጠቃ አይቀርም ተባለ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ከአለማችን ህዝብ 10 በመቶው በቫይረሱ እንደተያዘ ይገመታል

           ኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ አገራትና አለማቀፍ ተቋማት ከሚናገሩት በ20 እጥፍ ያህል የሚበልጡ ወይም ከ760 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቷል የሚል ግምት የሰጠው የአለም የጤና ድርጅት፣ በመላው አለም ከአስር ሰዎች አንዱ ወይም ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ 10 በመቶ ያህሉ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅቶ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል፡፡
በአለም የጤና ድርጅት የድንገተኛ ጉዳዮች ሃላፊ ዶ/ር ማይክ ራያንን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው፣ ድርጅቱ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግና መረጃዎችን በመሰብሰብ ባስቀመጠው ግምት፤ 10 በመቶው የአለማችን ህዝብ በቫይረሱ ሳይጠቃ አይቀርም ብሏል። በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በቀውስ ውስጥ የምትናጠው አለም፣ ወደ ከፋው ምዕራፍ እየገባች ነው ያሉት ዶ/ር ማይክ፤ በደቡብ ምስራቅ እስያ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአውሮፓና ምስራቅ ሜዲትራንያን አካባቢዎች ደግሞ ስርጭቱና የሞት መጠኑ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
ወርልዶሜትር ድረገጽ ያወጣው መረጃ እንደሚለው፤ ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም 36.52 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን በማጥቃት 1.06 ሚሊዮን ያህሉን ለህልፈተ ህይወት ሲዳርግ፣ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 27.48 ሚሊዮን ያህል ደርሷል፡፡ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ አሜሪካ በ7,787,879፣ ህንድ በ6,841,813፣ ብራዚል በ5,002,357፣ ሩስያ በ1,260,112 እንዲሁም ኮሎምቢያ በ877,683 የቫይረሱ ተጠቂዎች እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም መረጃው ያመለከክታል፡፡
ወረርሽኙ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ በአፍሪካ አገራት በድምሩ ከ1.54 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱትና ወደ 38 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ኦልአፍሪካን ዶት ኮም የዘገበ ሲሆን፣ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር በአንጻሩ 1.28 ሚሊዮን ያህል መድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሰሃራ አገራትን ኢኮኖሚ ዕድገት በ3.3 በመቶ ያህል እንደሚቀንሰውና 40 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያንን ወደ ከፋ ድህነት ሊያስገባ እንደሚችልም የአለም ባንክ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተዳምሮ፣ በመላው አለም 115 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ወደከፋ ድህነት ያስገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአለም ባንክ ማስታወቁን የዘገበው ቢቢሲ፣ በአለማችን በቀን ከ1.9 ዶላር በታች ገቢ የሚያገኙ ወይም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር በመጪው አመት 150 ሚሊዮን ያህል ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡



Read 14481 times
Administrator

Latest from Administrator