Print this page
Saturday, 10 October 2020 13:30

በአንድ ዓመት የተጠናቀቀው እንጦጦ ፓርክ ዛሬ ይመረቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • በኢትዮጵያ ግዙፉ የአርት ጋለሪ ይከፈታል
           • በኮሮና ህይወታቸው ላለፈ ሃኪሞች መታሰቢያ ይደረጋል


           በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፓርክ ዛሬ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና የውጭ አገር ዲፕሎማቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል።
ግንባታው አንድ ዓመት ተኩል ገደማ የፈጀው የእንጦጦ ፓርክ፤ በ5 የግንባታ ሳይቶች ላይ በርካታ መዝናኛዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
በአጠቃላይ 29 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተነገረለት ከእንጦጦ እስከ አቃቂ የሚዘልቀው የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፓርክ ከ2 መቶ አመታት በላይ የቆዩ ታሪካዊ ቅርሶችን ያካተተ ከኢትዮጵያ ግዙፉ የአርት ጋለሪ የሚገኝበት ሲሆን የአርት ጋለሪ ከዛሬ ጀምሮ ለጐብኚዎች ክፍት ይሆናል ተብሏል።
በ5 ሳይቶች ተከፋፍሎ የተገነባው የእንጦጦ ፓርክ፤ በውስጡ የፈረስ መጋለቢያ ሜዳ እስከነ ፈረሶች ጋጣው፣ ባህላዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና በቀድሞ ነገስታት  የግብር አዳራሽ አምሳል የተሰሩ ባህላዊ ምግብ ቤቶችን ጨምሮ ዘመናዊ ካፊቴሪያዎች እንዲሁም ለጥንዶችና በቡድን ለሚዝናኑ የተዘጋጁ መናፈሻዎች፣ የህዋ መመልከቻ ማማና፣ የብስክሌት መጓጓዣና ሌሎችንም ይዟል።
በፓርኩ ውስጥ የአርት ጋለሪውን ጨምሮ በልዩ ዲዛይንና ጥበብ የተሰሩት ህንፃዎችና ቅርፃ ቅርፆች በሙሉ የኢትዮጵያውያን ጥበበኞች የእጅ ውጤት መሆናቸውም ተነግሯል።
ከነገ እሁድ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ጀምሮ ለጐብኚዎች አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው የእንጦጦ ፓርክ በዛሬው እለት ሲመረቅም፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ የህክምና ባለሙያዎች ልዩ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ይካሄዳል ተብሏል። የሙዚቃና የተለያዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች የምረቃ ስነ ስርዓቱ አካል ይሆናሉ ተብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት በተጀመረው የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት እስካሁን ሦስት ፓርኮች የተመረቁ ሲሆን እነሱም የእንጦጦ ፓርክ፣ የአንድነት ፓርክና የወዳጅነት አደባባይ ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ የአድዋ ማዕከልን ጨምሮ በግንባታ ላይ የሚገኙ በርካታ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ሲሆኑ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በክልሎች እንደሚጀመሩ ታውቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ወንጪ፣ በደቡብ ኮይሻ፣ በአማራ ጐርጐራ ላይ ዘመናዊ የቱሪዝም ፓርኮች የሚገነቡ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ገንዘብ ማሰባሰብያ “ገበታ ለሀገር” የተሰኘ መርሃ ግብር ተዘርግቷል።

Read 5367 times