Print this page
Saturday, 10 October 2020 16:15

ከልብ ወለድ ባሻገር

Written by  ሻሎም ደሳለኝ
Rate this item
(6 votes)

 "--አብሮ መቆም ትከሻ መለካካት መስሎናል። ካልተጠፋፋን መኖር የምንችል አይመስልም። ይህ ደሞ ሰላምና ፍቅር በሚሰብኩ የእምነት ተቋሟት ዘንድ ተግባራዊ ሲሆን ትርፉ ተስፋ መቁረጥ ነው። “ሐሰተኛው በእምነት ስም” ይህ ማህበረሰባዊ ችግራችን ላይ የድርሰትን ጠሀይ አውጥቶ በገሀድ እንድንፈታተሽ ፤ በሀቅ እንድንተዛዘብ እድል የፈጠረ ስራ ነው። --"
    
           “ Joseph Conrad: ‘My task which I am trying to achieve is, by the power of the written word, to make you hear, to make you feel-it is, before all, to make you see. That-and no more, and it is everything.’”
ዓለማየሁ ገላጋይ ገጣሚ ቢሆን ብዬ ተመኝቼ አውቃለሁ። የ’ዚህ ድፍረቴ ምክንያት ግን ገጣሚነቱን አለማወቄ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ከላይ የጠቀስኩት የጆሴፍ ኮንራድ ንግግር፤ ለድርሰት በቅጡ የሚስማማ ነው፤ በተለይ ለግጥም። ዓለማየሁ ደሞ በቃላት ምስል የሚፈጥርና በከች አርጌ ቃላት ካባ የደፋ ደራሲ ነው። ከዓለማየሁ ውጭ ልቦለድ እንደ ግጥም ተፅፎ ያየሁት በ Edmond Rostand ተደርሶ፣ በባሴ ሀብቴ የተተረጎመውን Cyrano De Bergerac የተሰኘውን መጽሐፍ ነው።
ዓለማየሁ ቃላቶቹ ከች አርጌ ብቻ አይደሉም። ጦፊጥ ጭምር ናቸው። ምሰላውም “ገፀባህሪያቱንና መቼቱን” እንድንረሳው እድል የሚሰጥ አይደለም። ለምሳሌ ያህል የበፍቅር ስሙን፣ የአቶ ቢዘንን የቤት አቀማመጥ ማንሳት እንችላለን። ያንን ድርሰት ያነበበ ሰው፤ “አንበሳ የከተማ አውቶብስ” ባየ ቁጥር የእነ ታለ ቤት ትውስ ላይለው አይችልም። የዓለማየሁ ብዕር የሰዓሊ ብሩሽና ቀለም ነው። ተደራሲዎቹም ማተሚያ ቤቶቹ ነን። አዕምሮና ልቦናችን ደግሞ የህትመቱ ማረፊያ ወረቀቶች። ከጥቂት አመታት ወዲህ  ድርሰቶች የተለየ መልክ መያዝ የጀመሩ ይመስላል። ለጥናትና ምርምር የዋለ የጊዜ ወዘና መፅሐፎቹ ላይ አርፈው አይተናል።
እርግጥ አንዳንድ ደራሲያንና የልቦለድ አድናቂዎች Research ተኮር የሆኑ Expermental Novel አይነት ድርሰቶች ጣዕም ሲሰጧቸው አይታይም። ነገር ግን አድካሚና በአግባቡ ከተኳለ፣ ለማህበራዊ ሂስ አቻ የሌለው መሳርያ ነው። ጋሽ ስብሃት በተደጋጋሚ፤ ድርሰቶቹ ሁሉ ለመዝናኛነት (Entertainment purpose) የተፃፉ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል። ዓለማየሁ ገላጋይ ግን በ"ሐሰተኛው በእውነት ስም" ስራው ላይ አላማ አድርጎ የተነሳው አብይ ጉዳይ እንዳለ ያሳብቃል። እሱ ራሱም አንድ ሁለት ቃለ መጠይቆች ላይ ሲናገር ተደምጧል። “ከደስታ ባለፈ” የሚለውን “የማንይንገረው ሸንቁጥ” የመጽሐፍ ርዕስ በተዛምዶ ቃላት ልተካና ዓለማየሁ ገላጋይ “ከልቦለድ  ባሻገር” ሀገር በቀል እምነቶችን የማስተዋወቅ ሚና መጫወት ዋነኛ ግቡ ሆኖ ተስተውሏል።
እርግጥ አለማየሁ የመጀመሪያው ሰው አይደለም። በድርሰቱ ውስጥ የተገለፀው የጋሽ ፀጋዬ ገ/መድህን “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” አንዱ ማሳያ ነው። በፀፀት የኋሊት ተጉዞ የልጅነቱን ዘመን እያስታወሰ፣ አቴቴን ሲያወድስ ታይቷል። ከፀጋዬ ባልተናነሰ ደግሞ ገጣሚና ጋዜጠኛ ሰሎሞን ዴሬሳ፣ ሁለት ኃያላንን አቻ አድርጎ “ቀለም” በተሰኘ የዘበት ዕልፊቱ ስብስብ ግጥሞቹ ውስጥ አሳይቷል።
“ከንግዲህ
አቴቴ ጨሌ ሲፈስባት
ከብርሃን የሳሳ ግልበብ ጋርደንላት
ቄጠማ ጎዝጉዘን ቀለም እንርጭላት…
እንቁ ሶፈር የሰማየ ሰማያት ‘ንባ
ኒል የወላዲተ አምላክ ካባ…
ዝርዝር አለፍ፥ እልፍ አእላፍ ቀለማት
እንደ አክርማ ስፌት፥ እንደ ስንደዶ ጥልቀት
ለአቴቴ ይረጭላት፥ እንደ ሀቅ ተረት”  (ገፅ-30)
ታሪካችን ሁሉ አንደኛ የማይወጣበት እሽቅድድሞሽ ነው። ፃድቁም-ሀጥዑም አትሌት ነው። እጁ ላይ ያሰረው ሰዓት ከፋሽንነት አይዘልም። ደቂቃም ሆነ ሰዓት አይመዘግብም። የተወለድንበትን ቀን የሚተርኩልን ሰዎች እንኳ ምልክት የሚያደርጉት “የአያ እከሌ ላም ላስረኛ ግዜ የወለደች ሰሞን” አይነት ነው። ቅብብላችን ቃላዊ። ከአፍ ለአፍ ያልተፋታ። የዚህ ውጤት ደግሞ እንደ ዮናኤል ልቦለድ የታሪክ ኀሰሳችንን “ከፍፃሜው ወደ ጅማሬው” እንዲሆን አድርጎታል።
ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም አንዱ ግን “ጎን-ለጎን የማያኳሁን ቀጭን መንገድ (ገፅ-61)” መምረጣችን ነው። አብሮ መቆም ትከሻ መለካካት መስሎናል። ካልተጠፋፋን መኖር የምንችል አይመስልም። ይህ ደሞ ሰላምና ፍቅር በሚሰብኩ የእምነት ተቋሟት ዘንድ ተግባራዊ ሲሆን ትርፉ ተስፋ መቁረጥ ነው።
“ሐሰተኛው በእምነት ስም” ይህ ማህበረሰባዊ ችግራችን ላይ የድርሰትን ጠሀይ አውጥቶ በገሀድ እንድንፈታተሽ ፤ በሀቅ እንድንተዛዘብ እድል የፈጠረ ስራ ነው።
ደራሲው ዓለማየሁ ገላጋይ፤ ለድርሰቱ በሰጠው ስያሜ በኩል ብዙ የሚነግረን ሀቅ አለው። ከላይ እንደ መግቢያ የተጠቀምኩት የገጣሚ ሰሎሞን ዴሬሳ ስራ ላይ ሁለት የማይገናኙ ኃያላን ሴቶችን አንድ መጎናፀፊያ ሲያለብሳቸው አስተውለናል፡፡ ያውም ነገረ ስራችን ሁሉ “ታቦት-ከጣኦት” ምን ህብረት አለው? ተብሎ በሚታሰብበት ከበብ ውስጥ:-
“እንቁ ሶፈር የሰማየ ሰማያት ‘ንባ
ኒል የወላዲተ አምላክ ካባ…”
ብሎ የማርያምን ካባ “እንደ አክርማ ስፌት፥
እንደ ስንደዶ ጥልቀት ለአቴቴ ይረጭላት፥
እንደ ሀቅ ተረት”
--እያለ የተለያዩትን ሲያቀራርብ፤ የማርያምንም ለአቴቴ ሲደርብ እናያለን።
በ"ሐሰተኛው በእውነት ስም" ውስጥ እንደ ዘይትና ውሃ ሁለት የማይስማሙ ቃላት በስያሜ ክር ተሰፍተዋል፤ ባንድ ውለዋል። “ሀሰት” እና “እምነት”። ወደ ውስጥ ስንዘልቅም የምናገኘው ይሄንኑ ነው። ነፀብራቅ እና ናትራን፣ አላዛር እና አሮን፣ ኤልዛቤል እና ሠርዌ ተፋላሚያን ናቸው። በገፀባህርያት ብቻ አይወሰንም። በመቼትም ጭምር እንጂ። ቅንብቢት ውስጥ እንኳ ቅ/ልደታም፤ ጠንቋይ ማረፊያም በአቻነት ተሰይመዋል። ጠጅ ሳር፣አርቲ፣ ከሴ ብቻ አይደለም፤ የባህር ዛፍ ዝንጣፊም ብቅ እንቅን ከሙታን ከተማነት ሲታደጓት ይታያል።
ሠርዌ እንደ መናኝ ነው። እሱ እንደ አቡነ አረጋዊ፣ ባይጡ እንደ ዐይናቸው፣ ችምቻሚው እንደ ዐይን ውሃቸው ሆነው የተሳለ ይመስላል። አላዛር ላጽቂት ደሞ እንደ ቁራ። በሌላ በኩል ቃሊቲን ማየት ይቻላል። ለደግነቷ ወሰን ላፍቃሪነቷ ደባል የላትም። ከሷ በላይ ፃድቅ ከወዴት? ረድ ሠርዌን ስታገኘው የአክብሮት ዝናብ ከአፉ ሰማይ ላይ ይዘንባል። “አይነስውሩ መላአክ!” እንዲህ ያለ መከባበር በማን ዘንድ አየን? እውነተኛ አምላኪዎች ሲገናኙ መጠፋፋት አይታሰብምና።
አሜሪካዊው Robert Ingersoll  «An honest God is the nobles work of man” ይላል ተብሎ በሩቅ ያለ ሰው እሳቤ ሲጠቀስ ታዝበናል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ተዋነይ አስቀድሞ፤
«ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ
ወ ፈጣሪ ፈጣረ ኪያሁ” ብሎ ክዷል። አላዛር ላፅቂት ምድር ከሚሰነጥቀው የፈጣሪ የግርምት ሳቅ፣ እምዬ አገሩን ሊታደግ አስቦ ይሆን ከኢትዮጵያዊው ይልቅ የአሜሪካዊውን አባባል ለንግግሩ ማጣቀሻነት የተጠቀመው? ወይስ ከተዋነይ ይልቅ ሮበርት ማንትስ ስለሚቀርበው? ለኔ ጥርጣሬ የተስማማው ምላሽ ግን የአላዛር ለገዛ ታሪኩ ባዳ መሆን የሚለው ነው።
ዶ/ር አሮን “የእምቦሳ ሰሮን” ምንነት አስመልክቶ የሰጠው ማብራሪያ፣ ለዚህ የጥርጣሬ ምላሽ እውነተኛነት ማረጋገጫ ይመስላል። ለትርጓሜው ፍቺ በአገር ተወላጅነት ለጉዳዩ ከቀረቡት ጋዜጠኞች ይልቅ ዶ/ር አሮን ልከኛው ሰው ሆኖ ይታያል። (ገፅ 51-52-53) ይሄን መሰል የምሁራኖቻችንን ሽንቆጣ፣ ደራሲው አጽንኦት የሰጠው ይመስላል። እንደ እውቀት ማህደርነታቸው፣ እንደ መጠይቃዊ አሰላስሎት ክህሎታቸው ሲራመዱ የማይታዩትን፣ "ማደግና ማወቅ የሚሰጠውን ነፃነት ተጠቅማችሁ፣ ከአሉባልታ ፀድታችሁ መርምሩ" የሚል መልዕክት ተላልፎበታል።
በቅርቡ አንዲት ሴት “እኔ ማርያም ነኝ” ብላ ተነስታ ነበር። እውነት ይሁን አይሁን የማረጋገጥ አቅም ያላቸው ሀይማኖታዊ እሳቦቱንና አስተምሮቱን የሚያውቁ የሀይማኖት አባቶች ቢሆኑም እንኳ ይህች ሴት “ማርያም ነኝ” ከማለቷ በስተጀርባ ያለውን ምስጢር ለመፈልፈል መጣር፣ የጋዜጠኞችና የአጥኒዎች ድርሻ መሆን ነበረበት ብዬ አስባለሁ። ይሄ ካልሆነ ግን በምሁራኑና በተራው ማህበረሰብ መሀል ያለው መግባቢያ አሉባልታ ብቻ ይሆናል። ድርጊቱም “ኢየሱስ ነኝ” ብሎ የመጣውን ሀበሻዊ አንገት ከቆረጡት ንጉስ ተለይቶ የሚታይ አይደለም ባይ ነኝ።
ብዙ ጊዜ በእኛ አገር ምሁራን ዘንድ (ጥቂቶቹን አይመለከትም) ሰው የለፋበትን ከመቀበል ባሻገር ተሳትፎ የማድረግና ጅምር መንገዱን ገፍቶ ሄዶ የመጨረስ ችግር ይስተዋላል። ለዚህም ይመስላል፣ ሙሴ ፀሊም “የትኛው ሀበሻ ነው እንደዚህ አይነት ትልቅ ጥናት የሰራው?… ስለ እኛ ፍልስፍና፣ ሥነፅሁፍ፣ ታሪክ፣ ሥነ ሰብ…በሙሉ ጥናቱ የባዕዳን አይደለም?" (ገፅ-53) እያለ የሚሞግተው። ይሄኔ ነው “እዚህ አገር ሰራተኛው ሳይሆን ለማኙ ነው ትጉ" (ገፅ-27) የሚለው የአላዛር ላጽቂት ስላቅ የሚጠዘጥዘን።
“መጽሐፌን ሰው ሲያይብኝ አልወድም፤ በመጽሐፌ ውስጥ እኔን የሚያዩኝ ይመስለኛል” ይሄ የአላዛር ንግግር እንደ መጽሐፍቶቹ ሁሉ የደራሲውን ማንነት አሾልኮ የሚያሳይ ይመስለኛል። ድርሰትን ከደራሲው ህይወት ጋር በቀጥታ ማገናኘት ተገቢ ባይሆንም፣ አንዳንዴ ግን አሾልከው የሚነግሩን ነገር ይጠፋው አይመስለኝም።
በዓሉ ግርማ “ደራሲው” በሚለው ስራው ላይ ጋሽ ስብሃትን ገፀባህሪ አድርጎ እንደተጠቀመው ይነገራል። ይሄን ፈለግ ዓለማየሁ በዶ/ር አሮን በኩል ያስቀጠለ ይመስላል። ሀያሲ አብደላ እዝራ፤ ከእነ መልኩ--ከእነ ፀጉሩ ተስሎ አይተናል። “ይበል!” የሚለው ማን ነበር?
ጽሁፌን ከመቋጨቴ በፊት ግን ደፋሮችንና ትጉሃንን ላመስግን፡፡ መልካም ሳምንት!



Read 2052 times