Wednesday, 14 October 2020 00:00

ለምለም ኃ/ሚካኤል - በ"ላሊበላ"

Written by  አጥናፉ - ከወልድያ
Rate this item
(1 Vote)

  የላልይበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮሐ ምድር ወደ ታች ከተፈለፈሉ በኋላ ወደ አለቱ ስር ሰደው ወደ ላይ የበቀሉ ዘመን አይሽሬ አለማቀፍ አስደናቂ ቅርሶችና ያገራችን ጌጦች ናቸው። አስደናቂነታቸው ጥቂት ቀናት አይቷቸው ለሚሄድ ጎብኝ አይደለም። እዚያው ጧት ማታ ቤተ-ጊዮርጊስ አናት ላይ ተቀምጦ እምባው ቸርፈፍ እስከሚል ፈዞ ለሚመለከታቸው የላስቴ ነዋሪም ጭምር ነው። ከቤተ አማኑኤል ግርጌ ሆኖ አንገቱ እስኪሰበር ሽቅብ እያየ ትናንት ማታ አይቶት ዛሬ ጧትም እንደገና ሲገረም ቅዳሴ የሚያልፍበትን የላስታ ሰውንም ያካትታል። ታዲያ እንዲህ ያሉትን የንጉስ ወቅዱስ ላሊበላን ፍልፍል ቤተ-መቅደሶች አንድ አላፊ አግዳሚ ወይም ጎብኝ በሁለት ባንድ ቀን ጨረፍታ አይቷቸው ሲደነቅ፣ የጠዋት የማታ ተመልካቹ “ገና ምኑ ተነካና” ብሎ በበኩሉ መገረሙ አይቀርም። ላስታ ላሊበላ ተወልዶ አድጎ በእህል ዉሃ ምክንያት ከስፍራው ገለል ላለ ሰው ደግሞ የእነዛ ቋጥኞች ናፍቆት ሲያስቸግረው ውሎ ያድራል። ይቅርብኝ ብሎ ደህና እንጀራውን ትቶት የተመለሰም አይጠፋም። እውነትም እየዋለ እያደረ ሲሄድ ይሻለዋል እንጂ፣ የመጀመሪያ ጥቂት ቀናትን ከሮሐ አይረሴ ቤተ-መቅደሶች ጋር ተለያይቶ መሰንበት ቀላል አይመስልም። ይቅር ይበለውና እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት መሳለም የለመደ ሰው ሌላ ቤተ ክርስቲያን ተሳልሞ፣ ከእግዜር ጋር የሚገናኝ የማይመስለዉ ጥቂት አይደለም።
እርግጥ ዛሬ የተነሳሁት ስለ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናቱ ለመጻፍ አልነበረም። ይልቁንስ ቅዱስ ላሊበላን ተንተርሳ በአዲስ ዘፈኗ ስለተከሰተችው የዘመናችን ዘፋኝ ለምለም ኃ/ሚካኤል ዘፈን ለመመሰጥ ነዉ። ከዘፈኗም ‹‹ላሊበላ; የተሰኘዉን ለዚያዉም ግጥሙን ብቻ እንዲህ አይቸዋለሁ ለማለት ያህል ነው። እና “አይኔ አለማየ እግሬ ደርሶ (2)…” እያልን በጭብጨባና በዝማሬ ታጅበን ወደ ላስታ ብቅ እንበል። ላሊበላ የዘፈኑ ርዕስ ሲሆን ከምስል ቅንብሩ ጋር 5 ደቂቃዎችን ይወስዳል። በግጥሙ በኩል ወንደወሰን ይሁብን። በወገብ ባንገታቸዉ ብጥስ ቅንጥስ ካሉበት እስክስታ ባዮችና ራሷን ዘፋኟን እንዲሁም በዘፈኑ የተሳተፉትን
በሙላ እጅግ እያደነቅን፣ እስቲ ግጥሞቹን አንድ ባንድ እንዝለቅባቸዉ፡፡
ቅዱስ ላሊበላ ነው አሉኝ ቤቱ
ልሂድ አይን አይኑን ልየው ማልጀ
ላስታ ላሊበላ ነው አሉኝ ቤቱ
ልንገረው በዚያው ልሳለም ሄጄ።
መቸስ በልጅነት “እኔ ማገባው ረጅም፣ ጥርሱ የሚያምር ጀግና፣ ተጫዋች፣ ትፍትፍ ቀሚስ ሚገዛልኝ...” ምናምን ያላለች ኮረዳ ተፈልጋ አትገኝም። ወንድም እንዲሁ፡፡ "..ወንዱ ልብስተ ጥላ [ምናባዊ ሴት] በሰብዓዊ ሴት፤ የሴቷ ልቡሰ ጥላ [ምናባዊ ወንድ] በሰብዓዊ ወንድ ካልተለወጠ፣ ሴትና ወንድ አንድ አካል አንድ አምሳል ይሆናሉ፤ብዬ አላምንም።›› እንዲል ዳኛቸዉ ወርቁ፣ ‹‹አደፍርስ; በተባለ የልቦለድ መጽሐፉ፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥም ለግጥሙ ገጸ-ሰብ ይሄን የመሰለው የልብ ሰው ያለው ላስታ
ላሊበላ ነው የተባለች አንደሆነ “ላስታ ላሊበላ ነው አሉኝ ቤቱ” ብላ የልቧን ሰውና ላሊበላን ባንድነት ልትሳለም አንድ አካል አንድ አምሳል ለመሆን መንገድ ትገባለች። ወደ መሀል ግድም ግን “ትዝታህ እያጀበኝ ወዳንተው መገስገሴ” የሚል ስንኝ ስለምታሰማን፣ አዲስነቷ ለላስታ ላሊበላ እንጂ የከንፈር ወዳጅነታቸዉ የሰነበተ መሆኑንም ለማወቅ ይቻላል። መንገድ የምትገባዉም …
“ልሳለም ልሳለም ውዴን
ጸሐይ ሳትወጣ ልያዝ መንገዴን
ልሳለም ልሳለም ውዴን
ውዬ ደጁ ላይ ላውጋው የሆዴን” ብላ ነዉ። መንገድ ስትገባ ጸሐይ ሳትበረታ፣ ጠራራት ሳይመታት በማለዳ ባጭር ታጥቃ የፍቅር ጓዟን አዝላ ነው፤ ብቻ በደህና ትግባ እንጂ፤ ስትደርስ ልትስም ልትሳለም ብቻ ሳይሆን ሶራ (የነገስታት ምንጣፍ) ተነጥፎላት ከደጁ አረፍ ብላ የሆዷን ልታወጋውም ጭምር ነው አሳቧ። ታዲያ በልቧ ላይ ጉብ ብሎ፡ ገደል ዳገት ያስቧጠጣት፡ ማር የሆነ የሰከነ ገላና ደርባባ የውበት ባለቤት ኖሯል ለካ። እንዲህ ከሆነ
“ማሬዋ ስክን ገላዋ
ስክን ገላዋ
ማሬዋ ደርባባዬዋ
ደርባባዬዋ” ቢባል ታዲያ ምናለበት?
ንጉስ ወቅዱስ ላሊበላ እንደተወለደ ንቦች ከበውት ስለነበር የስሙ ስያሜም ከንቦችና ከማር ጋር በቀጥታ እንደመገናኘቱ አቀንቃኟም “ማሬዋን” በማሩ አገር ማግኘቷ ቀድሞም አይቀሬ ነገር ነበረ ብንል ሳያምርብን አይቀርም። ማሬዋም ቦታዉን
አግኝቷል፡፡
ታዲያ እንደ ልደት ተሳላሚ ቀናትን ምን አልባትም ወራትን በባዶ እግሯ ተጉዛ “አይኔ አለም አየ እግሬ ደርሶ…” ካለች በኋላ የመውደድ ነገር የባሰ ጭንቅ ከጭንቅም ህመም፡ የህመሟም ስር መሰረት “አባ” ለመባል የደረሰ ጉልምስናን አልፎ፡ እንደ ማር ጠጅ እድሜው በገፋ ቁጥር፡ አናት ሚበጠርቅ መውደድ እየሆነ መምጣቱንና ስክን ገላ መሆኑ ደሞ መውደዷን እንዳባባሰባት እንገነዘባለን። የጸጸትን ክብደት ለመግለጽ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን ‹‹መዉደድ አባ ጸጸት" ሲል እንደተብሰለሰለ፡፡ እሷም ህመምን
ጨምራበት “ህመም አባ ውዴ አንተ ስክን ገላ ሆይ” ስትል፡ አባ የምናከብረዉ የበሰለ ሰዉ የአክብሮት መጠሪያ መሆኑን ባህላዊ እዉቀታችን ይነግረናል፡፡ እና ‹‹አባ›› እስከመባል በደረሰ ዉድ ፍቅር ስለምትሰቃይ ከንፈራችንን መጠን እንድናዝንላት ታደርገናለች፡፡ አክላም ‹‹ለመሆኑ የዉዶች ሁሉ ዉድ መሆንህንና ስክን ገላነትህን ታዉቃለህን?›› እያለች ለራሱ ስትነግረዉ እንሰማለን። ይሄን ስንኝ ጨምሮ ተከታዮቹ ጥቂት ስንኞች ደግሞ ቀደም ሲል “ውየ ደጁ ላይ ላውጋው የሆዴን” እንዳለችው ሶራዋ
ላይ አረፍ ብላ ያሳለፈችውንና የሆዷን እየነገረችው ነው፣ ለስክን ገላዋ: ለማሬዋና ለደርባባዋ።
የመንገዱን ውጣ ውረድ እወቅልኝ አይነት ወይም መልሱን አውቀዋለሁ ግን እስቲ ካንተ ልስማው የሚመስል “መንገድም እንዳልደክም ፍቅርህ ስንቅ አይሆንም ወይ?” የሚል ጥያቄ ጣል ታደርግለታለች። ግንኮ በሱ ፍቅር ጉልበት በርትታ እዚህ እንደደረሰች ራሷ አሳምራ ታውቀዋለች። ያዉ ጀምበሯን በምዕራብ ደጃፍ እያየናት ‹እስካሁን ቀን ነበረ ማለት ነዉ› ብሎ እንደመጠየቅ አይነት። እሱ ደግሞ መልሱን ራሷ እንደምታዉቀዉ ያዉቃልና “ኧረ ይቺ ልይ ዛሬ” ብሎ አንገቱን ሰበር: ጥርሱን ገለጥ አድርጎ ዝም ሲል ሊታየን ይችላል። መለስ ትልና ደግሞ “ትዝታህ እያጀበኝ ወዳንተው መገስገሴ” እያለችዉ ጥንዶቹ ጨዋታቸዉን ይቀጥላሉ። በዚህ ስንኝ ደግሞ የፍቅራቸዉ ጅማሬ ቀደም ያለ እንደነበር ድንገት ስሙት ተብለናል። እንግዲህ ግጥሙ ዉስጥ ባልተገለጠ አጋጣሚ ተለያይተዉ ኖሮ ያለበትን በወሬ ሰምታ "ቅዱስ ላሊበላ ነው አሉኝ ቤቱ" ትልና ወደ ቀየዉ አቅንታ እናገኛታለን። ስታቀናም ለነፍሷም ለስጋዋም ነዉ፤ ‹‹አንድም ለስጋዬ ነው አንድም ደሞ ለነፍሴ” እንዳለች። "ለነፍሴ" ስትል ሁለት ጉዳዮችን ለመግለጥ አስባ
እንደተነሳች ልብ ይሏል። አንድም ዳግማዊ ኢየሩሳሌምን ተሳልማ፣ በሰማይ አገር ለነፍሷ ስንቅ ለማስቀመጥ፤ ሁለትም ጥማችንን አርክተን ረሀባችንን አስታግሰን ‹‹እሰይ ነፍሴ ገባች; እንደምንል ነፍሷን ለማግባት ስትል ነዉ ወደሱ የገሰገሰችዉ። ግስጋሴዋም በብርታት ሲሆን መበርታትም ለሷ ወደሱ መምጣት ነዉ። እናም ደጋግማ ‹‹በረታሁ በረታሁ፣ ወዳንተ መጣሁ›› ብላ ትነግረዋለች።
አስቀድማ አንድም ለነፍሴ ብላለችና ለነፍሷ ስትል ‹‹ልሳል ልሳለም ቅዱስ ንጉሱን፤ ያውቀዋል ባንተ አንጀት ማራሱን›› ብላ ከአስራ አንዱ ዉቅር አብያተክርስቲያናት አንዱን ብትሳለም በሱ በወዳጇ በኩል የለመነችዉ ይሆንላትና ስለቷን
ለማስገባት ደግሞ እንደገና በሌላ ቀን ‹‹ጸሐይ ሳትወጣ ልያዝ መንገዴን; ለማለት ዘዴ እያመቻቸች እንደሆነ አይተን እንዳላየ እናልፋትና ወደ ቀጣዩቹ ስንኞች እንሰግራለን። ትቀጥልና “መንገድም እንዳልደክም ፍቅርህ ስንቅ አይሆንም ወይ?” ስትል ቀደም ባለዉ በዚህ ስንኝ መልሱን የምታዉቀዉን
ጥያቄ እንደጠየቀች ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ‹‹እያለኝ ልቤ አንድ አንተን ፍቱን፤ እንደምን ልፍራው ገደል ዳገቱን›› ስትል እነሆ መልሱን ራሷ ይዛ ከተፍ ስትል እጅ ክንጅ ትጨበጣለች። አሁንስ ቢሆን ህመም የከረመበት ሰዉ፡ ብቻ መዳኒት አለ ይባል እንጂ፡ ነፍሱን በጨርቁ ጫፍ ወገቡን ደግሞ በገመድ ተቋጥሮ፡ የደብረ ዳሞን አስፈሪ ገደል እየተንዘፈዘፈ ከመንጠላጠል ማን ሊመልሰዉ ይችላል? አንግዲህ ብለን ብለን ወደ አዝማቾቹ ዘንድ ደርሰናል፤ አዝማቾቹን እንዝለላቸዉና ወደ ዘማቾቹ ታጥቀን እንዝለቅ፡ ካልሆነም ነጠላችንን አጣጥለን ወደ ደጀሰላም።
‹‹ደጀሰላሙ ላይ ትቸው ለአምላክ የነፍሴን›› ፡ ካህናት መክፈልት (ህብሰተ-መና)
የሚቋደሱበት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚሰራ ነዉ ደጀሰላም። እና በነፍሷ ለመታሰብ፡ እህል ዉሃ ነገር እነሆ ብላ ወደ መስኩ ጉራ ማለቷን እየነገረችን እንደሆነ ለማሰብ ይቻላል። ነገር ግን ደጀሰላም የተባለዉ ማህሌት ለማለት ተፈልጎ ሊሆን እንደሚችል የመጠርጠር መብታችንን ተጠቅመን እንጠረጥራለን (በደጀሰላም ትይዩ የሚታየዉ ምስልም ማህሌት ነዉ)። እና እዚህ ግድም
ፍንትዉ ማለት የነበረባት ነገር ነበረች ለማለት ያህል ነዉ ከተሳካ፡፡
ጥርጣሬያችንን እዚሁ ደጀሰላም ትተን ‹‹ውዬ አብሬው በመስኩ ሳድብ ሳድስ መንፈሴን›› ትበለንና ወደ መስኩ አብረናቸዉ ጎራ ብለን መንፈሷን ወደ መስኩ ነፍሷን ደግሞ ወደ ደጀሰላሙ፡ ለየብቻ ስታሰማራቸዉ አይተን እንገረም። ምናልባት መገረማችን የሚነሳዉ፡ ነፍስና መንፈስን ለመለያየት የሚበቃ ብቃት ከማጣት ወይም ቀድሞም ነፍስና መንፈስ እንዴት ተለያይተዉ መንገድ ይገባሉ ወደሚል ተጠየቅ ስለሚወስደንም ሊሆን ይችላል። እንዲህ ሲደፈርስ ደግሞ ወደ መስክ ጎራ ብሎ ማደብ፤
መደፍርሱን ያሰክናል የጨገገዉን ይገልጣል።
መቸስ በፍቅር መሀል ወደ ከረረ ጠብ የማያመራ ኩርፊያ እንዲያም ሲል ለቁርጥ የማያደርስ የፍቅር ማብሰያ ብጤ ጠብ መኖሩ አይቀርም። እንዲህ ሲሆን ደሞ እነ መምሬ እሸቴ ወዴት ሂደዉ?
‹‹ፋኖስ ላምባዬን ይዤ ከሶራው ላይ ማምሸቴ
አስማምቶኝ ነው ከፍቅርህ ምክራቸው ቄስ እሸቴ›› ጸብ ሰንብቶበት ተቆጥቦ፣ የቆዬ ፍቅር በነቄሴ ገላጋይነት ሰላም ሲወርድለት እንዳድስ ይጎመራል። በዚያ ምሽት ከምን ላድርግሽ መባል የግድ ስለሚሆን በፋኖስ በላምባ ብርሀን ታጅባ ሳቅ ሳቅ እያለች ሶራዋ ላይ ጉብ ያለች እመቤት በምናባችን ትከሰታለች። ሲነጋ ደግሞ፡
‹‹ልሳል ልሳለም ቃኝቸው ልግባ
ሰርክ ያንተን እጹብ ውቅር ድንቅ አምባ›› እያለች ደጁን ረግጣ ትመለሳለች። እርግጥ ነዉ ዉቅር አብያተ-ክርስቲያናቱ ለራሱ ለጧት ማታ ተሳላሚዉም አድሮ አዲስ መሆናቸዉ ተደጋግሞ ተነግሮላቸዋል። ግን እሷም በረታሁ ወዳንተ መጣሁ ካለች ጀምሮ ልሳል ልሳለም እያለች ሰርክ አዲስ፡ እጹብ ድንቅ የሆኑትን የሮሐ ፍልፍል ቤተ-መቅደሶች ሰላም ሰጊድ ማለት እየለመደች ነዉ።
ከስግደትና ከስለቷ ስትመለስ ደግሞ ‹‹ሳርም ሳበጃጅ ውዬ ደጅህ፤ አለብኝ ጉዳይ የማዋይህ›› ይከተላል። እኛስ ‹‹ይሄ ለምወዳት ልጅ አይመጥንም፤ ሀሳቤንም አይገልጥልኝም፡ እንዴት ይሄን ለሷ?›› እያልን ስንት የፍቅር ደብዳቤ ቀዳደን ጥለን የለ? እሷም ጉዳይዋን ለሱ የምትነግርበትን ቋንቋ ለመምረጥ ሳታነሳ ሳትጥል እንዲሁ አፍ እንዳመጣ አትተነፍስም፡፡ ‹‹ከእንጨት መርጦ ለታቦት፤ከቃል መርጦ ለኪነት›› እንዲሉ፡-
ማሬዋ!!
ስክን ገላዋ!!
ስክን ገላዋ!!
ማሬዋ ደርባባዬዋ!!
ደርባባዬዋ!! --- እያለች ትቀጥላለች፡፡

Read 1864 times