Print this page
Sunday, 11 October 2020 00:00

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር በኮቪድ ለተጐዱ 24 ሙዚቀኞች ድጋፍ አድርጓል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የሮያሊቲ ክፍያን የሚሰበስብ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ሊገባ ነው

         የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ህብረት ጋር በመተባበር በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በእጅጉ ለተጐዱ 24 የሙዚቃ ሰዎች ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ። ህብረቱና የጋራ አስተዳደር ማህበሩ ከትላንት በስቲያ መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በካፒታል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ድጋፉን ያደረጉት 113 ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ተመልካች አልባ (ቨርቹዋል ኮንሰርት) በማድረግ በተገኘው ገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የሙዚቃ ዘርፉ 365ቱንም ቀናት 24 ሰዓት የሚደመጥና ያለማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጥ ዘርፍ ቢሆንም የዘርፉ ባለሙያዎች በመጀመሪያ በ1996 ዓ.ም በኋላም በ2007 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣውን የሙዚቀኞችን መብት በእጅጉ የሚያስጠብቅ አዋጅ ከእውቀት ማነስ ሳይጠቀሙበት መቆየታቸውን የገለፁት የህብረቱና የጋራ አስተዳደር ማህበሩ አመራሮች ሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ታግሎ የጋራ አስተዳደር ማህበሩ ከመመስረቱ ከሁለት ወራት በፊት ህይወቱ ቢያልፍ ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በኤልያስ የልደት ቀን የሙዚቃ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር በሙዚቃ አመንጪዎች፣ ከዋኞችና የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲዩሰሮች በሶስቱ ማህበራት አማካኝነት የኤሊያስ መታሰቢያ ሆኖ መመስረቱን የሙዚቃ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ኃይለሚካኤል ጌትነት (ሃይሌ ሩትስ) ተናግሯል፡፡
ከዛ በኋላ በተደረገ እንቅስቃሴ፣ የሮያሊቲ ክፍያ ቀመር ተሰርቶ ለአዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት መግባቱንና መጽደቁን የገለፀው ሃይሌ ሩትስ ይህንን የሮያሊቲ ክፍያ እውን ለማድረግና ለመሰብሰብ 85 የዓለም አገራት የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ ከውጭ ለማስገባት ማህበሩ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጿል።
ቴክኖሎጂው በሆቴሎችና በባሮች ውስጥ የሚቀመጥና ሆቴሉ ወይም ባሩ የተጠቀመውን የሙዚቃ መረጃ እየሰበሰበ ወደ ክፍያ ቀመሩ ቋት የሚከትትም ነው ተብሏል፡፡
የአጋራ አስተዳደር ማህበሩና የማህበራት ህብረቱ አመራሮች ሙዚቀኞቹ ዳዊት ይፍሩ፣ ፍቅር አዲስ ነቅአጥበብ፣ ኃይለሚካኤል ጌትነት (ሃይሌ ሩትስ) እና ሄኖክ መሀሪ ጨምረው እንዳብራሩት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዙሪያ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ “ንጋት” የተሰኘውን አልበም ሰርተው ለከተማ አስተዳደሩ ማበርከታቸውንም አስታውቀዋል። ማህበሩን ይበልጥ ለማጠናከርና ሙያተኛውን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የሁሉም ባለሙያ እገዛና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ትክክለኛ ባለሙያ ለሆኑና መስፈርቱን ለሚያሟሉ አባላት በቅርቡ ተሻሽሎ የተሰራውን የአባልነት መታወቂያ ከጥቅምት 15 ጀምሮ መስጠት እንደሚጀምሩ ገልፀዋል፡፡ የሮያሊቲ ክፍያ ህግ በኤሊያስ መልካ ስም ሊሰየም ነው እየተባለ በማህበራዊ ሚዲያው የሚናፈሰውና አውታር መልቲ ሚዲያን ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር ጋር እየደባለቁ ማምታታቱ ተገቢና አስፈላጊ አለመሆኑንም ሃይሌ ሩትስ አብራርቷል፡፡
የሙዚቃው ዘርፍ ማለትም በስቱዲዮ ሙዚቃ መቅረጽ፣ ውዝዋዜም ሆነ የትኛውም እንቅስቃሴ ለኮቪድ 19 ተጋላጭ የሚያደርግ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ወደ ሙዚቃ እንቅስቃሴ መግባት አደገኛ ነው ያለው ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ፣ በተመልካች አልባ (ቨርቹዋል ኮንሰርት) እና በመሰል ስራዎች ዘርፉን ለማነቃቃት ሙከራ ይደረጋል ብሏል፡፡

Read 1292 times
Administrator

Latest from Administrator